Monday, May 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩና ምርታቸውን ያላስመዘገቡ ባለሀብቶች ምርቶቻቸውን መላክ አይችሉም

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በውልና በኢንቨስትመንት እርሻ የለማ ለወጪ ንግድ የሚቀርብ ሰሊጥ መጠንና የኮንትራት ውል በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ያላስመዘገቡ ላኪዎች ከታኅሳስ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በኋላ ምርታቸውን ማስመዝገብ እንደማይችሉ ተገለጸ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባወጣው ማስታወቂያና ይህንን እንዲያስፈጽም ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ እንዳስታወቀው በውልና በኢንቨስትመንት እርሻ የለማ ምርትን በሚመለከት በወጣው መመርያ መሠረት ምርታቸውን ያላስመዘገቡና ማረጋገጫ ያላገኙ ላኪዎች ምርታቸውን መላክ የማይችሉ መሆኑን ያመለክታል፡፡

በመመርያው መሠረት በውልና በኢንቨስትመንት እርሻ የለማና የተሰበሰበ የሰብል ምርት መጠን መረጃ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለሚኒስቴሩ ሲቀርብ እንዲሁም ምርቱ በምርት ገበያው መረከቢያ ማዕከል ቀርቦ በትክክል የተለካ የምርት መጠንን የሚገልጽ  ማረጋገጫ መረጃ ማቅረብም ይጠበቅባቸዋል፡፡

በመሆኑም በዚህ ድንጋጌ መሠረት የተሰጠው የጊዜ ገደብ የምርት መጠኑን አስታውቀው ያላስመዘኑ እንዲሁም ያላሳወቁ አስመራቾችና ላኪዎች ቀነ ገደቡ የተጠናቀቀ በመሆኑ ምርት ገበያው የሚዛን አገልግሎት እንዳይሰጥ ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡  

እንደሚኒስቴሩ ገለጻ በውልና በኢንቨስትመንት እርሻ የለማ የሰሊጥ ምርት ይዞ የሚቀርብ ካለ አገልግሎቱ የማይሰጠው መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በመመርያው መሠረት አስመራች ከአምራች የተረከበውን ምርት በአካባቢው ወደሚገኝ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቀርቦ መጠኑን ሳያረጋግጥ ወደ ግብይት ማቅረብ የተከለከለ መሆኑን የሚደነግግ በመሆኑ ምርታቸውን ማስመዝገብ ያልቻሉ ነጋዴዎች መላክ አይችሉም ተብሏል፡፡

በመሆኑም ሚኒስቴሩ የሰሊጥ ምርት ግብይት ቀነ ገደብ የተጠናቀቀ መሆኑን በመጥቀስ ከዚህ በኋላ መስተናገድ አይችሉም የሚለው ትዕዛዝን በተመለከተ የኢትዮጵያ ጥራጥሬ የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማኅበር ትናንት ባካሄደው ስብሰባ በአግባቡ የሚሠሩ የሰሊጥ ነጋዴዎች ስላሉ እነዚህን መደገፍ ስለሚገባ ሚኒስቴሩ የአንድ ወር ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጥ ውሳኔ ማሳለፉ ታውቋል፡፡

የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤዲኦ አብዲ እንደገለጹት ሚኒስቴሩ ሕጋዊ የሆነ አሠራር ለመተግበር ትክክል ቢሆንም የተሰጠውን የጊዜ ገደብ በማራዘም ትክክለኛ ነጋዴዎች እንዳይጎዱ ማድረግ ተገቢ ስለመሆኑ ማኅበሩ ያምናል፡፡

በዚህ ውሳኔ መሠረትም ማኅበሩ የቀነ ገደብ ማራዘሚያው ይሰጠው ዘንድ በዛሬው ዕለት ደብዳቤ ያስገባል ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ ኤዲኦ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ባወጣው መመርያ መሠረት በውልና በኢንቨስትመንት እርሻ የለማ ምርት ተብሎ እየተመዘገበ ያለው መጠን እጅግ የተጋነነ ሆኖ መኘቱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

እንደ ምንጮቻችን ገለጻ በመላ አገሪቱ አለ ተብሎ ከሚታሰበው ምርት በላይ አስመርተናል ተብሎ ምዝገባ የተደረገ ሲሆን ይህም የሌላቸውን ምርት በማስመዝገብ ከገበያ በመግዛት ለመላክ የሚደረግ ሕገወጥ ሥራ ለመሥራት የታሰበ መሆኑን ያመለክታል ብለዋል፡፡ ከማኅበሩ የሥራ ኃላፊዎች መገንዘብ እንደተቻለውም አለ ተብሎ እስካሁን የተመዘገበው የሰሊጥ ምርት መጠን በእጅጉ የተጋነነ ሲሆን ሕገወጥ አሠራር ስለመኖሩ የሚያመለክት እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

እንደ ምንጮች ገለጻ ከሆነ በዚህ የምርት ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ በተጠቀሰው መንገድ የተመረተው አጠቃላይ ሰሊጥ 200 ሺሕ ቶን ይሆናል ተብሎ የተገመተ ሲሆን ምርቱ አለኝ ብለው ያስመዘገቡት ግን 400 ሺሕ ቶን በመሆኑ ይህ ልዩነት መፈጠሩ በራሱ በዚህ ግብይት ውስጥ ችግር ያለመሆኑን ያሳያል ተብሏል፡፡

እንዲህ ያሉ ችግሮች ቢኖሩም በትክክል ሕጋዊነትን ጠብቀው ምርቱን ለማቅረብ የሚችሉ ግን መጎዳት ስለሌለባቸው ለእነዚህ ተብሎ ቀነ ገደቡ እንዲራዘም የሚሹ መሆኑን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ነጋዴዎቹ ለምን እንዳላቀረቡ ባሰባሰቡት መረጃም ሰባት የሚሆኑ ነጋዴዎች የሎጂስቲክና የመሳሰሉ ችግሮች በቀነ ገደቡ ያላቸውን ምርት ማስመዝገብ አላስቻለንም በማለታቸው ተጨማሪ ጊዜ ተሰጥቶ ምርቱ በሕጋዊ መንገድ እንዲገበያይ የማራዘሚያ ጥያቄ እንደሚቀርብ ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ግን የሰሊጥ ምርት በአሁኑ ወቅት በተሻለ ሁኔታ እየተገበያየ መሆኑን የሚያመለክተው ማኅበሩ ሕገወጥነትን ለመከላከል እነርሱም የሚተጉ ስለመሆናቸው ተገልጿል፡፡

በውል ወይም በኢንቨስትመንት እርሻ የተመረቱ ምርቶችን በማስመዝገብ ያለማውጣት በመመርያው መሠረት የተከለከለ በመሆኑ ከዚህ በኋላ የሚቀርቡ ምርቶች ካሉ ሚኒስቴሩ አስተዳደራዊ ዕርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡

ከመመርያው ውጪ ምርት ይዘው የተገኙ ካሉም ሕጋዊ ዕርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚችል ካገኘነው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሚኒስቴሩ በውልና በኢንቨስትመንት እርሻ የለማ ምርት የግብይት አፈጻጸም መመርያ ቁጥር 929/2015ን ያወጣበት አንዱና ዋነኛ ዓላማ በውልና በኢንቨስትመንት የተመረቱ ምርቶች ግብይት ሥርዓት ውስጥ የሚታዩ ሕገወጥ ድርጊቶችንና የሚቀርብ የተዛባ የምርት መረጃዎችን በመከላከል ፍትሐዊና በውድድር ላይ የተመሠረተ ግብይት ሥርዓትን በማሳለጥ በወጪ ምርቶች ለወጪ ገበያ በማቅረብ የገቢ ግኝትን ማሳደግ በማስፈለጉ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች