Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የመሬት ይዞታን በመረጃ ቋት የማንበር ትልም

በመንግሥታዊ ተቋማትና በልማት ድርጅቶች ሥር የሚገኙ ይዞታዎች መረጃቸው በማዕከል የተደራጀ ባለመሆኑ የተነሳ በርካታ ሕገወጥ ተግባራት ሲፈጸሙ ይታያል፡፡ በተለይም በተቋማት ሥር የሚገኙ አንዳንድ ሹማምንት ሥልጣናቸውን ተጠቅመው የማኅበረሰቡን ሀብት ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው ሲወሳ ሰነባብቷል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን ሁሉ ተግዳሮቶች ለመቅረፍ የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ይናገራል፡፡ ወ/ሮ ሌንሳ መኰንን የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የተቋሙን ሥራ አስመልክቶ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን እንዴት ተመሠረተ?

ወ/ሮ ሌንሳ፡- ተቋሙ የተመሠረተበት ዋና ዓላማ በመንግሥታዊ ተቋማትና በልማት ድርጅቶች ሥር የሚገኙ ይዞታዎች የመረጃ ቋት እንዲኖራቸው ለማድረግ ታልሞ የተቋቋመ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ ከተቋቋመ ከሁለት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በተለይም በመንግሥት ሥር ያሉ ተቋማት ‹ምን ያህሉ ለልማት ውለዋል?› የሚለውን ለመለየት መንግሥት አብዛኛውን ጊዜ ችግር ውስጥ ሲገባ ይታያል፡፡ ይህንንም ችግር ለመታደግ ተቋሙ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ የፌዴራል መንግሥት በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ያሉትን የመሬት ይዞታዎች ምን ያህል አልምቷል? አላለማም? የሚለውን ለማወቅ ወጥ የሆነ መረጃ የለም፡፡ በዚህም የተነሳ ሕገወጥ የመሬት ወረራ እንዲከሰት መንገድ ከፍቷል፡፡ ተቋሙም እነዚህን ክፍተቶች ለመቀልበስ ለመንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ተጠሪ የሆኑ ተቋማትና የልማት ድርጅቶች ይዞታዎቻቸው የሚመዘገብበት በማዕከል የተደራጀ የመረጃ ቋት እንዲኖር ኮርፖሬሽኑ ያለ የሌለ አቅሙን አውጥቶ እየሠራ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እስካሁንም በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ፣ በሐረርና በሶማሌ ላይ ተቋሙ በቴክኖሎጂ በመታገዝ የመሬት ይዞታዎች የመረጃ ቋት እንዲኖራቸው ማድረግ ችሏል፡፡ ይህንንም በቀጣይ በሌሎች ከተሞች ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት አገልግሎቶችን ትሰጣላችሁ?

ወ/ሮ ሌንሳ፡- ተቋሙ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች በሦስት ይከፈላሉ፡፡፡ አንደኛው የፌዴራል ተቋማት የያዙት የመሬት ይዞታዎች በአጠቃላይ ኦዲት ማድረግና ለያዟቸው  ይዞታዎች ካርታ በማዘጋጀት ወደ ካዳስተር ማፕ ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ያልለሙ፣ የለሙና በልማት ላይ ያሉ ቦታዎች በመረጃ በማፅዳት ለውሳኔ እንዲቀርቡ ያደርጋል፡፡ ለውሳኔ ሲቀርቡም ተቋሙ ምን ላይ እናልማ? የትኛውንስ ይዞታ በምን ዓይነት ሁኔታ በምን ዓይነት ዘርፍ እናልማው? የሚለውን ነገር የመለየት ሥራን ተቋሙ እየሠራ ይገኛል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ተቋሙ የማያለማውን የመሬት ይዞታ፣ ምን ዓይነት ልማት ላይ ነው? የሚለውን ለማወቅ የመረጃ ቋት ውስጥ እንዲቀመጥ የሚያደርግ ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት የተለያዩ የውሳኔ ሰጪ አካላት መረጃውን በመጠቀም ወደ ውሳኔ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ በሌላ በኩል በጆይንት ቬንቸር ጋር በመሆን ከውጭ አገር የሚመጡ ትልልቅ ኢንቨስተሮች በመታገዝ በኢትዮጵያ ደረጃ የሌሉ አሠራሮችን ከአገር በቀል ኢንቨስተሮች ጋር በማስተሳሰር ይዞታዎችን የማልማት ሥራ የሚሠራ ይሆናል፡፡  

ሪፖርተር፡- ሕገወጥ የመሬት ወረራ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ ተቋሙ ምን እየሠራ ነው?

ወ/ሮ ሌንሳ፡- እንዳልከው ሕገወጥ የመሬት ወረራን መከላከልና ትክክለኛ የሆነ የመረጃ ቋት እንዲኖር ማድረግ የተቋሙ ዋና ዓላማው ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሕገወጥ የመሬት ወረራም ከሚከሰትባቸው ውስጥ አንዱም የፌዴራል ተቋማት የያዟቸው የመሬት ይዞታዎች ናቸው፡፡ እነዚህም ይዞታዎች አብዛኛውን የማኅበረሰብ ክፍል እንደማያውቃቸውና በርካታ ሕገወጥ የሆነ ተግባራት ሲፈጸምባቸው ማየት ከተለመደ ቆይቷል፡፡ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ተቋሙ ሊቋቋም ችሏል፡፡ በፌዴራል ተቋማት ሥር ያሉ ይዞታዎችም በቴክኖሎጂ የተደገፉና የመረጃ ቋት እንዲኖራቸው ለማድረግ ተቋሙ ያላሳለሰ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህንንም ተፈጻሚ ለማድረግ ከኢንሳና ከሌሎች ተቋሞች ጋር እየሠራ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የሕዝብ ሀብትን ለመታደግ እንዲሁም ያሉትን አሠራሮች በመረጃ ቋት ሥር ለማስፈን እየተሠራ ያለው ሥራ ገና ቢሆንም፣ ተቋሙ ወደፊት ወጥ የሆነ አሠራር የሚዘረጋ ይሆናል፡፡ በዘርፉም ትኩረት ተደርጎ ከተሠራ በርካታ ሕገወጥ የመሬት ይዞታዎችን መታደግ ይቻላል፡፡  

ሪፖርተር፡- ከሌሎች ተቋሞች ጋር በቅንጅት እየሠራችሁ መሆኑን ተናግራችኋል፡፡ ምን ያህል ለውጥ አምጥታችኋል?

ወ/ሮ ሌንሳ፡- በርካታ ሥራዎቻችንን የምንሠራው ከተለያዩ የግል ተቋማት ጋር ነው ማለት ይቻላል፡፡ በዋናነት ግን ከስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ጋር እየሠራ ይገኛል፡፡ ከተለያዩ ተቋማት መረጃ ሲሰባሰብ ለምን መረጃው እንደሚሰበሰብና ካርታውም እንደሚሠራ በተቋማት በኩል በቂ የሆነ ግንዛቤ ስለሌለ፣ ይህንን ከአጋር ተቋማችን ጋር በመሆን እየሠራን ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት እያንዳንዱ መረጃን የተጣራ ለማድረግ፣ ከክልሎች ጋር ሆኖ በቅንጅት እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት የመንግሥት ይዞታዎች የመሬት አጠቃቀምና የመሬት ምዝገባ ምን ይመስላል? ምን ያህል ተጠቅመውበታል? የሚለውን ለመለየት ኮርፖሬሽኑ ከተለያዩ ተቋሞች ጋር እየሠራ ይገኛል፡፡ ይህም ሕገወጥ የመሬት ይዞታዎችን ከመታደግ ባለፈ በፌዴራል መንግሥት ሥር የሚገኙ ተቋማት የመረጃ ቋት እንዲኖራቸው ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት ተችሏል፡፡ በዘርፉም ቀስ በቀስ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ ለውጦችን ለማምጣት ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በቀጣይነት የሚሠራ ይሆናል፡፡ ይህ ከሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚስተዋለውን ሕገወጥ የመሬት ይዞታዎች ወረራን በቀላሉ ማስቀረት ይቻላል፡፡   

ሪፖርተር፡- እስካሁን በምን ያህል ከተሞች ላይ ተደራሽ ሆናችኋል?

ወ/ሮ ሌንሳ፡- በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ፣ በሐረሪና በሶማሌ ክልል ተደራሽ ሆነናል፡፡ ይሁን እንጂ በቀጣይ በሁሉም የክልል ከተሞች ተደራሽ ለመሆን ከእያንዳንዳቸው የክልል መስተዳድር ኃላፊዎች ጋር እየተነጋገርን ይገኛል፡፡ በቅርቡም ከኦሮሚያ ክልል ጋር ተነጋግረን ጨርሰናል፡፡ በዚህም መሠረት ወደ ሥራ የምንገባ ይሆናል፡፡ በእርግጥ አብዛኛውን ጊዜ እንደዚህ ዓይነት ሥራዎችን ስንሠራ ረዥም ጊዜ ያስፈልገናል፡፡ ነገር ግን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በፍጥነት ወደ ሥራ በመግባት በተቋማት እየተፈጸመ ያለውን ሕገወጥ የመሬት ይዞታዎች መታደግ ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም ለማድረግ ኮርፖሬሽኑ ከተለያዩ ተቋሞች ጋር በጋራ የሚሠራ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን ለመሥራት አስባችኋል?

ወ/ሮ ሌንሳ፡- በቀጣይ ትልቁ ሥራችን የሚሆነው ቅድም የጠቀስኩልህ ሦስት ዋና ዋና መርሐ ግብሮችን በመጠቀም፣ በተለያዩ የክልል ከተሞች መድረስ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ከጥር 18 እና 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ኢንተርናሽናል ፎረም በአዲስ አበባ ለማካሄድ ዕቅድ ይዘናል፡፡ ፎረሙም እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ፈሰስ የሚደረግበት ሲሆን፣ ፎረሙ የሚካሄደው በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም ይሆናል፡፡ ፎረሙም የሚካሄድበት ዋና ዓላማ በፌዴራል ተቋማት ሥር የሚገኙ ይዞታዎችን በጤና፣ በቤቶች ልማት፣ በቱሪዝም፣ በአይሲቲና በትምህርት ላይ መሠረት ያደረጉ ኢንቨስትመንቶች ወደ ከተሞች ለማምጣት ያለመ ነው፡፡ ይህንንም ማድረግ ከተቻለ በርካታ የልማት ይዞታዎችን ከሕገወጥ አሠራር እንዲወጡ ማድረግ ይቻላል፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በአሁኑ ወቅት ከ21 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ሰብዓዊ ዕርዳታ ይፈልጋል›› አቶ አበራ ሉሌሳ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ምክትል ጸሐፊ

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ላለፉት 89 ዓመታት በመላ አገሪቱ የሰብዓዊነት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በድርቅ፣ በበሽታና በግጭት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የምግብ፣ የመጠለያ፣ የመድኃኒትና የ24 ሰዓት...

ከቢሻን ጋሪ እስከ ዶባ ቢሻን እንክብል

ዶባ ኢንዱስትሪያል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሦስት ዓመታት በላይ ጥናትና ምርምር ያደረገበትንና ለገበያ ያበቃውን ዶባ-ቢሻን እንክብል የውኃ ማከሚያ...

ለሴቶች ድምፅ ለመሆን የተዘጋጀው ንቅናቄ

ፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በፆታ እኩልነት፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲሁም የሴቶችን ማኅበራዊ ችግር በማቃለል ዙሪያ በተለያዩ ክልሎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ...