ለኩላሊት ሕክምና ሆስፒታል ግንባታ ገቢ ማሰባሰቢያ የጎዳና ሩጫ ጥር 7ቀን 2015 ዓ.ም. እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡
በአዲስ አበባ ‹‹ለወገኔ እሮጣለሁ›› በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው ውድድሩ የሚገኘው ገቢ በአርቲስት ሰሎሞን ቦጋለ አስተባባሪነት ለሚገነባው የኩላሊት ሕክምና ሆስፒታል ግንባታ ይውላል ተብሏል፡፡
የአምስት ኪሎ ሜትር ውድድር መነሻውንና መድረሻው በዋሽንግተን አደባባይ አድርጎ እንደሚከናወን ጥር 2 ቀን በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫው ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ወጣቶች ቢሮ፣ ሬስ ፎር ኤቨር፣ ፊት ኮርነር እንዲሁም ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር ውድድር መሰናዳቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ከ2,000 በላይ ተካፋዮች ይሳተፉበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል፡፡
የኩላሊት ሕክምና ሆስፒታል ግንባታ ለማከናወን እንቅስቃሴ ላይ የሚገኘው ‹‹ኅብረት ለበጎ›› የበጎ አድራጎት ድርጅት፣ የሆስፒታል ግንባታውን ለማጠናቀቅ ከ14 በላይ ፕሮጀክቶች ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ የገለጸ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ የጎዳና ሩጫው አንዱ የገቢ ማሰባሰቢያ መንገዱ እንደሆነ ተገልጾ፣ በውድድሩ የከተማው ነዋሪ ተካፋይ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ማኅበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን አካቶ በሚከናወነው በዚህ ውድድር ላይ ለሚካፈሉ ተሳታፊዎች ከአሜሪካ ተሠርቶ የመጣ ቲሸርት መዘጋጀቱ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ለበጎ ዓላማ ሲባል በቅናሽ ዋጋ መቅረቡ ተጠቅሷል፡፡
‹‹ኅብረት ለበጎ›› የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት ከተመሠረተ አንድ ዓመቱ ሲሆን፣ ሆስፒታል ለመገንባት መሬት ከተረከበ ዓመት ከሦስት ወር እንዳለፈው የቦርድ ሰብሳቢው አርቲስት ሰሎሞን ቦጋለ በጋዜጣዊ መግለጫው አስረድቷል፡፡
ድርጅቱ ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ በገንዘብ ዕጦት የተቸገሩ በርካታ ሕፃናትና ጎልማሶች በአገር ውስጥ እንደሁም ከአገር ውጭ ማሳከም መቻሉ ተጠቅሷል፡፡
በዚህም መሠረት የተለያዩ የልብ ሕሙማንን በደቡብ አፍሪካ፣ ጀርመን፣ ህንድ፣ እንዲሁም አሜሪካ ሕክምናቸውን እንዲያደርጉ ድጋፍ ማድረግ መቻሉን የቦርዱ ሰብሳቢ አስታውሷል፡፡
ቀድሞ ታካሚዎች ወደ ተለያዩ አገሮች አምርተው እንዲታከሙ ድጋፍ ሲያደርግ የቆየ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ፣ በሒደት ግን ሆስፒታሉን ለመገንባት ውጥን ወጥኖ መነሳቱን ተከትሎ፣ ለገጣፎ፣ ለገዳዲ 60 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ተረክቦ ግንባታ ለመጀመር እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡
የመሬት ርክክቡ ከተጠናቀቀ በኋላ ከክልሉ መንግሥት ጋር በመተባበር 90 ሚሊዮን ብር ካሳ ከተከፈለ በኋላ፣ መሠረታዊ ጉዳዮች ተጠናቀው ግንባታ ለመጀመር ከጫፍ መደረሱን የቦርድ ሰብሳቢው አርቲስት ሰሎሞን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ አብራርቷል፡፡