በሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም. የታለመለት የነዳጅ ድጎማ አተገባበር ከተጀመረ ወዲህ በመጀመርያዎቹ አምስት ወራት፣ መንግሥት ከታክስ አምስት ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡ ታወቀ፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ታኅሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በወሰነው የነዳጅ ውጤቶች የዋጋ ግንባታና የትርፍ ህዳግ አሠራር አማካይነት እንዲሰበሰብ ተወስኖ፣ በሐምሌ ወር የተጀመረው የነዳጅ ውጤቶች መሸጫ ዋጋ ማስተካከያና የታለመለት ድጎማ ላይ ተግባራዊ የሆነው የታክስ አሰባሰብ፣ እስከ ኅዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ባሳየው ውጤት አምስት ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰሃረላ አብዱላሂ ለሪፖተር እንደገለጹት፣ ከነዳጅ እንዲገኝ የታቀደው የታክስ መጠን በዋጋ ግንባታው ላይ እንዲገባ ከተደረገ ወዲህ፣ በመጀመርያው የነዳጅ ውጤቶች መሸጫዎች ክለሳ በ25 በመቶ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ በሁለተኛው የዋጋ ክለሳም በተጨማሪ 25 በመቶ ተግባራዊ ተደርጎ የነበረ ሲሆን፣ ታኅሳስ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በተደረገው ሦስተኛ የዋጋ ክለሳ ደግሞ ሌላ 25 በመቶ ተጨምሮ አሁን 75 በመቶ መድረሱን ዋና ዳይሬከተሯ ተናግረዋል፡፡
የነዳጅ ውጤቶች የዋጋ ግንባታና የትርፍ ህዳግ አሠራር የሚደነግገው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ፣ በነዳጅ ውጤቶች ላይ ስለሚጣሉ ታክሶች፣ ቀረጥና ልዩ ልዩ ክፍያዎች፣ ‹‹የነዳጅ ውጤቶች መሸጫ ዋጋ ሥሌት በሕግ የተጣሉ ታክሶችን ባካተተ ሁኔታ ይዘጋጃል፤›› ይላል፡፡ ሆኖም ምን ያህል መጠንና ምን ዓይነት ታክሶች እንደሚሰበሰቡ ውሳኔው አይጠቅስም፡፡
ውሳኔው በማስቀጠል የማዘጋጃ ቤት ቀረጥ፣ የመንገድ ፈንድ፣ መዋጮ፣ ለነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የሚሆን የተቆጣጣሪ አካል ክፍያዎችን በዋጋ ግንባታው ምን ያህል መጠን ይዘው እንደሚካተቱ በዝርዝር ያስረዳል፡፡ ቤንዚንና ነጭ ናፍጣ መሸጫ ዋጋ ላይ ለማዘጋጃ ቤት ቀረጥ በሊትር ሁለት ሳንቲም እንዲደመር ሲያደርግ፣ ለተቆጣጣሪ አካል ደግሞ የአውሮፕላን ነዳጅና ኬሮሲንን ጨምሮ ስድስት የነዳጅ ውጤት ዓይነቶች መሸጫ ዋጋ ላይ በሊትር 1.5 ሳንቲም ይደምራል፡፡ ለመንገድ ፈንድ መዋጮ በቤንዚን ዋጋ ላይ 9.5 ሳንቲም ሲደመር፣ በነጭ ናፍጣ መሸጫ ዋጋ ላይ ደግሞ ስምንት ሳንቲም ይደመራል፡፡ ኬሮሲን፣ የአውሮፕላን ነዳጅ፣ ቀላልና ከባድ ጥቁር ናፍጣ የማዘጋጃ ቤት ቀረጥና የመንገድ ፈንድ መዋጮ አይደመርባቸውም፡፡
በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት ለድጎማ የሚውለው ገንዘብ ምንጭ የሚሆኑት፣ ከነዳጅ የሚሰበሰብ ታክስና ከተለያዩ ምንጮች ከሚገኝ ድጋፍ በሚል ሁለት ምንጮች ናቸው፡፡
‹‹እንደሚታወቀው እንደሌላው ምርት ነዳጅ ላይ ታክስም ሆነ ቫት አይጣልም ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም ዋጋ ግንባታውም ላይ እስከ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ድረስ አይካተትም ነበር፤›› ሲሉ ወ/ሮ ሳሃረላ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ሆኖም እሳቸው ይህን ቢሉም አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በዘርፉ ተሳትፎ የሚያደርጉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ባለሙያ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ነዳጅ ላይ መጠኑ ከፍተኛ ያልሆነ ኤክሳይዝ ታክስና ቫት ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ ይጣል ነበር፡፡ ኤክሳይዝ ታክስ 30 በመቶ፣ ቫት ደግሞ 15 በመቶ ቢሆንም ነዳጅ ላይ ይጣል የነበረውን መጠን ዝቅ በማድረግ በአንድ ሊትር ሁለትና ሦስት ብር በዋጋ ግንባታው ላይ ይገባ ነበር ብለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ መጠኑ ባይወሰንም በሕግ አግባብ ግን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ላይ ሠፍሮ ተግባራዊ እየሆነ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡