Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምየብራዚል ፕሬዚዳንት ተቃዋሚዎችና የዴሞክራሲ ደጋፊዎች በብራዚል

የብራዚል ፕሬዚዳንት ተቃዋሚዎችና የዴሞክራሲ ደጋፊዎች በብራዚል

ቀን:

የብራዚል ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ ከተመረጡ ሁለት ወራት ሊሞላቸው ጥቂት ቀናት ሲቀር ነበር የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዣየር ቦልሶናሮ ደጋፊዎች ሳኦ ፖሎን በተቃውሞ ያጥለቀለቁት፡፡

አራት ሺሕ የሚደርሱ የቦልሶናሮ ደጋፊዎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች በባስ እየተጓዙ ወደ ሳኦፖሎ የገቡት ከተቃውሞው አንድ ቀን አስቀድሞ ታኅሳስ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ቢሆንም፣ በወቅቱ ጉዳዩን ማስቆም ባለመቻሉ፣ በከተማዋ ከሚገኙ ደጋፊዎቻቸው ጋር በመቀላቀል በማግስቱ ብራዚልን ያስደነገጠ ተቃውሞ አድርገዋል፡፡

አንዳንዶች ‹‹መፈንቅለ መንግሥት ነው›› ብለው እስኪገልጹት ድረስ የተደረገው ተቃውሞ በጎዳና ላይ ያበቃ አልነበረም፡፡ ይልቁንም የደኅንነት አባላት ጭምር እስኪተቹ ድረስ ተቃዋሚዎች ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥትን፣ የአገሪቱን ኮንግረስና ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሕንፃዎች ጥሰው ገብተዋል፣ ንብረት አውድመዋል፡፡

- Advertisement -

አልጀዚራ በተቃውሞ ወቅት የተቀረፁ ምሥሎችን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የቦልሶናሮ ደጋፊዎች የሕንፃዎቹን መስታዎት ሰባብረዋል፣ በኮንግረሱና በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውስጥ የሚገኙ ፈርኒቸሮችን አውድመዋል፡፡

አረንጓዴና ቢጫ ቀለም እንዲሁም የቦልሶናሮ መንግሥት መገለጫ የሆነው ዓርማ ያለበትን ሰንደቅ ዓላማ በመልበስ የፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥትን ወረዋል፡፡

ለሦስት ሰዓታት ያክል በቆየው ተቃውሞ የደረሰው ውድመት መጠን ባይታወቅም፣ ከ1,500 በላይ ተቃዋሚዎች መታሰራቸውንም አሥፍሯል፡፡

በጥቅምት 2015 ዓ.ም. የፕሬዚዳንትነት ወንበሩን በምርጫ ያሸነፉት ሉላ፣ ታኅሳስ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ነበር ቃለ መሃላ የፈጸሙት፡፡ ሆኖም ከሳምንት የዘለለ ዕድሜ ሳያስቆጥሩ በሺዎች በሚቆጠሩ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ደጋፊዎች ተቃውሞ ተነስቶባቸዋል፡፡ ሆኖም ተቃውሞው ከተለያዩ አቅጣጫዎች ‹‹ኢ-ዴሞክራሲያዊ ነው›› ተብሏል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)፣ አሜሪካ፣ አውሮፓና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም አውግዞታል፡፡

በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የዴሞክራሲ አቀንቃኞችም የቦልሶናሮ ደጋፊዎችን ተቃውመው ጥር 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ሠልፍ አድርገዋል፡፡

ቢቢሲ እንደሚለው፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ደጋፊዎችን በመቃወም በሳኦፖሎ በተደረገ ‹‹ሠልፍ ቦልሶናሮ ወደ እስር ቤት መግባት አለባቸው›› የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

ሉላ በመባል በስፋት የሚታወቁት የ77 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ፣ ተቃዋሚዎች በተለይ በሦስቱ የመንግሥት ከፍተኛ ተቋማት ላይ ያደረሱትን ጉዳት ‹‹የሽብር ድርጊት›› ሲሉት፣ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዴሞክራሲ አቀንቃኞችም ‹‹ጉልበታቸውን ዴሞክራሲን ለማጥፋት የሚጠቀሙትን እናወግዛለን›› ብለዋል፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በብራዚል ከሁለት ወራት በፊት የተደረገው ምርጫ ተቀባይነት የለውም ቢሉም፣ በርካታ ሕዝቦች በምርጫው፣ በመንግሥትና በዴምክራሲ ያምናሉ ሲሉም የዴሞክራሲ አቀንቃኞች አክለዋል፡፡

ጽንፈኝነት ትልቁ ችግር መሆኑን፣ ሁሉም የራሱን ሐሳብ ያራምዳል እንጂ በውይይት፣ በመቀራረብና ችግሩን መፍታት በሚችልበት ዙሪያ ውይይት አለመደረጉንም አክለዋል፡፡

ከሁለት ወራት በፊት በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤቱን ያልተቀበሉት የ67 ዓመቱ ቦልሶናሮ በታኅሳስ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ሥልጣን ለተከታያቸው ሉላ ከማስረከባቸው አስቀድመው ወደ አሜሪካ ያቀኑ ሲሆን፣ በሕመም ምክንያት ፍሎሪዳ በሚገኝ ሆስፒታል መግባታቸው ታውቋል፡፡

ተቃውሞ ከተቀሰቀሰ ከስድስት ሰዓታት በኋላም የሳቸው ደጋፊዎች ያደረሱትን ጉዳት ያወገዙ ሲሆን፣ ‹‹ተቃውሞውን አበረታተዋል›› ተብለው ለሚነሳባቸው ጥያቄም ኃላፊነት እንደማይወስዱ በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡ ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የብራዚሊያን ገዥ ኢባኒስ ሮቻ ለ90 ቀናት ከሥራ አግዷል፡፡ የብራዚሊያ የደኅንነት ዋና ፀሐፊ አንደርሰን ቶሪስም ከሥራ ተሰናብተዋል፡፡ 

በቦልሶናሮ ደጋፊዎች የተደረገውን ተቃውሞ በአገር ውስጥ ብቻ ያሉት ሳይሆኑ ከውጭ ያሉም እየተቃወሙ ነው፡፡ እሳቸው ለሕክምና ፍሎሪዳ ቢሆኑም፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ሰውየውን አሳልፈው እንዲሰጡ መጠየቃቸውን ቢቢሲ አስፍሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...