Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልቱሪዝም ከሰላም ስምምነቱ ማግሥት

ቱሪዝም ከሰላም ስምምነቱ ማግሥት

ቀን:

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰበት የቱሪዝም ዘርፍ በቅጡ ሳያገግም በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት ይበልጡኑ ጎድቶታል፡፡ በተለይ በርካታ ቱሪስቶች የሚጎርፉባቸው የአማራ፣ የትግራይና የአፋር ክልሎች ላለፉት ሁለት ዓመታት በጦርነት ውስጥ መክረማቸው እነሱን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ የፈተነ ነበር፡፡

ጦርነቱን አስመልክቶ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የሚለቁት ዜና፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ ኤምባሲዎችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በየማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው የሚለጥፉት ከአገር ውጡ ዘመቻና የጉዞ ማስጠንቀቂያዎች ጦርነት የሌለባቸውን የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎች ሁሉ የጎዳ ነበር፡፡

ቱሪዝም ሚኒስቴር ኮቪድ-19 ወረርሽኝና ጦርነቱ በዘርፉ ላይ ያደረሱትን ጉዳት ከባለድርሻ አካላት ጋር አጥንቶ ከዚህ ቀደም እንዳስታወቀውም፣ ኮቪድና ጦርነቱ ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ ኢትዮጵያን ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ አሳጥተዋል፡፡

- Advertisement -

ይህ ደግሞ በ1950ዎቹ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት መመሥረትን ተከትሎ እያደገ ለመጣውና በፖለቲካ አለመረጋጋት፣ በድርቅ፣ በእዝ ኢኮኖሚ፣ በጉዞ ገደብ ተፈትኖ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ እየተሻሻለ የመጣውን የቱሪዝም ዘርፍ ወደኋላ የመለሰ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አሸናፊ ካሳ እንደነገሩን ደግሞ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት በኋላም ጦርነቱ ዘርፉ እንዲዳከም፣ አንዳንዶች ከሥራው እንዲወጡ አሊያም ዘርፍ እንዲቀይሩ አድርጓል፡፡

ቱሪዝምኤምባሲ ‹‹ጦርነትና ግጭት በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ ያለው ተፅዕኖ›› በሚል በድረ ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍም ጦርነትና አለመረጋጋት በቱሪዝም ዘርፉ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ግጭቱ ባለበት ወቅት ብቻ ሳይሆን ግጭቱ ከተጠናቀቀ በኋላም የሚቀጥል ነው፡፡

ከጥቅምት 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ሁለት ዓመታት ያስቆጠረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ በጥቅምት 2015 ዓ.ም. መገባደጃ ላይ በመንግሥትና በሕወሓት ተወካዮች መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት የግጭቱን መጠናቀቅ አብስሮ፣ ለቱሪዝም ዘርፉ ተስፋን ቢፈነጥቅም፣ መልሶ ማጠናከር ግድ ይላል፡፡

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የቱሪዝም ዘርፉ እየተነቃቃ መሆኑን የሚገልጹት አቶ አሸናፊ፣ በኮቪድና በኋላም በጦርነቱ የተፈተነውን ዘርፍ ወደነበረበት ለመመለስ በርካታ ሥራዎች እንደሚጠብቁም ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ አሸናፊ፣ የቱሪዝም ዘርፉ እንደ ቀድሞው ጎብኚዎችን እያስተናገደ ነው ባይባልም፣ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ካንቀላፋበት እየነቃ ይገኛል፡፡ በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት በእርቀ ሰላም ለመፍታት እንቅስቃሴ ከተጀመረ ወዲህ ጎብኚዎች ለመጎብኘት ያላቸውን ፍላጎት አስመልክተው ለአስጎብኚ ድርጅቶች ጥያቄ መላክ ጀምረዋል፡፡

ሆኖም መገናኛ ብዙኃን፣ መንግሥትና ግለሰቦች እንዲሁም በዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶች ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ከሚያደርጉት ጥረት በተጨማሪ ዘርፉን ዳግም ለቱሪስት ለማዘጋጀት መንግሥትና የዘርፉ ተዋናዮች የበለጠ መሥራት አለባቸው፡፡

ጦርነቱ የቱሪስቶችን ፍሰት ከመቀነሱም በተጨማሪ መሠረተ ልማቶች ላይ ያደረሰውን ጉዳት መጠገንና በአካባቢው ነዋሪዎችም ሆነ ጎብኚዎች ሥነ ልቦና ላይ የተፈጠረውን ጫና የቱሪዝም ዘርፉን ዳግም በተለያዩ መንገዶች በማስተዋወቅ መቀልበስም ያስፈልጋል፡፡

የኳታር ቱሪዝም ባለሥልጣን ‹‹ከፖለቲካ አለመረጋጋት በኋላ የቱሪዝም ዘርፍ ዳግም እንዴት ማነቃቃት ይቻላል›› በሚል ባሰፈረው ጽሑፍም፣ በፖለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ ያለፉ አገሮች የሚያስተናግዷቸው ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ቁጥር እያሽቆለቆለ ይሄዳል፡፡ ይህም በግብፅና ታይላንድ በነበረው አለመረጋጋት ታይቷል፡፡

በፖለቲካ አለመረጋጋት ያለፉ አገሮችም ዘርፉን ዳግም ለማነቃቃት የተለያዩ ዕርምጃዎች መወሰድ አለባቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የቀውስ ጊዜ አስተዳደር ማለትም በየመገናኛ ብዙኃን የሚሠራጩ የተጋነኑ አሉታዊ ዘገባዎችን መገደብና የጎብኚዎችን ደኅንነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን ማበረታታት እንዲሁም ለቱሪስቶችና ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ማበረታቻ መስጠት ዘርፉ እንዲያገግም ከሚረዱ መፍትሔዎች ይካተታሉ፡፡

ሆኖም ከማበረታቻ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ‹‹ኦቨርላንድ›› ማለትም ከካይሮ ወይም ከሌላ አገር በመኪና ተነስተው እያቆራረጡ ኢትዮጵያ የሚመጡ ጎብኚዎች የኢትዮጵያን ድንበር ሲያቋርጡ 100 ሺሕ ዶላር ማስቀመጥ የሚጠበቅባቸው መሆኑ፣ በጎብኚዎች ዘንድ ቅሬታ ማስነሳቱን ፕሬዚዳንቱ ይገልጻሉ፡፡

ጉዳዩን ለቱሪዝም ሚኒስቴር አሳውቀውና ሚኒስቴሩ ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር ተነጋግሮ ወደፊት መመርያ እስኪወጣ አስጎብኚ ድርጅቶች ኃላፊነት ወስደው ጎብኚዎች ኢትዮጵያ እንዲገቡ ቢደረግም ከአንድ ዙር በላይ በአግባቡ መሥራት አልተቻለም፡፡

አንድ በሞያሌ በኩል የገባ ጎብኚ 100 ሺሕ ዶላር ሞያሌ አስቀምጦ በመተማ ለመውጣት ቢፈልግ አሠራሩ የተመቸ አለመሆኑም ኦቨርላንደርስን እያስተጓጎለ ነው፡፡ አቶ አሸናፊ እንደሚሉትም፣ 30 ያህል አቋራጭ ጎብኚዎች ከድንበር የተመለሱበት ጊዜ አለ፡፡

‹‹ኦቨርላንደርስ በጣም ታዋቂና ለቱሪዝም ዘርፉ አብሪዎች ናቸው›› የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ከቦታ ቦታ በሰላም መንቀሳቀሳቸው ብቻ ለኢትዮጵያ ገጽታና ቱሪዝም የሚያበረክተው አንድምታና ለዘርፉ ማደግ ያለው አስተዋጽኦ ሊታሰብበት እንደሚገባም ይጠቁማሉ፡፡

እነሱ በየቦታው በደረሱ ቁጥር ልምዳቸውንና ስለደረሱበት ሥፍራ በማኅበራዊ ትስስር ገጽ መልቀቃቸው ለሌላው ጎብኚ ትልቅ ትርጉም እንዳለውና መንግሥት ለእነሱ የተለየ አመቺ አሠራር መዘርጋት እንዳለበትም ያክላሉ፡፡

‹‹የኦንላይን ቪዛ ቶሎ አይመልስም፣ ፈጣን አይደለም›› የሚሉ አስተያየቶች ከጎብኚዎች እንደሚደርሳቸው በመግለጽም፣ ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ጉምሩክ፣ አየር መንገድና ኢሚግሬሽን አንድ ላይ መሥራት አለባቸው ብለዋል፡፡

ቱሪዝም ሚኒስቴር ኦቨርላንደርስ ሲገቡ ሕጋዊ ፈቃድ ያለው አስጎብኚ ድርጅት እንዲይዛቸው ማድረጉ መልካም ቢሆንም፣ ጎብኚዎች ዋጋ ይወደድብናል እንደሚሉና በቡድን ለሚመጡት ሳይሆን በሞተር ሳይክል ለሚመጡ ጎብኚዎች ሌላ አሠራር እንዲዘረጋም ይጠይቃሉ፡፡

ዓምና በዚህ ወቅት በርካታ ዳያስፖራ ገብቶ እንደነበር በማስታወስም፣ በዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶች ብዙ ዝግጅት ቢያደርጉም፣ አብዛኛው ቤተሰብ ጥየቃ በመምጣቱ ሥራው ብዙም እንዳልነበር ገልጸዋል፡፡ ዘንድሮ የተወሰኑ የቱሪዝም ሙያተኞች እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ነገር ግን እንደ በፊቱ ለመሆን ብዙ መሥራት እንደሚጠይቅ አክለዋል፡፡

‹‹ትግራይ ተከፈተ›› መባሉ ብቻ ብዙ ቱሪስት ያመጣል፣ ታዋቂውን የተፈጥሮ መስህብ ኤርታሌን ለማየት የሚመጡ ቱሪስቶች አዲስ አበባ ትራንዚት አድርገው፣ መቀሌ ገብተው አፋር የሚሄዱ በመሆኑም የሰላም ስምምነቱ ለዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በጦርነት ጊዜ የጉዞ ኢንሹራንስ ከፍተኛ መሆንና ኤምባሲዎች ‹ግዴታ ካልሆነ እዚህ ቦታ እንዳትሄዱ፣ ከሄዳችሁ ጥንቃቄ አድርጉ› በማለት በየመልኩ የሚያወጡት የጉዞ ክልከላ ችግር ያለበትን ቦታ ብቻ ሳይሆን ሌላውን ሁሉ መጉዳቱንም ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ‹‹መንግሥት በቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ግንባታ እያካሄደ ነው፡፡ ነገር ግን ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረጉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ አንድም ቀን በዘርፉ ከተሰማሩ ድርጅቶችና ባለሙያዎች ጋር ተወያይተው አያውቁም›› ያሉት አቶ አሸናፊ፣ መንግሥት በዘርፉ ከተሰማሩ አስጎብኚ ድርጅቶች ጋር እንዲቀራረብና የባለሙያዎችን ግብዓት እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡

‹‹ቱሪዝም ከመሠረተ ልማት ባለፈም ከፍተኛ ማስተዋወቅ ይፈልጋል፡፡ መሠረተ ልማቱ ሲጠናቀቅ ሳይሆን ከአሁኑ መሥራት፣ ፓኬጅ እየተቀረጸ መሄድ አለበት›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡

መንግሥትና የንግዱ ማኅበረሰብ በሚወያይበት መድረክም፣ ቱሪስቱ ኢትዮጵያ ሲገባ ችግር እንዳይገጥመውና በመጀመርያ ምልከታው አሉታዊ ነገር እንዳይይዝ አየር መንገድ፣ ጉምሩክ፣ ኢሚግሬሽን፣ ቱሪዝም ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አብረው መሥራት፣ መንግሥትም የቱሪዝም ተቋምን የሰው ኃይልና የቁሳቁስ አቅም ግንባታ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...