Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርብሔራዊ ሀብታችን ከሙሰኞች እንዲጠበቅ ምን ይደረግ?

ብሔራዊ ሀብታችን ከሙሰኞች እንዲጠበቅ ምን ይደረግ?

ቀን:

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

አንድ መንግሥት አልፎ ሌላ መንግሥት ሲተካ ከሚነሱት መሠረታዊ ነገሮች አንዱ ሙስናና ሙሰኝነት ነው፡፡ ከሙስናና ሙሰኝነት ጋርም ጉቦና ጉቦኝነት ይነሳል፡፡ ይህ ጉዳይ ግን ብሔራዊ ብቻ ሳይሆን፣ ዓለም አቀፍ ባህሪ አለው፡፡ ከሺሕ ዓመታት በፊትም ሲወሳ ነበር፡፡ ታላላቅ ሊቃውንትም ሙሰኝነትና ጉቦኝነትን በሚመለከት ብዙ ድርሳናትን ጽፈዋል፡፡ በአገራችንም ሙሰኝነትንና ጉቦኝነትን ለመቋቋም የደርግ መንግሥት ‹‹ብሔራዊ የሠርቶ አደር ቁጥጥር ኮሚቴ›› የተሰኘ መሥሪያ ቤት አቋቁሞ ነበር፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥትም ‹‹ፀረ ሙስና ኮሚሽን›› የተሰኘ መሥሪያ ቤት አቋቁሞ ነበር፡፡ ለመሆኑ ሙስና ምንድነው? ጉቦስ?

ሙስናና ጉቦ

ሙስናና ጉቦ በባህሪያቸው ተወራራሽ ሲሆኑ፣ አንዱ የሌላው መገለጫም ይሆናሉ፡፡ ለምሳሌ የዓይነትም ሆነ የመንፈስ ጉቦ ተቀባይ ወይም ሰጭ ሙሰኛ ሲሆን፣ ሙሰኛም አንዳች በነፃ ማከናወን ያለበትን በጉቦ ወይም በመተያያ፣ ወይም በገጸ በረከት የሚቀበል ወይም የሚሰጥ ነው፡፡ ስለሆነም አንዱ በሌላው ውስጥ የሚገኝ፣ አንዱ የሌላው መገለጫ የሆነ ቃል መሆኑ ነው፡፡ ሆኖም ለግንዛቤ ያህል ሁለቱንም አንድ በአንድ እንመልከታቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሙስና ምንድነው?

በኢትዮጵያ ሙስና የሚለው ቃል አመጣጡ ከግዕዝ ቋንቋ ነው፡፡ ይህ ቃል «ጥፋትና ብልሽት» ከሚለው ግርድፍ ፍችው በላይ ሰፍቶ «ኮራፕሽን» ከሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ጋር ተመሳሳይ ትርጉም ይዟል፡፡ በመደበኛ የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ትርጉም “ኮራፕሽን” (ሙስና) ማለት ከጥሩ ወይም ከጤነኛ ሁኔታ መለወጥ፣ ከነበረበት የጥራት ደረጃ መቀነስ፣ የሞራል ውድቀት፣ ዋጋ ማጣት፣ መቆሸሽ፣ በጉቦ መለወጥ፣ ታማኝ አለመሆን፣ በስህተት ወይም በመጥፎነት መበከል እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

ከጽንሰ ሐሳብ አኳያ ሙስና በውስጡ የሚያካትታቸውን ገጽታዎች በተመለከተ ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ በዚህም ምክንያት በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ትርጉም ማግኘቱ ቀላል አልሆነም፡፡ ይህ ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ ሙስናን፣ የመንግሥት ሥልጣን ተጠቅሞ፣ ሐቀኝነትና ታማኝነት ገሸሽ አድርጎ፣ መልካም ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት በመፈጸም የሕዝብ ሀብትን ለግል ጥቅም በማዋል፣ በሕዝብና በመንግሥት ላይ የሚፈጸም ጥፋት/ጉዳት በሚለው አገላለጽ መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ ምክንያትም ሙስና በፖለቲከኞች፣ በመንግሥት ሠራተኞችና በባለሥልጣናት የሚታይን በሥልጣን ያላግባብ መገልገልን ለመግለጽ የምንጠቀምበት ቃል ነው፡፡ ከዚህም በላይ ሙስና በየትኛውም የሕይወት ዘርፍ የሚታይን ብልሹ አሠራር የሚያመለክት ነው፡፡

ዊልያም ፒት የተባለው እንግሊዛዊ መስፍን (1708-1778) «ወሰን የሌለው ሥልጣን፣ የባለሥልጣናትን አመለካከት እንደ ብል ወይም እንደ ምስጥ እንክት አድርጎ የሚበላ ሲሆን፣ ይህም የሕጋዊ ሥርዓት ማክተሚያ የሕገወጥነት መጀመርያ ይሆናል…» ሲል ይገልጸዋል፡፡ በእርግጥም የሕጋዊ ሥርዓት ማክተሚያ ሲቃረብ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሕገ መንግሥታቸውን የሚፃረር ተግባር ያከናውናሉ፡፡ ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ባህሪ ያለው ጉቦና ሙስና ይስፋፋል፡፡ የበደል መረቡ በሰፊው ይዘረጋል፡፡ ኤድዋርድ ጊቦን የተባለው ኢጣሊያዊም (1737-1794) «ሙስና አስተማማኝ የሕገ መንግሥት ልቅነት ዋነኛ መገለጫ ባህሪ ነው…» በማለት የሮማውያን ዘውዳዊ ሥርዓት መዳከምና መውደቅን አስመልክቶ ባዘጋጀው መጽሐፉ ላይ እንደጠቀሰውም፣ የወጣው ሕገ መንግሥት ከወረቀት ያለፈ ፋይዳ ላይኖረው ይችላል፡፡ ሎርድ አክቶንም (1834-1909) «ሥልጣን ለሙስና እንደሚዳርግ የታወቀ ሲሆን፣ ፍፁማዊ ሥልጣን ደግሞ ፍፁም ሙሰኛ ያደርጋል…» በማለት ለአቡነ ማንዴላ በጻፉት ማስታወሻ መግለጻቸውን ከሥራዎቻቸው እንረዳለን፡፡ በጥቅሉ ሙሰኝነትና ጉቦኝነት እጅግ ከፍተኛ ቁርኝት ያላቸው ሲሆኑ፣ የዕድገት ማነቆዎችም ናቸው፡፡

ጉቦ ምንድነው?

«ጉቦ» የሚለው ቃል አዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት፣ «ፍርድን ለማጣመምና ሐሰትን እውነት ለማስመሰል ለሐሰተኛ ዳኛ የሚሰጥ መማለጃ ነወ፡፡ ጉቦ ቁሳዊና መንፈሳዊ በረከት ሊሆን ይችላል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ሕገወጥ ድርጊትን ለመሸፋፈን ለመፈጸም ለጥፋት ፍርድን ለመገምደል ያገለግላል፤» በማለት ይገልጸዋል፡፡ በዚህ ትልቅ መዝገበ ቃላት የምናገኘው ታላቅ የሚስጥር ፍቺ «ጉቦ ቁሳዊና መንፈሳዊ በረከት» ከሚለው አገላለጽ ነው፡፡ ይህን ትርጉም አዘጋጁ ሲሰጡ ዘርዘር አድርገው የመስጠት ዕውቀት ሳይኖራቸው ቀርቶ ሳይሆን፣ በፊውዳሉ ሥርዓት መልዕክቱ በዚያ መንገድ ተሸፍኖ ካልተላለፈ በስተቀር በምልጃ፣ በደጅ ጥናት፣ በማወደስ፣ በማስቀደስ፣ በመስገድ፣ የሚገለጽ መንፈሳዊ በረከት ተብሎ ቢገለጽ የሳንሱርን መቀስ ማለፍ ስለማይችል እንደነበረ ልብ ይሏል፡፡ ይሁንና «ጉቦ ቁሳዊና መንፈሳዊ በረከት ሊሆን ይችላል» በሚል የቀረበ ስለሆነ ቁሳዊው በገንዘብ፣ በንብረት፣ በከብት፣ በምርት፣ በልዩ መልክ በተዘጋጀ ስጦታ ሲሆን፣ መንፈሳዊው ደግሞ በማይጨበጥ፣ በማይዳሰስ፣ በማይታይ መንገድ የሚሰጥ መሆኑ ነው፡፡

ስለዚህም የአዲስ አማርኛ መዝገበ ቃላትን ፍች ተከትለን የጉቦን ትርጉም ለማብራራት ስንሞክር በአብዛኛው «ቁሳዊና መንፈሳዊ በረከት» የሚባለው በዓይነት የሚሰጥ ሲሆን፣ ከጥቃቅን በረከቶች ጀምሮ እስከ ከፍተኛ እንደሆነ በማያሻማ ሁኔታ እንረዳለን፡፡ ፍርድን ለማጓደል፣ ለመገምደል፣ ሕገወጥ ድርጊትን ለመፈጸም ለመሸፋፈን… ሐሰትን ዕውነት ለማስመሰል ከሆነ በስጦታ መልክም ይምጣ፣ በበረከት፣ በእጅ ማራሻም ሆነ በጉርሻ፣ በምልጃም ይሁን በደጅ ጥናት፣ በማሞገስም ሆነ በማሞካሸት፣ የቅዱሳን ሁሉ ቅዱስም ሆነ የብፁአን ሁሉ ብፁዕ አድርጎ በግልም ሆነ በጋራ ማቅረብ የማይገባን ጥቅም ለማግኘት ከሆነ ያው «ጉቦ» ነው፡፡

ይህንኑ ቃል ዌብሰተር የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ መስረቅ፣ መዝረፍ፣ ማጭበርበር፣ ማታለል፣ ከፍተኛ እምነት የተጣለበትን ዳኛ ወይም ባለሥለጣን ኃላፊነቱ እንዲዘነጋ የሚሰጥ ሽልማት ስጦታ ውለታ … በማለት ያፍታታዋል፡፡ ብላክስ ሎው የተባለው የታወቀ መዝገበ ቃላት ደግሞ (አነስተኛም ይሁን ከፍተኛ) በሕጋዊ ኃላፊነት ያለን ባለሥልጣንን (በአንድ ጉዳይ ላይ ያለውን) አመለካከት፣ አስተሳሰብ በተፅዕኖ ለማሳመን ሲባል ማንኛውንም ዋጋ ያለውን ነበር በስጦታ፣ በበረከት፣ በድርጎ፣ ወይም በሌላ መልክ መስጠትና መቀበል እንደሆነ ይገልጸዋል፡፡

እንዲሁ በሌላ መዝገበ ቃላት ትንታኔ «የራስ ያልሆነን ሀብትና ንብረት በተለያየ መልኩ መውሰድ፤» ማለት እንደሚሆኑ በቀጥታ እኪስ ውስጥ ዘው ብሎ ባይገባ፣ ቤት ሰርስሮ ሳጥን ሰብሮ በድፍረት ባይሰርቅ፣ አሳቻ ቦታ ቆሞ ባይነጥቅ፣ የዚያን ከዚህ አምጥቶ የማይሆነውን «ይሆናል» የሚሆነውን «አይሆንም» በሚል ወይም ልብን አፍዝዞና አደንግዞ ባይወስድ፣ ጉቦ የራስ ሐቅ ያልሆነን ሀብት፣ ንብረት ወይም ሌላ መንፈሳዊ ስጦታ፣ በሥልጣን ተጠቅሞ መቀበል፣ መሥረቅ፣ መዝረፍ፣ ማጭበርበር፣ ማታለል መሆኑን እንረዳለን፡፡

በእርግጥም መንግሥት የጣለበትን ከፍተኛ ኃላፊነት ዘንግቶ ሥልጣኑን ለሕዝብ ዕድገትና ብልፅግና ማዋል ሲገባው የራሱን ጥቅም ማሳደድ ከሆነ በቢሮ ውስጥ መቀመጡ በስተቀር ጫካ ከገባ ወንበዴ፣ ጨለማን ተገን አድርጎ ቤት ከሚሰረስር ሌባ፣ አካባቢውን በቁጥጥር ሥር አድርጎ ከሚዘርፍ ነጣቂ፣ እሰው ኪስ ከሚገባ ሞሽላቃ ሌባ ሊለይ አይችልም፡፡

ጉቦ በጉልተኛው ሥርዓት መተያያ፣ እጅ መንሻ፣ ፊት መፍቻ፣ ቲፕ ወዘተ. የወግ ስሞቹ ሲሆኑ መደለያ፣ መማለጃ፣ መሸንገያ፣ ወዘተ. የሐሜት መጠሪያዎቹ ነበሩ፡፡ የማዕረግ ስሞቹ ደግሞ አምኃ፣ ገጸ በረከት፣ ሙገሳ፣ ውደሳ፣ ቅደሳ፣ በመባል ይታወቁ ነበር፡፡ የሐሜት ስሞቹ መደለያ፣ ማለዘቢያ፣ መማለጃ፣ መሸንገያ፣ የማይነጥፍ የቅቤ ማሰሮ፣ ቢሆኑም ማስታወሻ፣ መታሰቢያ፣ ስጦታ፣ የሚሉት ደግሞ ከቁልምጫ ስሞቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

«የመንግሥት ገቢ የሚሰበስብ ባለሥልጣን፣ ማር የፈሰሰበት ምላስ» የሚል የህንዶች ተረት ይጨምርበታል፣ «ተሹሞ የማይበላ ተጥዶ የማይፈላ የለም» የሚል የአገራችንን አባባልም ይጠቀሳል፡፡ «ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል» ተብሎም እንደትልቅ ነገር አዋቂ ተብዬዎች በምክር ስም የሚሰጡት ምሳሌያዊ አነጋገር ነው፡፡

ስጦታና ጉቦ

‹‹ስለጉቦና ጉቦኝነት ስናነሳ ጠለቅ ብለን ማየት ያለብን ዓበይት ነጥቦች አሉ፡፡ ችግሩ በአንድ አገር ዳር ድንበር ተከልሎ የሚቀር ሳይሆን፣ ዓለም አቀፍ በህሪ ያለው እንደመሆኑ መጠን ሥረ መሠረቱን መመርመር ለሚወሰደው ዕርምጃ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ‹‹የስጦታና የጉቦ ዝምድና እንዴት ይቆጠራል?›› ብለን አመጣጡን ብንጠይቅ የሥርዓተ ማኅበር ዕድገት ማስተዋል ይጠይቃል፡፡ ‹‹የጉቦ እናት ስጦታ፣ የስጦታ እናት መስዋዕት፣ የመስዋዕት እናት ሰው፣ የሰው እናት ተፈጥሮ›› ማለት ግን ዝርዝር ፍልስፍና በመሆኑ ለጊዜው ስለስጦታና ጉቦ የቅርብ ዝምድና መግለጽ ብቻ ይበቃል፡፡ ይህም የቅርብ ዝምድና በአያሌ ሊቃውንት ትኩረት ተደርጎበት ተተንትኗል፡፡ ከቃሉ አንስተን እንየው፡፡

‹‹ስጦታ›› የሚለው ቃል በደኅንነት ዓመታዊ መጽሔት ትርጉም መሠረት አምኃ፣ ገጸ-በረከት፣ መተያያ እጅ መንሻ፣ ፊት መፍቻ የሚል ነው፡፡ በሌላው ትርጉሙ ደግሞ ደስታ መግለጫ ቁሳቁስ፣ አንዱ ለሌላው በነፃ የሚሰጠው ዕቃ፣ ንብረት፣ ሀብት፣ … ነው፡፡ ስጦታ ግን ለአንድ ጊዜም ሆነ ለዕድሜ ልክ ሊያገለግል ይችላል፡፡ ይሁንና የልደት በዓል፣ ወይም የዓመት በዓል ወይም የሌላ በዓል ደስታ መግለጫ የወረቀት ስጦታን ከሙክት፣ ከገረወይና ቅቤ፣ ከቤት ወይም ከሌሎች ከፍተኛ ስጦታዎች እኩል ማየት ያስቸግራል፡፡

ያለ ምስክርና በምስክር ፊት የሚሰጡ ስጦታዎች እንዳሉ ሁሉ መንግሥትን በሚወክሉ መሥሪያ ቤት በሕግ መፅደቅ ያለበት ስጦታ እንዳለም የታወቀ ነው፡፡ ማርሴይ ማውስ የተባለው የፈረንሣይ ፈላስፋ እንደገለጸው ስጦታ ከጥንት ሰዎች፣ ዕቃን በዕቃ ከመለወጥ ልማድ የመጣ ነው፡፡ በእሱም እምነት መሠረት ‹‹ዕቃን በገንዘብ መሸጥና መለወጥ ባልነበረበት ጊዜ ሕዝቡ ዕቃውን በዕቃ በመለወጥ ወይም በመሰጣጣት ይጠቀም ነበር፡፡ ይህም ስጦታ ወይም ልውጫ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ፈቃደኝነት፣ በተግባር ግን ግዴታ ነው፤›› ሲል ይተነትናል፡፡ የፈላስፋው ማርሴይ ማውስ አገላለጽ በእኛ አባባል ‹‹ስጦታ የውዴታ ግዴታ›› ቢሆን እናቶች ሕፃናት ልጆቻቸውን ለማስተኛት ‹‹እሹሩሩ›› ቢሉ ወይም እንዳያለቅሱ ‹‹ማባበያ›› ቢሰጡ የውዴታ ግዴታ ተግባራቸውን አከናወኑ ማለት ነው፡፡ ስጦታን ሁሉ በጉቦ መልክ ማየት አስቸጋሪ ነው፡፡ ስጦታን ያዘነን ሰው ለማስደሰት፣ የቀን ጨለማ የዋጠውን ከችግሩ ለማውጣት በሕይወት እምነት ያወጣውን የወደፊት ተስፋውን ብሩህ ለማድረግ ከሆነ ጀምስ ቶማስ የተባለው ባለቅኔ፣

‹‹ስጡት ድንጉል ፈረስ ይጋልብበታል፣

ስጡት መልካም ጀልባ ይንሳፈፍበታል፣

በባህርም ሆነ በባህር ዳርቻ ይደሰትበታል፡፡

ስጡት ጥሩ መጽሐፍ እንዲያገኝ ዕውቀት፣

ምንም ደሃ ቢሆን ልብሱ ቢደረት፣

አይጠላም መዝናናት አይጠላም ቅኝት›› በማለት ስለጥሩ ስጦታ ይገልጽልናል፡፡ ስለስጦታ ከጻፉት ሌሎች ምሁራን አንዱ አሜሪካዊው ደራሲ ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን ሲሆን፣ ይህም ሰው ‹‹ስጦታ›› በሚል ርዕስ የጻፈውን ድርሰት የሚጀምረው ‹‹የስጦታን ሕግ በተመለከተ አንዱ ጓደኛዬ እንዳለው የስጦታ አመልካቹን ባህሪና አስተሳሰብ የሚመሳሰል መሆን ይኖርበታል፡፡ ይሁንና የብዙዎቻችን የስጦታ ምርጫ ከእኛ ጋር ዝምድና የሌላቸውና እኛን የማይክሱ ናቸው፡፡ ስጦታዎች እኛን፣ እኛን ማለት ይኖርባቸዋል፡፡ ስለዚህም ባለቅኔ የግጥሙን፣ በግ አርቢ ጠቦቱን፣ ገበሬው ጥሬውን፣ ሠዓሊው ሥዕሉን፣ ልጃገረድ የሠራችውን የእጅ መሃረብ ማምጣት ሲችሉ ብቻ ነው ስጦታ ስጦታ ሊባል የሚችለው፡፡ ትክክሉና አስደሳቹ ስጦታም ይኸው ነው፡፡ እንደ እኔ፣ እንደ እኔ ስጦታ የሚያበረክትልኝ ሰው አንጥረኛ ቤት ሄዶ ወርቅ ገዝቶ ቢያመጣልኝ የአንጥረኛውን የፈጠራ ሥራ እንዳደንቅ ያደርገኛል፡፡ ምናልባት እንዲህ ያለውን ስጦታ ንጉሦችን ወይም ራሳቸውን እንደ ንጉ ለሚቆጥሩ ትልልቅ ሰዎች ያስደስት ይሆናል፡፡ ለእኔ ቢቀርብልኝም ግን እንደ ርካሽ ብቻ ሳይሆን፣ ስሜን ለማጥፋት እንደተሰኘኝ አድርጌ አየዋለሁ፤›› ብሏል፡፡

ሪልፍ ዋልዶ ኢመርሰን ቀጥሎም ‹‹ጥቅምን ለማግኘት ሲባል በተለይ በቢሮ ውስጥ ለሚሠራ ሰው የሚሰጠው የስጦታ ዓይነትና የአሰጣጥ ሁኔታ ግን እንዴት ማሰኘቱ አይቀርም፡፡ ስጦታው፣ በተሰጠው ሥልጣን እንዲባልግ ለማድረግ ከሆነ ተቀባዩን ብቻ ሳይሆን አቀባዩንም ቢሆን ይቅርታ ልናደርግለት አይገባም፡፡ በጉቦ መልክ የሚመጣውን ስጦታ የምንቀበለው በወዳጅነት መልኩ መስሎን ከሆነም በማር የተጠቀለለ መራራ ምግብ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ስለዚህም ከወዳጆቻችን የሚቀርቡልንን ስጦታ እኛ የገዛነውን ያህል በደስታ ብንቀበለውም ሰጭያችን በስጦታ መልኩ ሳይሆን በሚፈልገው መንገድ ውለታውን እንድንመልስለት ያበረከተው ተቀማጭ ሀብት መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል፤›› ሲል ያስጠነቅቃል፡፡

ስጦታን በሚመለከት ብዙዎቻችን ብዙ የምናውቀው ጉዳይ አለ፡፡ ልጆቻቸው ቢታመሙ ወይም ራሳቸው አደጋ ላይ ቢወድቁ ወይም በጣም የሚፈልጉት ነገር ቢኖር ለማንም ይሁን ለምን ‹‹ሕይወቴን ሳይቀር እሰጣለሁ›› የሚሉ አሉ፡፡ ይህም የሚያመለክተን ስጦታም ከመስዋዕት ጋር ዝምድና እንዳለው ነው፡፡ የሆነ ሆኖ የጥቂት ሰዎችን ፍላጎት ለማርካት ሲባል የብዙኃንን ጥቅም የሚፃረር ስጦታ እንደሌሎቹ ማኅበራዊ ጠንቆች ሁሉ ሊወገድ የሚገባው ልማድ ነውና ይህንን ለረዥም ጊዜ የቆየ አጉል ልምድ ለማስቀረት ሕዝባዊ ቁጥጥርና ትግል ያስፈልገዋል፡፡ የሕዝባዊ ቁጥጥር ዓላማም በማንኛውም መልክ የሚከሰቱት የአስተዳደር በደሎችን፣ ሕገወጥ ብልፅግናን፣ ምዝበራንና በሥልጣን መባለግን መዋጋት ነው፡፡ በስጦታ መልክ በሚቀርብ ጉቦ ፍትሕን ማዛባት፣ ሕግንና ደንብን መጣስ የብዙኃንን ጥቅም ስለሚጎዳ የዕድገት ፀር መሆኑንም መታወቅ ይኖርበታል፡፡  

ጥቂት የሙስናና የጉቦ ሥልቶችና ዓይነቶች

አዲስ ነገር ለማግኘት ወይም ካለው ለመጨመር፣ ግብር ለማስቀነስና ለመታለፍ፣ የንግድ ተቀናቃኞችን ለማጥፋትና የራስን ሥራ ለማስፋፋት፣ በጨረታ ለማሸነፍና ሚስጥሩን ለመሸፋፈን፣ ከተመን በላይ ለመሸጥና ለመግዛት፣ ገበያ ሞቅ ወዳለበት አካባቢ ለመሄድና ለመመለሰ፣ ጥሬ ዕቃን ከአገር ውጭ ለማስወጣትና ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት፣ መናኛ ሸቀጦችን ለመሸጥና ለመለወጥ፣ በሥራ ላይ የማይውሉ የመለዋወጫ ዕቃዎቻቸው ዋጋ እንዲያወጡ ለማድረግ፣ ጥሬ ዕቃዎቻቸው በገበያ የማይገኝ ፋብሪንዎችን ለማስገዛት፣… ከሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመገናኝት ሁኔታዎችን በማመቻቸት ጉቦ መቀበል አለ፡፡

በአገራችንም ሆነ በሌላ በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች በሙስና በግብር መታለፍ ወይም አለመሰብሰብ ሳቢያ የሚቦጠቦጠው የመንግሥትና የግለሰብ ወይም የቡድን ሀብት እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ የዛሬ 32 ዓመትና ከዚያ በፊት የደርግ የሠርቶ አደሩ ቁጥጥር ኮሚቴ መዛግብት ያመለክቱት እንደነበረው ሁሉ ከአንድ ግለሰብ ከ1-10 ሚሊዮን የሚደርስ የመንግሥት ውዝፍ ግብር የሚፈለግበት ግለሰብ ሙስናን እንደ መሣሪያ በመጠቀም በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ጉቦ እንዲከፍል ይጠየቅ እንደነበረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከአሥር ሚሊዮን ተነስተን እስከ መቶ ቤት ያለውን ስናሰላ በጉቦ ምክንያትና  ለጉቦ የሚወጣው ገንዘብ ብዛት ምን ያህል እንደሆነ መረዳት እንችላለን፡፡

ይህም ኃላፊነታቸውን ለዘነጉ ሰዎች የሚሰጠው ደመወዝ፣ አበል፣ ትራንስፖርት፣ ሌላም ሌላም የማፈሰው የብር መዓት ሳይጨመር ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ ከዕዝ ኢኮኖሚ ወጥተን ወደ ነፃ ኢኮኖሚ የገባን ስለሆነ ማለትም፣ ከብዙ ልማት ጋር ብዙ የሥልጣን መባለግና ማባለግ የሙስና ዘዴው እጅግ ብዙ ስለሆነ ሊጨምር እንጂ ሊቀንስ አይችልም፡፡ ለምሳሌ አንድ ከውጭ የሚመጣ የንግድ ዕቃ ለማምጣት ከታሰበበት ጊዜ ጀምሮ ትርፍና ኪሳራው ስለሚታሰብ የት ቦታ በዝቅተኛ ዋጋ እንደሚገዛ፣ ምን ዓይነት ደረጃ ሊጻፍበት እንደሚገባ፣ እንዴት እንደሚጫን፣ እንዴት እንደሚራገፍ፣ እንዴት የቀረጥን መስመር ሰብሮ ወይም ሕጋዊ ካባ ለብሶ እግለሰቡ መደብር እንደሚገባ ሲሰላ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በቁሳዊና መንፈሳዊ ሙስና ታጅቦ የሚሆንበት ጊዜ ይኖራል፡፡

ሁሉንም የሙስና ብልግና ወይም የሥልጣን ብልግናን ለመግለጽና አፀያፊነቱን ለመግለጽ በእጅጉ ሰፊ ቦታና ጊዜ የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ እንዲያው ለመሆኑ አገራችን የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው አስመጪና ላኪዎች የሚነግዱባትና የትርፍ ትርፍ የሚዝቁባት፣ በአጭር ጊዜም በሙስና ሮኬት ተወንጭፈው በከፍተኛ የብልፅግና ደረጃ የሚደርሱባት፣ በሐቅ ሲሠሩ የሚከስሩባትና የሚደኸዩባት፣ ሞላጫ ሌቦች በቁጥጥር አካል ቢጠየቁ ያለምንም ተፅዕኖ እንዲለቀቁ ለማድረግ፣ የሐሰት ሰነድ አዘጋጅቶ የተለየዩ እርከኖችን እንዲያልፉ ለማስቻል፣ የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ንብረት አስመስሎ ከቦታ ቦታ ለማዘዋወር ወዘተ. ጥረት የማይደረግባት ናትን? ለመሆኑ ሰዎች በተሾሙ ማግሥት የተወለወለ ብርጭቆ መስለው የሚታዩት ሠርተው ባገኙት ደመወዝ በልተውና ጠጥተው ነው? እንዴት ነው በተሾሙ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ባለ ቪላና ባለፎቅ የሚሆኑት? ልጆቻቸውን 70 እና መቶ ሺሕ እየከፈሉ የሚያስተምሩት? ይህ እንግዲህ በጎን የሚያወጡት ሌላ ወጪ ከሒሳብ ሳይገባ ነው፡፡ ለመሆኑ ሕዝብ የማያውቀው ገበና አለ?

የዛሬ 40 ዓመት አንድ ሻለቃ የአንድ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሲሠሩ አስተዳደሩ ያረፍዳል፡፡ ለምን እንዳረፈደ ሲጠይቁት የሚያልባት ላሙ ተሰብራበት ወደ ወጌሻ ሲወስድ እንደረፈደበት እየተቅለሰለሰ ይነግራቸዋል፡፡ እሳቸውም ለብዙ ጊዜ ሲበሽቁ ስለነበር፣ «ዋናዋን ላምህን በጊዜ ገብተህ ብታልባት አይሻልም?» በማለት በሰው ፊት እንዳዋረዱት ትዝ ይለኛል፡፡ ታዲያ ያ ባለላም ዛሬ ቱጃር ሲሆን እሳቸው ግን ቆረቆንዴያቸው ወጥቶ እግራቸውን እየጎተቱ ይኳትናሉ፡፡

ሙሰኝነት ራስን በማስተዋወቅም ይከሰታል

ራስን ለማስተዋወቅ በፖለቲካ ኢኮኖሚ በማኅበራዊ ኑሮ መስክ የሚከፈል ሙስናም አለ፡፡ ሙዚቃ ሻጭ የካሴትን ወይም የሸክላ ወይም የሲዲ ገበያው እንዲደራለት ብቻ ሳይሆን፣ ሙዚቀኛው ራሱ ከሌላው የበለጠ እንቅስቃሴ፣ ከዝናው የበለጠ ዝና፣ ከተወዳጅነቱ የበለጠ ተወዳጅ፣ እንዲሆን ለልዩ ልዩ ባለሙያዎች የሚሰጥ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብም አለ፡፡ ደራሲው፣ ሠዓሊው፣ ቀራፂው፣ ተዋናዩ፣ ጸሐፊ ተወኔቱ፣ ስማቸው በጋዜጣ በሬዲዮ በቴሌቪዥን ተጋኖ እንዲነገርላቸው የመንግሥት ሠራተኞችን በገንዘብም ሆነ በአፍ የሚደልሉም ሆነ የሚያባብሉ ጉቦ አልሰጡም ተብለው ሊዘለሉ አይችሉም፡፡ እነዚህን ሰዎች ከመዓቱ ሊሠራቸው የሚችለው «ዝና ወደ አልበርት አይንሽታይን ሄደች እንጂ አልበርት አይነሽታይን ወደ ዝና አልሄደም፤» የሚባለው ብቻ ነው፡፡

ጉቦ በምርምር መስክ

ጉቦ የሚሰጠውም ሆነ የሚቀበለው ለግል ጥቅም ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ለአገር  የሚጠቅም የምርምር ሥራ ለመሥራትም የተለያዩ ችግሮችን በጉቦ ማለፍ የሚያስገድድበት ሁኔታ አለ፡፡ ኧርነስት ሃርበርግ እ.ኤ.አ. በ1966 «የምርምር ደሴት» በሚል ርዕስ በደረሱት የምርምር ሒደትን በሚያሳይ ሥዕል እንደገለጹት «አንድ ሰው ስለአንድ ነገር ተመራምሮ ውጤት ለማስገኘት ፍላጎት ካለው በመጀመርያ የሚጠቀሱ አዋቂዎች ጋር ፊት ለት መጋፈጥ ይኖርበታል፡፡ ጋሊሊዩ ጋሊሊ መሬት መሽከርከሯን ሲያረጋግጥ «ውሸት ነው» እንዳሉት ማለት ነው፡፡ የአዋቂዎችን ኬላ ሰብሮ ካለፈም የብዙ ሰዎችን ቀኖናዊ አመለካከት የሚነካ አስተሳሰብ መለወጥን ያህል ከፍተኛ ተግባር የሚከናወነው በዋዛ አይደለም፡፡ በዚህ በኩል የሚደረገው ጥረት ከተሳካ ምርምሩ ወደ መላምት ይሸጋገራል፡፡ መላምቱን ለማረጋገጥ ግን ወደ ተግባራዊነት ለመቀየር የሚያስፈልጉትን ቁሳቁሶች ለመግዛት ጉቦ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ መላምቱ በሙከራ ተረጋግጦ በሕዝብ እንዲታወቅ ለማድረግ የጥቂት ግለሰቦችን ጥቅም መንካቱ ስለማይቀር ይህንን ማነቆ ለማለፍ ሌላ ጉቦ ያስፈልጋል፡፡ «ይች ባቆላ ካደረች አትቆረጠምም» ይሉና «ወንድም ጉዞህ ወዴት ነው?» በማለት የሚጠይቁ ቢኖሩ ማንነትንና የሚሄዱበትን አቅጣጫ ብቻ ማስረዳት አይበቃም፡፡ ይህንን ሁሉ ካለፉ በኋላ የምርምር ውጤትን በከፍተኛ ደረጃ ጥቅም ላይ ለማዋል እንዲቻል ከመንግሥት ወይም ከሌላ ድርጅት ወረቀት መጠየቁ ስለማይቀር ወረቀቱ የሚገኘው በወራት ይሆንና ካለበለዚያ «በጀት የለንም»፣ «የምርምሩ ውጤት ምን ያህል አስተማማኝ ነው?» ከዕቅዳችን ጋር አይሄድም…» የሚሉ ምክንያቶች ይደረድራሉ፡፡ ምናልባትም «ፈቃጁ የሉም፣ የበታች ሹሙ ፈቃድ ላይ ናቸው፣ ለዕረፍት ወጥተዋል፤» ሊባል ይችላል፡፡ «የተጠናው እንደገና እንዲጠና» ቢባል ለታማኙና ለአሳማኝ አጥኚ የሚፈለገውን መስጠት ይኖራል፡፡ ብርታት ያለው ሰው እነዚህን ሁሉ አልፎ ለኅብረተሰቡ የሚፈይደውን ውጤት ያቀርባል፡፡ ለመሆኑ ለኅብረተሰቡ የሚጠቅም ውጤት ለማቅረብ ሲባል ለሚከናወን ምርምር ይህን ያህል መሰናክለ ማለፍ የሚያስፈልገው ለምን ይሆን? ብለን ብንጠይቅ ያ ዞሮ ዞሮ «የጉቦ» ጣጣ መሆኑን እንረዳለን፡፡ 

በሙስናና በጉቦ ስለተጨማለቀ ብልሹ አስተዳደር

በሌሎችም አገሮች ቢሆን፣ ማንኛውም ሠራተኛ በሥልጣኑ ሥር እንዲንበረከክና መጥፎ ድርጊት ሲፈጸም «አሜን» ብሎ እንዲቀበለው ለማድረግ በልዩ ልዩ የቢሮክራሲ ሥልቶች መጠቀም ጥንትም ሆነ ዛሬ የተለመደ ነው፡፡ ይልቁንም በበርካታ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በመንግሥት ሀብትና ንብረት እንዲሁም፣ ሥልጣን በንግድም ሆነ በሌላ መንገድ ለመጠቀም በጥቅሉ የማይፈነቀል ድንጋይ የለም ማለት ይቻላል፡፡ በእነዚህ የልማት ድርጅቶች ግልጽነት የጎደለውን አሠራር በማስፈን የሚፈጸመው ደባ እንዲህ በቀላሉ መተንተን አስቸጋሪ ነው፡፡ ሁነኛ ሰዎችን በዋና ዋና መዋቅሮች እንዲሁም ሕዝባዊ ማኅበራት በማስቀመጥ፣ በልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅሞች በመያዝ፣ የሥልጣን ተቀናቃኞቻቸው በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ በማሰለልና አደገኛ ሆነው ካገኟቸው ምንም ያህል ለድርጁቱ ጠቃሚ ዕውቀት ይኑራቸው ልዩ ልዩ ስሞችን በመቀባትና የሐሰት ወሬ በማስወራት፣ እነሱ ከሳሽ፣ እነሱ ፈራጅ፣ መሆን በከፍተኛ ወንጀል በመቅጣት፣ አንገታቸውን እንዲደፉ ማድረግ፣ ወይም በመንግሥት ሀብትና ንብረት ጠበቃ ቀጥረው መቀመቅ እንዲወርዱ በማድረግ፣ በኃላፊነት ያሉትን በማንኛውም ጊዜ ሊያፈናቅሏቸው እንደሚችሉ በማስፈራራት፣ ለእንባ ጠባቂዎቻቸው አግባብ ያልሆነ ወረታ በመክፈል፣ የሕዝብንና የመንግሥትን አደራ ወደጎን ትቶ በሥልጣን በመባለግ፣ ያላግባብ የደመወዝ ዕድገት በመስጠት፣ ዘመድ አዝማድን በቀጥታ ወይም በተለዋጭ በመቅጠር፣ የሙስና/ጉቦ ሥልትን አስፋፍቶ መኖርም አለ፡፡

በቀድሞው ማስታወቂያ ሚኒስቴር «ማን የማን ዘመድ መሆኑ የሚታወቀው በለቅሶ ጊዜ ነው፤» ይባል ነበር፡፡ በእርግጥም በቀድሞው ማስታወቂያ ሚኒስቴር «ጌታዬ፣ ጌታዬ፣» እያለ ከሚያለቅሰው ያላነሰ «ጋሽዬ፣ አብዬ፣ አጎቴ፣» ወዘተ. እያለ ያለቅስ እንደነበር የታወቀ ነው፡፡ አንድ የቀድሞ የመብራት ኃይል ባለሥልጣን «ምነው የአገርህን ሰዎች አበዛህ?» ተብለው ቢወቀሱ «ጌታዬ፣ እኔ የአገሬን ሰው ስቀጥር፣ ሌላውም እንደዚያ ሲያደርግ አገሩ ሁሉ ተቀጠረ ማለት አይደለም?» ሲል እንዲህ ያለው ጤነኛ ያልሆነ ድርጊት እንደሕጋዊ ቆጥሮ መለሰ ይባላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ባለጉዳዮችን ማጉላላት፣ ሕግን አጣሞ ለመተርጎም መሞከር፣ ለጉዳዩ ቁም ነገር አለመሰጠት፣ ባለጋራን ለመጥቀም የተነሱ መስሎ መታየት፣ ተስፋ ለማስቆረጥ መሞከር፣ ጉዳዩ በእጃቸው እያለ በሌሎች እንዳለ አስመስሎ መንገር፣ ሰዎች በቀላሉ አግኝተው የሚያነጋግሯቸው ሰዎች በእነሱ አማካይነት ለመደለል ሐሳብ ማቅረብ፣ መልካም ፍፃሜ ያገኘውን ጉዳይ እንዳላለቀ፣ ገና ብዙ እንሚቀረው እየተነተኑ ለጉቦ ማዘጋጀት ጥቂቶቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡

ዴሞክራሲ አለ በሚባልባቸው አገሮች እንኳን ሥልጣን ለመያዝ በማድረግ ውድድር ተመራጭም ሆነ አስመራጭ መራጩን በልዩ ልዩ መንገዶች በማግባባት ሊሠራና ሊሆን የማይችል ተስፋ መስጠት የመራጩን ልቦና የሚማረኩ ቃላት በማዥጎድጎድ ከሚሰጡት የከርፈር መደለያ ሌላ በፖርቲዎቻቸው አስተባባሪነት ከፍተኛ ገንዘብ በማዋጣት የድምፅ ወረቀት እስከ መግዛት የሚደርሱበት ሁኔታ አለ፡፡ በነዚህ አገሮች «ገንዘብ የፖለቲካ የወተት ላም ናት» የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡

ሙሰኝነትን ለመታገል የኪነ ጥበብ ሰዎች ሚና ምን መምሰል አለበት?

እንደሚታወቀው ሁሉ መላ አካላችን በአዕምሮ ቁጥጥር ሥር ባይሆን ኖሮ እጅም፣ እግርም፣ ዓይንም፣ … እንደፈለጋቸው በሆኑ ነበር፡፡ በየአንዳንዱ ሕዋስ ውስጥ ቁጥጥር መኖሩን የሚገነዘብ ግን በእያንዳንዱ ማኅበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ (ከቤተሰብ ኃላፊ ጀምሮ) ቁጥጥር እንዳለም ያውቃል፡፡ ነገር ግን ተፈጥሮ ራሷ ከቁጥጥር ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላት እንደመሆኗ መጠን አንድ ሥርዓትም ቁጥጥር ያስፈልገዋል፡፡ በዚህ ረገድ የኪነ ጥበብ ሰዎች ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ልዩ ልዩ ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡ ከዋና ዋናዎቹ ሕዝባዊ ተቆጣጣሪዎች ውስጥ በኪነ ጥበብ ዘርፍ የተሠማሩትን እንደምሳሌ ብንጠቅስ በዓለማችን የተጫወቱት ሚና እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1828-1908 የነበረው ኖርዌያዊው ደራሲ ሔንሬክ ኢብሰን በዓለም ዝናው ገኖ የሚነገርለት በወቅቱ በአገሩ የነበሩትን ከበርቴዎች በኅብረተሰቡ የሚፈጽሙትን ደባ በማጋለጥ፣ የሥርዓቱን አቀንቃኞች በማውገዝ፣ ጉቦኝነትን፣ የአስተዳደር በደልን፣ ፍትሕና ርትዕ መጓደልን በመንቀፍ ምርጥ ሥራዎቹን ትቶልናል፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ለአገሩ ምን መሥራት እንዳለበት ጠቁሞናል፡፡

ለብዙዎቻችን እንግዳ ያልሆነው ዝነኛው እንግሊዛዊ ጸሐፊ ተውኔት ዊልያም ሼክስፒር (ከ1564-1616 እ.ኤ.አ.) በሥልጣን ስለመባለግ፣ ስለሕገወጥ ብልፅግና፣ ራን ከሁሉም በላይ አድርጎ ስለመውደድ፣ ለራስ ጥቅም ሲባል የሌላውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኑሮ ስለማናጋት በሰፊው አስተምሮ ያለፈ ታላቅ የሥነ ጽሑፍ ሰው ነው፡፡ ሩሲያዊው ደራሲ አንቷን ቸኮቭም (1860-1904 እ.ኤ.አ.) እንደዊልያም ሼክስፒር ዝነኝነትን አትርፎ የሄደው በሕዝባዊ ተቆጣጣሪነቱና ሕዝባዊ አመለካከቱ ነው፡፡ ይኸው ከአንድ ጭሰኛ ቤተሰብ ተወልዶ የዓለማችን ድንቅ ሰው የሆነ ሩሲያዊ በወቅቱ የነበረውን የሩሲያ ሕዝብ ኑሮ የኖረና ስለዚያ ሕዝብ ጻፈ ብቻ ሳይሆን፣ ትግሉን እየታገለ፣ ፍትሕ፣ እኩልነትና ዴሞክራ እንዲኖር፣ ባላባታዊ አገዛዝ ይፈጽመው የነበረውን ግፍ ማጋለጥ ብቻ ሳይሆን፣ የኅብረተሰቡ ባህልና ወግ እንዲዳብር፣ የአገሪቱ የተፈጥሮ ሀብት እንዲጠብቅና ሕዝቡ ካለማወቅ የሚፈጽመውን ጥፋት እንዲያቆም በማስተማር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ ደራሲ ነው፡፡ ቸኮቭ በአስቂኝ ተውኔቶቹ ሕዝብ ከኋላቀር አስተሳሰብ ተላቆ አገሩን መገንባት እንዳለበት አስተምሯል፡፡

አንድ ሰው ሕዝባዊ ተቆጣጣሪ ነው ሲባል የጠፋውን ስለጠቆመ (ስላጋለጠ) ወይም ያጠፋውን ስለያዘና ስለቀጣ ብቻ አይደለም፡፡ የጥፋት አባሪና ተነባባሪ መሆን እንደሚያስጠይቅ ሁሉ፣ በአንፃሩም ምርትን ከፍ ያደረገና በፈጠራ ችሎታው ለአገር ለወገን የሚጠቅም ነገር የሠራ፣ የአገር አንድነትና ነፃነት ተጠብቆ እንዲኖር የበኩሉን አስተዋጽኦ በጋራና በግል ያበረከተ ሁሉ ሕዝባዊ ተቆጣጣሪ ነው፡፡ ስለዚሁ ጉዳይ የሠርቶ አደሩ ቁጥጥር ኮሚቴን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ እንደሚያመለክተው ሥራ እንዲሻሻል፣ የሥራ ኃይልና የሥራ አመራር ሳይንሳዊ በሆነ ዘዴ እንዲደራጅ የሚረዳ አካል በማንኛውም መልኩ ቢሆን ሥራን የሚያሻሽል፣ የሚሠራ፣ ከጥፋት ይልቅ ልማትን የሚዘወትር ሁሉ ሕዝባዊ ተቆጣጣሪ መሆኑን ያመለክታል፡፡

አገራችንም ‹‹ሀሁ በስድስት ወር፣ አቡጊዳ ቀይሶ፣ ፀረ ኮሎኒያሊስት፣ ሽፍንፍን ሚዛን፣ ትዝብት፣…›› የመሳሰሉት ተውኔቶች በሬዲዮ፣ በጋዜጣና በቴሌቪዥን የሚቀርቡ ግጥሞችና ታሪኮች፣ በየአደባባዩ፣ በሕዝባዊና በመንግሥታዊ ድርጅቶች የተሣሉ ሥዕሎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የሚጻፈው ጽሑፍ፣ ሥዕል፣ ቅርፅ … ግን በአንድ ጊዜ ተቀባይነት ያገኛል ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም ሕዝባዊ አመለካከት የጎደላቸው አድኅሮች ኃይላት ተቃውሞ ሊያስነሱ ይችላሉ፡፡ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሊካሄድባቸውም ይችላል፡፡ አብዮታዊ እንቅስቃሴን የሚቃወሙ ወግ አጥባቂዎች ሁሉ ተራማጅ አመለካከት ይኖራቸዋል ብሎ ማሰብም አስቸጋሪ ነው፡፡ ሔንሪክ ኢብሰን በተቃዋሚዎቹ ‹‹አርቆ የማያስብን ጠባብ አመለካከት ያለው ግለሰብ›› በማበል ተዘልፏል፡፡ ሰር ፍራንሲስ ቤከን የተባለው እንግሊዛዊ ፈላስፋና ደራሲም በጠላቶቹ ሸር ጉቦ እንዲቀበል ተደርጎ ከተከሰሰ በኋላ ቅጣት ደርሶበታል፡፡ እንግሊዛዊው ጆርጅ ቤርናንድሾውም ቢሆን አንዱ ሰይጣን ሌላ መልዓክ እንደገና አንዱ ሰው ሌላው አውሬ ቢያደርገውም፣ ዘጠና ዓመት የልደት በዓሉን ሲያከብር በመላው ዓለም እንደታሰበለት ይነገራል፡፡ ብዙዎቹ የኪነ ጥበብ ሰዎች በሕዝባዊ አመለካከታቸው የሕዝባዊ ቁጥጥር አባላት ናቸው ብለን ማጠቃለል የምንደፍረውም በዚህ ነው፡፡ ብሔራዊ ሀብታችን ሊጠበቅና ሊዳብር የሚችለውም በሕዝባዊ ቁጥጥር ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...