Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹የተገኘው የሰላም ጭላንጭል ወደ ፍጹም አስተማማኝ ደረጃ በሙሉነት እንዲያድግ ሁላችንም በኃላፊነት ልንሠራ...

‹‹የተገኘው የሰላም ጭላንጭል ወደ ፍጹም አስተማማኝ ደረጃ በሙሉነት እንዲያድግ ሁላችንም በኃላፊነት ልንሠራ ይገባል›› ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ቀን:

በዕለተ ልደቱ ሰማያውያንንና ምድራውያንን በአንድነት አገናኝቶ ስለ ሰላም እንዲዘምሩ ያደረገ የሰላም አለቃ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ አምስት ዓመተ ልደቱ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ፡፡

እግዚአብሔር ከሰው ጋር ሰላም መፍጠሩን የገለጸው በትንቢት ወይም በምሳሌ ወይም በቃል ብቻ አልነበረም፤ እጅግ በሚያስደንቅ የተዋሕዶ ተግባርም እንጂ፣ በአበሳ ኃጢአት መነሻነት በጠላትነት ተፈርጆ የነበረውን የሰው ልጅ መውደዱ ብቻ ሳይሆን፣ ጭራሽ ሰውነቱን ሰውነት አድርጎ ወይም አካሉን አካል አድርጎ መገለጡ፣ የሰላሙ ጥልቀትና ምጥቀት ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ የሚያስገነዝብ ነው፡፡ የሰማይ ሠራዊትም ‹‹የሰው ልጅን እጅግ ወደደው›› በማለት በከፍተኛ አድናቆት የዘመሩለት የሰውን ሰውነት ተዋሕዶና የራሱን አካል አድርጎ በመንበረ ጸባኦት እንዲቀመጥ አድርጎት በማየታቸው ነው፡፡

ይህ የዕርቀ ሰላም ውጤት ነው፣ ዕርቀ ሰላም የማይፈታው ችግር እንደሌለ ይህ አምላካዊ ዕርቅ ግዙፍ ማስረጃ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን የታረቀው በምሕረትና በይቅርታ ብቻ አይደለም ወይም ላቅ ያለ ቁሳዊ ስጦታ በመስጠትም አይደለም፣ እግዚአብሔር ሰውን የታረቀው ‹‹ሰው በመሆን›› ነው፣ በዚህ ምሥጢረ ተዋሕዶ እግዚአብሔር ሰው ሲሆን ሰውም እግዚአብሔርን የመሆን ዕድል በማግኘቱ በውጤቱ ሰው በተዋሕዶተ ቃል በመንበረ ጸባኦት ተቀምጦ ሰማያውያን መላእክትን ጨምሮ የፍጥረታት ሁሉ ገዥ ሊሆን ችሏል፡፡

እግዚአብሔር እጅግ የሚወደን መሆኑን የምናውቀው ‹‹እኛን መስሎ ሳይሆን እኛን ሆኖ በመካከላችን በመገኘቱ›› ነው፣ ታዲያ እግዚአብሔር እኛን ይህን ያህል ከቀረበንና ከወደደን እኛም በዚሁ መጠን ልንዋደድ አይገባንምን? እንድናደርገውና እንድንፈጽመው የሰጠን አደራስ ለሰው ሁሉ እንዲህ ያለ ፍቅር እንዲኖረን አልነበረምን? ሰዎች በየትም እንኑር በየት እርስ በርስ በመፈቃቀርና በመዋደድ በሰላም የመኖር አምላካዊ ግዴታ እንዳለብንስ ዘነጋነውን? በሰላምና በፍቅር የመኖር ጉዳይ ለሰዎች እንደ መብት ሳይሆን እንደ ግዴታ ነው፡፡ ምክንያቱም የነገርየው ውስጠ ይዘት የመኖርና ያለመኖር አንድምታ አለውና ነው፡፡

እግዚአብሔር በሕይወት እንድንኖር እኛን ፈጥሯል፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ቀዋሚ ፈቃዱ ነው፣ በመሆኑም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማክበር ለሰው ልጆች ሁሉ የውዴታ ሳይሆን የግዴታ ኃላፊነት አለብን፣ ይልቁኑም በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለማዊው አመራር የምንገኝ ኃላፊዎች ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማክበር ይጠበቅብናል፡፡ የሰውን ሕይወት ለመጠበቅ የሰው ሕይወት መጥፋት አለበት የሚል የተሳሳተ አካሄድ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት የለውም፡፡

ምክንያቱም በአንድ በኩል እያጠፉ በሌላ በኩል እጠብቃለሁ የሚል አካሄድ ከኪሣራና ከጥፋት ነጻ አያደርግምና ነው፡፡ በዚህ ስሑት አስተሳሰብ ዓለም በሽቅድምድም እያመረተችው ያለው የፍጥረተ እግዚአብሔር ማጥፊያ መሣሪያ ከአጥፊነት በቀር የአልሚነት ሚና አለው ብሎ መናገር ፈጽሞ አይቻልም፡፡

በዚህ አጥፊ መሣሪያ የእግዚአብሔር ፈቃድ ተጥሶ ሕፃናትና እናቶች፣ አቅመ ደካሞችና አረጋውያን በሕይወት የመኖር ዕድል አጥተዋል፡፡ ይሁንና ቸርነቱ የማያልቅበት እግዚአብሔር አምላክ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን የተከሰተው ችግር በከፊልም ቢሆን ረገብ ብሎ የሰላም ጭላንጭል እንድናይ አድርጎናል፡፡ ይህ ሰላም የእግዚአብሔር ስጦታ ነውና ልንወደው ልናከብረውና ልንጠብቀው ይገባል፡፡

ሰላም በጠፋ ጊዜ በወገኖቻችን ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ በዓይናችን አይተናል፡፡ ይህ ዓይነቱ ክስተት ሊቆም እንጂ ሊቀጥል አይገባም፡፡ ስለዚህ የተገኘው የሰላም ጭላንጭል ወደ ፍጹም አስተማማኝ ደረጃ በሙሉነት እንዲያድግ ሁላችንም በኃላፊነት እንድንሠራ በዚህ አጋጣሚ በአጽንዖት አደራ እንላለን፡፡

በመጨረሻም በተከሰተው አለመግባባት በአጠቃላይ በሕዝባችን ላይ የደረሰው ስብራት ከባድ በመሆኑ የዓለም ማኅበረሰብ የተቻለውን ድጋፍ ሁሉ በማድረግ ሕዝባችንን እንዲያግዝ፣ መንግሥታችንና ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችም የተጀመረውን የሰላም ጉዞ እንዳይቀለበስ በከፍተኛ ኃላፊነት እንዲሠሩ፣ ኢትዮጵያውያን የሆናችሁ ልጆቻችንም በተለመደው የመተጋገዝ ቅዱስ ባህላችን መሠረት እርስ በርስ በመረዳዳት ይህንን ፈተና እንድናልፈው በእግዚአብሔር ስም አባታዊ መልዕክታችንን ከአደራ ጋር እናስተላልፋለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...