Wednesday, February 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉብኝት

የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉብኝት

ቀን:

‹‹አፍሪካ ዓለም አቀፍ ትብብር የሚታይባት አኅጉር መሆን አለባት፡፡ ለጂኦ ፖለቲካል ጥቅም ሲባል፣ ኃይል ያላቸው አገሮች የሚወዳደሩበት መሆን የለባትም፤›› ሲሉ ከወር በፊት የአሜሪካ-አፍሪካ ጉባዔ በአሜሪካ ሲካሄድ የተናገሩት የወቅቱ በአሜሪካ የቻይና አምባሳደርና አሁን ላይ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ አምስት የአፍሪካ አገሮችን ጎብኝተዋል፡፡

ኢትዮጵያ፣ ጋቦን፣ አንጎላ፣ ቤኒንና ግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የጎበኛቸው አገሮች ናቸው፡፡

ለቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ ማግሥት የመጀመርያ ጉብኝታቸውን በአምስት የአፍሪካ አገሮች ያደረጉት ሚስተር ጋንግ፣ የመጀመርያ መዳረሻቸው ኢትዮጵያ ነበረች፡፡

ሳውዝ ቻይና ሞርኒግ ፖስት እንዳሰፈረው፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ጉብኝት ለአፍሪካ ድጋፍና አጋርነትን ለማሳየት ያለመ ነው፡፡ አገሮቹም ቻይና ከአፍሪካ ጋር ላላት ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ቁልፍ ናቸው፡፡

ቤጂንግ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ጠንካራ የሚባል ሲሆን፣ በኢትዮጵያም በማምረት፣ በኃይል፣ በመሠረተ ልማት የተሠማሩ ከ400 በላይ ኩባንያዎችና ድርጅቶች አሏት፡፡ በዋሽንግተን የናሽናል ዲፌንስ ዩኒቨርሲቲ የቻይና አፍሪካ ኤክስፐርት ፖል ናንቱሊያ እንደሚሉትም፣ በኩባንያዎቹ የተያዙት ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ አራት ቢሊዮን ዶላር ያህል የሚያወጡ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ለቻይና ዋና የደኅንነት አጋርም ናት፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2015 ወዲህ በዘርፉ የተጠናከረ ግንኙነት እንዳላቸውም ዘገባው ያሳያል፡፡

ቻይናና ኢትዮጵያ የተጠናከረ ግንኙነት ቢኖራቸውም፣ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የብድር ጫና አለባት፡፡ በ2000 እና በ2020 መካከል ኢትዮጵያ ከቻይና 13.7 ቢሊዮን ዶላር መበደሯን በቦስተን ዩኒቨርሲቲ ግሎባል ዴቨሎፕመንት ፖሊሲ ሴንተር ቻይና ለአፍሪካ አገሮች ያበደረችው ዳታቤዝ ያሳያል፡፡ ከ2021 ወዲህ ደግሞ ኢትዮጵያ ቻይናን ጨምሮ የውጭ ብድሯን ዳግም ለማዋቀር እየሠራች ትገኛለች፡፡

እንደ ቺን ጋንግ ገለጻም፣ ቻይና መጠኑ ያልታወቀ ዕዳ ለመሰረዝ ቃል ገብታለች፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድና ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር የተገናኙት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ትግራይን መልሶ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ቻይና ታግዛለች ብለዋል፡፡

ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ጋር የተወያዩት ቺን፣ በኮቪድ-19 ገደብ ምክንያት የተጎዳውን የሰው ለሰው ሁለትዮሽ ግንኙነት መልሰው እንደሚያጠናክሩና በኅብረቱ በኩል ለአኅጉሪቷ አዳዲስ ዕድሎችን እንደሚያመቻቹም ጠቁመዋል፡፡

የቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም ሲካሄድ የተገቡ ቃሎችን ለመተግበር እንደሚተጉና አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤትና በሌሎች እንደ ጂ20 ባሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ውክልና እንዲኖራት እንደሚሠሩም አክለዋል፡፡

በኮቪድ-19 ምክንያት የተጣለውን የጉዞ ገደብ ተከትሎ ተቋርጦ የነበረው የሥልጠና የትምህርት ፕሮግራም እንደሚቀጥልም አክለዋል፡፡

በጆሃንስበርግ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ኢማኑኤል ማታምቦ እንደሚሉትም፣ የአፍሪካና ቻይና ግንኙነትን ማጠናከር በአኅጉሪቷ የሚገኙ አገሮች በተናጥል የሚያደርጉትን ግንኙነት ለማመቻቸት ያግዛል፡፡ አፍሪካ ከቻይና ጋር በሚኖራት ግንኙነትም የበለጠ ተጠቃሚ ትሆናለች፡፡

ከኢትዮጵያ ወደ ጋቦን ያቀኑት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ከጋቦን ፕሬዚዳንት ዓሊ ቦንጎ ጋር ተወያይተዋል፡፡ ቻይና በጋቦን የቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሽየቲቯን እንደምታጠናክርም ተናግረዋል፡፡

ቺን የአንጎላውን ፕሬዚዳንት ጆአው ሎሬንሶ የጎበኙት፣ አንጎላ ከቻይና ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመረችበትን 40ኛ ዓመት በምታከብርበት ዕለት ነበር፡፡

ፕሬዚዳንት ሎሬንሶ እንዳሉት፣ አንጎላ ከጦርነት ከወጣች በኋላ ቻይና በተለያዩ መሠረተ ልማቶች ያደረገችው ድጋፍ ከፍተኛ ነው፡፡ በቻይና ድጋፍ አየር ማረፊያዎች፣ የሃይድሮ ፓወር ጣቢያዎች መንገዶችና ወደቦች ግንባታ እየተከናወነ ነው፡፡ አንጎላ ከጦርነት በኋላ በኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማት እንድታንሰራራም ቻይና የማይተካ ሚና ተጫውታለች፡፡

ቺን፣ ከአንጎላ በመቀጠል ወደ ቤኒን ነበር ያቀኑት፡፡ በቤኒን ኮቶኑ ከተማ የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ፓትሪክ ታሎን አነጋግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ታሎን አገራቸው ከቻይና ልምድ መቅሰም ትፈልጋለች ብለዋል፡፡ የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው፣ ቤኒን ለቻይና ተቋማት ደኅንነት እንደምትሰጥ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፣ መንግሥታቸው በርካታ የቻይና ኩባንያዎችን በቤኒን እንደሚሰማሩ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡

የቺን የመጨረሻ መዳረሻ ግብፅ ነበረች፡፡ ግብፅ የቻይና ቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሸየቲቭ ዋና ተጠቃሚ ናት፡፡ ከደኅንነት ጋር በተያያዘ ቻይናና ግብፅ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፣ ቻይና አዲሱን የግብፅ ዋና ከተማ በቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሺየቲቭ እየገነባች ትገኛለች፡፡

አንጎላ፣ ኢትዮጵያና ግብፅ ከቻይና ጋር የረዥም ጊዜ ግንኙነት ያላቸው አገሮች ናቸው፡፡ ሆኖም ቻይና ከእነዚህ አገሮች ጋር ለመሥራት በየአገሮቹ መካከልና ውስጥ ሰላም መስፈን እንዳለበት ታምናለች፡፡

ቻይና በአፍሪካ ድንበር ተሻግሮ የሚከሰትም ሆነ የእርስ በርስ ጦርነት በሰላም እንዲፈታ እንደምትሠራ ከዚህ ቀደም ማስታወቋ አይዘነጋም፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...

ንግድ ባንክ ከቪዛና ማስተር ካርድ ጋር ተደራድሮ ያስጀመረው የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂና ፋይዳው

ከውጭ ወደ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መጠን...

ይኼ አመላችን የት ያደርሰን ይሆን?

እነሆ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ። ‹‹አዳም ሆይ በግንባር ወዝ ትበላለህ››...