Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዓይን ባንክና የብሔራዊ የደምና ቲሹ ባንክ ትስስር

የዓይን ባንክና የብሔራዊ የደምና ቲሹ ባንክ ትስስር

ቀን:

በዳግማዊ ምኒልክ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ቅጥር ግቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ከብሔራዊ የደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ጋር ትስስር ሊፈጥር ነው፡፡ ለትስስሩም ስኬታማነት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ የታመነበት መተዳደሪያ ደንብ ፀድቆ ለተግባራዊነቱ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡

የዓይን ባንኩ የአስተዳደርና የፋይናንስ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ ተስፋዬ በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መተዳደሪያ ደንቡን አስመልክቶ እስካሁን በተካሄደው እንቅስቃሴ ከአገልግሎቱና ከባንኩ የሰው ኃይል ጋር የተያያዙ ምደባዎች ተመዝነውና ደረጃ ወጥቶላቸው ለሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የተላከ ሲሆን አዲስ የሥራ መዋቅርም እየተዘጋጀ ነው፡፡

ባንኩ ከብሔራዊ የደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ጋር ለመተሳሰር ያነሳሳው ምክንያት፣ በገጠመው የበጀት እጥረት የተነሳ የዓይን ብሌንን የመሰብሰብ፣ የመጠበቅና የማሠራጨቱን አገልግሎት በተሟላ መልኩ ለማከናወን ባለመቻሉ፣ በዚህ ላይ ደግሞ የሠራተኞች ቁጥር እየጨመረና በአንፃሩ ደግሞ ደመወዙ የመክፈል አቅሙ እየሳሳ በመምጣቱ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹ባንኩ የሚጠበቅበትን አገልግሎት የሚሰጠው በሦስትዮሽ አካሄድ ነው፤›› ያሉት አቶ ዮናስ፣ ይህም የጤና ሚኒስቴር የበላይ ጠባቂ ሲሆን በጀት ግን የሚያገኘው ከአጋር ድርጅቶችና ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መጠነኛ ክፍያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይህም ሆኖ ከአጋር ድርጅቶች የሚያገኘው የፋይናንስ ድጋፍ ወጪውን መሸፈን እንዳልቻለ፣ እስከናካቴው የሚለግሱትንም የፋይናንስ ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያቋረጡ እንደመጡ ከሥራ አስኪያጁ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ይህንንም ችግር ጉዳዩ በይበልጥ ለሚመለከተው የጤና ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ጊዜ ማሳወቁን፣ ሚኒስቴሩም የችግሩን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ከብሔራዊ የደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ጋር እንዲሠራ መፍቀዱን፣ ትስስሩም የተጋረጠበትን የበጀት ችግር በመፍታት፣ በየክልሎቹ ቅርንጫፍ የዓይን ባንኮችን ለማቋቋም በማመቻቸት ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ዮናስ አባባል ለአንድ የዓይን ብሌን የመሰብሰብ፣ የማከማቸትና የማሠራጨት ሒደት ከ27,000 ብር በላይ ይፈጃል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ባንኩ ብሌኑን ቀደም ሲል ቃል ከገቡት ለጋሾች የሚሰበስበው በነፃ ስለሆነ የአገልግሎት ክፍያውን በጣም አነስተኛ ነው ያደረገው፡፡

በዚህም መሠረት ለመንግሥት ጤና ተቋም አንዱን የዓይን ብሌን 3,800 ብር፣ ለግል ጤና ተቋም ደግሞ 7,000 ብር እንደሚያስከፍል አቶ ዮናስ አመልክተው፣ በመንግሥት ጤና ተቋም የብሌን ተከላ አገልግሎት ፈልጎ ነገር ግን የተጠየቀውን ገንዘብ መክፈል አቅም የሌለው ታካሚ አገልግሎቱን በነፃ እንደሚያገኝ አስረድተዋል፡፡

የዓይን ብሌን ባንክ እንደተመሠረተ በዓመት ዘጠኝ ግፋ ሲል ደግሞ አሥር፣ የዓይን ብሌኖችን ለግልና ለመንግሥት ጤና ተቋማት ያሠራጭ እንደነበር፣ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ግን ዓመታዊ የብሌን ሥርጭት መጠኑን ከ200 እስከ 250 ከፍ ማድረጉን፣ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ እስከዛሬ ድረስ ደግሞ በአጠቃላይ 2,900 የዓይን ብሌኖችን ለተጠቀሱት የጤና ተቋማት ማሠራጨቱን አቶ ዮናስ ተናግረዋል፡፡

ከሥራ አስኪያጁ ገለጻ ለመረዳት እንደተቻለው፣ የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ሥራውን የሚያካሂደው ዓለም አቀፍ ደረጃን በጠበቀ መልኩ ነው፡፡ ለዚህም ዋና መሥሪያ ቤቱ አሜሪካ ሲያትል የሚገኘው ‹‹ሳይት ላይን ኢንተርናሽናል›› የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በየሁለት ዓመት የባንኩን የሥራ እንቅስቃሴ በመገምገምና በማወዳደር 95 በመቶ ነጥብ እየሰጠውና ለብቃቱም ዕውቅና እየቸረው አሁን ያለበት ደረጃ ሊደርስ ችሏል፡፡

የዓይን ባንኩ ሜዲካል ዳይሬክተር ሆኖ የሚሾመው ‹‹በኮርኒያ ሰርጀሪ ሰብ ስፔሻሊስት›› የሆነ ባለሙያ ነው፡፡ ሹመቱን የሚሰጠውና ለተሿሚውም ደመወዝ የሚከፍለው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣ ባንኩም ለተሿሚው ክብር መጠበቂያ የሚሆን መጠነኛ ገንዘብ እንደሚከፍል ነው የተናገሩት፡፡

ተሿሚውም አልግሎት የሚሰጠው በቀን ለአንድ ሰዓት ሲሆን፣ በዚህም የብሌን አቀማመጥና አያያዝን እንደሚገመግም፣ ከዚህ ጋር ተያያዥ የሆኑ ሌሎች ሥራዎች ካሉ እንደሚያከናውን፣ ሥራ ከበዛም ከአንድ ሰዓት በላይ ሊቆይ እንደሚችል ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ በቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡

በተያያዘ ዜና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥር 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው 16ኛ መደበኛ ስብሰባው ካፀደቃቸው ረቂቅ ደንቦች አንዱ የኢትዮጵያ የደም እና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ማቋቋሚያ ደንብ ነው፡፡ ስለፀደቀው ደንብ የጤና ሚኒስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ በሰጠው ማብራሪያ እንደተመለከተው፣ በተለይም ካሁን በፊት በጤና ሚኒስቴር፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮና በኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የሦስትዮሽ ስምምነት ተቋቁሞ፣ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ድጋፍ ሲተዳደርና አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው የዓይን ባንክ አገልግሎት፣ በኢትዮጵያ ደም እና ቲሹ ባንክ አገልግሎት እንዲሰጥና ተያያዥነት ያላቸውን ተግባራትን እንዲያከናውን የሚያስችል ሥልጣን ያለው ተቋም ሆኗል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...