Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የህሊና ሸክሞቻችን!

ሰላም! ሰላም! የሰላም ነፋስ ሽው ማለት ከጀመረ ወዲህ በሌላው መስክ የወሬው ሰርከስ ደርቷል አሉ። በዚህ መሀል ደግሞ አሉባልታውና ሐሜቱ እንደ ማጣፈጫ ጠብ እየተደረገ ነው። ወሬና አሉባልታ ባይኖሩልን ኖሮ፣ ኑሮ እንደሚሰነዝርብን የከባድ ሚዛን ቡጢ ዘመን እንሻገር ነበር? እንኳን የ‘ትራንስፎርሜሽን’ ተራ ቁጥር ልንቀያይር? የምሬን እኮ ነው። እናላችሁ ሰሞኑን በማለት፣ በመባልና በማስባል ሰንጠረዥ ጨዋታ ብዙ ስሰማ ነፍሱን ይማረውና ‘አልን፣ ተባልን፣ አስባልን’ ያለው ድንቅ ጸሐፊ ትዝ አለኝ። መቼም ነፍስ ይማር የምንለው ሰው ቁጥር፣ ከዋጋ ግሽበቱ ጋር የእናት ልጅ ሆኗል መሰል። ደግሞ ‘ዲኤንኤ’ እናስመርምር ብላችሁ በቋፍ ያለውን ሥጋ ለባሽ ‘ዴሊት’ እንዳታስደርጉት አደራ። ‹‹ጥናቱ ቀርቶብኝ ወሬ በጋቱኝ›› አለች አሉ። እንጃ ማን እንደሆነች። ለማንኛውም ወሬ በደራበት በዚህ ዘመን ውስጥ አዋቂ ነኝ ባይ ቀላማጅም ስለበዛ፣ ቢያንስ ላለመበለጥ ቀደም ብሎ መገኘት የጊዜው ብልጠት ነው ብላችሁ እንዳይገርማችሁ፡፡ መገረም ድሮ ቀረ እንዳትሉኝ ብቻ!

የአሉባልታውያንን ማንነት ከምንመረምር የሚያምርብንና የምንችለውን ‘አሉን’ ብንመረምር፣ ይኼን ጊዜ ስንት ደህና ነገር ይገኝ ነበር። አንዴ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ነዳጅ ካላወጣን በስተቀር ችግራችን አይፈታም ብለው የሚያስቡ ሰዎች ይገርሙኛል…›› አለኝ። ‘የማይገርመውና የማይራገም ሰው አለ?’ እያልኩ በውስጤ፣ ‹‹አንተ ምን ትላለህ?›› ስለው፣ ‹‹ሐሜቶቻችንና አሉባልታዎቻችን እኮ በሙያተኛ ቢጠኑ፣ ከነዳጅ የበለጠ ስንት የመፍትሔ ሐሳብ ይፈልቅ ነበር?›› ነበር ያለኝ። ምንጭ እየደረቀ እሱ ከአሉባልታዎቻችን መፍትሔ እንዲፈልቅ ያስባል። አይ አብዝቶ መማር ግን አንዳንዴ። እኔማ ምን እለዋለሁ ያው እንኳን እሱ የመረጃና የደኅንነት ቢሮ ሳይቀር ሰርጎ በማይገባበት በልቤ አዳራሽ፣ ‹‹የደላው ሙቅ ያኝካል…›› ብዬ ተረትኩበት፡፡ ‹‹ባልተርት ተራችነቴን በምን አስታውሰው ነበር?›› ነው ያለችው? ኧረ እኔ የት አውቄያት? ደላላ ነኝ እንጂ ሁሉን አዋቂ ነኝ እንዴ? ስምንተኛው ሺሕስ ስምንትን ሲያይ ባሰበት መሰል፡፡ ባሰበት የሚለው ምን አስታወሰኝ መሰላችሁ? የሰው አመል ተለዋዋጭነት፣ ቅብጥብጥነት፣ ስልቹነት፣ ነገሮችን በቶሎ መርሳት (ሾርት ሜሞሪ ነው ያሉት?)፣ ወረተኝነት… ስንቱን ልንገራችሁ እንዳልል እናንተ ከእኔ በላይ ስንቱን ጉዳ ጉድ ታውቁታላችሁ፡፡ በጣም እንጂ!

እና ተባለ አሉ። ምን ተባለ? ‘ሰላም ከሰፈነ በቅርቡ ከፍተኛ በጀት ተመድቦ በርካታ ሥራ ሊከፈት ነው አሉ።’ እናቶች ዕልልታቸው ቀለጠ። ‘ተመርቀው ሥራ ያጡ ልጆቻችንን ሥራ አገኙ’ ብለው ነዋ። ማን ነው እሱ እንዲህ የሚለው? በዩቲዩብ የተለቀቀ መረጃ ነው ተባለ፡፡ ‘ቆይ ግን እኛ ያልተጣራ መረጃ ከመቀባበል ውጪ ሌላ አናውቅም እንዴ?’ ብሎ የጠየቀ ከቀጣፊዎች የዩቲዩብ ገጽ ላይ ‘ብሎክ’ ሲደረግ፣ ጉዳዩን በአንክሮ የሚከታተሉ ደግሞ አፋቸውን በእጃቸው ብሎክ አደረጉት ተባለ። ማነው ያለው? ወሬውን ይዞት የመጣው ነዋ። እናንተ ደግሞ፣ ‘እንዴ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ያለ ‘ፍሪደም ኦፍ ስፒች’ አለ? ኦ ማይ ጋድ’ እያሉ ከተሜዎች ሙድ ያዙ ተባለ፡፡ ከፖለቲከኞች ወገን አክራሪ የሚባሉት ደግሞ፣ ‹‹ይህችን ቀርቶ የዝንብ ጠንጋራም እናውቃለን፣ ይህ ሁሉ የተተረተው በእኛ ነው?›› እያሉ በየስርቻው ያልተንሾካሾኩ የሉም አሉ፡፡ የርቀት ፖለቲካዊ ትግሉን ‘ካንስል’ በማድረግ ጋደድ ብለው ፎቶ እየተነሱ ‘ሼር’ አደረጉ። እዩ፣ ለይኩ (ላይክ አድርጉ)፣ ኮምቱ (ኮሜንት ጻፉ) እየተባለ ተነዛ። ‘ተንጋዶ ፎቶ የመነሳታቸው ሚስጥር የአቋም ይሁን ‘የፊዚካል’ እስኪጣራ ሙሉ መግለጫ ከመስጠት ተቆጥቤያለሁ ብሎ መንግሥት መግለጫ አወጣ ተብሎ ተወራ። ካወሩ አይቀር እንዲህ ነው እንጂ!

‹‹መንግሥት እየተቆጠበ ሰውን ምን ነካው፣ እዚህም እዚያም ከቫይረስ እየተላፋ በሽታው ፈጀው…›› ሲባል ግን ሁሉም ድምፁን አጥፍቶ፣ ‘እስኪ የምናሸንፍበትን ጨዋታ እንጫወት’ ተባባለ። ተባብሎ ተማምሎ ‘ኤፍኤሞች’ ዘንድ እየደወለ ዘፈን ካልመረጥን ብሎ ቀወጠ። “ለማን ነበር?” ጋዜጠኛው አየር ላይ ነው። “ለምርጫው ነዋ!” አድማጩ ጋዜጠኛው ላይ ንቀት እየጀማመረው ነው። ‹‹እሺ የማንን ዘፈን ነበር?›› ጋዜጠኛው ትህትናው ቀጥሏል። አድማጭ፣ ‹‹የኃይለየሱስ ግርማን ‘ማናችን ነን አጋም ማናችን ነን? ማናችን ነን ቁልቋል ማናችን ነን?’ የሚለውን…›› ጋዜጠኛው ግራ እየተጋባ፣ ‹‹ይኼ እኮ የብሶት ነው…›› ሲለው አሉ፣ ‹‹አውቃለሁ፣ ከፍሬንዴ ጋር እኩል ተመርቀን ቀድሞኝ ሥራ ሲጀምር አጋም ልሁን ቁልቋል ጠፋኝና…›› ስልኩ ተቋረጠ። ‹‹ሄሎ! ሄሎ! አድማጫችን ስልኩ…›› ሳይጨርሰው ጋዜጠኛውም መብራት ድርግም አለ አሉ። እንግዲህ ምርጫው እንደ ባቡር ‘ሸከተፍ… ሸከተፍ…’ እስኪል ዘፈኑን ማስታወስ ነው። ኦ! ለካ የዘመኑ ባቡር በኤሌክትሪክ ነው የሚሠራው፣ እንደ ከሰል ባቡር አይሸከታትፍም፡፡ እኛም እስቲ ሰላምን አስፍነን ሰው እንሁን፣ ሰው እንምሰል!

ከባድ የጭነት መኪና ላሻሽጥ መከራዬን እያየሁ እዚህ እኛ ሠፈር አስቸኳይ ስብሰባ አለ ተብዬ ተጠራሁ። ያው ጥሪውም የደረሰኝ ፋታ በሚያሳጣ ‘ሚስድ ኮል’ ነው። ‹‹ማንጠግቦሽን ወክያለሁ…›› ብላቸው፣ ‹‹የለም በዛሬው ስብሰባችን የሚተላለፈው ውሳኔ ለፍርድ ቀን የምትጠየቅበት ስለሚሆን ራስህ መምጣት አለብህ…›› ተባልኩና ሄድኩ። የፍርድ ቀን በሰዓቱ ሊደርስ በቀን ሦስቴ እንዳንበላ ሥራ ያስተጓጉልብናል። አጉል ይሉኝታና ምንተ ህፍረት ስንቱን ያስችለናል እናንተ፣ እንዲያው እኮ፡፡ ምፅዓትን ፍራቻ ሳይሆን ወደ ስብሰባው ያስኬደኝ ከነዋሪዎች የመገለል ፍራቻም ነው። ተገኘሁና ማዳመጥ ጀመርኩ። የስብሰባው መሪዎች እነ ባሻዬ ናቸው። አጀንዳው ደግሞ ‘ለአገራዊ ምክክር ጊዜ የአካባቢው ሰዎች እንዴት በንቃት በመሳተፍ የሚፈልጉትን መናገር እንዳለባቸው’ ነው። ‹‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባ›› ብለው ተረቱንም ጉዱንም ለምን እንዳሳጠሩት እንጃ። አሃ! ለካ የእኛ ሰው ነፃነቱ እጁ ውስጥ እንዳለ ነጋሪ አያስፈልገውም፡፡ ገባኝ! ገባኝ! አያችሁ ሲገባችሁ መካሪም አታላይም አያስፈልጋችሁም!

ሳዳምጥላችሁ አንዱ ተነስቶ፣ ‹‹ከታዋቂ ልብስ ስፌት ድርጅት እኔ ነኝ ያለ ሙሉ ልብስ እንድናሰፋ እኔ እነጋገራለሁ…›› ብሎ ይቀመጣል። “ወግድ!” ብሎ ሌላው ይነሳል። ‹‹እጀ ጠባቡ፣ ቡልኮውና ጋቢው የት ሄዶ ነው በአገራዊ ምክክር መድረክ ላይ ፈረንጅ መስለን ፎቶ የምንነሳው?›› ብሎ ይወበራል። ‹‹መቼ ይሆን ይኼን ሰውዬ የልማት ተነሽ ሆኖ ከአጠገባችን የሚርቅልን?›› ብላ ከወዲያ ማዶ አንዷ ስታማው ይሰማል። የማይሰማ የለም፣ ስታሙ ይኼን ይኼን ቢያንስ አትርሱ፡፡ ማኪያቶና ድራፍት ላይ ሆናችሁ የብርጌዱንና የክፍለ ጦሩን አሠላለፍ በብሉቱዝ በመታገዝ ለማብራራት ስትሞክሩ የነበራችሁ ምነው ድምፃችሁ ጠፋ? ለካ ረስቼው እርስ በርስ እየተማማችሁ ነበር ለካ? ወይ ጊዜ? ጊዜ እኮ ውሉን የማይስት፣ ላይ የነበረውን ታች፣ ታች የነበረውን ላይ፣ የተፋቀሩትን እሳትና ጭድ፣ ዓይንህን አያሳየኝ የተባባሉትን ሰምና ወርቅ… ያደርጋል፡፡ ለነገሩ በጊዜ አመካኘን እንጂ ጊዜ እኮ የሚዘወረው በእኛ ነበረ፡፡ ‹ለካ ነበር እንዲህ ቅርብ ነበር› ያሉት እቴጌ ጣይቱ ይህንን ዘመን ቢያዩ ምን ይሉ ነበር? እኔ እንጃ ነው መልሴ!

 ነገሩ ሁሉ ተረሳ። ይከናወናሉ የተባሉት ሥራዎቸን የሚያስታውስ ሰው ጠፋ። እነ ባሻዬን ጨምሮ ‘በአገራዊ ምክክር መድረክ አገርኛ ይለበስ? ወይስ ፈረንጅኛ?’ እንደገና ክርክር ተጀመረ። ‹‹ሲጀመር…›› ስትል ‘ፈረጅኛ ይልበስ’ የሚለውን ሐሳብ ደግፋ አንዷ ተነስታ፣ ‹‹ሲጀመር ብሎ አማርኛ የለም…›› ብሎ ከእጀ ጠባብያውያን አንድ ተቆርቋሪ ያቋርጣታል። ‹‹ዋት ኤቨር…›› ብላ ስትቀጥል ግን ለምን እንደሆነ እንጃ ‘ዘራፍ!’ የሚል ጠፋ። ቀጠለች ‹‹…በእኔ ‘ኦፒኒየን’ የግል ብትሉ የመንግሥት ተቋማት በእንግሊዝኛ መጠሪያ አብደው… የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ስያሜ አገር ለቆ ተሰዶ፣ ‘ብሮድካስቲንግ፣ ኮርፖሬሽን፣ ኮሙዩኒኬሽን፣ ‘ክላስተር፣ ፕላስተር’ እየተባለ ሁሉም ፈረንጅኛ ለብሶ ሳለ፣ ፌርማታዎቹ ‘ትሬን ስቴሽን’ ተብለው የተሰየሙለት ባቡራችን ሳይቀር እኮ ነው? ታዲያ በመጪው ምክክራችን እጀ ጠባቡን ለብሶ እንደ እንጀራ ልጅ የሚቁለጨለጨው ምን በወጣው? ‘አይ አም ሲሪየስ’!›› ስትል ጠባቡ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ፀጥ አለ። እጀ ጠባባውያን የተረቱ መሰለ። ‹‹ለነገሩ ልክ ነሽ፣ እንደ አያያዛችን ከሆነማ እንዲያውም ተነፋነፉን ዘመናዊ ቦላሌ ሁን ብለን መሳቂያ መሆናችን አይቀርም። እነ ‘ፐብሊክ ሰርቪስን’ ጠቅሰው አንበሳ አውቶብሶች ለዚህ ምስክር መሆን አለባቸው…›› ብለው አንገት ደፉ አዛውንቱ ባሻዬ። ምነው አዘናችሁ? አንገት መድፋት ብርቅ ነው እንዴ? ሰሞኑን በእነ እንቶኔ ሠፈር ትርምስ ስንቱ አንገቱን ደፍቷል እኮ? ያውም የንፁኃንን ደም ያስገበረ ትርምስ፡፡ ፈጣሪ ያተራምሳቸውና!

አመካኝተን ለመብላት ብቻ ተስማምተን፣ ትውልድ የሚወርሰውን መላ ቅጡ የጠፋ ጉራማይሌ ባህልና ቋንቋ ሥራ ያውጣው እያልን ተበተንን። ምሁሩን የባሻዬ ልጅ ከስብሰባው በኋላ ሳነጋግረው እንደ ነገረኝ ከሆነ ያስገርማል፡፡ ‹‹አንበርብር ከእንግዲህ ወዲያ የፊደል ግድፈት፣ የቃላት ቅደም ተከተል መዛባትም ሊከሰት ግድ ነው። ዳሩ አትሥጋ፣ አትሸበር። በመጨረሻው ዘመን ይህ ሊሆን ግድ ነው…›› ነበር ያለኝ። እኔ ስለመጨረሻው ዘመንም ሆነ ስለገዳፊዎቹ ማንነት የማጣራበት ጊዜ አልነበረኝም። ‹‹መንግሥት ያልተቸገረበትን እኔ ምን ቤት ነኝ?›› ብላቸው ባሻዬን፣ ‘መዝሙረኛውን አስታወስከኝ’ ብለው፣ ‹‹ኧረ እኔስ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድነው?›› ያለውን አውጥተው አነበቡልኝ። ‘እስኪ መጀመርያ እኛም እንደ ሰው ክብር አውቀን፣ ሥርዓት ኖሮን እዚያ ብፅዕና ላይ እንድረስ። አይመስልዎትም ባሻዬ?’ ያልኩት ለራሴ ነበር። ለራስ የተነገረ ነገር ለሌላው ማድረስ መልካም ቢሆንም፣ የዘመኑ ሰው ግን ማዳመጥ የሚፈልገው በራሱ መንገድ የሚፈስለትን ተራ ወሬ ስለሆነ መታቀብ ልማዴ እየሆነ ነው፡፡ እላፊ የለመደ ትውልድ የሌላውን እንደማይምር አጠገባችን ዞር ዞር ማለት ብቻ ይበቃል፡፡ ኪሳራው የበዛብን እኮ በዚህና በሌላው መሰል ምክንያት እንደሆነ ካልተረዳን፣ ዛሬን አልፈን ነገ ለመድረስ አሳር ይሆንብናል፡፡ አሰሩና አሳሩ በዝተው እኮ ነው መስቀለኛ መንገድ ላይ የቆምነው!

በሉ እንሰነባበት። ያልኳችሁን የጭነት መኪና አሻሽጬ ስጨርስ ገዥው፣ ‹‹ውክልና ሰጥቼህ እየተከታተልክ ሥራ ካላሠራህልኝ?›› ብሎ የማልንቀው ድርድር አቀረበልኝ። እሺ አልኩና ተያይዘን ውልና ማስረጃ። ያው እንደምታውቁት ብትወክሉም ባትወክሉም፣ ብትወከሉም ባትወከሉም ሠልፍ አያጣችሁም። ‹‹ለመሠለፍ ብቸኛው መሥፈርት ኢትዮጵያዊ ሰፋ ሲልም አፍሪካዊ ሆኖ መገኘት ብቻ ነው…›› ይለኝ ነበር አንድ ወዳጄ። አንዱ ታዲያ የሆነ ፋይሉን ‘ፎቶ ኮፒ አድርገህ ና’ ተብሎ ደርሶ ሲመጣ ከኋላው የነበረ ሠልፈኛ መንገዱን ይዞታል። ‹‹ይቅርታ ወንድሜ ታሳልፈኝ?›› አለው። ‹‹ለምንድነው የማሳልፍህ?›› ብሎ ያኛው ሙግት። ‹‹እቀድምሃለሁ። ‘ኮፒ’ አድርግ ተብዬ እኮ ነው…›› መለሰ መንገድ የተዘጋበት። ‹‹አላሳልፍም፣ ስትፈልግ በሱዳን በኩል ዞረህ ና…›› አይለውም? ይኼ የግብግብ ወሬና ተረብ ተነሳ። ሲነሳበት ደግሞ ይሉኝታ የለውም፡፡ ምድረ ይሉኝታ ቢስ!

‹‹እኔ እንደ ማንም ማስተዋልና ማገናዘብ ያልፈጠረበት ነፃ አውጪ ነኝ ባይ ማንንም ታግዬ በዝረራ እጥላለሁ ስል ሰምተኸኛል?›› ሲል ነገር የተፈለገው ሰው በእጁ የያዘውን ወረቀት ጣለው። ‹‹ማነህ ወንድም ወረቀቱን ጣልከው፣ አጉል ጀግንነትህን ትተህ ወረቀትህን አንሳው…›› አለ አንዱ ተደርቦ። ‹‹ውልና ማስረጃ ነው የመጣነው እንጂ በረሃ ነው የወጣነው? ምንድነው የምሰማው?›› ይላሉ አንዲት የደስ ደስ ያላቸው አዛውንት። ‹‹ያው ነው እማማ፣ የስም ለውጥ ነው…›› ይላቸዋል ቀጭን ልጅ እግር። “አሳልፈኝ!” እያለ ገሚሱ ነገር ይሸሻል። አዛውንቷ መልሰው፣ ‹‹አይ ጉድ፣ እንዲህ የመጣችሁበትን ዓላማ እየሳታችሁ ነው አገራችንን መጫወቻ የምታደርጉት? አይ ጉድ!›› ይላሉ። ወዲያው ሊወክለኝ አጣድፎ የወሰደኝ ወዳጄ፣ ‹‹ሰው ግን እያደር ፖለቲከኝነቱ ብሶበታል እባክህ። እንዴት ነገር እንደሚያላምጥ ታያለህ?›› ሲለኝ አንዷ ሰምታው፣ ‹‹እንጀራና ማስቲካ በእኩል ዋጋ እየተሸጡ ምን እናላምጥ ታዲያ?›› አለችው። በምን ቀን ነው ውክልና ለመቀበል የተስማማሁት እባካችሁ? ለሥራ ውክልና ሄጄ የፖለቲካ ጦርነት ውስጥ ስገባ የተሰማኝ አንድ ነገር ነበር፡፡ ለመሆኑ ለሕመም ወይም ለሞት ውክልና ቢኖር ምን እንደራረግ ነበር? ጉልበተኛና በሀብቱ የተመካ መጫወቻ ሆነን መቅረታችን አልነበር? አንዳንዴ ሳስበው ከራስ ጋር የሚያጣሉ ሐሳቦችን መናቅ አያስፈልግም፡፡ ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ ስለማይታወቅ መጠንቀቅ መልካም ነው፡፡ ከመጠንቀቅ በተጨማሪ ደግሞ ሒደቱን ለማሳመር የመጀመርያው ረድፍ ላይ መገኘት ብልህነት ነው፡፡ ያለበለዚያ የህሊና ሸክሞቻችንን አንችላቸውም፡፡ መልካም ሰንበት! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት