- ክቡር ሚኒስትር ላቀረብነው የውይይት ጥያቄ ፈቃደኛ ስለሆኑና በአጭር ቀጠሮ በመገናኘታችን ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
- በጭራሽ ምስጋና አያስፈልገኝም። ተቃዋሚ ፓርቲ ስትባሉ ብትቆዩም እኛ ስንመጣ ተፎካካሪ ያልናችሁ በምክንያት ነው።
- በምን ምክንያት ነው?
- ዋናው ምክንያት ተቀራርበን መሥራት እንዳለብን ስለምናምን ነው።
- ሌላው ምክንያትስ?
- ሌላው ተቃዋሚ የሚለው ስያሜ ጠላትነትን የሚያመላክት በመሆኑ ተገቢ አይደለም ማረም አለብን ብለን ነው።
- መልካም ነገር ተግባር ነው ክቡር ሚኒስትር፣ ነገር ግን ተቀራርበን እየሠራን ነው ለማለት ያስቸግራል።
- እንዴት?
- ዛሬ እርስዎ ፈቃደኛ ሆነው ተገኙ እንጂ ስለጀመራችሁት የጫካ ፕሮጀክት ምንነት ለመወያየት በተደጋጋሚ ጊዜ ያቀረብነው ጥያቄ ምላሽ አላገኘም።
- ስለ ጫካ ፕሮጀክት ምንነት በፓርላማ ሳይቀር ማብራሪያ እንደሰጠንበት ነው የማውቀው። አልሰማህም?
- ሰምቻለሁ ክቡር ሚኒስትር።
- ታዲያ?
- የተሰጠው ግን ማብራሪያ ብቻ ነው።
- አልገባኝም?
- የተሰጠው ማብራሪያ ጥያቄ እንዳይነሳ ለማድረግ እንጂ ግልጽ ለመሆን የተሰጠ ማብራሪያ ነው ብለን እኛ አናምንም።
- ለምን?
- ምክንያቱም የሕዝብ ተወካዮቹን ጥያቄ ባትጠይቁም እንድትረዱት ተብሎ የተሰጠ ማብራሪያ እንጂ ጥያቄ ለመመለስ ተፈልጎ አይደለም።
- ለምን እንደዚያ አልክ?
- ምክንያቱም እኛ መሠረታዊ ጥያቄዎች አሉን። የተሰጠው ማብራሪያ ግን የፕሮጀክቱ ወጪ በበጀት እንደማይሸፈን ብቻ የሚገልጽ ነው።
- የእናንተ ጥያቄ ምንድነው?
- የጫካ ፕሮጀክት ቤተ መንግሥት ግንባታ የሚከናወንበት ቦታ ላይ ጥያቄ አለን።
- ቦታው ላይ ያላችሁ ጥያቄ ምንድነው?
- መንግሥት በይፋ ባይናገረውም ግንባታው እየተካሄደ ያለው በቅርቡ የተቋቋመው ሸገር ከተማ ውስጥ እንደሆነ ደርሰንበታል።
- ታዲያ ምን ችግር አለው?
- ይህ ግንባታ በአዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ አከላለል መሠረት አዲስ አበባ ውስጥ የሚካሄድ አይደለም።
- ኦኮ ምን ችግር አለው?
- በሕገ መንግሥቱ መሠረት የፌዴራሉ መንግሥት መቀመጫ አዲስ አበባ ነው።
- ሕገ መንግሥቱ እንደዚያ አይልም።
- ምንድነው የሚለው?
- የፌዴራሉ መንግሥት ዋና መዲና አዲስ አበባ ነው የሚለው።
- ታዲያ የፌዴራሉ መንግሥትን መቀመጫ ወደ ሌላ ቦታ መቀየር ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጭ አይደለም?
- በጭራሽ አይጋጭም።
- ይጋጫል እንጂ ክቡር ሚኒስትር?
- ምናልባት ትላንት ከበላኸው ነገር ጋር ተጋጭቶብህ እንዳይሆን?
- ምን በላሁ?
- እራት?
- የምን እራት?
- የኤምባሲዎች እራት!
- ጥያቄዎችን በመመለስ ግልጽኝነትን ከማስፈን ይልቅ ጥያቄዎችን ለማድበስበስ በምን እንደምታመኻኙ እውቃለሁ።
- በምን እናመኻኛለን?
- ባልነበረው እራት!
[ክቡር ሚኒስትሩ ለኢንቨስትመንት ማስፋፊያ የሚሆን መሬት እንዲሰጣቸው ተደጋጋሚ ጥያቄ ያቀረቡትን ባለሀብት ቅሬታ ለማዳመጥ በያዙት ቀጠሮ መሠረት ከባለሀብቱ ጋር በቢሯቸው ተገናኝተዋል]
- ክቡር ሚኒስትር ለውይይት ያቀረብነውን ተደጋጋሚ ጥያቄ ዘግይቶም ቢሆን በመቀበልዎ አመሰግናለሁ።
- ምሥጋናህ በነገሮች ባይታጀብ ጥሩ ነበር።
- አጠፋሁ እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ዘግይቶም ቢሆን ጥያቄያችንን በመቀበልዎ ማለት ምን ማለት ነው? ሽሙጥ አይደለም? ደጅ አስጠናኸኝ ማለትህ አይደለም?
- እንደዚያ ይረዱታል ብዬ አላሰብኩም ክቡር ሚኒስትር።
- ለማንኛውም ለመወያየት የፈለጋችሁበትን አጀንዳ ማቅረብ ትችላለህ።
- አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር።
- እንደሱ ይሻላል።
- እ…?
- ምሥጋና እንደዚህ ንፁህ ሆኖ በጠቃሚ ነገር ሲታጀብ ነው ደስ የሚለው።
- ምሥጋናን በዚህ ደረጃ ይወዳሉ ብዬ ስላልገመትኩ እንጂ ንፉግ ሆኜ እኮ አይደለም።
- አሁንም እየተፈታተንከኝ ነው።
- ምን አጠፋኹ ክቡር ሚኒስትር?
- ምሥጋና አብዝተው ይወዳሉ እያልከኝ ነው?
- እንደዚያ ማለቴ አልነበረም ክቡር ሚኒስትር፣ እንደዚያ ይረዱታል ብዬም አላሰብኩም።
- ለማንኛውም ለመወያየት ወደ ፈለጋችሁበት አጀንዳ ብንገባ?
- እሺ ክቡር ሚኒስትር፣ ማመስገኔን ትቼ ወደ ጉዳዬ እገባለሁ።
- እንዴት ያለ ነገር ነው?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ከዚህ በኋላ ስለምሥጋና ካነሳህ ውይይቱን በገዛ ፈቃድህ እንደተውከው እቆጥረዋለሁ።
- እሺ ክቡር ሚኒስትር አመሰግናለሁ። ጉዳዬንም ቀጥታ ማቅረብ እጀምራለሁ።
- እንዴት ሆኖ?!
- ምን አሉኝ?
- በል ቢሮዬን ለቀህ ውጣ!
- በስህተት ነው የደገምኩት ክቡር ሚኒስትር፣ ይቅርታ ያድርጉልኝ?
- ከዚህ በላይ ማዳመጥ ስለማልችል ውጣልኝ፡፡
- አስቤው አይደለም ክቡር ሚኒስትር፣ በዚያ ላይ ይቅርታ እየጠየኩ ነው?
- አልችልም አልኩህ እኮ?!
- ለነገሩ ምሥጋናዬን ካልተቀበሉ ሌላ ነገር እሺ አይሉኝም።
- ሌላ ምን?
- እ…
- ግዴለም ንገረኝ።
- ይቅርታ!
- ውጣልኝ!