ከባህላዊ ወርቅ አምራቾች ወርቅ ገዝተው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ በሚል ምክንያት፣ ከተቀማጭ ሒሳባቸው ስድስት ቢሊዮን ብር ባንቀሳቀሱ አቅራቢዎች ላይ ምርመራ ተጀመረ።
የወርቅ አቅራቢነት የሥራ ፈቃድ ከክልሎች በማውጣት ለብሔራዊ ባንክ ወርቅ የሚያቀርቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ባለፈቃዶች ባለፉት ጥቂት ወራት፣ ከተቀማጭ ገንዘባቸው ስድስት ቢሊዮን ብር ያንቀሳቀሱ ቢሆንም፣ ለብሔራዊ ባንክ ያቀረቡት የወርቅ መጠን አነስተኛ ከመሆኑም በላይ ጨርሶ ያላቀረቡ እንዳሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል።
ማንኛውም ግለሰብ በባንክ የሚገኝ ተቀማጭ ገንዘቡን ማንቀሳቀስ የሚችልበት አሠራርና ገደብ፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወጣ መሆኑን የጠቀሱት ምንጮቹ፣ በባንክ ተቀማጭ ያለው ማንኛውም ሰው በቀን ማውጣት የሚችለው የገንዘብ መጠን፣ እንዲሁም በእጁ ማንቀሳቀስ የሚችለው የገንዘብ መጠን ላይ ብሔራዊ ባንክ ገደብ መጣሉን ተናግረዋል።
ነገር ግን ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠው የገንዘብ ማንቀሳቀስ ገደብ በልዩ ሁኔታ የወርቅ ማቅረብ ፈቃድ ያላቸው ግለሰቦች ላይ እንዳይፈጸም መደረጉን፣ ይህ የሆነበትም ምክንያት የተመረተ ወርቅ ያለ ችግር ለብሔራዊ ባንክ መቅረብ የሚችልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እንደሆነ አስረድተዋል።
ይህ የብሔራዊ ባንክ ገደብ በወርቅ አቅራቢዎች ላይ ተፈጻሚ እንዳይሆን ሲደረግም፣ አቅራቢዎቹ ካንቀሳቀሱት የገንዘብ መጠን ጋር እኩል የሆነ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ የማቅረብ ኃላፊነት እንደሚወስዱ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም. አንስቶ ባሉት ጥቂት ወራት ውስጥ ስድስት ቢሊዮን ብር ያንቀሳቀሱት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወርቅ አቅራቢዎች፣ ለብሔራዊ ባንክ ወይም ብሔራዊ ባንክ ውክልና ለሰጠው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያቀረቡት ወርቅ ሁለት ቢሊዮን ብር ብቻ የሚያወጣ መሆኑን አክለዋል።
ሪፖርተር የተመለከተው አንድ ሰነድ እንደሚያመለክተው፣ በሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም. ብቻ 209 ወርቅ አቅራቢዎች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደቡብ ምዕራብ ዲስትሪክትና በዚህ ዲስትሪክት ሥር ከሚገኙ ቅርንጫፍ ባንኮች 1.28 ቢሊዮን ብር አንቀሳቅሰዋል።
አቅራቢዎቹ ከባህላዊ ወርቅ አምራቾች ወርቅ ገዝተው ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ በማለት 1.28 ቢሊዮን ብር ቢያንቀሳቅሱም፣ እስካሁን ድረስ ለብሔራዊ ባንክ ያቀረቡት የወርቅ መጠን 248 ሚሊዮን ብር ብቻ የሚያወጣ ነው።
ለአብነት ያህል 29.8 ሚሊዮን ብድር ያንቀሳቀሰ አንድ አቅራቢ እስካሁን ያቀረበው የወርቅ መጠን 0.85 ኪሎ ግራም ብቻ ሲሆን፣ የዚህም ዋጋ 3.06 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን ሰነዱ ያመለክታል። ይህም ማለት ወርቅ አቅራቢው ካንቀሳቀሰው ገንዘብ ውስጥ 26.3 ሚሊዮን ብሩን ለሌላ ዓላማ አውሎታል፣ አሊያም የገዛውን ወርቅ በሕገወጥ መንገድ ከአገር በማስወጣት ሸጦታል የሚል ጥርጣሬ ፈጥሯል።
በተመሳሳይ 15 ሚሊዮን ብር ያንቀሳቀሰ ሌላ አቅራቢ እስካሁኑ ወር ድረስ ያቀረበው የወርቅ መጠን 0.4 ኪሎ ግራም ብቻ ሲሆን፣ ያቀረበው ወርቅ ደግሞ 1.68 ሚሊዮን ብር ብቻ የሚያወጣ ነው። በመሆኑም ይህ አቅራቢ ካገኘው ካንቀሳቀሰው ገንዘብ ውስጥ 14 ሚሊዮን ብር ለሌላ ዓላማ አውሎታል፣ አሊያም ከአምራቾች የገዛውን ወርቅ በሕገወጥ መንገድ ከአገር አውጥቶ ሸጦታል ተብሏል። በሌላ በኩል ወደ 30 የሚጠጉ አቅራቢዎች በተጠቀሰው ሐምሌ ወር ውስጥ የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ ቢያንቀሳቅሱም፣ እስከ ዛሬ ድረስ ምንም ዓይነት ወርቅ አላቀረቡም። ለአብነት በሐምሌ ወር 33.9 ሚሊዮን ብር ያንቀሳቀሰ አንድ አቅራቢ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ወርቅ አላቀረበም።
በአጠቃላይ ከባህላዊ ወርቅ አምራቾች ወርቅ ገዝተው ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደቡብ ምዕራብ ዲስትሪክት ቅርንጫፍ ባንኮች 1.28 ቢሊዮን ብር ያንቀሳቀሱት አቅራቢዎች፣ 1.08 ቢሊዮን ብር የት እንዳደረሱት እንደማይታወቅ ሰነዱ ያመለክታል።
‹‹ይህ ሁኔታ የሚያሳየው የወርቅ ኮንትሮባንድ የደረሰበትን አሳሳቢ ደረጃ ነው። ስለሆነም መንግሥት ይህንን ሁኔታ ለመቆጣጠር በመወሰን የወንጀል ምርመራ ማካሄድ ጀምሯል፤›› ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የማዕድን ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት ከማዕድን ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከብሔራዊ ባንክ የተውጣጣ የባለሙያዎች የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩን የሥራ ኃላፊው አረጋግጠዋል።
በወርቅ ኮንትሮባንድ ንግድና ምርት ላይ ታዋቂ የሆኑ ሰዎች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ከብሔራዊ ባንክ የተገኘ አንድ የሰነድ መረጃ ያመለክታል። እነዚህ ታዋቂ ግለሰቦችም ከህንድ፣ ከቻይና፣ ከዓረብ አገሮች፣ ከሶማሊያና ከሌሎች አገሮች ዜጎች ጋር ትስስር ፈጥረው እንደሚንቀሳቀሱና ከእነዚህ የውጭ ዜጎችም ወደ አገር ውስጥ የባንክ ሒሳቦቻቸው ገንዘብ ሲተላለፍ መቆየቱን፣ ይህም በተጀመረው ምርመራ እንደተደረሰበት መረጃው ያመለክታል።
በተጨማሪም በ2015 በጀት ዓመት የመጀመርያ አምስት ወራት ብቻ፣ 32 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ወርቅ በሕገወጥ መንገድ ከአገር ሊወጣ ሲል ተይዞ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉን ሰነዱ ጠቁሟል።
|
|