Wednesday, February 28, 2024

አደጋ የተደቀነበት የሐሳብ ነፃነት በኢትዮጵያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹ሐሳብ ሁሌም ቢሆን መውጫ መንገድ አጥቶ አያውቅም፤›› የሚለውን ብዙዎች ይጋሩታል፡፡ ሚዲያ ወይም መደበኛ የኮሙዩኒኬሽን ዘዴዎችን ብቻ ሳይሆን፣ እጅግ በርካታ የሐሳብ ፍሰት መንገዶች እንዳሉም ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ሙዚቃ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ሥነ ጥበብ፣ የባህል ክዋኔዎች፣ አልባሳትና መዋቢያዎች የመሳሰሉት ሁሉ የሐሳብ መፍሰሻ መንገዶች እንደሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ እጅግ ያደገው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ደግሞ የሐሳብ መፍሰሻ አማራጮችን እያሰፋ መሄዱ ነው የሚነገረው፡፡

ያም ቢሆን ግን መንግሥታት ወይም ጉልበት ያላቸው የሐሳብ ነፃነት ላይ ለምን አፋኝ የሆኑ ሕጎችን ይደነግጋሉ? የሚለው ጉዳይ ሁሌም ቢሆን ሲያከራክር ነው የሚታየው፡፡ በኦስሎ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ምሁሯ ክሪስቲን ስኬር ኦርጌሬት (ዶ/ር) እ.ኤ.አ. በ2008 ያቀረቡት ጥናት ሐሳብ የፈለገውን ያህል ቢታፈንም፣ መውጫ መንገድ አጥቶ አያውቅም የሚለውን ሐሳብ አጉልተው ያወሳሉ፡፡

ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮን) እንደ መነሻ ያደረጉት የሚዲያ ምሁሯ ክሪስቲን፣ ‹‹መንግሥት ቴዲ አፍሮን ፖለቲካ ዘፈነ ብሎ በሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ሙዚቃው እንዳይደመጥ አገደ፡፡ የቴዲ አፍሮ ሙዚቃ ግን ከታክሲ እስከ ግሮሰሪ በሁሉም ቦታ ይደመጣል፤›› ሲሉ ነበር እንደ ማሳያ በጥናታቸው ያቀረቡት፡፡

ክሪስቲን ‹‹When will the daybreak come?›› (Popular music and political processes in Ethiopia) በሚል ርዕስ ባቀረቡት በዚህ ጥናታቸው፣ ኢትዮጵያ ያልተገደበ የሐሳብ ግብይት የሚያስፈልጋት አገር መሆኗን በማንሳት ሞግተዋል፡፡ ሐሳብን መገደብ የማይቻል መሆኑን አጠንክረው የሚያወሱት ምሁሯ፣ ሙዚቃና የኪነ ጥበብ ሥራዎች ላቅ ያለ ፖለቲካዊና አገራዊ ጉዳዮች የሚነሱባቸው ቢሆኑም፣ ኢትዮጵያ ከዚህ ዓይነቱ ነፃ የሐሳብ ገበያ ብዙ ልታተርፍ እንደምትችል በጥልቀት አስረድተዋል፡፡

ምሁራን ይህን መሰል አስተያየት ሲሰጡ ቢታዩም፣ በኢትዮጵያ ግን ዛሬም ቢሆን ፖለቲካ ዘፈንክ ወይም ትችት በሙዚቃ ሠርተህ አቀረብክ ብሎ ሰዎችን ማሰር የቀረ አይመስልም፡፡

ከሰሞኑ በጥበብ ስሙ ቴዲ ዮ በመባል የሚታወቀው የራፕ ሙዚቀኛ ‹ወንበርሽ› ከተባለ የነጠላ ሙዚቃ ሥራው ጋር በተገናኘ የገጠመው ሁኔታ፣ ለዚህ እንደ አንድ ማሳያ ሆኖ እየቀረበ ይገኛል፡፡

ድምፃዊው ለአጭር ጊዜም ቢሆን በዚህ ፖለቲካ ነክ ሙዚቃው ታሰረ መባሉ፣ በኢትዮጵያ አሁንም ድረስ የሐሳብ ነፃነት ከባድ ጫና እየደረሰበት እንደሚገኝ እንደ አንድ ምሳሌ እየቀረበ ነው፡፡

ታኅሳስ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋዜጠኞች ላይ የደረሰው እስራትም፣ የሐሳብ ነፃነት አካል የሆነው የሚዲያ ነፃነት ምኅዳር በኢትዮጵያ እየጠበበ ነው የሚል ትችት እያስነሳ ነው፡፡ አንድ ቤቶች ገንቢ (ሪል ስቴት) ድርጅትን ከደንበኞች ጋር የገባበት ችግርን በተመለከተ የምርመራ ዘገባ ለመሥራት የተንቀሳቀሱት የፋና ጋዜጠኞች ተይዘው በአጭር ጊዜ ከእስራት ቢወጡም፣ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር የሰነበተው፡፡

የምርመራ ዘገባው እንዳይሠራ ፍርድ ቤት ጭምር ትዕዛዝ አወጣ መባሉ ጉዳዩን የበለጠ ትኩረት ሳቢ አድርጎታል፡፡ የምርመራ ዘገባ ሊሠራበት የነበረውና ጋዜጠኞቹን አሳስሯል የተባለው የሪል ስቴት ድርጅት የምርመራ ዘገባ ሊሠራብኝ ነው ብሎ  ክስ መመሥረቱ ደግሞ፣ ጉዳዩን የውዝግብ ምንጭ ነበር ያደረገው፡፡

በኢትዮጵያ የሚዲያ ዘርፉን የሚመራው የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በጉዳዩ ላይ መግለጫ እስከሚያወጣበት ድረስ ጉዳዩ ከባድ ውዝግብ አስነስቶ ነው የከረመው፡፡

 የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 29፣ እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013ን ያጣቀሰው የባለሥልጣኑ መግለጫ፣ ‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራዎች እንዲቆሙ ትዕዛዝ የመስጠት አዝማሚያ እየታየ ነው፤›› በማለት ነበር የጉዳዩን አሳሳቢነት የገለጸው፡፡

የባለሥልጣኑ መግለጫ አክሎም የምርመራ ጋዜጠኝነት በስፋት እንዲሠራ አቅጣጫ የሰጡት ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እንደነበሩ ይጠቅሳል፡፡ የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራ አንዱ የመንግሥት ፍላጎት መሆኑንም መግለጫው ያወሳል፡፡

ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢቲቪ፣ በፋናና በዋልታ በመሳሰሉ የመገናኛ ብዙኃን ተከታታይ የምርመራ ዘገባዎች እንደሚሠሩ እንደተናገሩት ሁሉ፣ አሁን ደግሞ የፖለቲካ ገበያን (Political Market Place) በተመለከተ ተከታታይ ዘገባ እንዲሠራ የመንግሥት ባለሥልጣናት እየቀሰቀሱ ነው፡፡

‹‹ፖለቲካ ሸቀጥ እስከሆነ ድረስ ሀብታም ሚኒስትርን በገንዘብ ይገዛል፣ ሚኒስትር አክቲቪስት ይገዛል፡፡ አንድ ሀብታም፣ አንድ ሚኒስትርና አንድ ዩቲዩበር የፈለጉትን ያደርጋሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ አሁን እየሆነ ነው፤›› በማለት በቅርቡ ለብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ማብራሪያ ሲሰጡ ነበር፡፡

ይህንኑ የፖለቲካ መሸቀጥ ጉዳይ በየሚዲያው የተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናት እያስተጋቡት ነው፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል ማስተባበሪያ ሚኒስትሩ አቶ ዛዲግ አብረሃና በፓርላማ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጂጌ፣ ከሰሞኑ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው ሚዲያው ፖለቲካን እንደ ሸቀጥ የማቅረብን ችግር እንዲዋጋ ጥሪ ሲያቀርቡ ታይተዋል፡፡ ፖለቲካ በሐሳብ የበላይነት ካልተመራ፣ እንዲሁም የተዳከሙ ተቋማት ከተፈጠሩ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ዕውን ለማድረግ ኢትዮጵያ እንደምትፈተን የተናገሩት ባለሥልጣናቱ፣ ሚዲያው ፖለቲካ ለገበያ መቅረቡን፣ ሙስናንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንዲዋጋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የመንግሥት ባለሥልጣናቱ ይህን ቢሉም ሚዲያው በዚህ በኩል የሚጠበቅበትን ለመወጣት አስቻይ ሁኔታ በኢትዮጵያ እንደሌለ የሚናገሩ በርካታ ናቸው፡፡ የሚዲያ ነፃነት አድማስ በኢትዮጵያ እየጠበበ መምጣቱን በማስረዳት፣ መንግሥት ለመገናኛ ብዙኃን ነፃነትና ለሐሳብ ብዝኃነት መረጋገጥ ተገቢ ጥበቃ እያደረገ አይደለም ሲሉ ይተቻሉ፡፡

መንግሥት የሚፈልገውን ብቻ ሳይሆን የማይፈልገውን ለመስማት ያለው ዝግጁነት ተጨባጭነት የጎደለው ነው ሲሉም ይሞግታሉ፡፡

በሌላ በኩል በሚዲያ ነፃነትም ሆነ በሐሳብ የበላይነት ላይ የሚቃጡ አፋኝ ዕርምጃዎች ምንጫቸው ከመንግሥት ብቻ እንዳልሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ የሐሳብ ብዝኃነት በሐሳብ ገበያው ውስጥ እንዲሰፍን ሁሉም ወገን ድርሻ እንዳለውም ያስገነዝባሉ፡፡

ለአብነት ያህል በቅርቡ ቴዲ ዮ የተባለው የራፕ ሙዚቀኛ ፖለቲካ ዘፈነ በሚል በማኅበራዊ ሚዲያዎች ከባድ ዘመቻ ሲደረግበት ነበርም ይላሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ድምፃዊ ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) የመንግሥት ባለሥልጣን አወዳሽ ሙዚቃ ተጫወተ ተብሎ ከባድ ዘመቻ በማኅበራዊ ሚዲያዎች እንደገጠመው ይናገራሉ፡፡

የሐሳብ ገበያው በኢትዮጵያ አድጓል ሊባል የሚችለው ሰዎች የሐሳብ ነፃነታቸውን ተጠቅመው ብዝኃነት ያላቸው ሐሳቦችን ሲያንሸራሽሩ እንደሆነም እነዚህ ወገኖች ያሰምሩበታል፡፡ የሐሳብ ነፃነት በነፃነት የማሰብ፣ የመናገር፣ አስተያየት የመስጠትና አመለካከትን ማራመድ ብቻ ሳይሆን የማይስማማ ሐሳብና አመለካከትንም መስማት የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን ሲናገሩ ይደመጣል፡፡

ይህን የሚያጠናክር አስተያየት የሚሰጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት መምህር መኩሪያ መካሻ (ረዳት ፕሮፌሰሩ)፣ የሐሳብ ገበያው በአንድ ወገን ካልተመራ የሚለው ፅንፍ የወጣ አመለካከት አገሪቱን እንደጎዳት ይናገራሉ፡፡

‹‹ሁላችንም የተለያዩ ሐሳቦች አሉን፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ የሐሳብ ፍሰቱ የአንድ ወገን (ሞኖሎጂክ) የበላይነት የሚታይበት ነው፡፡ ሁልጊዜ የአሸናፊዎችን ሐሳብ ካልሰማችሁ ሊባል አይገባም፡፡ አንዱ የሌላውን ወገን መስማት ካልቻለ እንዴት መግባባት ይቻላል? የሚዲያ ሚናም ቢሆን ሁለት የተራራቁ ሐሳቦችን ወደ መሀል ማምጣት ነው፡፡ ወይም የተለየ አማራጭ ሐሳብ እንዳለ ማሳየት ነው፤›› በማለት የሐሳብ ብዝኃነት አስፈላጊነትን አብራርተዋል፡፡

በግለሰቦች ወይም አጋጣሚዎችና ክስተቶች ላይ ከመነጋገር ይልቅ፣ በመሠረታዊው የሐሳብ ገበያ ብዝኃነት ላይ ንግግር ሊኖር እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡ ‹‹እንደ አገር መከተል የሚገባን ገንቢ ወይም ‹ዲያሎጂክ› የሆነ ብዝኃነት ያለው የሐሳብ ገበያ እንዲሰፍን መደገፍ ነው፤›› በማለትም ያክላሉ፡፡

በአገሪቱ ፅንፍ የወጣ የፖለቲካ ባህል ማራመድ ብዙ ችግር እንደፈጠረ የሚናገሩት መኩሪያ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ በሐሳብ ነፃነት ላይ የሚደቀኑ አደጋዎች ምንጫቸው የፖለቲካ ባህሉ ፅንፍ መርገጥ እንደሆነ ያሰምሩበታል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጋዜጠኞች፣ ሚዲያዎች፣ አክቲቪስቶች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ፣ ራሳቸው ፖለቲከኞች ጭምር የግል ሐሳብ አስተያየታቸውን በማንፀባረቃቸው በተለያዩ መንገዶች ችግር እየገጠማቸው ነው ይባላል፡፡

የሕግ ባለሙያውና የቀድሞ የኦፌኮ ፓርቲ ፖለቲከኛና ጠበቃ አቶ ወንድሙ ኢብሳ ከሰሞኑ ችሎት በመድፈር ተከሰው መታሰራቸው፣ የዚሁ ነፀብራቅ መሆኑ ሲነገር ሰንብቷል፡፡ አቶ ወንድሙ ከመታሰራቸው በፊት በነበሩ ቀናት በአዲስ አበባ በባንዲራና በብሔራዊ መዝሙር ጉዳይ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የተፈጠሩ ችግሮችን በተመለከተ መንግሥትን ሲተቹ እንደነበር አንዳንዶች በመጥቀስ፣ የታሰሩት በችሎት መድፈር ነው መባሉን ክፉኛ ሲተቹት ሰንብተዋል፡፡

ከአቶ ወንድሙ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ብቻ ሳይሆን ከሕግ አግባብ ውጪ እየተፈጸሙ ነው ስላሏቸው እስራቶች ታኅሳስ 21 ቀን መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)፣ ጉዳዩ እንዲስተካከል መጠየቁ ይታወሳል፡፡ ‹‹ከዚህ ቀደም በጋዜጠኞች፣ በፖለቲከኞችና በአክቲቪስቶች ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ እስር ሲፈጸም እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህንን አስመልክቶ ኢሰመጉ በተደጋጋሚ ጊዜ መንግሥት የማስተካከያ ዕርምጃዎችን እንዲወሰድ ሲወተውት የቆየ ቢሆንም፣ ጉዳዩ አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል፤›› በማለት ነበር በመግለጫው ያስታወቀው፡፡

በጋዜጠኞች ላይ የሚፈጸመውን ከሕግ ውጪ የሆነ እስራት በተመለከተ ሰፊ ጽሑፍ በቅርቡ ያስነበቡት አቶ ዘላለም ሽፈራው ወልዴ ፣ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2021 አዲስ የሚዲያ አዋጅ አገሪቱ ማፅደቋን ተከትሎ በዘርፉ ለውጥ ይመጣል በሚል ብዙ ተስፋ ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በአዲሱ ሕግም ‹‹በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል በወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ፣ ክሱ በቀጥታ በዓቃቤ ሕግ አማካይነት ፍርድ ቤት መቅረብ አለበት፤›› የሚል አንቀጽ መቀመጡን ጸሐፊው ሕጉን በማጣቀስ አስረድተዋል፡፡

ጋዜጠኛ ወይም በሚዲያ ወንጀል ፈጽሟል  ተብሎ የተጠረጠረ ወገን ሳይታሰር ክሱን ይከታተል የተባለው ደግሞ፣ የሐሳብ የበላይነት እንዲረጋገጥ ከማሰብ መሆኑን ይሞግታሉ፡፡ ሕጉ ይህን ቢልም ነገር ግን ከሕግ ውጪ እስራት መቀጠሉ ለሚዲያ ነፃነትም ሆነ ለሐሳብ ብዝኃነት መስፈን አደጋ መሆኑን ጸሐፊው አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -