Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በደብረ ብርሃን 103 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ሊሰማሩ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በደብረ ብርሃን ከተማ በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ እንዲሁም በአገልግሎት ዘርፍ ለመሰማራት ባለሀብቶች ከ103 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማስመዝገባቸውን የከተማው አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በአሁኑ ወቅት በደብረ ብርሃን ከተማ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች ከ700 በላይ ኢንቨስትመንቶች መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ ከ103 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ለመሰማራት ወደ ከተማዋ መምጣታቸውን የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መመርያ ኃላፊ አቶ ብርሃን ገብረሕይወት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ በአምራች ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ከ163 በላይ ኢንዱስትሪዎች ምርት እያመረቱ እንደሚገኙና በዚህም ለ25 ሺሕ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ገልጸዋል። ከ103 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ይዘው በከተማዋ በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት ለማድረግ የተመዘገቡት ባለሀብቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡ ደግሞ ለ120 ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር አቶ ብርሃን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ዓመት ብቻ ከ24 በላይ ኢንዱስትሪዎች ሥራ እንደሚጀምሩ የተጠቀሰ ሲሆን፣ እነዚህ ያስመዘገቡት አጠቃላይ ካፒታልም ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ 

ኢንዱስትሪዎቹ በእንጨት፣ በብረታ ብረት፣ በመኪና መገጣጠሚያ፣ በባጃጅ መገጣጠሚያ፣ በጨርቃ ጨርቅና በጠርሙስ ማምረት ዘርፎች ላይ የተሰማሩ እንደሆኑ አቶ ብርሃን ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

ሁሉም ባለሀብቶች ከአገር ውስጥ የተውጣጡ ሲሆን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ከተረጋገጠ በኋላ፣ ከከተማ አስተዳደሩ በአፋጣኝ መሬት እንዲያገኙ መደረጉን አቶ ብርሃን ለሪፖተር አብራርተዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በአጠቃላይ ከ720 ሔክታር በላይ መሬት በሁሉም ዘርፍ ለተሰማሩ ኢንቨስተሮች ማቅረቡንም አቶ ብርሃን ጠቅሰዋል፡፡    

ደብረ ብርሃን ከተማ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እየተስፋፋባት የምትገኝ ሲሆን፣ በዚህም ሰፊ የሥራ ዕድል እየተፈጠረና በቴክኖሎጂ የተሻሉ ኢንዱስትሪዎችም ከተማዋን ምርጫቸው እያደረጉ መሆኑ ይስተዋላል።

ወደ ከተማዋ በርካታ ኢንቨስተሮች እየገቡ እንደሆነ የሚገልጹት የደብረ ብርሃን ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብእሸት፣ የአገልግሎት አሰጣጡ የተሻለ መሆኑ ከተማዋን ተመራጭ እንዳደረጋት ይገልጻሉ፡፡

በተለያዩ የኢንቨስመንት ዘርፉ ላይ የሚሰማሩ ባለሀብቶች ከመምጣታቸው አስቀድመው፣ በቂ መሬት ቀድሞ እንደሚዘጋጅና አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት የማድረግ ልምድ መኖሩንም ምክትል ከንቲባው ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡ 

በተለይ በአግሮ ፕሮሲንግ፣ በጨርቃ ጨርቅ፣ በእንጨት፣ በብረታ ብረት፣ እንዲሁም በኬሚካል ዘርፎቹም ቀድመው ምቹ የሆኑ ቦታዎች እንደተዘጋጁ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ ከመሠረተ ልማት አቅርቦት አንፃር በተወሰነ ደረጃ የተሻለ መሆኑ ተመራጭ እንዳደረገው የሚገልጹት አቶ ብርሃን፣ የመንገድና የመብራት አቅርቦት እየተሻሻለ መምጣቱን ያወሳሉ፡፡

በከተማዋ 360 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያከፋፍል ጣቢያ መኖሩና፣ ማኅበረሰቡ ለሰላም የሚሰጠው ዋጋ ከተማዋን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ካደረጓት መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውንም አቶ ብርሃን ገልጸዋል፡፡

የቁሳቁስ መወደድ፣ የባንክ ብድር ማግኘት፣ የብረታ ብረት እጥረት፣ የሲሚንቶ፣ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ተግዳሮቶች ግን የተጀመረውን ኢንቨስትመንት እየፈተኑ መሆናቸውን ጠቅስዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ባለሀብቱ በሚፈልገው መጠን መሠረተ ልማት አለመሟላት ውስንነት መኖሩ ጠቅሰዋል፡፡

በሩብ ዓመቱ ከ40 በላይ ባለሀብቶች በራሳቸው የመሬት ካሳ ክፍያ ከፍለው በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ለመሰማራት ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን አቶ በድሉ ተናግረዋል፡፡

ከጥር 4 እስከ 14 ቀን 2015 ዓ.ም. የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ለመሳብ የደብረ ብርሃን ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ንግድና ፋይናንስ ኤክስፖ ያሰናዳ ሲሆን፣ በዚህም በርካታ ባለሀብቶችን ለመሳብ መታቀዱ ተገልጿል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በየሦስት ወራቱ የውይይት መድረክ አሰናድቶ አጠቃላይ እንቅስቃሴውን እንደሚከታተል የሚያስረዱት ምክትል ከንቲባው፣ መሬት ተረክበው ያላለሙ ባለሀብቶች ጊዜውን ጠብቆ ዕርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አቶ በድሉ ያብራራሉ፡፡

ከአምራች ዘርፉ በተቃራኒ በአገልግሎት ዘርፉ በተለይ በሆቴል ዘርፍ ላይ ችግር መኖሩን የሚያነሱት አቶ በድሉ፣ ባለፉት ዓመታት ለ23 ባለ ኮከብ ሆቴሎች ግንባታ መሬት እንዲሰጣቸው በክልሉ መንግሥት መወሰኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

የክልሉ መንግሥት በወሰነው መሠረት ለባለሀብቶቹ ከጨረታ ነፃ የሆነ የግንባታ መሬት መፈቀዱንና የተወሰኑት ወደ ግንባታ መግባታቸውን የገለጹት ምክትል ከንቲባው፣ የተቀሩት በዲዛይን ጥናት ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ 

የደብረ ብርሃን ከተማ 124 ሺሕ ሔክታር መሬት የቆዳ ስፋት ሲኖራት፣ በውስጧ 24 የከተማ ቀበሌዎች፣ 13 የገጠር ቀበሌዎች እንዲሁም ሁለት ሳተላይት ከተሞች እንዳሏት ተጠቅሷል፡፡   

   

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች