Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየጤና መድን አገልግሎት ትግበራና ማነቆዎች

የጤና መድን አገልግሎት ትግበራና ማነቆዎች

ቀን:

ወ/ሮ የዓለምነሽ ወርቁ የግላኮማ ሕመምተኛ ናቸው፡፡ ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ በመሆኑ በታመሙ ቁጥር ወጪው መቀነታቸውን ያስፈታቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በስሚ ስሚ ያገኙት መረጃ ግን ሁኔታዎችን መቀየሩን ይናገራሉ፡፡

በጤና መድን አገልግሎት ተመዝግበው ሕክምና ማግኘት መጀመራቸው ለሕክምና ያወጡት የነበረውን ወጪ አስቀርቶላቸዋል፡፡

 እንደ ወ/ሮ የዓለምነሽ ለመድኃኒትና ለምርመራ ምንም ገንዘብ አያወጡም፡፡ የጤና መድን አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆናቸውም ደስተኛ ናቸው፡፡ ሆኖም ከከነማ ፋርማሲ መድኃኒትና ተገቢውን አገልግሎት ማግኘት ችግር ሆኗል ይላሉ፡፡

አንዳንዴ የምዝገባ ዕድሳት አድርገውም ስማችሁ አልመጣም እንደሚባሉ፣ የግላኮማ መድኃኒት ለሦስት ወራት የሚሰጥ ቢሆንም፣ በአቅርቦት እጥረት ምክንያት ለአንድ ወር ብቻ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ እንደዚህም ሆኖ ከጤና መድን ያገኙት ዕፎይታ እንደሚልቅ ይገልጻሉ፡፡  

የጤና መድን አገልግሎት አሉብኝ ብሎ ከዘረዘራቸው ችግሮች ውስጥ አንዱ የመድኃኒት እጥረት ነው፡፡

በሌላ በኩል የጤና ተቋማት የአገልግሎት ጥራት መጓደልና የባለሙያዎች ሥነ ምግባር ጉድለት በስፋት የሚታዩ ችግሮች መሆናቸውን ከኢትዮጵያ የጤና መድን አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

ከጤና መድን ጋር ተያይዞ በጤና ተቋማት በስፋት የሚታየውን ችግር ይቀርፋል፣ አገልግሎቱንም በበላይነት ይቆጣጠራል የተባለ የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ብሔራዊ ምክር ቤት ከሳምንት በፊት በይፋ ሥራውን ጀምሯል፡፡

ምክር ቤቱ በዋነኛነት የአባላት መዋጮን የመተመን፣ ጥናት የማድረግና ብልሹ አሠራርን የመገምገም ተግባር የተሰጠው ሲሆን፣ በዓመት ሁለት ጊዜ እየተገናኘም ይመክራል፡፡

የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ የጤና አገልግሎት ሽፋን 90 በመቶ ደርሷል፡፡ በኢትዮጵያ አማካይ የዕድሜ ጣሪያ ከነበረበት ከ50 በታች ወደ 66 ዓመት ደርሷል፡፡

ለዚህም የጤና መድን አገልግሎት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን፣ የአገልግሎቱ መጀመር በዋነኛነት ከኪስ በሚወጣ የሕክምና ወጪ ሳቢያ ዜጎች ለከፋ ድህነት እንዳይጋለጡ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የጤና ወጪ በመንግሥት 34 በመቶ፣ ከዜጎች 30 በመቶ፣ 32 በመቶ ከረጂ ተቋማትና 2.5 በመቶ በኢንሹራንስ የሚሸፈን መሆኑን በመጠቆም፣  ከዜጎች የሚወጣው የሕክምና ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ፣ በጤና መድን የሚሰበሰበው መዋጮ ዜጎች ለከፋ ድህነት እንዳይጋለጡ እንደሚያግዝ አክለዋል፡፡

የጤና መድን ሥርዓት የመተግበሩ ዓላማ ዜጎች ከከፍተኛ የሕክምና ወጪ ጫና ድነው ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት በፍትሐዊነትና ቀጣይነት ባለው መንገድ እንዲያገኙ ለማስቻል ነውም ብለዋል፡፡

የተሻለ ገቢ ያለው ዝቅተኛ ገቢ ያለውን፣ ጤነኛው ታማሚውን የሚደጉምበትን ሥርዓት በመፍጠር የዜጎችን የቆየ የመደጋገፍ ባህል እንደሚያጠናክር ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የጤና መድን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍሬሕይወት አበበ፣ የጤና መድን የሙከራ ትግበራ በ2003 ዓ.ም. እና 2004 ዓ.ም. በአራት ክልሎች (በትግራይ፣ በአማራ፣ በደቡብና በኦሮሚያ) በተመረጡ 13 ወረዳዎች መጀመሩን አስታውሰው፣ ለሁለት ዓመታት ከተተገበረ በኋላ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን ገልጸዋል፡፡

የተገኘው ውጤት አመርቂ በመሆኑ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ለአሥር ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል፡፡

በዚህም ከ45 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የጤና መድን አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ያልሆኑትን ወደ ትግበራው ለማስገባት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ምንም እንኳን በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ ቢሆኑም፣ በርካታ ችግሮች እንደነበሩ፣ ከዚህም ውስጥ የአገልግሎት ጥራትን፣ የባለሙያ ሥነ ምግባር ጉድለትንና የመድኃኒት እጥረትን በዋቢነት አንስተዋል፡፡

በተለይ አገልግሎቱን በሚመሩ ባለድርሻዎች የአመራር ቁርጠኝነት አለመኖር፣ እርስ በርስ አለመደጋገፍና ገቢን መሠረት ያደረገ መዋጮ አለመኖር ሌላው ችግር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለይም የኢትዮጵያ የጤና መድን አገልግሎት በመረጃ አያያዝና አደረጃጀት ወደኋላ የቀረ በመሆኑ፣ ትግበራው ከዚህ በበለጠ እንዳይጓዝ ምክንያት ሆኗል ተብሏል፡፡

ይሁን እንጂ በአሥር ዓመታት ውስጥ የበርካቶችን ችግሮች የቀረፈ አገልግሎት መስጠቱን፣ ከዚህ ውስጥ የነፍስ ወከፍ የጤና አገልግሎት አጠቃቀም ከነበረበት 0.3  ወደ 2.3 ማደጉንና ከ45 ሚሊዮን የጤና መድን አገልግሎት ተጠቃሚ በ2013 ዓ.ም. 4.8 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡ ተገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ምንም አቅም የሌላቸው ወይም ዓመታዊ መዋጮ መክፈል የማይችሉ ስምንት ሚሊዮን ያህል ዜጎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ናቸው፡፡

የመድን አገልግሎቱ የመንግሥት ሠራተኞችንና ጡረተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን፣ የአገልግሎት መዋጮው ከመንግሥት ሠራተኞች የደመወዛቸውን ሦስት በመቶ እንዲሁም ከጡረተኞች አንድ በመቶ የሚሰበሰብ ነው፡፡

አገልግሎቱ የተጀመረው በመንግሥት ሠራተኞችና ጡረተኞች ላይ ይሁን እንጂ ሌሎች ለፔሮል የሚከፍሉ ወይም ከአሥር በላይ ሠራተኞች ያሏቸውን ተቋማት ሠራተኞች ወደ አገልግሎቱ እንደሚገቡ ተገልጿል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...