Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበጦርነቱ የተጎዱና የወደሙ የጤና ተቋማት መልሶ ለማቋቋም 1.4 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተባለ

በጦርነቱ የተጎዱና የወደሙ የጤና ተቋማት መልሶ ለማቋቋም 1.4 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተባለ

ቀን:

በአበበ ፍቅር

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በጦርነትና ግጭቶች ወቅት የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ ሰሞኑን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በጦርነትና በግጭት ወቅት ጉዳት ከደረሰባቸው ተቋማት መካከል የጤና ተቋማት ይገኙበታል ብሏል፡፡

- Advertisement -

በገንዘብ ሚኒስቴር አስተባባሪነት በተደረጉ ጥናቶች በጦርነት የወደሙ ተቋማትን ወደ ነበሩበት ለመመለስ ቢያንስ እስከ ሦስት ዓመት እንደሚፈጅ፣ 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚስፈልግ የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በተለይ የጤናው ዘርፍ ጉዳቱ ሰፊ ከመሆኑ አንፃር ሰፊ በጀትና ግብዓት የሚጠይቅ በመሆኑ ችግሩን በአፋጣኝ ለመፍታት፣ እንዲሁም በአንድ ጊዜ ተደራሸ ለማድረግ አስቸጋሪ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፣ አቅርቦቱን ከሆስፒታል ወደ ጤና ጣቢያ ከዚያም ወደ ጤና ኬላዎች በማውረድ ለማዳረስ እንደታሰበ ገልጸዋል፡፡

በግጭት ቀጣና ይኖሩ ለነበሩ ዜጎች የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ አስቸጋሪ እንደነበር አንስተው፣ በቅርብ ከተደረገው የሰላም ስምምነት በኋላ በትግራይ ክልል ሰብዓዊ አገልግሎቶችን ለማድረስ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ተገብቷል ብለዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ከጤና ሚኒስቴርና ከተጠሪ ተቋማት የተውጣጡ ከ30 በላይ የባለሙያዎች ቡድን ወደ አላማጣ፣ ሽረ፣ ኮረም፣ አክሱምና ዓድዋ በመላክ የተለያዩ ሥራዎች በመሠራት ላይ ናቸው ሲሉም አብራርተዋል፡፡ 

በአላማጣና በሽረ 12 ሆስፒታሎችና 28 የጤና ጣቢያዎች ወደ ቀድሞው ሥራቸው እንዲመለሱ የተደረገ ሲሆን፣ ከ95 በመቶ በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ ተፈጽሟል ብለዋል፡፡

የመድኃኒትና የሕክምና ግብዓት ሥርጭትን በተመለከተ በጎንደር መድኃኒት አቅራቢ በኩል ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ፣ እንዲሁም በደሴ ቅርንጫፍ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የሕይወት አድን መድኃኒቶችና የሕክምና ግብዓቶችን በሽረና በአላማጣ በኩል ለሚገኙ የጤና ተቋማት ማድረሳቸውን ሚኒስትሯ አብራርተዋል፡፡

ከማዕከላዊ ደም ባንክ 200 ዩኒት ደም ተዘጋጅቶ ወደ አክሱም በመላክ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፣ በመንግሥታቱ ማኅበርና በአጋር ድርጅት ሦስት አንቡላንሶች ለአክሱም፣ ለሽረና ለዓድዋ ሆስፒታሎች ተሰጥተዋል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የዓለም የጤና ድርጅትና ኢንተርናሽናል ቀይመስቀል ማኅበር አማካይነት ግምታቸው ከ81 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ የፀረ ወባ፣ የስኳር፣ የኩላሊ እጥበት፣ የፀረ ቲቢና የፀረ ደም ግፊት እንዲሁም ለሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት የሚውሉ የሕይወት አድን መድኃኒቶችን ወደ መቐለ ማድረስ ተችሏል ያሉት ሚኒስትሯ፣ ለመደበኛ ክትባት አገለግሎት የሚውሉ ወደ 113 ሺሕ ብር ግምት ያላቸው መድኃኒቶችም አብረው መላካቸውን አብራርተዋል፡፡

በአጠቃላይ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ 243,615 ብር ግምት ያላቸው አስፈላጊ የሆኑ መድኃኒቶችና ሌሎች ግብዓቶች በመንግሥት በኩል ማድረስ ተችሏል ብለዋል፡፡

ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሚሆኑ 1.1 ሚሊዮን ሕፃናት የኩፍኝ ክትባትን ለመስጠት በመንግሥትና በአጋር ድርጅቶች በኩል እየተሠራ ነው ተብሏል፡፡

በዚህም በመጀመሪያ ዙር ከታቀደው ከ165 ሺሕ በላይ ሕፃናት ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ መከተብ የተቻለ ሲሆን፣ ከኅዳር 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ የጤና ተቋማት በተሰጡ አገልግሎቶች 105 ሺሕ ዜጎች ተደራሽ ሆነዋል ሲሉ ጤና ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች በጤናው ዘርፍ የተሠሩ ዋና ዋና ተግባራትን ሚኒስትሯ በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

በዚህም ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በአማራ ክልል 40 በመቶ ሆስፒታሎችንና 415 ጤና ጣቢያዎችን፣ በአፋር አንድ ሆስፒታልና 20 ጤና ጣቢያዎችን እንዲሁም በኦሮሚያ 33 ጤና ጣቢያዎችን መልሶ በማቋቋምና በማደራጀት መደበኛ ሥራቸውን እንዲጀምሩ ተደርጓል ብለዋል፡፡

የላብራቶሪ ምርመራን ለማጠናከር ከአሜሪካ የልማት ተራድâ በተደረገ ድጋፍ ለአማራ ክልል 191፣ ለትግራይ ዘጠኝ እንዲሁም ለአፋር 50 በአጠቃላይ 250 የሚሆኑ ማይክሮስኮፒ መሠራጨታቸውን፣ በአጠቃላይ እስከ አሁን ለአማራና ለአፋር ክልሎች ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ የሕክምና ግብዓቶች መከፋፈላቸውን ገልጸዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሯ ማብራሪያ፣ ከግጭት ጋር በተያያዘ ለሚሰጡ የሕክምና አገልግሎቶች የሚውሉ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ 40 ሚሊዮን፣ ለኦሮሚያ 80 ሚሊዮን ግምት ያላቸው መድኃኒቶችና የሕክምና ግብዓቶች በሦስት ዙር ማሠራጨት ተችሏል፡፡

ለተፈናቃይ ወገኖች በተጠለሉበት ማዕከላት የጤና አገልግሎቶችን ለማድረስ ጊዜያዊ ክሊኒኮች ተደራጀተው ድጋፍ እንዲሰጡ የተደረገ ሲሆን፣ ተደራሽ ላልሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ደግሞ ከ114 በላይ ተንቀሳቃሽ የጤናና ሥርዓተ ምግብ ቡድኖችን በማሰማራት መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶች እንዲሰጡ ተደርጓል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...