ኢትዮጵያውያን የሆኑ ጸሐፍት፣ ሊቃውንትና መዘምራን፣ መነኮሳትና ቀሳውስት እጅግ የሚያስደንቅ ሥራ አላቸው፡፡ ይህውም እንዲህ ነው፡፡ ጥቁርና ቀይ ቀለመ አሽተው የፍየልንና የበግን ቆዳ ፍቀው የመቃውን ብርዕ ቀርጸው በእጃቸው እየጻፉ የሃይማኖት መጻሕፍታቸውን በማበርከታቸው በጣም ልናመሰግናቸው ይገባናል፡፡
ስንክሳር የተባለውን በእጅ የተጻፈውን ትልቁን መጽሐፍ ድጉሱ እጅግ የተዋበ አንድ ሰው ብቻውን ሊያነሳው የማይችል የነቢያት የሐዋርያት የጻድቃን የሰማዕታት ታሪክ የተጻፈበት ትልቅ መድበል ነው፡፡ ይህም መጽሐፍ ደብረ ቢዘን በተባለው ስመ ጥሩ በሆነው ተአምራታዊ ገዳም ውስጥ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ በቀድሞዎቹ ዘመናት ውስጥ እጅግ ጥሩ ጥሩ በሆኑት በእጅ በተጻፉት መጻሕፍት በጣም ሀብታም ነበረች፡፡ ዳሩ ግን አሁን ከመጻሕፍቶቿ ብዙዎቹ በውጭ አገር መሆናቸው በጣም ያሳዝናል፡፡ ብዙዎቹ በእንግሊዝ አገር በሎንዳን ቤተ መጻሕፍት ሌሎቹም በፓሪስ የቀሩትም በሮሜ ቤተ መጻሕፍትና በሌሎቹም አገሮች ይገኛሉ፡፡ ብዙዎቹም ደግሞ እጅግ ጥሩ ጥሩ የሆኑት በግራኝ ብዝበዛ ጊዜ ተቃጥለዋል፡፡ ዛሬም ደግሞ ብዙ መጻሕፍት በኢትዮጵያ ይኖራሉ፡፡ ዳሩ ግን ግእዝ ተማሪዎችና መርማሪዎች (የአጻጻፍ ሊቃውንትና ደራሲዎች) ያለ ችግር እንዲያገኙአቸው ከነስማቸው አስመዝግቦ ያሉበትን ቦታ ማስታወቅ ያስፈልግ ነበር፡፡
- አባ ጋስፓሪኒ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ›› (1948)