Sunday, May 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የውጭ ኩባንያዎች የንግድ ውል ማፍረስ ምጣኔ እየጨመረና ጉዳት እያስከተለ መሆኑ ተጠቆመ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያና በተለያዩ አገሮች ኩባንያዎች መካከል በሚካሄድ የንግድ ልውውጥ እየተፈጠሩ ያሉ የንግድ ግድፈቶች (ትሬድ ዲፎልት) መጠን እየጨመረ ስለመምጣቱ ተጠቆመ፡፡ ችግሩ ከዚህ ቀደም የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ችግሩን ለመቅረፍ የተደረጉ ያሉ ጥረቶች የተሳኩ አለመሆናቸው፣ ጉዳዩን አሳሳቢ እያደረገው ነው፡፡ ባለፈው ቅዳሜ የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ጉዳዮችን አስመልክቶ በተደረገ ምክክር ላይ ይህ ችግር በቀዳሚነት ትኩረት ያገኘ ጉዳይ ነበር። 

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አቶ ውቤ መንግሥቱ፣ በዚህ ችግር ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ የንግድ ውልን ካለማክበር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች (የትሬድ ዲፎልት) መጠናቸው እየጨመረ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በትብብር ሊሠሩበት ይገባል ብለዋል።

በ2014 በጀት ዓመት ብቻ ከ25 በላይ የኢትዮጵያ ላኪዎች በተለያዩ አገሮች ከሚገኙ ኩባንያዎች ጋር ውለታ ገብተው ወደ ውጭ ለላኩት ምርት ክፍያ ያልተፈጸመላቸው መሆኑን በመግለጽ ለንግድ ምክር ቤቱ አቤቱታ ማቅረባቸውን ጠቁመዋል፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያ ነጋዴዎችና ላኪዎች በተለያዩ አገሮች ከሚገኙ ተቀባይ ኩባንያዎች ሊያገኙት ይገባ የነበረ ያሉ የክፍያ መጠን ከ50 ሺሕ እስከ 292 ሺሕ ዶላር የሚደርስ መሆኑንም አቶ ውቤ ገልጸዋል፡፡  

ይህ ለኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ብቻ የቀረበ አቤቱታ ሲሆን፣ ለሌሎች ንግድ ምክር ቤቶች፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ተመሳሳይ አቤቱታዎች እየቀረቡላቸው መሆኑ የችግሩን አሳሳቢነት ያሳያል ብለዋል፡፡ 

እነዚህ የኢትዮጵያ ላኪዎች የገጠማቸውን ችግር በራሳቸው መንገድ ሄደው መጨረስ ባለመቻላቸው፣ ንግድ ምክር ቤቱ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኤምባሲዎችና ከፍትሕ ሚኒስቴር ተነጋግሮ መፍትሔ እንዲሰጣቸው እየጠየቁ እያሉ መሆኑን አቶ ውቤ ገልጸዋል፡፡ 

የንግድ ውልን አለማክበር እየተፈጸመ ያለው በተቀባይ የውጭ ኩባንያዎች ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ኩባንያዎችም ጭምር የሚፈጸም እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በ2014 የበጀት ዓመት ብቻ 21 የሚሆኑ የውጭ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ኩባንያዎች ጋር ባደረጉት የንግድ ስምምነት መሠረት ለላኩት ዕቃ ተገቢውን ክፍያ እንዳላገኙ ጠቅሰው ለኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት አቤቱታ ማቅረባቸውን አውስተዋል፡፡ በመሆኑም ችግሩ በሁለቱም ወገን የሚከሰት መሆኑን አመላክተዋል፡፡ በዕለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የሰጡት አስተያየት የሚያመለክተውም የንግድ ልውውጥ ላይ የሚፈጠረው ግድፈት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ነው፡፡ 

የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ በነበሩበት ወቅት ችግሩን በደንብ የሚያውቁት መሆኑን ያስታወሱት የአሁኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በተለያዩ አገሮች የተመደቡ አምባሳደሮች የራሳቸውን ጥረት ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ 

‹‹ከበፊት መሥሪያ ቤቴ (ንግድ ሚኒስቴር) የማውቀው በርካታ የትሬድ ዲፎልቶች አሉ፤›› ያሉት አምባሳደር ምሥጋኑ፣ ‹‹አንዱ በእኛ ኤክስፖርተሮች በኩል የሚፈጸም ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ከገዥዎች በኩል የሚፈጸም ነው፡፡ በመሆኑም ሚሲዮኖቻችን ከየአገሩ ንግድ ምክር ቤቶች ጋር በመነጋገር ትሬድ ዲፎልቶችን እንዲንቀንሱ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል›› ብለዋል፡፡ 

በተለያዩ አገራት የሚመደቡ አምባሳደሮች በብዙ ሚሊዮን ዶላሮች የሚገመት ትሬድ ዲፎልቶች እንዳሉ በማወቅ እነዚህን ለመፍታት ጉዳዮች ከንግድ ምክር ቤቶች ጋር መሥራት እንደሚጠበቅማቸው አስገንዝበዋል፡፡  

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ከሰጡ ዲፕሎማቶች መካከል ዱባይ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንፅላ የተወከሉት ዲፕሎማት የትሬድ ዲፎልቱ ችግሩ ከዕውቀትና ከልምድ ማነስ ጋር በተያያዘ የሚፈጠር እንደሆነ ገልጸዋል።

‹‹በአግባቡ ውል ሳይገቡ ወይም ደግሞ ውል ገብተው ማድረግ ያለባቸውን ባለመገንዘብ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት እንዲሁ ባክኖ የሚቀርበት ሁኔታ እየታየ ነው፤›› ያሉት እኚሁ የዱባይ ዲፕሎማት፣ ችግሩ አሳሳቢ በመሆኑ መፍትሔ የሚያስፈልገው እንደሆነም አመልክተዋል፡፡  

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ የኢትዮጵያ ነጋዴዎች የሚያደርጉት የንግድ ስምምነት ጥንቃቄ የተሞላውና ሕጋዊ መሆኑን ማረጋገጥ የሚጠይቅ ነው፡፡ ‹‹ዱባይ ያሉና ከእኛ አገር ነጋዴዎች ጋር የሚዋዋሉ ነጋዴዎች አንዳንዶቹ አየር ላይ ያሉ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በትክክል አድራሻ የሌላቸው በመሆኑ ችግሩን አብሶታል፡፡ በዚህ ምክንያት የሚፈጠረው ነገር በጣም የሚያሳዝን ስለሆነ ይህ ጉዳይ አንድ ቦታ ላይ መቋጫ ካልተበጀለት ጉዳቱ ሊቀጥል ይችላል›› በማለት ሥጋታቸውን አካፍለዋል፡፡ በመሆኑም የአገር ውስጥ የንግድ ማኅብረሰብን ስለ ጉዳዩ ግንዛቤ እንዲኖረው በአግባቡ በማስተማር ጤናማ የንግድ ውል እንዲዋዋል ማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ለዚህም የንግድ ምክር ቤቶች የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ኤምባሲዎች እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ላይ ከንግድ ምክር ቤቶች ጋር በቅርበት መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል። 

እሳቸው የወከሉት በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በዚህ ጉዳይ ላይ አበክሮ እየሠራ መሆኑንና የዚህ ንግድ ምክር ቤት አባል የሆኑ ነጋዴዎች የሚፈጽሟቸውን የንግድ ስምምነቶች በማየት ድጋፍ እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር የንግድ ስምምምነቶች አስገዳጅ ውል ቢዘጋጅላቸው ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት ለመፍታት የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

እንዲህ ያለው የንግድ ፎዲልት እንደ አገር ከፍተኛ የሆነ ችግር እየሆነ መምጣቱ፣ በተለያዩ መንገዶች ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ እንዲያውም የአንዳንድ አገሮች ኩባንያዎች በውለታቸው መሠረት ለሰጡት አገልግሎት በተደጋጋሚ ክፍያ ሳይፈጸምላቸው በመቅረቱ ወይም ኤልሲ ተከፍቶ ውጭ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ባንኮች ወኪሎች ገንዘቡ ተቀንሶ ባለመከፈሉ ምክንያት ከኢትዮጵያ አስመጪዎች ጋር አንሠራም እስከማለት ደርሰዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ክስተቶች የሚያስከትሉት ተፅዕኖ የሚያርፈው ክፍያውን ሳይፈጸም በቀረው ኩባንያ ላይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ገጽታ ጭምር የሚያበላሽ እንደሆነ ይገለጻል፡፡ 

በተለይ ኤልሲ ተከፍቶላቸውና ዋስትና ተገብቶላቸው ወደ አገር ለሚገቡ እቃዎች፣  አንዳንድ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ዕቃውን ለላከው የውጭ ኩባንያ ገንዘቡን በትክልል የማያስገቡ በመሆኑ የውጭ ኩባንያዎቹ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጭምር አቤቱታ እስከማቅረብ መድረሳቸው ይታወሳል፡፡

ኤልሲ ለከፈቱላቸው ኩባንያዎች ዕቃ ከገባ በኋላ ክፍያ መፈጸም የሚገባቸው የአገር ውስጥ ባንኮች ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተገቢውን አስተዳደራዊ ዕርምጃ ቢወስድም፣ አሁንም ተመሳሳይ ችግሮች እየቀረቡ ስለመሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡   

የንግድ ስምምነቶች ተፈጻሚ የማይሆኑበትን ምክንያት በተመለከተ፣ ተጨማሪ ማብራሪያ ለሪፖርተር የሰጡት አቶ ውቤ፣ አንዳንዱ ምርቱን ወስዶ ገንዘብ አልከፍልም በሚል የሚፈጠር ነው፡፡ አንዳንዱ ደግሞ በስምምነታችን መሠረት ተልኮልኝ በነበረው ናሙና ልክ ምርቱ ስላለደረሰኝ አልከፍልም በሚል የሚፈጠር አለመግባባት መሆኑን ገልጸዋል። አንዳንዶቹ ምርቱ የደረሳቸው ዘግይቶ እንደሆነ በመጥቀስና ይህንንም ምክንያት በማድረግ ክፍያ እንደማይፈጽሙ፣ ይህም ኩባንያዎቹን ኪሳራ ላይ እንዲወድቁ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል። 

በአብዛኛው ከኢትዮጵያውያን ላኪዎች በኩል ችግር የሌለ መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ ውቤ፣ ከዚህ የሚላኩ ምርቶች በውሉ መሠረት መድረሳቸውን ከመረጃዎቹ እንደተረዱ ገልጸዋል። ነገር ግን ተቀባይ ኩባንያዎቹ በተሰጠው ናሙና መሠረት ምርቱ ከደረሳቸው በኋላ አንዳንዴ የዋጋ መውረድና መውጣት ሲያጋጥማቸው የገቡትን የንግድ ስምምነት እንደሚያፈርሱ አቶ ውቤ አስረድተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ከውጭ ያዘዙትን ዕቃ ከተረከቡ በኋላ፣ በተገቢው ስምምነት መሠረት ክፍያ የማይፈጽሙትና ክስ የሚቀርበብባቸው ደግሞ ክፍያውን ላለመፈጸም ሳይሆን በውለታቸው መሠረት ያዘዙት ዕቃ ካለመቅረቡ ጋር ተያይዞ እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡ አቶ ውቤ በዚህ ሐሳብ የሚስማሙ ሲሆን፣ ደረጃውን ያልጠበቀ፣  የመገልገያ ጊዜው ያለፈበት ምርት እንደሚመጣ ይገልጻሉ። ይህ በሚሆንበት ጊዜ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች የገቡትን የንግድ ስምምነት ላለመፈጸም የሚገደዱበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ጠቁመዋል። በመሆኑም ችግሩ ከኢትዮጵያውያን ኩባንያዎች ብቻ ሳይሆን ከውጭ አቅራቢ ኩባንያዎች ጭምር የሚመነጭ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ 

ይህንን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ መፍትሔዎች ያሉ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ውቤ፣ አንድ ነጋዴ ወደ ስምምነት ሲገባ ምን ምን ማሟላት እንዳለበት ማገዝ አንዱ ነው ብለዋል፡፡ የተፋረሱ ስምምነቶች ሲታዩ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ነጋዴዎችን ስህተት ላይ የሚጥላቸው መሆኑን የዚህ ምክንያትም የንግድ ስምምነቱን ሲፈጽሙ መጠንቀቅ የሚጠባቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች ካለመረዳት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ገልጸዋል። ስለሆነም ከዚህ በኋላ ችግሩን ለማቃለል በንግድ ስምምነት ባህሪያትና ይዘቶች ላይ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ከዚህም ባሻገር ማናቸውም የንግድ ስምምነቶች ከመደረጋቸው በፊት የግድ ሊካተቱ የሚገቡ ነጥቦች አስገዳጅ ሆነው በመንግሥት ሊወጡ እንደሚገባ ተገልጿል።

‹‹በተለያዩ አገሮች ያሉ ኤምባሲዎች ኢትዮጵያውን ኩባንያዎች የሚያደርጓቸው የንግድ ስምምነቶች እንዲደርሳቸው ተደርጎ የማጣራት ሥራ እንዲሠሩ ማድረግም አንድ መፍትሔ ሊሆን ይችላል፤›› ያሉት አቶ ውቤ፣ ይህንን በማድረግ በውጭ የሚገኘው ኩባንያ በትክክል የሚታወቅና በውለታው መሠረት ክፍያውን መክፈል አለመክፈሉን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል አስረድተዋል። አንዳንድ የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ኪሳራ ላይ የወደቁበት ምክንያት ሲታይ ዕቃውን ለመግዛት የተስማማውና በስምምነቱ መሠረት የተረከበው በውጭ የሚገኘው ኩባንያ በውሉ ላይ ባሰፈረው አድራሻ መሠረት ሊገኝ ባለመቻሉ ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ከኢትዮጵያ ኩባንያ ጋር የንግድ ውል ለመፈጸም የተሰናዳ የውጭ ኩባንያ ውል ከመፈጸሙ በፊት የተመዘገበና በህግ የሚታወቅ ስለመሆኑ ቀድመው ሊያረጋግጡ የሚችሉበትን አሰራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። 

አንዳንድ የቀረቡ አቤቱታዎቻችን ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች ውጤት የተገኘባቸው ቢሆንም፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና በኤምባሲዎች መካከል የሚደረጉ የደብዳቤ ልውውጦች አድካሚ በመሆናቸው ቀድሞ የማጣራት ሥራ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል፡፡

እንዲህ ካለው አጀንዳ በዘለለ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ከንግዱ ኅብረተሰብ ያገናኘው መድረክ የዲፕሎማሲ ኢኮኖሚውን ለማጠናከር ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡ በተለይ አምባሳደር ምሥጋና እንዲህ ያለው መድረክ የግልና የመንግስት ግንኙነትን ሊያጠናክር በሚችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ሥራችንን የኢንቨስትና የውጪ የንግድ ሥራችንን ለማስፋት በየቦታው የምናደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ከፕራይቬት ሴክተሩ ውጪ የሚደረጉ አይደሉም፡፡ መንግሥት ነጋዴ አይደለም፤›› ያሉት አምባሳደሩ ኤክስፖርት የሚያደርገው የግል ዘርፉ በመሆኑ ዕውቅና በመስጠት ድጋፍ በማድረግ ውጭ ንግድን እንዲስፋፋ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኢንቨስትመንት ወደ አገር እንዲገባ በማድረግ ረገድ ኤምባሲዎች የምትጫወቱት ሚና ትልቅ በመሆኑ ይህንን ለማድረግ ከግል ዘርፉ ጋር መሥራት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ 

አክለውም ‹‹ከውጭ የሚመጣ ኢንቨስተር መንግሥት የሚሰማውን ያህል የግል ዘርፉን የሚሰማ በመሆኑ የግል ዘርፉ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን፣ የተቃረነ መረጃ መስጠት የለበትም፡፡ እኛ ከምንሠራው በተቃራኒ የሚሠራ ከሆነ፣ አስቸጋሪ ነው፤›› ያሉት አምባሳደር ምሥጋኑ፣ ስለዚህ አገርን በጋራ የሚያስተዋውቅና የመሸጥ ሥራ በጣም ሊሰጠው የሚገባ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ 

‹ከመንግሥት ጋር ተናባቢ የሆነ መረጃ የመስጠት ሥራ በቅንጅት ካልተሠራ በቀር፣ አወንታዊ የገጽታ ግንባታ ውጤት እንደማይመጣ ጠቅሰዋል፡፡ አያይዘውም፣ ብዙ ጊዜ የምናየው ከውጭ የሚመጡ ኢንቨስተሮች ተሰነካክለው የሚሄዱት በመንግሥት ቢሮክራሲ ብቻ ባለመሆኑ እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ሊታረሙ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንት ሁኔታ በጥቅል (በፓኬጅ) አድርጎ መሸጥ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆን እንዳለበት፣  ለዚህ ደግሞ የተመረጡ አገራት ላይ ትኩረት ያደረገ የፕሮሞሽን ሥራ ጠቀሚ መሆኑን አምባሳደር ምሥጋኑ አስረድተዋል።

እንደ ቡና፣ ሰሊጥና ሌሎች ምርቶቻችን ለሁሉም በሚሆን አይነት የፕሮሞሽን ሥራ እያስተዋወቁ ተፈላጊውን ግብ መምታት እንደማይቻል፣ በመሆኑም ኤምባሲዎች ይህንን ከግንዛቤ ያስገባ ሥራ እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል፡፡ 

በዚህ መድረክ ላይ ንግድ ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በተለያዩ መንገዶች ሊደግፉን ይገባል ብሎ በርካታ ጥያቄዎችን ያነሳ ሲሆን፣ በተለይ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ያለንን ግንኙነት ለማጠነከር መረጃ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ኤምባሲዎቹ በሚኙባቸው አገሮች ውስጥ በሚካሄድ የንግድ ትርዒቶች ላይ ተሳታፊ ለመሆንም በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጥያቄ ያቀረበው ንግድ ምክር ቤቱ፣ በተለያዩ የአቅም ውስንነቶች ሲያጋጥሙም ኤምባሲዎች ትብብር ይደረግል ብለዋል፡፡ ሌሎች በትብብር ሊሠሩባቸው ይችላሉ የተባሉ የተለያዩ ጉዳችን ያቀረቡት አቶ ውቤ፣ እስካሁን ግን ከኤምባሲዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ይበል የሚያሰኝና ውጤት የተገኘባቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በዚህ መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ኅብረተሰብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የገበያ ዕድሎችን በአግባቡ እየተጠቀሙ ያለመሆኑ ተወስቷል፡፡ በተለይ ከዱባይ የተወከሉ ዲፕሎማት የኢትዮጵያ ምርቶች ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችሉ በርካታ ዕድሎች ያሉበት አገር ቢሆንም፣ ከዚህ አኳያ የእኛ የንግድ ማኅረበሰብ በዱባይ ባሉ ትልልቅ የንግድ ዕድሎች በአግባቡ እየተጠቀምነው ነው ብለው አያምኑም፡፡

በየሳምንቱ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩነቶች የሚካሄዱ በመሆኑ ቢያንስ ከዋና ዋናዎቹን መርጣችሁ የንግድ ኅብረተሰቡ የሚወከልበትን ሁኔታ በጋራ ብናካትታቸው አፍሪካውያን በብዛት እየተሳተፉ ነው፡፡ 

በዕለቱ የንግድ ምክር ቤቱ ባቀረባቸው ጥያቄዎች ዙሪያ አስተያየት የሰጡ አምባሳደሮች በግልጽ ያስተላለፉት መልዕክት ኤምባሲዎቹ የሚገኙበት አገሮች ብዙ የንግድ ዕድሎች መኖራቸውን ነው፡፡ ይህንን ዕድል በአግባቡ ለመጠቀም ንግድ ምክር ቤቶች መጠንከር እንደሚኖርባቸው ነው፡፡ በኤምባሲዎች በኩል ያሉትን የንግድ ዕድሎች ለንግድ ምክር ቤቶች በማሳወቅ በዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል፡፡ በተለይ የጣልያንና የኮርያ አምባሳደሮች ከንግድ ምክር ቤቱ ጋር እስካሁን የተሠሩ ሥራዎች ውጤት እያስገኙ ሲሆን በእነርሱ በኩል በተመቻቹ ፕሮግራሞች የተለያዩ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በጋራ ለመሥራት መቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ሒደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚሠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

አምባሳደር ፍጹም አረጋ ደግሞ ኤምባሲያቸው ለንግድ ምክር ቤቱ አስፈላጊውን ዕገዛ እንደሚያደርግ አሳውቀው ነገር ግን የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን ንግድ ምክር ቤቱ ጠንካራ መሆን እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ እርሳቸው ባሉበት አገር በርካታ ዕድሎች ያሉ መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደር ፍጹም የንግድ ምክር ቤቱ አባል የሆኑ የግልና የመንግሥት ድርጅቶች እያንዳንዳቸው አዳራሽ ተከራይተውና ራሳቸውን ማስተዋወቅ ይኖርቸዋል፡፡ 

ስለዚህ ንግድ ምክር ቤቱ አቅሙን በደንብ ማየት እንደሚገባውን ለማስታወቂያ የራሱ የሆነ በጀት ካልኖረው አስቸጋሪ ስለሚሆን እዚህ ላይ ጠንከር ብሎ መሥራት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ 

በአምባሳደሮችና በንግድ ምክር ቤቱ መካከል እንዲህ ያለው መድረክ ሲዘጋጅ የመጀመርያ ቢሆንም ቀጣይነት እንዲኖረው በቋሚነት በየዓመቱ ለማካሄድ ዕቅድ ያላቸው መሆኑን የተናገሩት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ እዘዘው፣ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲውን ለማጠናከር ንግድ ምክር ቤቱ ሊያደርግ ይገባል ተብሎ ከአምባሳደሮቹ የተሰጠውን ምክረ ሐሳብ ይዘው እንደሚሠሩበት ቃል ገብተዋል፡፡ 

   

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች