Monday, March 20, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ሙዚቃ አንድ ሰው ሐሳቡን በነፃ የሚገልጽበት በር ነው›› ዓይነ ስውሯ ድምፃዊት ስንታየሁ...

‹‹ሙዚቃ አንድ ሰው ሐሳቡን በነፃ የሚገልጽበት በር ነው›› ዓይነ ስውሯ ድምፃዊት ስንታየሁ በላይ

ቀን:

በለጋ ዕድሜዋ ነበር የሙዚቃ ፍቅር ያደረባት፡፡ የሙዚቃ ፍቅሩም ካደረባት ጊዜ ጀምሮ የዕውቋ ድምፃዊት አስቴር አወቀ ሙዚቃዎችን ታንጎራጉር ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን እንደ የዕለት ተግባሯ ከቤቷ ደጃፍ ላይ ቁጭ ብላ በምታንጎራጉረው ሙዚቃ የተማረከው የቤት አከራይዋ፣ በአካባቢው የሚገኘውን የ‹‹ፋና ራያ›› ሙዚቃ ቡድንን እንድትቀላቀል ሐሳብ ያቀርብላታል፡፡

በዚህም ወቅት ነበር ድምፃዊት ስንታየሁ በላይ የሙዚቃ ህልሟ ዕውን የመሆን መንገድ የተከፈተ፡፡ ድምፃዊት ስንታየሁ ተወልዳ ያደገችው በሰሜን ወሎ ራያ ቆቦ አካባቢ ሲሆን፣ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቷን ቆቦ በሚገኘው ካቶሊክ ትምህርት ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በቆቦ ሁለተኛ ደረጃ ቀጥላም ደሴ በሚገኘው የመምህራን ትምህርት ኮሌጅ ትምህርቷን አጠናቃለች፡፡

የዓመት ከስድስት ወራት ልጅ እያለች የማየት ችሎታዋን ያጣችው ስንታየሁ፣ ሙዚቃን እየሰማችና እያደነቀች በማደጓ በቀላሉ ወደ ሙዚቃ ኢንዱስትሪው ልትቀላቀል መቻሏን ትናገራለች፡፡ የ‹‹ፋና ራያ›› የባህል ቡድንን ከተቀላቀለች በኋላ የተለያዩ ሙዚቃዎችን በማዜም የበርካታ ሙዚቃ አፍቃሪዎችን ቀልብ መሳብ ችላለች፡፡

ገና በለጋ ዕድሜዋ ሙዚቃን ስታንጎራጉር ቤተሰቦቿ ትምህርቷ ላይ እንድታደላ ይገፋፏት እንደነበር የምትናገረው ድምፃዊቷ፣ ይህም በተወሰነ መልኩም ቢሆን በሙዚቃ ሕይወቷ እንቅፋት ሆኖባት እንደነበር ለሪፖርተር ታስረዳለች፡፡

በልጅነቷ ጋዜጠኛ የመሆን ህልም እንደነበራት፣ ሙዚቃንም አንድ ሰው ሐሳቡን በነፃ የሚገልጽበት በር ነው ትላለች፡፡ በልጅነቷም ሙዚቃ ስትለማመድ ከቤተሰቧ ጋር መጋጨቷን፣ በዚህም የተነሳ ከአንድ ሁለት ጊዜ ከቤት ተጣልታ ወጥታ እንደነበር ትገልጻለች፡፡

ስንታየሁ እንደ አስቴር አወቀና ሐመልማል አባተ ዓይነት ዘመናዊ የአዘፋፈን ሥልት ያላት ድምፃዊ  ስትሆን፣ የባህላዊ አዘማመር ሥልቶች መጠቀሟ ድምጿን የተለየ ውበት እንዲላበስ አድርጎታል፡፡ በልጅነቷ ሙዚቃ ስታንጎራጉር ጎረቤቷን ጨምሮ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ችሎታ እንዳላት ይነግሯት እንደነበር የምታወጋው ድምፃዊቷ፣ በማኅበረሰቡ ግፊት ምክንያት ወደ ሙዚቃ ኢንዱስትሪው ልትቀላቀል ችላለች፡፡

ታዋቂው ሙዚቀኛ ግሩም መዝሙር ፕሮዲውሰር ያደረገውና ‹‹ፀደይ›› የሚል ስያሜ ያለው የሙዚቃ አልበሟን ያወጣችው ድምፃዊቷ፣ አልበሙ ለሙዚቃ አፍቃሪያን ጆሮ እስኪደርስ ድረስ በርካታ ውጣ ውረዶችን አይታለች፡፡ ‹‹ፀደይ›› የተሰኘው አልበም በውስጡ ከያዛቸው መካከል ‹‹አባነነኝ፣ ናልኝ፣ ስትሄድ፣ መጣልኝና ሎሌ›› ሲሆን፣ ሎሌ የተሰኘው ሙዚቃ ድምፃዊቷ በተለየ ሁኔታ ቀልቧን ሊስበው እንደቻለ ለሪፖርተር ተናግራለች፡፡

አብዛኛውን የሙዚቃ ሥራዎቿ ‹‹ፍቅር›› እና ‹‹ሰላም›› ላይ የሚያጠነጥን መሆኑን የምትናገረው ድምፃዊቷ፣ አልበሟን ለማውጣት ከዓመት በላይ ጊዜ እንደፈጀባት ታስረዳች፡፡ የሙዚቃዎቹ ዜማ፣ ቅንብር እንዲሁም ግጥሞቹ ላይ ታላላቅ የሙዚቃ ተዋናይ የሆኑ አርቲስቶች የተሳተፉበት ሲሆን፣ ‹‹አባነነኝ›› የተሰኘው ሙዚቃም ቪዲዮ ክሊፕ ተሠርቶለታል፡፡

ሙዚቃን ከልጅነቷ ጀምሮ በተለየ ሁኔታ የምታየው ድምፃዊቷ፣ በለጋ ዕድሜዋ ያጣችው ዓይኗ ከሙዚቃ ሕይወቷ ምንም እንዳላገዳት ትናገራለች፡፡ ከልጅነቷም በቤት አከራዩዋ ምክንያት ወደ ‹‹ፋና ራያ›› የባህል ሙዚቃ ቡድን መቀላቀሏ፣ አሁን ለደረሰችበት ፍሬ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የምትገልጸው ድምፃዊቷ፣ በአንድ ወቅትም በቴሌቪዥን መስኮቶች ከሚቀርቡት የሙዚቃ ውድድሮች መካከል አንዱ በሆነው ፋና ላምሮት ላይ መወዳደር ችላለች፡፡

በዚህ ውድድር ላይ ብዙም ዙር መጓዝ እንኳን ባትችልም፣ የበርካታ ሙዚቃ አፍቃሪያንን ቀልብ ስባለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ የምሽት ክለቦች፣ እንዲሁም መድረኮች ሙዚቃዎቿን በማቅረብ ችሎታዋን አስመስክራለች፡፡ በሙዚቃ ኢንዱስትሪው ውስጥ ሆነ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ዓይነ ሥውራን ድምፃውያን ድምፃቸው የማይሰማ መሆኑን የምትናገረው ስንታየሁ፣ እነዚህን ሁሉ ችግሮችን አልፋ ለዚህ መብቃቷ ፈጣሪን ታመሠግናለች፡፡

እንደ ክራርና ማሲንቆ ያሉ የኢትዮጵያ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎችን ከምዕራብ አፍሪካ የሙዚቃ መሣሪያዎች ጋር አጣምሮ የያዘው አልበም ከወጣ በኋላ ከቤተሰቦቿ ዘንድ አድናቆትን ማግኘት ችላለች፡፡ ከብዙ የሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ አድናቆትን ያገኘውን አልበም እዚህ ደረጃ እንዲደርስ አበጋዝ ክብረ ወርቅ፣ ዓለማየሁ ደመቀ፣ ታዋቂው ሙዚቀኛ ግሩም መዝሙርና ሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች አስተዋጿቸው የጎላ ነው ትላለች፡፡

የሙዚቃ ኢንዱስትሪው ላይ አካል ጉዳተኞች ያላቸውን ችሎታ በማውጣት መሳተፍ እንዳለባቸው የምትናገረው ድምፃዊቷ፣ በቀጣይም ኮንሰርትና ተጨማሪ አልበሞችን ለማውጣት ማቀዷን ታስረዳለች፡፡ የሙዚቃ ጉዞዋን አሐዱ ብላ ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ለኢንዱስትሪው በተለየ ሁኔታ ትኩረት መስጠቷ ለዚህ ፍሬ እንዳበቃት ትናገራለች፡፡ በሙዚቃ ትምህርት ዘልቃ ሳትገባ ድምፃዊ የሆነችው ስንታየሁ፣ ከልጅነቷ ጀምሮ ከትምህርት ጎን ጎን ሙዚቃ በማንጎራጎር ለዚህ መብቃት ችላለች፡፡      

‹‹ወደ ሙዚቃ ሕይወት ስገባ ብዙም እዘልቅበታለሁ ብዬ አስቤም አላውቅም፤›› የምትለው ድምፃዊቷ፣ በአንድ አጋጣሚ እነዚህን ሁሉ መንገዶችን መጓዝ መቻሏን ገልጻለች፡፡ በትምህርት ቤት ውስጥ ሙዚቃን ታንጎራጉር እንደነበር፣ ለዚህም ስኬት መነሻዋ ልጅ እያለች የምትሰማቸው ሙዚቃዎች ውስጧ በመቅረቱ መሆኑን ታስረዳለች፡፡

በሙዚቃ አማካይነት የተሠራጨው ‹‹ፀደይ›› የሚል ስያሜ ያለው የሙዚቃ አልበም ፕሮዲውስ ያደረገው ታዋቂው ሙዚቀኛ ግሩም እንደገለጸው፣ ኢትዮጵያን፣ ኢትዮጵያን የሚሸት አልበም ፕሮዲውስ ለማድረግ ከሰላም ኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ተደርጎ ነበር፡፡

በስምምነቱ መሠረትም አርቲስቶችን የመፈለግ ሥራ መሥራቱንና በርካታ የዘርፉ ተዋናዮችም በዚህ መሳተፋቸውን አክሏል፡፡   

በዚህ ሒደቱ ውስጥም ስንታየሁ በላይ ተሰጥዖዋ የተለየ መሆኑን፣ ያወጣችውም አልበም አብዛኛውን ትራኮች በ‹‹ላይቭ›› ዓይነት የሙዚቃ አቀዳድ የተቀዳ መሆኑን ፕሮዲውሰሩ አስረድቷል፡፡

ከመጀመርያው ጀምሮ ጎበዝ ዓይነ ስውር ድምፃዊ የመፈለግ ሥራ መሥራቱን፣ የዚህም ዋና ዓላማ አካል ጉዳተኞች በኢንዱስትሪው መነቃቃትን እንዲኖራቸው ለማድረግ ታስቦ መሆኑን ገልጿል፡፡

‹‹ፀደይ›› የዓይነ ሥውር ድምፃዊት ስንታየሁ ገሚሱ አልበም ረቡዕ ጥር 3 ቀን 2015 ዓ.ም. በተለያዩ የዘርፉ ተዋናዮችና የሙዚቃ አፍቃሪያን በተገኙበት በግዮን ሆቴል ለምርቃት በቅቷል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ዜጎች የተፈተኑበት የኑሮ ውድነት

በኢትዮጵያ በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት የበርካታ ዜጎችን አቅም...

በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚደረጉ ድጋፎች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ተጠየቀ

በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚደረጉ ድጋፎች ዘላቂነት እንዲኖራቸውና በተቀናጀ መልኩ...

ወደ ኋላ የቀረው የሠራተኞች ደኅንነት አጠባበቅ

በአበበ ፍቅር ለሠራተኞች የሚሰጠው የደኅንነት ትኩረት አናሳ በመሆኑ በርካታ ዜጎች...