Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከውጭ በሚገቡ የተወሰኑ ምርቶች ላይ የጉምሩክ ቀረጥ ማሻሻያ ተደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የገንዘብ ሚኒስቴር ከዓመት በፊት በሥራ ላይ የዋለውን የጉምሩክ ታሪፍ ማሻሻያ መሠረት በማድረግ፣ በአገር ውስጥ የሚገኙ አምራቾችንና ገጣጣሚዎችን ተወዳዳሪ ያደርጋሉ ተብለው በተወሰኑ ምርቶች ላይ የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ማሻሻያ አደረገ፡፡

ሪፖርተር የተመለከተውና በገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ተፈርሞ ለጉምሩክ ኮሚሽን የተመራው ሰርኩላር እንደሚያስረዳው፣ 16 የሚደርሱ የታሪፍ አንቀጾች ላይ ማሻሻያው ከታኅሳስ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተቀባይነት በሚያገኙ የጉምሩክ ዲክላራሲዮኖች ላይ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡

ከመስከረም 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ይፋ ተደርጎ በነበረው የታሪፍ ጥራዝ ከ15 እስከ 25 በመቶ የሚደርስ የጉምሩክ ቀረጥ ልክ እንደሚጣልባቸው የተደነገጉት በደረቅ ጥራጥሬዎች ምድብ የተፈለፈሉና ቅርፊታቸው የተወገደ በተደረገው አዲስ የታሪፍ ማሻሻያ በኪሎ ግራም ዝቅተኛው አምስት በመቶ፣ ከፍተኛው 15 በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ልክ ተጥሎባቸዋል፡፡

ለአብነትም ምስር በኪሎ ግራም ቀደም ሲል ይጣልበት የነበረው 25 በመቶ፣ እንዲሁም ሽምብራ 15 በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ልክ ወደ አምስቶ በመቶ ዝቅ እንዲል መደረጉ ታውቋል፡፡

በሌላ በኩል ለምግብ ወይም ለመጠጥ ኢንዱስትሪዎች የሚያገለግሉ ዕቃዎች በኪሎ ግራም ይጣልባቸው የነበረው የ15 በመቶ የጉምሩክ ምጣኔ፣ በተሻሻለው የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ወደ አምስት በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡

የፕሮቲን ተዋፅኦዎች (ኮንሰትሬንትስ) እንዲሁም የሕፃናትና የሕሙማን ምግቦች፣ እንዲጣፍጡ ወይም እንዲቀልሙ የተደረጉ ሽሮፖች፣ በማንኛውም መጠን ስኳር የተጨመረባቸውን የፍራፍሬ ጭማቂዎች ሳይጨምር ለአልኮል መጠጥ ኢንዱስትሪዎች የሚያገለግሉ ግብዓቶች፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት የሚያገለግሉ በመሆናቸው የታሪፍ ምጣኔያቸው ከ15 በመቶ ወደ አምስት በመቶ ዝቅ መደረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

እንፋሎት ወይም ተን የሚያመነጩ ማፍያ ጋኖች (በዝቅተኛ ፕሬዠር እንፋሎት ማመንጨት የሚችሉ የቤት ውስጥ ሙቀት መስጫ፣ የሙቅ ውኃ ማፍያ ጋኖችን ሳይጨምር)፣ በከፍተኛ ሙቀት የሚሠሩ የውኃ ማፍያ ጋኖች ከዚህ ቀደም በኪሎ ግራም አምስት በመቶ የነበረው የጉምሩክ ምጣኔያቸው ተሰርዞ ከቀረጥ ነፃ እንዲሆኑ መደረጋቸው ታውቋል፡፡

ማቀዝቀዣ የተገጠመላቸው ተሽከርካሪዎች በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንደ ሥጋና ወተት ማቀነባበሪያ፣ የግብርና ምርቶችንና በአስቸኳይ ሊበላሹ የሚችሉ ምርቶችን ለማጓጓዝ የሚውሉ በመሆናቸው በጉምሩክ ታሪፉ ‹‹የተመደቡ›› በሚለው ውስጥ ተካተው፣ ከማናቸውም ቀረጥና ታክስ ነፃ እንዲሆኑ የገንዘብ ሚኒስቴር መወሰኑን፣ ለሁሉም የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ለሚፈጸምባቸው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች የተላከው ሰርኩላር ያሳያል፡፡

በሌላ በኩል በፀጉር ቀለም የዕቃ ዝርዝር ውስጥ የሚገኙት የፀጉር ማቅለሚያና ማንጫዎች (Bleaches) ቅባትንና ትሪትመንትን ሳይጨምር፣ በኪሎ ግራም የ25 በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ልክ ተጥሎባቸው በአዲስ ብሔራዊ ቁጥሮች እንዲተኩ መደረጉ ታውቋል፡፡

በጠፍጣፋው የተዳመጡ የብረት ወይም አሎይ ያልሆኑ የዓረብ ብረት ውጤቶች፣ ወርዳቸው 600 ሚሊ ሜትር ወይም ከዚያ የበለጠ፣ የለበሱ፣ የተነከሩ ወይም የተቀቡ፣ ቆርቆሮ የተነከሩ ወይም የተቀቡ ውፍረታቸው ከ0.5 ሚሊ ሜትር የበለጠ ወይም ያነሰ የብረት ዓይነቶች፣ በኪሎ ግራም 15 በመቶ የነበረው የጉምሩክ ምጣኔያቸው ተሰርዞ 25 በመቶ በሚል አዲስ የቀረጥ ልክ መተካቱ ተገልጿል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ካለፈው ዓመት መስከረም ወር ጀምሮ ተግባራዊ በተደረገው የጉምሩክ ታሪፍ ማሻሻያ እንዲቋረጥ በተደረገው የታሪፍ መደብ ጥያቄ ላነሱ የአሌክትሪክ ኃይል አመንጪ ግብዓት አምራቾችና ገጣጣሚ ድርጅቶች (ኢንዱስትሪዎች)፣ በታኅሳስ ወር መጀመሪያ የጉምሩክ ታሪፍ ማሻሻያ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች