Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትለዘመናት ከእንቅልፉ ያልነቃው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የወደፊት ዕጣ ፈንታ

ለዘመናት ከእንቅልፉ ያልነቃው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የወደፊት ዕጣ ፈንታ

ቀን:

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ‹‹ዘርፈ ብዙ የግምገማ ጥናትና የልማት ፍኖተ ካርታ›› በሚል ርዕስ ያስጠናውን ጥናት ለሁለት ቀናት ለክለብ አመራሮች፣ አሠልጣኞች፣ የዳኞች ማኅበር፣ የተጫዋቾች ማኅበር እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አቅርቧል፡፡ ጥናቱ በአሜሪካ ታውሰን ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር እንዲሁም የፌስ ኮርነር አማካሪ ጋሻው አብዛ (ዶ/ር) አማካይነት ለአንድ ዓመት ከመንፈቅ የተሠራ ነው፡፡

ጥናቱ በዋነኝነት በክለብ ፈቃድ አሰጣጥ፣ የክለብ የባለቤትነት ይዞታና የተጫዋቾች የደመወዝ ክፍያ አስተዳደር ጋር በተያያዘ ያጠነጥናል፡፡

ክለቦች በፕሮፌሽናል መንገድ እንዲመሩ ለማስቻል፣ በሊግ ውድድር ውስጥ ለመሳተፍ ሊያሟሉ የሚያስፈልጋቸው ዝቅተኛ መሥፈርቶችን ይዞ የክለብ ፈቃድ አሰጣጥ መመርያው በፊፋ ተሰናድቷል። ሆኖም፣ የፊፋ ክለብ ፈቃድ አሰጣጥ መመርያ (ሃንድቡክ) እንዳሰፈረው የክለቦች አቅም ከአገር አገር እንደሚለያይ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በመመሪያው አፈጻጸም ላይ የሚያርፈው የጫና መጠን ከአኅጉር አኅጉር ሊለያይ እንደሚችል ጥናቱ ይጠቁማል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የክለቦች ፈቃድ አሰጣጥ መሥፈርቶቹ በአነስተኛው ደረጃ መሟላት ያለባቸው መጠይቆች እንደመሆናቸው፣ በጊዜ ሒደት በሁሉም ዘንድ የመመሪያው ተፈጻሚነቱ የግድ እንደሚሆን ተመላክቷል። በኢትዮጵያ ተፈጻሚ የሚሆነው መመሪያ ካፍ ባሰናዳው ላይ የሚመረኮዝ ሲሆን፣ አምስት መመዘኛዎች ማለትም የስፖርት፣ የመሠረት ልማት፣ የሰው ኃይል፣ የሕግ፣ የፋይናንስ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡

የፊፋ ኮንግረስ በሙኒክ በ2006 ዓ.ም. ባወጣው ውሳኔ መሠረት፣ የክለብ ፈቃድ አሰጣጥ ከተመረኮዘባቸው መሠረታዊ ዓላማዎች መካከል፣ የክለብ ውድድሮችን ታማኝነት መጠበቅ፣ በእግር ኳስ ቤተሰብ ውስጥ የሙያ ደረጃን ማሻሻል፣ የስፖርት እሴቶችን ማሳደግ፣ እንዲሁም በፍትኃዊነት መርሆዎች ላይ መሠረት ያደረጉ መሆናቸው ጥናቱ ያመለክታል፡፡

በተጨማሪም ደኅንነቱ የተጠበቀ የግጥሚያ መድረኮችን ማመቻቸት፣ በክለቦች ፋይናንስ አያያዝ ዙሪያ ግልጽነትን ማሳደግ፣ በክለቦች የባለቤትነት ይዞታ ዙሪያ ግልጽነትን ማስፈን፣ እንዲሁም በክለቦች ቁጥጥር ውስጥ ግልጽነትን ማጎልበት የሚሉት በጥናቱ ተዳሰዋል፡፡ በሌላ በኩል መሥፈርቶቹን በማያሟሉ ከለቦች ላይ የሚጣለው ገደብ ወይም ቅጣቶች ከሚያካትቷቸው መካከል ማስጠንቀቂያ፣ መቀጮና ማስረጃ የማቅረብ ግዴታ ሲሆኑ፣ አስፈላጊ ከሆነም ነጥቦችን መቀነስ እንዲሁም አዲስ የተጫዋቾች ዝውውርን ወይም የተጫዋቾች ኮንትራቶችን ማገድ የሚያስችል ቅጣቶች ተቀምጠዋል፡፡

የእግር ኳስ ክለቦች  ፈቃድ የሕግ ማዕቀፍ

የክለብ ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያ መሥፈርቶች ከፊፋና ከካፍ የተላለፉ እንደሆኑ በስፋት ቢነገርም፣ መሠረታዊ የሆኑት መሥፈርቶቹ ከፊፋ አስቀድሞ የስፖርት ኮሚሽን በ2005 ዓ.ም. ባወጣው መመሪያ አስቀምጧል። ኮሚሽኑ በ2005 ዓ.ም. ባፀደቀው የስፖርት ማኅበራት ስለሚቋቋሙበት ሁኔታ ለመወሰን በወጣ መመሪያ አንቀጽ 14 ሥር ‹‹የስፖርት ክለቦች በመኖሪያ አካባቢና ከተሞች፣ በድርጅትና በፋብሪካዎች እንዲሁም ስፖርቱን ለንግድ (ለትርፋማነት) በሚጠቀሙ ባለሀብቶች ሊመሠረቱ የሚችሉ ሆኖ፣ ሕጋዊ ዕውቅና ለማግኘት የሚከተሉትን መመዘኛ ማሟላት አለባቸው፤›› በማለት ያስቀምጣል፡፡

በፕሪሚየር ሊጉ ሥር ያሉ ክለቦች ፣ የፊፋና የካፍ የክለብ ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያን ብቻ ሳይሆን የአገሪቷን ገዥ መመሪያ ሆኖ የሚገኘው በ2005 ዓ.ም. የፀደቀው የስፖርት ማኅበራት አደረጃጀት መመሪያን ተከትለው የሚጠበቅባቸውን መሥፈርቶች እንዲያሟሉ ማስገደድ የብሔራዊ ፊዴሬሽኑና የሊጉ ኃላፊነት ነው።

በጥናቱ ላይ በቀረበው ምክረ ሐሳብ መሠረት፣ ሊጉና ፌዴሬሽኑ ቀጥተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው አካላት፣ በጣምራ ለክለቦች የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሮችን በማዘጋጀት፣ አግባብነት ካለው ቢሮ ሄደው ፈቃድ የሚያወጡበትን መንገድ ሊያመቻቹ እንደሚገባ አቅርቧል፡፡ ከክለቦች ፈቃድ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በጥናቱ ከተሳተፉ ከ90 በላይ የእግር ኳሱ ቀጥተኛ የባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገው ቃለ መጠይቅ እንደተመለከተው ለረዥም ጊዜ ፌዴሬሽኑ የማስታመም ሥራ ላይ እንደቆየና መመሪያውን ለማስፈጸም ‹‹ቁርጠኝነት›› የተሞላበት አመራር መጥፋቱ ተጠቁሟል፡፡ በፊፋና ካፍ የተቀመጡትን መሥፈርቶች እንዲያሟሉ በመጠየቅ በኩል ብዙ መጓዝ እንደሚጠበቅም ተሳታፊዎች በተደጋጋሚ ገልጸዋል። በፈቃድ አሰጣጡ ትግበራ ላይ ጥብቅ ዕርምጃ ላለመወሰዱ ምክንያቶች እንደሆኑ በተወሰኑ ተሳታፊዎች መነሳቱን ጥናቱ ጠቅሷል፡፡

በጥናቱ ከቀረቡት ምክንያቶች መካከል ከአቅም በላይ የሆኑ ወቅታዊ ጫናዎች በዋናነት ተጠቅሷል። እነዚህም አገር ወክለው በካፍ የክለብ ውድድሮች ለመሳተፍ ያለፉ ክለቦችን ማገድ ብሔራዊ ጥቅምን ስለሚጎዳ፣ ክለቦች መሥፈርቶቹን አለማሟላታቸውን ሲነገራቸው ከየአካባቢው ከፍተኛ ባላሥልጣናት በግል ቀርበው በቀጣይ እንደሚሟሉ ቃል በመግባት መማፀን፣ ክለብ ላይሰንሲንግን በሚመለክት እስካሁን በተሰጡት የግንዛቤ ማስጨበጫ ወርክሾፖች የተካፈሉት ግለሰቦች የሚመለክታቸውና ወሳኔ ሰጪ አካላት አለመሆናቸው ተነስተዋል፡፡

የክለቦች የባለቤትነት ይዞታ

ሌላኛው በጥናቱ በስፋት የተዳሰሰው ጉዳይ የክለቦች የባለቤትነት ይዞታ ሲሆን  ክለባቱ ለረዥም ጊዜያት ሲያስተናግዷቸው የቆዩት በርካታ፣ ሥር የሰደዱና ውስብስብ እንከኖች፣ የክለባቱን ጥንካሬዎች እንዲውጧቸው ሆኖ ተመልክቷል።

እንደ ጥናቱ ተሳታፊ ምልከታ ከሆነ በመንግሥት ይዞታነት ሥር ያሉት ክለቦች ላይ ያተኮሩ ናቸው። በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ሥር ያሉ ክለቦች  የመንግሥት የፋይናንስ ጥገኛ መሆናቸው፣ የቦርድ አመራር አደረጃጀታቸው የመንግሥት የጎላ ጣልቃ ገብነት ማስተናገዱ፣ ተቋማዊ ቁመናቸው ደካማ መሆኑ፣ የብሔር መገለጫ መደረጋቸው እንዲሁም በተደራጀ ድርጅታዊ (አስተዳደራዊ) መዋቅር አለመዋቀራቸው በዋነኝነት ተነስተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በመስኩ በሠለጠነ ባለሙያ አለመመራታቸው፣ የፋይናንስ አስተዳደር ግልጽነትና ተጠያቂነት ጎልቶ የማይታይባቸው መሆኑ፣ በተደራጀ የበጀት ዕቅድ የሚመሩ አለመሆናቸውና የበጀት አጠቃቀም ጉድለት በተደጋጋሚ የሚታይባቸው መሆኑ እንደ ችግር መስተዋላቸው በጥናቱ ተመልክተዋል፡፡

በተለይ የተጫዋቾች ክፍያ አስተዳደር ዙሪያ ጉድለቶች መኖራቸው፣ የገቢ ምንጭ የማስፋፋት ተነሳሽነታቸው አናሳ መሆኑ፣ ለታዳጊና ተተኪ ተጫዋቾች ልማት አናሳ ትኩረት መስጠታቸውና የተሟሉ የመለማማጃና መጫወቻ ማዘውተሪያዎች እንዲሁም ስታዲየሞች እጥረት መኖራቸው ዋነኞቹ ናቸው። በተጨማሪ፣ በፖለቲካ ጫና ውስጥ የሚኖሩ መሆኑ፣ ለከፍተኛ የመፍረስ (የመቋረጥ ዕድል የተጋለጡ) መሆናቸው እንዲሁም ጊዜያዊ ስኬት (ሜዳ ላይ ያተኮረ) አሠራር በስፋት መስፈኑን በርካታ የጥናቱ ተሳታፊዎች ተጋርተውታል፡፡

የአፍሪካ የእግር ኳስ ክለቦች የባለቤትነት ይዞታ

በአውሮፓ ከሚገኙት የክለብ ባለቤትነት ይዞታ ሁለት ዓይነቶች ሲኖሩ የግልና የሕዝብ (ማኅበረሰብ) ብሎ ያስቀምጣችዋል፡፡ የአፍሪካ ተመክሮ ሦስተኛ የባለቤትነት ይዞታ ያለው ነው፡፡ የአፍሪካ ክለቦች የባለቤትነት ይዞታ ሦስት መልክ ሲኖረው የግል፣ የማኅበረሰብና የመንግሥት እንደሚተዳደሩ ያስረዳል፡፡

በምሳሌነትም የዛምቢያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኮሚቴ የሚመራ ሲሆን እ.ኤ.አ. ከ2020 ጀምሮ የዛምቢያ ፕሪሚየር ሊግ ከፌዴሬሽኑ ተገንጥሎ ራሱን ችሎ የሚተዳደር ሲሆን፣ የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ እንዲሁ ከሦስት ዓመት በፊት ከፌዴሬሽኑ ሥር ተላቆ መደራጀቱ በምሳሌነት ይቀርባሉ። በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2014 የውደድር ዓመት ተሳታፊ ከሆኑት 16 ክለቦች አብዛኛዎቹ በመንግሥት የሚደገፉ ናቸው፡፡ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና  ለረዥም ጊዜ ሕዝባዊ (የማኅበረሰብ) ሆነው ከቆዩ ክለቦች በቀር ሌሎቹ ክለቦች የገንዘብ ምንጫቸው የክልል፣ የዞን፣ ወይም የከተማ አስተዳደሮች ናቸው፡፡ በሊጉ ከሚሳተፉ ክለቦች ሁለቱ በማኅበረሰብ የባለቤትነት ይዞታ የሚተዳደሩት በዕድሜ አንጋፋ የሆኑት ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስ (87 ዓመት) የኢትዮጵያ ቡና (47 ዓመት) እና እግር ኳስ ክለቦች ናቸው።

ከመንግሥት የባለቤትነት ይዞታ ጋር በተያያዘ በፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች  አደረጃጀት አስተዳደር እንዲሁም አወቃቀር ላይ መንግሥታዊ የአሠራር ቅርፅ እንዲላበሱ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩ በጥናቱ የባለድርሻ አካላት ያነሱት ጉዳይ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ይህ ነባር አሠራር ለረዥም ጊዜ ሰፎኖ (በ1991 ከወጣው የኢትዮጵያ የስፖርት ፖሊሲ ጀማሮ) ከቆየበት ምክንያቶች አንዱ በአገሪቷ ውስጥ ያሉ ክለቦች  የሕግ ቅርፅና አመሠራረትን በተመለክተ ራሱን የቻለና የጠራ የሕግ ማዕቀፍ የሌለ እንደሆነ ሲነገር ቢቆይም፣ የአገሪቷ የሕግ ማዕቀፎች የመንግሥት ሚና የመደገፍ እንደሆነና ክለቦችን በባለቤትነት የሚመራው ሕዝቡ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡

የኢትዮጵያ ክለቦች  በንግዱ ዓለም የመመዝገባቸው ዓውድ

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ በ2011 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የንግድ ሥራ ፈቃድ መስጫ መደብ መመሪያ ቁጥር 17/2011 አውጥቷል። መመሪያው ከዘረዘራቸው ዘጠኝ ዋና የዘርፍ መደቦች መካከል፣ ስፖርት፣ በቀረቡት ሦስት ዋና የዘርፍ መደቦች ሥር ተጠቅሷል። የእግር ኳስ ክለብ ከቡድንነት ባሻገር፣ እንደ ድርጅት ዘመናዊ ክለቦች  የፋይናንስ አቅማቸውን ለሚገነቡበት የገቢ ምንጮችና ለዚያም የሚያከናውኗቸውን ተግባራት አንጥሮ ማውጣት ቢቻል፣ ክለቦች  ወጥ በሆነ አንድ የንግድ ዘርፍ ሳይሆን በተለያዩ የፈቃድ መስጫ መደቦች ሥር ተመዝግበው ሊሠሩ እንደሚችሉ ያሳያል።

በዚህ ረገድ፣ ዘመናዊ ክለቦች ቢያንስ ሰባት የገቢ ምንጮች እንዳሏቸው የስፖርት ቢዝነስ ሳይንሳዊ መረጃዎች በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ያሉ ክለቦች ግን ሲተገብሩት አለመስተዋሉ ተነስቷል፡፡ ጥናቱ ክለቦች ራሳቸውን ችለው መጓዝ እንዲችሉ አማራጭ መንገዶችን ያመላከተ ሲሆን፣ በፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ሥር ያሉ ክለቦችን ወደ ሕዝባዊነት መቀየር፣ መንግሥት እንደ አንድ ባለቤት የተወሰነ ድርሻ ወስዶ መቀጠል የተመዘገቡ ደጋፊዎችና ባለሀብቶች የባለቤትነት ድርሻ እንዲኖራቸው ለማድረግ ምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡

የተጫዋቾች ክፍያ አስተዳደር

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች  አሁን ባለው አሠራር እያንዳንዱ ክለብ በአማካይ 70 በመቶ (40 ሚሊዮን) ወጪው ለደመወዝ ክፍያ እንደሚውል ጥናቱ ያስቀምጣል፡፡ በዚህም ሥሌት አንደ ተጫዋች በአማካይ 2,667.00 ዶላር በወር ይከፈለዋል፡፡

ክለቦቹ ለተጫዋቾቻቸው የሚከፍሉት ክፍያ ለተጫዋቾቹ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ መሆኑ በበጎነት በጥናቱ ቢነሳም የክፍያው መጠን፣ በአንድ በኩል በረዥም የክለቦች የዕድገት ጉዞ ውስጥ የሚያዛልቅ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ በአንፃሩ እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ላለ አገር ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እንደ መንገድ፣ የጤና ማዕከላት፣ ትምህርት ቤቶች ባሉ መሠረተ ልማቶች ላይ ሊፈስ ሲገባው የመንግሥት ገንዘብ ለተጫዋቾች ክፍያ መዋሉ አግባብ አይደለም የሚሉ አስተያየቶች ተጋርተዋል።

ጥናቱ የተጫዋቾችን ከፍያ ጤናማ ለማድረግ ልማትን ያማከለ የደመወዝ ክፍያ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል፡፡ በዚህም ክለቦች ከስታዲየምና ከስፖንሰርሺፕ ከሚገኙ ገቢዎች የሰከነ አገራዊ የደመወዝ ክፍያ እንዲሰፍን የሚያግዝ ከመሆኑም ባሻገር ልማታዊ ሥራዎችን በሒደት ለማደራጀት እንደሚያስችል ያስቀምጣል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...