Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በስድስት ወራት የዳያስፖራና የውጭ የቱሪስት ፍሰት ግማሽ ሚሊዮን መድረሱ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ቱሪስቶች ድንበር አቋርጠው በተሸከርካሪ ሲገቡ ይጠየቅ የነበረው 100 ሺሕ ዶላር በሌላ አሠራር ተቀይሯል

በዚህ ዓመት ወደ ኢትዮጵያ ለኮንፈረንስና ለጉብኝት ከመጡ የውጭ ዜጎች በተጨማሪ፣ ወደ አገር ቤት የመጡ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ፍሰት ከ500 ሺሕ በላይ መድረሱ ተገለጸ፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝና የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ እንዲሁም ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ችግር ይፈጠራል በሚል ሥጋት ወደ አገር ውስጥ የገባው ቱሪስት ቁጥር በጣም ውስን ከመሆኑም በላይ፣ አጠቃላይ እንቅስቃሴው የለም በሚባል ደረጃ እንደነበር የቱሪዝም ሚኒስትር ደኤታ አቶ ስለሺ ግርማ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ምንም እንኳ በጉብኝትና በስብሰባ ወደ አገር የገባውን አጠቃላይ ቱሪስት፣ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎችን ለመለየትና ቁጥሩን በትክክል ለመናገር ከተለያዩ አካላት መረጋጋጥ የሚያስፈልገው ቢሆንም፣ አሁን ባለው መረጃ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን አቶ ስለሺ አስረድተዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በአገራዊና ዓለም አቀፋዊ ችግሮች ምክንያት ከውጭ አገር ቱሪስቶችን ወደ ኢትዮጵያ ይልኩ የነበሩ አስጎብኚ ድርጅቶች ጎብኚዎችን መላክ በማቆማቸው፣ በኢትዮጵያ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችና ድርጅቶች ከዘርፉ በቀላሉ ለቀው እንዳይወጡ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ማቆየት እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ በተጀመረው የሰላም ስምምነት ከዚህ ቀደም መሠረታቸውን በውጭ አገር አድርገው ቱሪስቶችን ይልኩ ከነበሩት ድርጅቶች መካከል፣ ከስምምነቱ በኋላ ቢያንስ 50 በመቶ የሚሆኑ በኢትዮጵያ ያለውን የሰላም ሁኔታ እየገመገሙ ስለመሆኑ፣ አንዳንዶቹ በኢትዮጵያ ካሉ ድርጅቶች ጋር እየተመካከሩና የተወሰኑት ደግሞ በግልም በድርጅትም በመሆን ጉብኝት እያደረጉ መሆኑን አቶ ስለሺ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ወደ አገር ቤት የገባው የዳያስፖራ ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ እንደጨመረ የገለጹት አቶ ስለሺ፣ በላሊበላ የገና በዓልን እንዲሁም በጎንደር የጥምቀት በዓልን ለማክበር የተጓዘው ዳያስፖራ ከፍተኛ እንደነበር አውስተዋል፡፡

በተመሳሳይ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ባሉ ሪዞርቶች ውስጥ ያለው አብዛኛው እንግዳ ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራ እንደሆነ ገልጸው፣ በተመሳሳይ የውጭ ዜጎች ፍሰት በአየር ትራንስፖርትም ሆነ ኢትዮጵያን ከሌላ አገሮች በሚያዋስኑ ድንበሮች አልፈው እየገቡ መሆኑን አስተውለናል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አሸናፊ ካሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በድንበር አቋርጠው ወደ አገር ቤት በሚገቡ ቱሪስቶች ፍሰት የተሻለ እንቅስቃሴ እያሳየ ነው፡፡ ነገር ግን የራሳቸውን ተሽከርካሪ ይዘው በሚገቡ ቱሪስቶች ላይ በመንግሥት የተጣለው የተሽከርካሪ ማስያዣ ገንዘብ ዘርፉን ሊጎዳው እንደሚችል ፍራቻቸውን ተናግረዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት መንግሥት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ባወጣው ሕግ መሠረት፣ አንድ ቱሪስት በድንበር በኩል በራሱ ተሽከርካሪ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ 100 ሺሕ ዶላር አስይዞ እንዲገባ ይገደዳል፡፡

ከኬፕታውን እስከ ካይሮ የተሰኘው መስመር ቱሪስቶች በተሽከርካሪ በሚያደርጉት ጉዞ አቆራርጠው አዲስ አበባ የሚደርሱበት እንደሆነ የገለጹት አቶ አሸናፊ፣ በርካታ አገሮችን አቆራርጠው ድንበር ላይ የደረሱ ቱሪስቶች ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ከልካይ የሆነ ሕግ በመሆኑ ማስተካከያ እንደሚያስፈልገው ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ባለፉት ዓመታት በነበረው ጦርነት ምክንያተ በአዲስ አበባ የሚገኙ በርካታ ኢምባሲዎች ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ የማስጠንቀቂያ ጽሑፎችንና ማሳሰቢያ አውጥተው የነበረ ቢሆንም፣ ብዙዎቹ እስካሁን ዕገዳውን ባለማንሳታቸው ቱሪስቶች እንደፈለጉ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት አለመቻላቸውን አቶ አሸናፊ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ቱሪስቶች በአገር ውስጥ የአገልግሎት አሰጣጥ በተለይም በጉምሩክ መጉላላት፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ረዥም የሆነ ሠልፍ፣ በኢምግሬሽን የተወሳሰበ አሠራርና መሰል የመንግሥታዊ አገልግሎቶች ውጣ ውረድ የበዛባቸው ስለሆነ መስተካከል እንዳለባቸው የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ በተመሳሳይ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉት ተዋንያን ሙያው የሚፈልገውን ዕውቀትና ክህሎት ያለው ባለሙያ በማሠልጠንና በማበረታት የተሻለ አገልግሎት ማቅረብ ላይ ችግር ስለመኖሩ አውስተዋል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ስለሺ ግን ከሁለት ወራት በፊት በኮንትሮባንድ የሚገባን ተሽከርካሪ በሕገወጥ መንገድ ወደ ገበያ አስገብቶ የንግድ ሥርዓቱን እንዳያበላሽ በሚል፣ አንድ ድንበር አልፎ የሚገባ ቱሪስት ተሽከርካሪውን ይዞ ተመልሶ ስለመውጣቱ ማረጋገጫ የሚሆን ማስያዣ 100 ሺሕ ዶላር ማስያዝ እንደሚኖርበት አስገዳጅ ሕግ ወጥቷል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ የማስያዣው ገንዘብ የቱሪስት ፍሰቱን የሚገድብ ከመሆኑም በላይ ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዳ በመሆኑ፣ የቱሪዝም ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ማስያዣው እንዲቀር፣ ተደርጓል ብለዋል፡፡ አንድ የውጭ አገር ጎብኚ ድንበር አቋርጦ ወደ አገር ለመግባት ሲያስብ በኢትዮጵያ ከተመዘገበ አንድ ሕጋዊ አስጎብኚ ድርጅት ጋር ውል በመግባት፣ አስጎብኚ ድርጅቱ ኃላፊቱን ተቀብሎ ጉብኝቱን ጨርሶ የያዘውን ተሽከርካሪ ይዞ እንዲወጣ የሚያደርግ አሠራር መቀየሱንና ሥራ ላይ መዋሉን አስረድተዋል፡፡

በዚህም ቱሪስቶቹ ድንበር አቋርጠው ሲገቡ በጉምሩክም ሆነ በሌሎች የደኅንነት ተቋማት የሚደረጉ ቁጥጥሮች እንዳሉ ሆነው ይህ ማስያዣ ክፍያ እንዲቀር በማድረግ፣ በአገር ውስጥ ከሚገኙ አስጎብኚ ድርጅቶች ጋር በማገናኘት የተሻለ የሥራ ዕድል እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኙ በርካታ ኢምባሲዎች ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ አውጥተውት የነበረውን ማስጠንቀቂያ አለማንሳትን በተመለከተ አቶ ስለሺ ሲያስረዱ፣ አገሮች በኢትዮጵያ ላይ የነበራቸውን የሰላም ጥርጣሬ እንዲቀይሩ ለማድረግ በኢትዮጵያ የሚገኙ አምባሳደሮችን ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ይዞ በመንቀሳቀስ ያለውን እውነታ እንዲረዱትና ለዜጎቻቸው እንዲያሳውቁ ተሠርቷል ብለዋል፡፡ በዚህም ፈረንሣይ፣ ቤልጂየምና ጀርመንን የመሳሰሉ አገሮች ያወጡት የጉዞ ማስጠንቀቂያ ረገብ እንዲል ማድረጋቸውን አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች