- ተጨማሪ አሥር ሚሊዮን ዩሮ ለኤሌክትሪክ ኃይል ሥራዎች ረድታለች
የፈረንሣይ መንግሥት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ላስከተለው ጥፋት መልሶ ግንባታ የሚውል የ32 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ሰጠ፡፡ ዕርዳታ መሰጠቱን የገለጹት የፈረንሣይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአውሮፓ ሚኒስትር የሆኑት ካትሪን ኮሎና በአዲስ አበባ ይፋ የሥራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡
ዓርብ ጥር 5 ቀን 2015 ዓ.ም. በፈረንሣይ ኤምባሲ በተደረገው የፋይናንስ ድጋፍ የፊርማ ስምምነት ወቅት ፈረንሣይ በሁለት ዘርፎች የመልሶ ግንባታውን እንደምትደግፍ ይፋ አድርጋ ስምምነቶቹን ተፈራርማለች፡፡ አንደኛውና ዋነኛው የ32 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ በግጭት ለተጎዱ የሰሜን አማራ፣ ትግራይና አፋር ክልሎች የግብርና ምርታማነትን ለማሻሻልና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ሁለተኛውና አሥር ሚሊዮን ዩሮ የሚሆነው የፋይናንስ ድጋፍ ደግሞ ስድስት ሚሊዮኑ ዩሮ አዲስ የፋይናንስ ድጋፍ ሲሆን፣ ቀሪው አራት ሚሊዮን ደግሞ ከዚህ ቀደም ለኤሌክትሪክ ኃይል የተሰጠውን ብድር ማራዘሚያ እንዲሆን ነው፡፡ በዚህ ድጋፍ በግጭቱ የተጎዱ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ማስተላለፊያ ፕሮጀክቶችን እንደሚያግዝ ተገልጿል፡፡
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከኢትዮጵያ በኩል ተገኝተው የተፈራረሙት የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው ሲሆኑ፣ ሌላኛው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሸብር ባልቻ ናቸው፡፡