Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የባህር ትራንስፖርት የመድን ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ ማሽቆልቆል መድን ሰጪ ኩባንያዎችን አሥግቷል

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከሞተር ቀጥሎ ከፍተኛ የመድን ሽፋን የሚሰጥበት ወደ አገር ለሚገቡ ምርቶች ዋስትና (የማሪን የመድን ሽፋን) መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ መሆኑ ተመለከተ፡፡ 

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የኢንሹራንስ ባለሙያዎች እንደሚጠቁሙት፣ የማሪን የመድን ሽፋን በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነሱ ዋና ምክንያት ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተያይዞ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች እየቀነሱ ከመምጣታቸው ጋር የተያያዘ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንትና የኒያላ ኢንሹራንስና ሥራ አስፈጻሚ ለሪፖርተር እንደገለጹትም፣ የማሪን መድን ሽፋን አስደንጋጭ በሚባል ደረጃ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ የማሪን ኢንሹራንስ ሽፋን ከዓመት ዓመት እየቀነሰ መጥቶ፣ በተለይም በ2015 የሒሳብ ዓመት ይህንን የመድን ሽፋን የሚጠይቁ ደንበኞች ቁጥር ከፍተኛ በሚባል ደረጃ መቀነሱ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ላይ ተፅዕኖ ስለመፍጠሩ አብራርተዋል፡፡  

አስመጪዎች ከዚህ ቀደም የሚያስመጡትን ዕቃ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት የቀነሱ መሆኑ የመድን ሽፋኑ እንዲቀንስ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን የገለጹት አቶ ያሬድ፣ የመድን ሽፋኑ ለምን እየቀነሰ እንደመጣ ለማወቅ በተደረገው ጥረት ማረጋገጥ የተቻለው የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ሳቢያ ደንበኞች የሚያመጡት ዕቃ እየቀነሰ በመምጣቱ አስገዳጅ የሆነውን የማሪን የመድን ሽፋን ለመግዛት ባለመቻላቸው ነው፡፡፡

የማሪን ኢንሹራንስ የተመረተው ሌተር ኦፍ ክሬዲት ተከፍቶላቸው ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ዕቃዎች ላይ መሆኑን ያስረዱት አቶ ያሬድ፣ ማንኛውም ኤልሲ ተከፍቶለት ወደ አገር የሚገባ ዕቃ በአስገዳጅነት የማሪን የመድን ሽፋን የሚገባለት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም የማሪን የመድን ሽፋን የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያ ከሞተር የመድን ሽፋን ቀጥሎ ከፍተኛ የዓረቦን ገቢ የሚያገኙበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ አሁን እየተፈጠረ ያለው ቅናሽ በኢንዱስትሪው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳረፈ ነው ተብሏል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት የውጭ ምንዛሪ አግኝተው ዕቃ ማስመጣት የቻሉት ጥቂት በመሆናቸው፣ ኢንሹራንሱን ኩባንያዎች በቀድሞው መጠን ልክ የመድን ሽፋኑን ለመሸጥ አላስቻላቸውም፡፡ ስለዚህ ብዙዎቹ አስመጪዎች ኤልሲ ባለማግኘታቸው ምክንያት የመድን ሽፋኑን ሊገቡ አይችሉም፡፡ ‹‹እኛም ወደ ደንበኞች ሄደን ምነው የማሪን የመድን ሽፋናችሁ ቀነሰ? ብለን ጠይቀን፣ የተረዳነውም የምናስገባው ምርት ስላነሰ የመድን ሽፋኑን ለመግዛት እንዳልቻሉ ገልጸውልናል፤›› ሲሉ ከአቶ ያሬድ ስለሁኔታው አስረድተዋል፡፡  

የማሪን የመድን ሽፋን መጠን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮት መካከል፣ መንግሥት መኪናን ጨምሮ ወደ 38 የሚሆኑ ምርቶች ኤልሲ እንዳይከፈትላቸውና እንዳይገቡ መከልከሉ እንደሆነ የዘርፉ አንቀሳቃሾች ይናገራሉ።

አቶ ያሬድም የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ የፈጠረውን ያህል አይሁን እንጂ፣ በተወሰነ ደረጃ የተወሰኑ ምርቶች የውጭ ምንዛሪ እንዳይፈቀድላቸው መከልከሉ የማሪን መድን ሽፋን መጠን ቅናሽ እንዲሰፋና የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ከዚህ የመድን ሽፋን ማግኘት ይችሉ የነበረውን የዓረቦን ገቢ እንዲቀንስ ማድረጉን ይገልጻሉ።

በተለይ ተሽከርካሪዎች እንዳይገቡ መከልከል የማሪን የመድን ሽፋን ላይም ሆነ ተሽከርካሪዎች ይሰጥ የነበረውን የመድን ሽፋን እንዲቀዘቅዝ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡ በገደቡ ምክንያት የሚገቡ ተሽከርካሪዎች መጠን መቀነስ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለተሽከርካሪዎች የመድን ሽፋን በመስጠት ያገኙት የነበረውን የመድን ሽፋን በተወሰነ ደረጃ ሊቀንስባቸው ችሏል፡፡ እንዲህ ያሉት ሁኔታዎች በጥቅል ሲታዩ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱና የተወሰኑ ዕቃዎች እንዳይገቡ ከመከልከሉ ጋ ተያይዞ የመጣ ችግር ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡  

የውጭ ምንዛሪ እጥረት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢንዱስትሪው ላይ የሚያሳርፈው ተፅዕኖ በግልጽ እንዲታይ እያደረገው ነው፡፡ የ2015 የሒሳብ ዓመት የኢትዮጵያን የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከማሪን የመድን ሽፋን ያሰባሰቡት የዓረቦን ገቢ ከቀዳሚው ዓመት ብልጫ የሚያሳይ በመሆኑ፣ ‹‹እንዴት የማሪን ሽፋን ቀነሰ ማለት ይቻላል?›› የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ያሬድ፣ በ2015 ዓ.ም. የመጀመርያዎቹ ወራት ከማሪን የመድን ሽፋን የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሰበሰቡት የዓረቦን መጠን ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ የጨመረ ቢመስልም፣ ይህ ገቢ የተገኘው ለተወሰኑ ምርቶች ከተሰጠው የማሪን የመድን ሽፋን ነው ይላሉ፡፡ ከተሰጠው የመድን ሽፋን አንፃር ካየነው ግን፣ ይህንን ሽፋን የሚገዙ ደንበኞች ቁጥር በእጅጉ የቀነሰ መሆኑን ያሳያል፡፡ ስለዚህ በመጠኑ አንፃር የመድን ሽፋን ተጠቃሚዎች በተጨባጭ ቀንሷል፡፡ አሁን ከማሪን የመድን ሽፋን የተገኘው የዓረቦን መጠን ጨምሮ ሊታይ የቻለው የማይቀሩ የሚባሉ እንደ ማዳበሪያና ነዳጅ የመሳሰሉ ምርቶች ዋጋቸው በከፍተኛ ሁኔታ ስለጨመረ በዚያ የሚሰበሰበው የማሪን የመድን ሽፋን ዓረቦን ከፍ ብሎ በመገኘቱ ነው እንጂ፣ ከዚህ ውጪ ያሉ የማሪን የመድን ሽፋኖች ቁጥር ባልተጠበቀ ሁኔታ ቀንሰው ታይተዋል፡፡ እንደ ነዳጅና ማዳበሪያ ላሉ ምርቶች ደግሞ የመድን ሽፋኖች በመንግሥት የሚሰጡ በመሆናቸው፣ ለእነዚህ የተሰጠው የማሪን ሽፋን ሲቀንስ ቀሪው የዓረቦን ገቢ መገኘት ከነበረበት ገቢ በታች ማስገኘታቸው ብቻ ሳይሆን መጠኑ ቀንሷል፡፡ 

ስለዚህ ከዘርፉ የተገኘው ገቢ መጨመሩ የተገኘውን ገቢ እንዳደገ አያመለክትም ብለዋል፡፡ ስለዚህ የተጣራ ተፅዕኖው ሲታይ የማሪን ኢንሹራንስ አስደንጋጭ በሚባል ደረጃ ቀንሷል ብለው፣ አሁን የጨመረ የሚመስለው የማሪን ኢንሹራንስ የዕቃው ዋጋ ጨምሮ ስለመጣ የመድን ሽፋኑም የሚሰጠው የምርቱን ዋጋ መሠረት አድርጎ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም የማሪን የመድን ሽፋን በሚገባው ደረጃ ሊያድግ የሚችለው ለገቢ ንግዱ የሚፈለገውን የውጭ ምንዛሪ ተመድቦ ምርቶቹ ሲገቡ ብቻ መሆኑንም ከተሰጠው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡      

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች