Saturday, April 1, 2023

የምዕራባዊያንና የቻይና የዲፕሎማሲ ፉክክር በኢትዮጵያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኢትዮጵያ ለቻይና ዕውቅና የሰጠችው እ.ኤ.አ. በ1970 እንደሆነ ታሪክ ያወሳል፡፡  ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በቀጣዩ ዓመት ቻይናን የጎበኙ ሲሆን፣ ከሊቀመንበር ማኦ ዜዶንግ ጋር የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የሚያጠናክር ጠቃሚ ስምምነቶች እንደተፈራረሙም ይነገራል፡፡ ቻይና ከዚያ በቀደመ ዘመንም ቢሆን ለኢትዮጵያ ጠንካራ አጋርነት ከሚያሳዩ ጥቂት አገሮች ተርታ ትመደባለች፡፡

በተለይ እ.ኤ.አ. ከ1936 እስከ 1941 ኢትዮጵያ በፋሽስት ጣሊያን በተወረረች ወቅት፣ ከጎኗ ከቆሙ ጥቂት የዓለም አገሮች ቻይና አንዷ ነበረች፡፡ በጊዜው ቻይናን ይመራ የነበረውና በኮሙኒስቶች ተሸንፎ ከተባረረ በኋላ፣ ታይዋንን ይዞ የተገነጠለው የቺያንግ ካይ ሼክ መንግሥት በይፋ ኢትዮጵያን ደግፎ በመቆም አጋርነቱን ማሳየቱ ይወሳል፡፡ የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ1949 ለተመሠረተው የቻይና ኮሙዩኒስታዊ መንግሥት ዕውቅና ለመስጠት ከዘገየባቸው ምክንያቶች አንዱ፣ ወደ ታይዋን ከተባረረው የቀድሞ መንግሥት ጋር መልካም ግንኙነት ስለነበረው እንደሆነ ይነገራል፡፡

የምዕራባዊያንና የቻይና የዲፕሎማሲ ፉክክር በኢትዮጵያ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክና ከፈረንሣይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪን ኮሎና ጋር

ኢትዮጵያ ለታይዋን ዕውቅና ባትሰጥም፣ ነገር ግን ከታይዋንም ሆነ ከቻይና ጋር መልካም ግንኙነት መሥርታ ቆይታለች፡፡ ለአብነት ያህል በ1956 ዓ.ም. የቻይና ልዑክ ኢትዮጵያን የጎበኘ ሲሆን፣ በዚያው ጊዜ ደግሞ ከታይዋን የግብርና ዕርዳታ አግኝታለች፡፡ ይሁን እንጂ በቀጣዩ ዓመት ከቻይና ጋር የቀጥታ ንግድ ግንኙነት ለመጀመር በይፋ ስምምነት ፈርማለች፡፡ ኢትዮጵያ ከምዕራባውያኑ ጋር በነበራት የጠበቀ ወዳጅነት እ.ኤ.አ. ከ1950 እስከ 1958 በነበሩት ዓመታት የታይዋንን ሉዓላዊ አገር የመሆን ጥረት ስትደግፍ ቆይታለች፡፡ ይሁን እንጂ በ1959 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዚህ ጉዳይ ላይ በተሰጠ ውሳኔ፣ ኢትዮጵያ ድምፀ ተዓቅቦ በማድረግ ገለልተኝነቷን አንፀባርቃለች፡፡ እነሆ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ኢትዮጵያ የቻይናንም ሆነ የታይዋንን ጥቅም ሳትጎዳ፣ ሁሉንም አቻቻይ የሆነ ሚዛናዊ ዲፕሎማሲን ስትከተል ቆይታለች፡፡

እርግጥ ነው በ1960ዎቹ የቻይና መንግሥት የኤርትራ ነፃ አውጪዎችን መደገፉ ይነገራል፡፡ ለደርግ መንግሥት የጦር መሣሪያ አንሸጥም እስከ ማለት ደርሶ እንደነበርም ይታወቃል፡፡ ያም ቢሆን ግን ቻይና በ1964 ዙ ኤንላይ የተባሉትን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ወደ አዲስ አበባ በመላክ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ሁለንተናዊ ግንኙነቷን ለማሻሻል ጥረት ማድረጓ ይወሳል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1978 የቦንጋ የዲዝል ኃይል ማመንጫ ጣቢያ እንዲተከል ቻይና ድጋፍ አድርጋለች፡፡ በ1975 የተጀመረውንና ዛሬም ድረስ ‹‹የቻይና መንገድ›› በሚል ስያሜ የሚጠራውን የወረታ ወልዲያ መንገድ በመገንባትም ረድታለች፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1988 ጀምሮ በየዓመቱ ለአሥር ኢትዮጵያውያን የምትሰጠውን የትምህርት ዕድልም አላቋረጠችም፡፡ ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ በቦታው ሲተካ ግን የኢትዮ ቻይና ወዳጅነት እጅግ ከፍ ወዳለ አጋርነት መሸጋገር ጀመረ፡፡ በብዙ ውጣ ውረዶች ያለፈው የኢትዮጵያ የቻይና ግንኙነት በተለይ በ1995 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ካደረጉት የቻይና ጉብኝት በኋላ በእጅጉ ተጠናከረ፡፡ በ1996 ዓ.ም. የቻይና ፕሬዚዳንት ጂያንግ ዜሚን በኢትዮጵያ ጉበኝት ማድረጋቸው፣ ለሁለቱ አገሮች ግንኙነት የበለጠ መጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2006 ዓ.ም. ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በቻይና የተካሄደውን የቻይና አፍሪካ ስብሰባ በመካፈል፣ ኢትዮጵያ ቻይና ከአፍሪካ ጋር ለምትሻው ግንኙነት መጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላት አሳይተዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒትር መለስና ከእሳቸው ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በተደጋጋሚ ጊዜ ወደ ቻይና ለመጓዝ የበቃው ጋዜጠኛና የውጭ ግንኙነት ባለሙያ ፍትሕ አወቅ የወንድወሰን፣ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በልዩ ትኩረት ይዛ መቆየቷን ይናገራል፡፡

‹‹የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በየአሥር ዓመታቱ ነው የሚለዋወጡት፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት በቻይና ወደ ሥልጣን የመጡት ሦስቱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ቀዳሚዋ የጉብኝት መዳረሻቸው ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት በጠባ ቁጥር የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ አፍሪካ ይመጣሉ፡፡ ሁልጊዜ አፍሪካ ሲመጡ ደግሞ ቀድመው ኢትዮጵያን በመጎብኘታቸው ዘንድሮ 33 ዓመት ተቆጠሩ፤›› በማለት፣ ከሰሞኑ ኢትዮጵያን የረገጡት ቺን ጋንግ ይህንኑ ታሪክ መድገማቸውን አውስቷል፡፡

‹‹ቻይናውያን ከዓለም ጋር ባላቸው ግንኙነት በየቀጣናው ዋና መግቢያ በር ብለው የለዩዋቸው አገሮች አሉ፡፡ በአፍሪካ አኅጉር ደግሞ ኢትዮጵያ ዋናዋ የግንኙነታቸው ማጠናከሪያ ድልድይ እንድትሆን ይፈልጋሉ፡፡ በቻይና ሦስተኛው ምዕራፍ አብዮት እየተካሄደ መሆኑን መሪዎች ይናገራሉ፡፡ እነ ማኦ ዜዶንግ የጀመሩት አብዮት የቻይናን የግዛት አንድነት ማረጋገጥና የባህል አብዮት ነበር፡፡ በዴንግ ዣኦ ፒንግ የተጀመረው ደግሞ የኢንዱስትሪ አብዮት ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በዢ ጂን ፒንግ የተጠነሰሰው የቀደመውን የቻይና ሥልጣኔና ኃያልነት መመለስ የሚል ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ እ.ኤ.አ. በ2013 ይፋ ያደረጉት የቤልትና ሮድ ፕሮጀክት (Belt and  Road Initiative) በአጠቃላይ ከ1.2 እስከ 1.3 ትሪሊዮን ዶላር እስከ 2027 የሚፈስበት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ዕቅድ ደግሞ ኢትዮጵያን ጭምር አንዷ ማዕከል ያደረገና ቻይና በመላው ዓለም እንድትንሰራፋ የሚያግዝ ግዙፍ ዕቅድ ነው፤›› ሲልም ፍትሕ አወቅ የቻይናን ፍላጎት ያብራራል፡፡

‹‹ቻይና በተለይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር ለ70ኛ ዓመት የአብዮት በዓል በሄድኩ ጊዜ ዢ ጂን ፒንግ ስለኢትዮጵያ ጠንካራ ንግግር ሲናገሩ አስታውሳለሁ፡፡ ኢትዮጵያ የማትናወፅ ወዳጃችን፣ ከአፍሪካ ጋር ለመተሳሰር ዋና በራችን ሲሉም ነበር፡፡ ቻይና ይህን የምትልበት ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ብቻ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ለማንም ያልተገዛች ነፃ አስተሳሰብና የራሷ አቋም ያላት አገር ናት፡፡ አሁን ሁለቱ አገሮች በኢኮኖሚ ይተሳሰሩ እንጂ ወደፊት በፖለቲካ ለመተሳሰርም፣ ኢትዮጵያ ለቻይኖቹ እንደ አንዷ ሞዴል አገር ነው የምትታየው፤›› በማለት ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር የበለጠ ለመቀራረብ ያላትን ፍላጎትም አብራርቷል፡፡

ቻይና በአዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ ኅብረትን ዋና መቀመጫ በ200 ሚሊዮን ዶላር ገንብታለች፡፡ እ.ኤ.አ. በ2006 ኢትዮጵያ ከሦስት የቻይና ኩባንያዎች ጋር የ1.5 ቢሊዮን ዶላር የቴሌኮም መሠረተ ልማት ዝርጋታ ስምምነት ተፈራርማ ነበር፡፡ ወደ 365 ሚሊዮን ዶላር የፈሰሰበት የተከዜ ኃይል ማመንጫ ግድብ አበዳሪና ገንቢም ቻይና ነበረች፡፡ ይህ የኃይል ፕሮጀክት ትስስር ደግሞ በግልገል ጊቤ ሦስት ፕሮጀክትም የበለጠ ሲጠናከር ነው የታየው፡፡ አሁን የቻይና ተቋራጮች ኢትዮጵያውያን በልዩ ትኩረት በሚያስገነቡት ታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ጭምር እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

እ.ኤ.አ. በ2010 ከቻይና ዘጠኝ መርከቦችን ለመግዛት የተስማማችው ኢትዮጵያ፣ በ2013 ደግሞ ወደ ሦስት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣውን የኢትዮ ጂቡቲ ባቡር መስመር ግንባታ ስምምነት ተፈራርማ ነበር፡፡ ቻይናውያን ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞንን በዱከም አካባቢ በ713 ሚሊዮን ዶላር በማስገንባት የጀመሩት የኢንቨስመንት እንቅስቃሴ፣ በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር አሳድገውታል፡፡

ኢትዮጵያና ቻይና ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረውን ይፋዊ ግንኙነታቸው፣ በተለይ በኢኮኖሚው መስክ ዛሬ ላይ ወደ ተጠናከረ ደረጃ መሸጋገሩ ይነገራል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1971 ቻይና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ለማግኘት ጥረት ስታደርግ ኢትዮጵያ እንደደገፈቻት ሁሉ፣ በቅርብ ጊዜያት ደግሞ ኢትዮጵያ የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ኢፍትሐዊ ዳኝነት ሰለባ እንዳትሆን ቻይና ድምፅን በድምፅ በመሻር መብቷ ብዙ ታግላለች፡፡

ቻይና በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ ቀዳሚዋ ናት፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2016 ጀምሮ ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ ፈሷል፡፡ የሁለቱ አገሮች የንግድ ግንኙነት ደግሞ በየዓመቱ የ22 በመቶ ዕድገት ያሳየ ሲሆን፣ ወደ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ልውውጥ መድረሱም ይነገራል፡፡ የቻይና ኩባንያዎች ከ1,200 በላይ ፕሮጀክቶችን ገንብተዋል፣ ከ60 ሺሕ በላይ የሥራ ዕድል በኢትዮጵያ ፈጥረዋል ነው የሚባለው፡፡

ይህ ሁሉ ሲታይ አዲሱ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት እጅግ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የዲፕሎማሲ ክንውን መሆኑ ተነግሯል፡፡ ጠቅላይ ሚኒትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን አስቀድመው መጎብኘታቸው በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የማይናወጥና ጠንካራ ግንኙነት ያሳያል ነበር ያሉት፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቺን ጋንግ አዲስ አበባ ሲገቡ የተቀበሏቸውና ሰፊ ውይይትም ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም ሲሆኑ፣ ሁለቱ አገሮች ታሪካዊ የሆነ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ወዳጅነት እንዳላቸው አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያና ቻይና መከባበርና የጋራ ጥቅምን ያስቀደመ ግንኙነት መገንባታቸውን አቶ ደመቀ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ‹‹ቻይና ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መከበር ያላትን ጠንካራ አቅም ለማመሥገን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቺን ጋንግ ጉብኝት ዕድል ፈጥሮልናል፤›› በማለት አቶ ደመቀ መናገራቸውም ተዘግቧል፡፡ ሁለቱ ሚኒስትሮች የጋራ ትብብር አጋርነት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውም ተዘግቧል፡፡

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአዲስ አበባ አገራቸው ያስገነባቸውን የአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል (Africa CDC) ዋና ጽሕፈት ቤትን፣ ከኢትዮጵያና ከአፍሪካ ኅብረት ባለሥልጣናት ጋር መርቀው ከፍተዋል፡፡

‹‹የአፍሪካ ሲዲሲ መቀመጫን ከአዲስ አበባ ለመውሰድ ጥረት ቢደረግም፣ ቻይና በኢትዮጵያ እንዲሆን ባላት ፅኑ ፍላጎት ግንባታው ተካሂዷል፤›› በማለት ፍትሕ አወቅ የፕሮጀክቱን ዲፕሎማሲያዊ አንድምታ ይናገራል፡፡

‹‹ከሁሉ በላይ መነሳት ያለበት ግን በቻይናና ኢትዮጵያ መካከል የዕዳ ስምምነት መፈረሙ ነው፤›› ይላል፡፡ ኢትዮጵያና ሌሎች ታዳጊ አገሮች የዕዳ ሽግሽግ እንዲደረግላቸው ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትን መጠየቃቸውን ያስታውሳል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ የዕዳ ሽግሽግ ጥያቄ በተለይ ቻይና ፈቃደኛ አልሆነችም በሚል በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ)፣ በፓሪስ አበዳሪዎችና በምዕራባውያን አገሮች ተቀባይነት ሳያገኝ ቆይቷል፤›› ሲልም ያስታውሳል፡፡

‹‹አሁን ግን ለኢትዮጵያ ትልቋ የብድር ምንጭ የሆነችው ቻይና የዕዳ ሽግሽግ ለማድረግ ተስማምታለች፡፡ ይህ ደግሞ ከሰሞኑ የተገኘ አንኳር የሚባል የዲፕሎማሲ ስኬት ነው፤›› በማለት ፍትሕ አወቅ ያስረዳል፡፡

ከሰሞኑ በትልቅ ደረጃ ትኩረት የሳበው የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት ብቻ ግን አልነበረም፡፡ የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ፣ እንዲሁም የፈረንሣይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪን ኮሎና ሰሞኑን ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውም እንዲሁ ትኩረት የሳበ ትልቅ ጉዳይ ነበር፡፡ ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እግርን ተከትለው መምጣታቸው ደግሞ፣ ምዕራባውዊያኑ ከቻይና ጋር በኢትዮጵያ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ፉክክር እያካሄዱ ነው የሚለውን መላምት የበለጠ አጠናክሮታል፡፡

የጀርመኗም ሆነ የፈረንሣይዋ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉብኝት በዋናነት በመንግሥትና በሕወሓት መካከል የተፈረሙ የሰላም ስምምነቶችን ገቢራዊነት ለመመልከት የተደረገ መሆኑ በሰፊው ተዘግቧል፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የአውሮፓ ኅብረትና የኢትዮጵያን ግንኙነት የሚወስን ስለመሆኑም በተመሳሳይ ተነግሯል፡፡ በሰላም ሒደት፣ በሰብዓዊ ረድኤትና በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገው የሁለቱ ባለሥልጣናት ጉዞ በተቃራኒው ደግሞ እንደ ቻይና ያሉ ኃያላን አገሮችን በዲፕሎማሲ ሽሚያው የመፎካከር ግብ ያለው መሆኑን በርካቶች እየተናገሩ ነው፡፡

ይህን የሚያጠናክር ሐሳብ የሰጡት አንድ የሪፖርተር ዲፕሎማሲ ምንጭ በበኩላቸው፣ አገሪቱ ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን አጠናክራ እስከ ቀጠለች ድረስ ከዚህ መሰሉ ዲፕሎማሲያዊ ሽሚያ ትጠቀማለች እንጂ አትጎዳም ይላሉ፡፡

‹‹ኢትዮጵያ በጦርነት በቆየችበት ባለፉት ጥቂት ዓመታት የገጠማት የውጭ ዲፕሎማሲያዊ ፈተና ክብደት በደርግ ዘመን እንኳን አልገጠማትም፡፡ መንግሥት በዚህ ፈታኝ ጊዜ የማስገንዘብ ግንኙነት ሲከተል የቆየ ሲሆን፣ ነገሮች ሲከሩና እየሻከሩ ሲሄዱ ደግሞ የማለዘብ የውጭ ግንኙነት ዘዴዎች ተከትሏል፤›› በማለት ዲፕሎማቱ ይናገራሉ፡፡

‹‹በተለይም ምዕራባውያኑ በጦርነቱ መካከል በኢትዮጵያ የሥርዓት (የመንግሥት) ለውጥ ካልመጣ እስከ ማለት ደርሰው ነበር፤›› ሲሉም ያስረዳሉ፡፡ ጉዳዩን ዓለም አቀፍ አጀንዳ አድርገው በፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ኢትዮጵያን ሲከሱ የቆዩትም በዚሁ መነሻነት መሆኑን ያብራራሉ፡፡

የምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ የተከተሉትን ሚዛኑን የሳተና ፅንፍ የወጣ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንዲቀለብሱ የሚያስገድዱ ክስስቶች ባለፉት ጥቂት ወራት መፈጠራቸውንም ነው የዲፕሎማሲ ምንጩ የሚናገሩት፡፡ ‹‹የሰላም ስምምነቱ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ በፐብሊክ ዲፕሎማሲው ዘርፍና በሕዝብ ግንኙነቱ ጠንካራ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ሌላው ወሳኝና ቁልፍ ጉዳይ በኢኮኖሚ ሪፎርሙ ብዙ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ይህ ሁሉ ምዕራባውያኑ ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ እንዲያዞሩና በትብብር እንዲሠሩ አስገድዷቸዋል፤›› ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ ‹‹ተቸንካሪ›› የሚባል የውጭ ግንኙነት እንደማትከተልና መንግሥትም ተራማጅ የሆኑ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዎችን እንደሚያራምድ ያብራሩት ዲፕሎማቱ፣ ከቻይናም ሆነ ከምዕራባውያኑ ወይም ከሌሎች ኃያላን አገሮች ጋር ‹‹አገራዊ ክብር፣ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት፣ እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብር›› ግንኙነት መመሥረት ላይ ትኩረት እንደምታደርግ ተናግረዋል፡፡

ሐሙስ ጥር 4 ቀን 2015 ዓ.ም.  ምሽት የኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት (Ethiopian American Civil Council) የተባለው በቅርብ ዓመታት፣ በተለይም በጦርነቱ ወቅት ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ድጋፍ ሲያደርግ የቆየው ተቋም በጎ የሚባል ዜና ይፋ አድርጓል፡፡

‹‹በአሜሪካ የዴሞክራት 117ኛው ምክር ቤት ሕወሓትን በመደገፍ በኢትዮጵያ ላይ ያወጣው የማዕቀብና ሌሎች አስገዳጅ ሕጎች በሙሉ ተሰርዘዋል፤›› ሲል ነው ምክር ቤቱ ይፋ ያደረገው፡፡

አዲሱ የሪፐብሊካን 118ኛው ምክር ቤት ኮንግረሱን ሙሉ ለሙሉ በመቆጣጠሩ የዴሞክራቶችን ሕጎች ዋጋ አጥተዋል ሲልም ካውንስሉ ገልጿል፡፡ ይህ መሰሉ ዜና ደግሞ ምዕራባውያኑ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ እያሻሻሉ እንደሚሄዱ ተጨማሪ ፍንጭ ሰጪ ሆኖ እየቀረበ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -