Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በኢትዮ ቴሌኮም ላይ ላደረሰው ኪሳራ ክስ ተመሠረተበት

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ኩባንያው በግማሽ ዓመት ስምንት ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን ገልጿል

ኢትዮ ቴሌኮም ከወር በፊት በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ተከስቶ በነበረው የቴሌኮም አገልግሎት መቆራረጥ፣ ለኪሳራ ዳርጎኛል ያለውን ሳፋሪኮም ኢትዮጵያን ተጠያቂ ለማድረግ ወደ ሕግ ማምራቱን አስታወቀ፡፡

ታኅሳስ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ከጠዋቱ 12፡32 እስከ ምሽት 1፡32 ሰዓት የአገልግሎት መቋረጥ እንዳጋጠመ፣ ይህም የሆነው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በአካባቢው እያካሄደ በነበረው የመስመር ዝርጋታ ምክንያት እንደነበር መግለጹ ይታወሳል፡፡

በጂቡቲ በኩል በሚያልፈው የዓለም አቀፍ የግንኙነት መስመር፣ እንዲሁም በአፋር ክልል የአገልግሎት መስመሮች በበርካታ ቦታዎች ላይ ለደረሰው ከፍተኛ ጉዳት ላጋጠመው ኪሳራ፣ ድርጊቱን የፈጸሙ አካላት በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እንደሚያደርግ ኢትዮ ቴሌኮም ከዚህ ቀደም ሲገልጽ ተሰምቶ ነበር፡፡

‹‹ከሳፋሪኮም ጋር እንደ ተወዳዳሪና እንደ አገልግሎት ተጠቃሚ ወይም ፓርትነር እየሠራን እንገኛለን፤›› ያሉት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ ይህም ከፍተኛ ሙያዊ ጨዋነት በተላበሰ መንገድ የሚከናወን እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በሰመራ ከተማ ደርሷል የተባለውን የአገልግሎት መቋረጥ በማስታወስ፣ ከፍተኛ ጉዳት በተቋሙም ሆነ በደንበኞቹ ላይ በመድረሱ ጉዳዩ በሕግ እንደተያዘና ውጤቱ ወደፊት የሚገለጽ መሆኑን፣ የኩባንያቸውን የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ለመገናኛ ብዙኃን ሐሙስ ጥር 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡

የቴሌኮም አገልግሎት ተቆጣጣሪ የሆነው የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን  ዕርምጃ ሊወስድባቸው የሚገባቸውን ጉዳዮችን በደብዳቤ ጭምር ማሳወቃቸውን የገለጹት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ከባለሥልጣኑ ጋር በግንባር የተደረገ ውይይት እንደነበር አስረድተዋል፡፡

‹‹እስካሁን ድረስ ያደረግነው አንቲ ኮምፒቲቲቭ ፕራክቲስ (ከሙያ ያፈነገጠ እንቅስቃሴ) የለም፤›› ሲሉ ያስረዱት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ‹‹ተወዳዳሪያችን ሆኖ ሲገኝ ለተቆጣጣሪ ባለሥልጣን አሳውቀናል፤›› ብለዋል፡፡

ገበያው ለውድድር የተከፈተ እንደመሆኑ በሚዲያ የተሰሙም ያልተሰሙም በርካታ ችግሮች አሉ ያሉት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ እነዚህም ገበያውን ባለማወቅ ወይም በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮ ቴሌኮም በ2015 በጀት ዓመት አጋማሽ 8.18 ቢሊዮን ብር ማትረፉ ታውቋል። ኩባንያው በ2014 በጀት ዓመት አጠቃላይ ያተረፈው ዘጠኝ ቢሊዮን ብር እንደነበር ገልጾ፣ ተቋሙ በበጀት ዓመቱ አጋማሽ የመሠረተ ልማት ኪራይን ጨምሮ የሞባይል ድምፅ፣ የኢንተርኔትና ሌሎች አገልግሎቶችን በማቅረብ 33.8 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡

በአይኤፍአርኤስ (IFRS) መሠረት ባደረገው የውስጥ ፋይናንስ ግምገማ፣ በግማሽ ዓመቱ ኩባንያው ስምንት ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በውጭ ምንዛሪ ገቢ ከሚያገኝባቸው ምንጮች 64.8 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን የተነገረ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የወጪ ቅነሳ ስትራቴጂን ተግባራዊ በማድረጉ በግማሽ ዓመቱ 3.5 ቢሊዮን ብር ማዳን መቻሉን ተገልጿል።

የኩባንያው የደንበኞች ቁጥር 70 ሚሊዮን መድረሱን፣ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት በሆነው ‹‹ቴሌ ብር›› እስካሁን 27.2 ሚሊዮን ደንበኞችን እንዳፈራና 217 ቢሊዮን ብር ዝውውር መፈጸሙን፣ ከ44 የተለያዩ አገሮች ጋር በመተሳሰር 1.6 ሚሊዮን ዶላር በዓለም አቀፍ ሐዋላ መቀበል መቻሉ ተጠቅሷል።

ኢትዮ ቴሌኮም በስትራቴጂው ከያዛቸው ጉዳዮች ውስጥ ተጨማሪ ገበያ ማስፋት አንዱ መሆኑን ሲገለጽ የነበረ ጉዳይ ሲሆን፣ ከሰሞኑ ወደ ደቡብ ሱዳን ያደረገው ጉዞም የአገሪቱ መንግሥት ላቀረበው የዓለም አቀፍ የቴሌኮም ግንኙነት አገልግሎት (ኢንተርናሽል ጌት ዌይ) የገበያ ጥናትና ንግግሮችን ለማድረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ኩባንያው ከዚህ ባሻገር በደቡብ ሱዳን ያለው የገበያ ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለውን ለማየት ወደ አገሪቱ ማቅናቱን አስታውቆ፣ በአገሪቱ ውስጥ ቁጥራቸው በርከት ያለ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች እንደነበሩና ነገር ግን በዚህ ወቅት ብዙኃኑ ከገበያ መውጣታቸውን ጠቁሟል፡፡

ከዋጋ ተመጣጣኝነት አኳያ ጥያቄዎች ያሉበት ገበያ ስለሆነ ለኢትዮ ቴሌኮም  መልካም አጋጣሚ ነው ያሉት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ በዚህ ወቅት በደቡብ ሱዳን ገበያ ገብተው በሚሠሩበት ሁኔታ ላይ ኩባንያቸው ጥናት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለሶማሊያ ‹‹የኢንተርናሽል ኮኔክሽን›› አገልግሎት እንደሚሸጥ ያስታወሰው ኢትዮ ቴሌኮም፣ ይህን አገልግሎት ደቡብ ሱዳኖች እንዲቀርብላቸው እንደሚፈልጉና ነገር ግን ይህንን መቀበል የሚችል መሠረተ ልማት ባለመኖሩ ያንን መሥራት እንደሚያስፈልግ፣ በጠቅላላው በአገሪቱ ገበያ ላይ ገብቶ መሥራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ  ከሚመለከታቸው የደቡብ ሱዳን ኃላፊዎችና ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ጋር ውይይት መደረጉ ተብራርቷል፡፡

በተጨማሪም የጂቡቲ ቴሌኮም ኩባንያ እያደረገ የሚገኘውን ሪፎርም መሠረት በማድረግ ኢትዮ ቴሌኮም አብሮ መሥራት በሚችልባቸው ጉዳዮች ላይ እየተነጋጋረ እንደሚገኝ፣ በአጠቃላይ ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚያደርገው ገበያን የማስፋት እንቅስቃሴ ዕውን ሲሆን ይፋ እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች