Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለተበላሹ ቀላል ባቡሮች ማስጠገኛ አንድ ቢሊዮን ብር በጀት ተያዘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የትራንስፖርት ታሪፍ ማሻሻያ ተደረገ

በብልሽት ምክንያት የትራንስፖርት አገልግሎት የማይሰጡ ቀላል ባቡሮችን ለማስጠገን፣ አንድ ቢሊዮን ብር በጀት መያዙን የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በመለዋወጫና በሌሎች ችግሮች ምክንያት ከ41 ቀላል ባቡሮች ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡት 18 ብቻ እንደሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት የጥገና በጀት መያዝ እንዳለበት ተገልጿል፡፡

ለተበላሹ ቀላል ባቡሮች ማስጠገኛ አንድ ቢሊዮን ብር በጀት መያዙን፣ የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው ይህንን የተናገሩት በተለያዩ ተሽከርካሪዎች የትራንስፖርት ታሪፍ ማሻሻያ መደረጉን በተመለከተ፣ ዓርብ ጥር 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡

እንደ አቶ ምትኩ ገለጻ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት የተለያዩ መለዋወጫዎችና ሌሎች በርካታ ችግሮች እንዳሉበትና በዚህም ሳቢያ አገልግሎት እየተሰጠ ያለው በ42 በመቶ አቅም ብቻ ነው፡፡

በዚህ መሠረት 23 ቀላል ባቡሮች የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የማይችሉ ሲሆኑ፣ ብልሽት ያልገጠማቸው 18 ባቡሮች ግን በቀን ከ56 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ተገልጋዮች አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን የቢሮ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

በአጠቃላይ የተለያዩ ችግሮች በገጠሟቸው በብልሽት ለቆሙ ቀላል ባቡሮች 60 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግም አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል በተለያዩ ከጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ታሪፍ ማሻሻያ ማድረጉን ቢሮው አስታውቋል፡፡

የታሪፍ ማሻሻያ የተደረገውም ለሚኒባስ ታክሲዎች፣ ለሚድ ባሶች (ሃይገርና ቅጥቅጥ)፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅትና ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የትራንስፖት አገልግሎት መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዚህም በሚኒባስ ታክሲ እስከ 2.5 ኪሎ ሜትር ሲከፍል የነበረው 3.50 ብር፣ ከጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ 4.00 ብር፣ ከ2.6 እስከ 5 ኪሎ ሜትር ሲከፈል የነበረው 6.50 ብር የነበረው ታሪፍ 7.00 ብር ሆኖ ተሸሽሏል፡፡

የሚኒባስ ታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች እስከ 30 ኪሎ ሜትር የጉዞ ርቀት አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን፣ በተለያዩ ኪሎ ሜትር ተከፋፍሎ እስከ 30 ኪሎ ሜትር ድረስ ሲከፈል የነበረው ነባር ታሪፍ ከ0.50 ሳንቲም እስከ 1.50 ብር የታሪፍ ማሻሻያ እንደተደረገበት ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

የሚድ ባስ (የሃይገርና ቅጥቅጥ) የትራንስፖርት አገልግሎት እስከ 28 ኪሎ ሜትር የጉዞ ርቀት አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን፣ ከትናንት ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ከ8 እስከ 12 ኪሎ ሜትር ሲከፈል የነበረው 7.50 ብር 8.00 ብር፣ ከ12 እስከ 16 ኪሎ ሜትር ሲከፈል የነበረው 9.50 ብር 10.00 ብር፣ ከ16 እስከ 20 ኪሎ ሜትር ሲከፈል የነበረው 12.00 ብር 13.00 ብር፣ ከ20 እስከ 24 ኪሎ ሜትር ሲከፈል የነበረው 14.50 ብር 15.00 ብር፣ እንዲሁም ከ24 እስከ 28 ኪሎ ሜትር ድረስ ሲከፈል የነበረው 17.00 ብር 18.00 ብር ሆኖ የታሪፍ ማስተካከያው እንደተደረገለት ተነግሯል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት እስከ 50 ኪሎ ሜትር የጉዞ ርቀት ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ ከአራት እስከ ስድስት ኪሎ ሜትር የነበረው 1.50 ብር 3.00 ብር፣ ከ6 እስከ 9 ኪሎ ሜትር 3.00 ብር 5.00 ብርና ሌሎችም እስከ 50 ኪሎ ሜትር የነበረው ታሪፍ እንደ ኪሎ ሜትሩ ርዝመትና እጥረት ከ1.00 እስከ 5.00 ብር ድረስ ታሪፍ ማሻሻያ እንደተደረገበት ቢሮው ጠቁሟል፡፡

ከቢሮው የተገኘው ሰነድ እንደሚያሳየው ከሆነ፣ እስከ 17 ኪሎ ሜትር የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጠው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር 4.00 ብር ነባር ክፍያ 7.00 ብር ተደርጓል፡፡

በተለይ ምሽት ላይ የታክሲ ሾፌሮች ከታሪፍ በላይ እንደሚያስከፍሉ ተሳፋሪዎች ሲያማርሩ ሲሆን፣ ከዚህ ጋር በተያያዘም ባለፈው ዓመት 33,289 ሾፌሮች እንደተቀጡ አዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አስታውሰዋል፡፡

‹‹ከ350 በላይ የቁጥጥር ሠራተኞች አሉ፤›› ያሉት ኃላፊው፣ ቢሮው ከታሪፍ በላይ በሚያስከፈሉ አሽከርካሪዎች ላይ ከዚህ በላይ ቁጥጥር እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች