Saturday, April 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሁሉም ክልሎች በንብረት ላይ የሚጣለው ታክስ ተመጣጣኝ እንደሚሆን ተገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በንብረት ላይ ለሚጣለው ታክስ (Property Tax)፣ አስፈላጊ የሕግ ማዕቀፎች እንደሚዘጋጁ የሚጣለው ታክስ በሁሉም ክልሎች ተመጣጣኝ እንደሚሆንና የፌደራል መንግሥቱ ‹‹የታክሱ ሥርዓት አንድ ወጥ እንዲሆን›› የማድረግ ኃላፊነቱን የጠበቀ ሕግ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ክልሎችም የታክስ ሰነዱን ወጥነት ማዕከል አድርገው ዝርዝር ሕጎችን እንደሚያዘጋጁ ታውቋል፡፡

የፌደሬሽንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ባለፈው ረቡዕ ጥር 3 ቀን 2015 ዓ.ም. በጋራ ባካሄዱት ሁለተኛ የሥራ ዘመን፣ አንደኛ የጋራ ልዩ ስብሰባ፣ የንብረት ታክስን የክልል መንግሥታትና የከተማ መስተዳድሮች በጋራ እንዲያስተዳድሩት ከመወሰኑ በፊት፣ ‹‹በንብረት ላይ የሚጣለውን ታክስ ማን በባለቤትነት ይምራው የሚል አጀንዳ የነበረ ሲሆን፣ የጋራ ምክር ቤቶቹ አባላት በአብላጫ ድምፅ ክልሎች ያስተዳድሩት የሚለውን መርጠዋል፡፡ አራት ድምፆች ተቃውመው የነበረ ሲሆን፣ አምስት ድምፆች ተዓቅቦ አድርገው ነበር፡፡

የተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ቋሚ ኮሚቴ በጋራ አቅርበዋቸው የነበሩት የፌደራል መንግሥት ወይም የክልል መንግሥታት ይሰብስቡት በሚሉት የውሳኔ ሐሳቦች ላይ ነበር ድምፅ የተሰጠው፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በፓርላማ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አዋጅ የማርቀቅ ሥራ የሚጀምር መሆኑንና ክልሎችም ይህን ማዕከል አድርገው የሚያወጧቸው ዝርዝር ሕጎች እንደሚኖሩ ነው፡፡

‹‹በሚወጣው አዋጅ ላይ ዝርዝር የአፈጻጸም መርሆዎች ይቀመጣሉ›› ሲሉ የተናገሩት አቶ አህመድ፣ የዋጋ መጠን በተመለከተ ‹‹ሁሉም ክልሎች ተመጣጣኝ እንዲሆን ነው የሚያደርጉት፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

የንብረት ታክስ አስፈላጊነቱን ሲያስረዱም፣ በኢትዮጵያ ያለው የታክስ አሰባሰብ ዝቅተኛ መሆኑንና የሚሰበሰበው መጠንም ከአጠቃላይ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት አንፃር ትንሽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የንብረት ታክስ መሠረታዊ ዓላማው ፍትሐዊነት ነው፡፡ ንብረት የሚያፈሩ ሰዎች ከአገሪቱ ሌሎች ዜጎች የተሻለ አቅም ያላቸው ናቸው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሁለቱም ምክር ቤት አባላት አስተያየታቸውን በመድረኩ ሰንዝረው የነበረ ሲሆን፣ የተወሰኑት በሐሳቡ አመጣጥ ላይና ተግባራዊነቱ ላይ ጥያቄ የፈጠረባቸውን ጉዳዮች ሰንዝረዋል፡፡ የቀድሞ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር የነበሩትና የተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) የሰነዘሩት አስተያየት፣ በውሳኔ ሐሳቡ ላይ የተቀመጠው የታክስ መጣል አስፈላጊነት የመንግሥት የወጪና ገቢ አለመመጣጠን መሆን ላይ ሲሆን፣ ‹‹መንግሥት ተጨማሪ ታክስ ይዘቶችን ከማስፋት ይልቅ ወጪ ቁጠባ ፖሊሲዎችን ለምን አያዘጋጅም?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በተጨማሪም አሁን ባለው ሁኔታ ንብረት የሚባለው የማይንቀሳቀስ ሀብትን ሲሆን፣ ነዋሪውም ይህን ቤትና መሰል ንብረት እንዴት እንደሚሠሩት እየታወቀ ታክስ ክፈሉበት መባሉ አግባብ አይደለም በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

‹‹ኅብረተሰቡ ብዙ የታክስ ጫና አለበት፣ ሠራተኛው እስከ 35 በመቶ ታክስ ይከፍላል፣ ቆጥቦ ቤት ሲሠራ ደግሞ አሁንም ታክስ ሊከፍል ነው፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በፌደሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ ከምክር ቤቶቹ ለተነሱት ጥያቄዎች አስተያየት ሲሰጡ፣ ይህ የታክስ ዓይነት ተግባራዊ ሲደረግ አራት መሠረታዊ ችግሮችን እንደሚፈታ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጻ፣ አንደኛው የታክስ ፍትሐዊነትን በዜጎች መካከል የሚያሰፍን ሲሆን፣ ሌብነትን ለመከላከልና ግልፀኝነትን ለማስፈን፣ የታክስ ዓውዱን የማስፋት፣ እንዲሁም ከተሞችን የማሳደግ አቅም እንዳለው በመዘርዝር ታክሱ ተግባራዊ መደረግ ያለበትን ምክንያቶች አስረድተዋል፡፡ ‹‹ሰው ንብረት ካፈራና የኢኮኖሚም እንቅስቃሴ ውስጥ ከገባ ታክስ መክፈል አለበት፣ ሕገ ወጥ ኢኮኖሚው በተወሰነ ደረጃ መስመር መያዝ አለበት፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

የሕግ ባለሙያውና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ታደሰ ሌንጮ (ዶ/ር) ስለ ንብረት ታክስ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ሲሰጡ፣ መሬትን መሠረት ያደረገ የንብረት ታክስ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜም ተግባራዊ ይደረግ የነበረና ለኢትዮጵያም አዲስ እንዳልሆነ ነው፡፡ አሁን ያሉት የታክስ ሕጎች የንብረት ታክስን በሕግ ማዕቀፍ እንደሚያውቁት፣ ነገር ግን የንብረት ባለቤቶች መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም በተለምዶ ‹‹የጣራና ግድግዳ›› በሚል የንብረት ታክስ እንደሚከፍሉ ተናግረዋል፡፡

ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የንብረት ታክስን እንዲያስተዳድሩ በምክር ቤቶቹ መወሰኑን እንደ ትክክለኛ ዕርምጃ የወሰዱት ታደሰ (ዶ/ር)፣ የፌደራል መንግሥት ለዚህ ዓይነት ታክስ እንዲያውም ሩቅ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ንብረቱ ያለበት አካባቢ ያለው አስተዳደር ለንብረቱ ዋጋ መኖር አስተዋጽኦ አለው፡፡ ባለንብረቱ ቤቱን ሲሸጥ መብራቱንም፣ መንገዱንም ደኅንነቱንም አብዛኛውን የአካባቢውን ይዘቶች ነው አብሮ የሚሸጠው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሕግ ባለሙያው በከተሞች መካከል ሊፈጠር ስለሚችል የሀብት ስፋት ሲያስረዱ፣ ትልቅ ችግር ሊሆን እንደሚችልና መንግሥት ለዚህ መፍትሔ ሊሆን የሚችል አሠራር ማምጣት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ‹‹በሀብታም ከተማ ዳጎስ ያለ ትርፍ ይገኛል፣ ደሃ ከተማ ደግሞ እንደዚያው ይጎዳል፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም ሲያስረዱ የክልል መስተዳድሮችም የንብረት ታክስን የብቻ ሥልጣናቸው ሳይሆን ማድረግ ያለባቸው፣ በየከተሞቹ ለሚገኙ መስተዳድሮች ሰጥተው በራሳቸው መሰብሰብ እንዳለባቸው ነው፡፡ ‹‹አዲስ አበባም ቢሆን በክፍለ ከተማ፣ ከተቻለም በወረዳም መውረድ ነው ያለበት፡፡ የንብረት ታክስ ከአንድ ቦታ ተሰብስቦ ለሌላ ቦታ ሊውል አይገባም፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች