Saturday, May 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የብርን አቅም ከውጭ የመገበያያ ገንዘቦች አኳያ የማዳከም ጉዳይ አከራካሪነቱ ቀጥሏል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ባለሙያዎች ብርን ማዳከም ይዞት ሊመጣ የሚችለው መዘዝ ከፍተኛ ነው ይላሉ

በሳምሶን ብርሃኔ

የብርን አቅም ከዶላርና ከሌሎች የውጭ መገበያያ ገንዘቦች አኳያ የማዳከም  ተገቢነት ባለሙያዎችን ማከራከሩን ቀጥሏል፡፡

እንደ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ያሉ ተቋማት የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም አቀፍ ገበያ የአገሪቱን ተፎካካሪነት ለመጨመር ብርን እንዲያዳክም ጫና እየፈጠሩበት ነው የሚሉ መረጃዎች እየተሠራጩ ሲሆን፣ ይህንንም ተከትሎ ጉዳዩ በማኅበራዊ የትስስር ገጾችና በሌሎች አውታሮች እያከራከረ ነው፡፡

ለመጨረሻ ጊዜ መንግሥት የብር አቅም እንዲዳከም (Devaluation) ውሳኔ ያስተላለፈው በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሥልጣን ዘመን ሲሆን፣ በወቅቱም ብር በ15 በመቶ እንዲዳከም ተደርጎ ነበር፡፡ ከዚያም በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር የውጭ ምንዛሪው ገበያ መሠረት በማድረግ (Depreciation) የብር አቅም እንዲዳከም ተደርጓል፡፡ ለአብነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ሲመጡ አንድ ዶላር 27 ብር አካባቢ የነበረ ሲሆን፣ በየዓመቱ ቢያንስ በ25 በመቶ እንዲዳከም ተደርጎ ከ53 ብር በላይ ደርሷል፡፡

በነባሩም ሆነ በአዲሱ የመንግሥት አስተዳደር የብርን አቅም የማዳከም ፖሊሲ ዓላማው፣ የአገሪቱን የወጪ ንግድ ለመጨመርና የገቢ ንግዱን ደግሞ ለመቀነስ ያለመ ነው፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት ብርን ካዳከመ በኋላ ይህንን ዓላማ ለማሳካት ሲቸገር ተስተውሏል፡፡ ባለፉት ሃያ ዓመታት ብር ከአምስት ጊዜ በላይ በመንግሥት ድንገተኛ ውሳኔ እንዲዳከም ቢደረገም፣ የወጪ ንግድ ገቢ ከሦስት ቢሊየን ዶላር ፈቅ ሊል አልቻለም፡፡ ምንም እንኳን ባለፈው በጀት ዓመት ወደ አራት ቢሊየን ዶላር ከፍ ቢልም፣  የገቢ ንግድ ወጪ ወደ 18 ቢሊየን ዶላር ከፍ ብሏል፡፡

ብርን የማዳከም ፖሊሲ ከወጭና ገቢ ንግድ አኳያ ያመጣው ለውጥ እምብዛም መሆኑን በመግለጽ፣ ከዚህ ዓይነቱ ዕርምጃ አገሪቱ ያተረፈችው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እንደሆነ ባለሙያዎች ያወሳሉ፡፡ በርግጥም መረጃዎች የሚያረጋግጡት ይህንኑ ድምዳሜ ነው፡፡ ዶላር፣ ፓውንድ፣ ዩሮና የመሳሰሉ የውጭ መገበያያዎች ከብር አኳያ ያላቸው ዋጋ በከፍተኛ መጠን በመጨመሩ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል፡፡ ከዘይትና ከስኳር አንስቶ እስከ የተለያዩ አልባሳቶች፣ እንዲሁም የተሽከርካሪዎች ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሳዩት ጭማሪ ባለፉት ሦስት ዓመት ከሃያ በመቶ ሳያልፍ፣ በኢትዮጵያ ከ150 በመቶ በላይ ጭማሪ ያሳዩበት ዋነኛ ምክንያት የብር አቅም መዳከም መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ መምህር ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር) በጉዳዩ ላይ ሐሳባቸውን በማጋራት ይታወቃሉ፡፡ በተደጋጋሚ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታና በተለያዩ ጊዜያት በትዊተር ገጻቸው ባሳፈሩት ሐሳባቸው፣ የብርን አቅም የማዳከም ዋጋ ግሽበትን ከማባባስ ባለፈ ሚና ሊኖረው አይችልም ይላሉ፡፡ የብርን አቅም ማዳከም የውጪ ንግድ ገቢን አይጨምርም፡፡ የገቢ ንግድ ወጪንም አይቀንስም የሚሉት ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር)፣ መንግሥት በምንም ዓይነት ሁኔታ የአይኤምኤፍን ምክር በመስማት የብርን አቅም ሊያዳክም አይገባም ሲሉ፣ ጥር 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል፡፡

ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር) የገለጹትን ሐሳብ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ተናግረው ነበር፡፡ የዛሬ አራት ዓመት ገደማ አዲሱ አስተዳደር ወደ ሥልጣን በመጣበት ወቅት የብርን አቅም ማዳከም የወጪ ንግድ ገቢን ከመጨመር አኳያ ያመጣው ለውጥ የለም ብለው የነበረ ቢሆንም፣ ከዚያ በኋላ መንግሥት ገበያ መር ብርን የማዳከም ፖሊሲ መከተሉ ብዙዎችን ያስገረመ ክስተት ነበር፡፡

ምንም እንኳን የብርን አቅም የማዳከም ጉዳይ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ሰሞኑን መነጋገሪያ ሆኖ ቢከርምም፣ መንግሥት ስለጉዳዩ ያለው ነገር የለም፡፡ በተለይም ይህን ዓይነት ዕርምጃ በከፍተኛ ሚስጥር የሚከወን እንደ መሆኑ መጠን፣ የመንግሥት ውሳኔ ምንም ይሁን ምንም ድንገተኛ ሊሆን እንደሚችል ከዚህ ቀደም የተወሰዱ ተመሳሳይ ዕርምጃዎች ያሳያሉ፡፡ የፋይናንስ ባለሙያ የሆኑት አምሐ ተፈራ (ዶ/ር) ብርን ማዳከም የመንግሥት ውሳኔ ሊሆን አይገባም ይላሉ፡፡

በሌላ በኩል ነጋዴዎች የምርቶችን ዋጋ የሚተምኑት በትይዩ ገበያ (ጥቁር ገበያ) ላይ ያለውን የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ከግምት ውስጥ በማስገባት በመሆኑ፣ መንግሥት የብርን አቅም ቢያዳክም የዋጋ ግሽበት ከማባባስ አኳያ ያለው ሚና በእጅጉ አናሳ ነው ሲሉ አንድ በተለያዩ የመንግሥት ፖሊሲዎች ላይ በአማካሪነት የተሳተፉ ባለሙያ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ትክክለኛው የብር ዋጋ በትይዩ ገበያ ላይ ያለው ነው ያሉት ባለሙያው፣ ‹‹ብር ያለ ቅጥ ዋጋው ተጋኗል፣ ስለዚህም ሊዳከም ይገባል፤›› ሲሉ ሞግተዋል፡፡

በተቃራኒው በተለይ ምርታማነት ሳያድግና ከውጭ የሚገቡ ነገር ግን በአገር ውስጥ በቀላሉ ሊተኩ የማይችሉ ምርቶችን በአገር ውስጥ የሚመረትበትን መንገድ መንግሥት ሳያመቻች፣ መንግሥት ብርን ማዳከም የለበትም የሚሉት አምሐ (ዶ/ር)፣ አሁን ባለው ሁኔታ ብር ከተዳከመ የዋጋ ግሽበትን ሊያባብሰው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ ከመጨመር አንፃር ሊያመጣው የሚችለው ለውጥ የለም የሚሉት አምሐ (ዶ/ር) ምርታማነትን ሳያሳድግ መንግሥት በውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ላይ ለውጥ ሊያደርግ አይገባውም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

በሌላ በኩል ያለፈው ዓመት መጨረሻ ድረስ ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ለመተግበር አስቦ የነበረው መንግሥት፣ በዚህ ረገድ ጊዜውን ከማራዘም ውጪ ለውጥ አለማድረጉ ታውቋል፡፡ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም (ዶ/ር)፣ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ሥርዓትን የመተግበር ጉዳይ አዲስ ነገር አይደለም ብለው፣ ሊተገበር ያልቻለው አንዳንድ ችግሮች ስለገጠመ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ የተለያዩ ምንጮች ለሪፖርተር እንዳረጋገጡት፣ ሁለተኛው የአገር በቀል ሪፎርም አጀንዳ ከያዛቸው ዋነኛ ግቦች ውስጥ አንዱ ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥ መተግበር ነው፡፡ ይህም በባንኮችና በትይዩ ገበያው መካከል ያለው የብር ዋጋ ከውጭ ምንዛሪዎች አኳያ ተመሳሳይ ይሆናል እንደ ማለት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች