የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እስከ ሚያዚያ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ባሉት አራት ወራት ውስጥ ጠቅላላ ጉባዔውን እንዲያካሂድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳሰቢያ ሰጠ፡፡
ቦርዱ መኢአድ ሚያዚያ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ያካሄደውን ጠቅላላ ጉባዔ አስመልክቶ በፓርቲው ተያይዘው የቀረቡ ሰነዶችን በቦርዱ ታዛቢዎች ከቀረበው ሪፖርት ጋር በማመሳከር ውሳኔ ማሳለፉን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ፓርቲው በጠቅላላ ጉባዔው ያካሄደው የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ እንዲሁም የተጓደሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫ እጅ በማውጣት መደረጉን ያስታወሰው ምርጫ ቦርድ፣ ይህም በአዋጅ አንቀጽ 74(3) መሠረት በየደረጃው ያሉ አመራሮች ምርጫ ግልጽ፣ ነፃና ፍትሐዊ እንዲሁም በሚስጥር በሚሰጥ ድምፅ አግባብ መሆን እንዳለበት ከተደነገገው ጋር የተቃረነ በመሆኑ ፓርቲው ሕጉን መሠረት በማድረግ በድጋሚ ጠቅላላ ጉባዔ ሊያካሂድ እንደሚገባ ገልጿል።
በፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ የተካሄደው የፓርቲው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በአዋጁ መሠረት በሚስጥር ድምፅ አሰጣጥ ሒደት ሚስጥራዊ በመሆኑ ዕውቀና መሰጠቱን የገለጸው ምርጫ ቦርድ፣ በአንፃሩ የማዕከላዊ ኮሚቴ ቁጥር በራሱ በማዕከላዊ ኮሚቴ መወሰኑ ከሕጉ ጋር ስለሚቃረን ፓርቲው በቀጣይ በሚያካሂደው ጠቅላላ ጉባዔ በማስወሰን የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ አድርጎ እንዲያቀርብ መወሰኑን አስታውቋል፡፡
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት በተሻሻለው የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ላይ በአዋጁ መሠረት ተሻሽለው መቅረብ ያለባቸውን አንቀጾች፣ ከሕጉ ጋር የሚቃረኑ የደንቡ አንቀጾች፣ የታገዱና በዝርዝር የሰፈሩት ድንጋጌዎች በተግባር እንዲፈጸሙ እንዲደረግ የጠየቀው ቦርዱ፣ በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ላይ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች በተከተለ መልኩ ጠቅላላ ጉባዔውን እንዲካሂድ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
በተመሳሳይ ምርጫ ቦርድ የአርጎባ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (አሕዴድ) ነሐሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ያካሄደውን ጠቅላላ ጉባዔ አስመልክቶ በፓርቲው ተያይዘው የቀረቡ ሰነዶችን በቦርዱ ታዛቢዎች ከቀረበው ሪፖርት ጋር በማመሳከር ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል፡፡
ቦርዱ ባደረገው ምርመራ ፓርቲው ያካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ያሻሻለው የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ላይ ያሉ ከአዋጅ ቁጥር 1162/2011 ጋር የሚቃረኑ አንቀጾች ተፈጻሚ እንዳይሆኑ፣ እንዲሁም ጠቅላላ ጉባዔው በቀጣይ ስብሰባው አስፈላጊውን ማስተካከያ አድርጎ ሪፖርት እንዲያቀርብ መወሰኑን ገልጿል፡፡