Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናመንግሥት የገጠር መሬትን ለብድር መያዣ ማዋልና የጋራ መሬት ባለቤትነትን በሕግ ለመወሰን አቀደ

መንግሥት የገጠር መሬትን ለብድር መያዣ ማዋልና የጋራ መሬት ባለቤትነትን በሕግ ለመወሰን አቀደ

ቀን:

  • ዕቅዱ የገጠር መሬት ግብይት ሥርዓትን ይፈጥራል
  • የመሬት ንብረት ባለቤትነት መብትን ያቋቁማል

መንግሥት አገሪቱ ካላት ሰፊ የገጠር መሬት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማግኘት፣ የገጠር መሬት ግብይትን በሁለተኛው አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም የትግበራ ዘመን ለመፍቀድና የጋራ መሬት ባለቤትነትን በሕግ ለመወሰን ማቀዱ ተሰማ።

ሪፖርተር የተመለከተው ሁለተኛው አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም መርሐ ግብር ረቂቅ ሰነድ እንደሚያስረዳው፣ እስከ ዛሬ የተተገበረው የገጠር መሬት አጠቃቀም መብት ደካማና በግብርና ዘርፍ እሴት እንዳይፈጠር ማነቆ እንደሆነ ያመለክታል።

በመሆኑም የገጠር መሬት ሀብትን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለመመንዘር የሚያስችል የገጠር መሬት ግብይት ሥርዓትን ለመፍጠር በሁለተኛው አገር በቀል የኢኮኖሚ መርሐ ግብር ዘመን መታቀዱን ረቂቅ ሰነዱ አመልክቷል።

- Advertisement -

በዚህም መሠረት የጋራ መሬት ባለቤትነትን በሕግ ለመወሰን የታቀደ ሲሆን ከዚሁ ጎን ለጎንም የገጠር መሬት አስተዳደርና የመሬት አጠቃቀም አዋጅ (456/2005) ላይ ለውጥ ለማድረግ ታስቧል።

የሚደረገው ማሻሻያም የመሬት አጠቃቀም መብቶችን በማጠናከር የገጠር መሬትን በዋስትና በማስያዝ ብድር ማግኘት የሚቻልበትን አሠራር ለመዘርጋትና የጋራ መሬት ባለቤትነትን በሕግ ለመወሰን ያለመ እንደሆነ ሰነዱ ያመለክታል።

የግብርና ዘርፉ በፖሊሲም ሆነ በንግድ ባንኮች የገንዘብ ድጋፍ የማያገኝ፣ የኢንሹራንስ ሽፋኑም የተወሰነ መሆኑን ከግንዛቤ በመውሰድ በገጠር መሬት አጠቃቀም ላይ የሚደረገው የሕግ ማሻሻያ የግብርና ፋይናንስ ስትራቴጂዎችንና መሣሪያዎችን በተጓዳኝ ለመተግበር ታሳቢ አድርጓል።

በዚህም መሠረት የገጠር መሬት የግብይት ሥርዓትን፣ የኮንትራት ግብርና፣ የካፒታል ገበያ፣ የሊዝ ፋይናንሲንግ፣ የፕሮጀክት ፋይናንሲንግ፣ የመሳሰሉ አማራጭ የገንዘብ ድጋፎችን ዘርፉ እንዲያገኝ ለማድረግ ውጥን ተይዟል።

የገጠር መሬት ግብይት ሥርዓትን ለመዘርጋት የተያዘው ዕቅድ የገጠር መሬትን ለብድር ማስያዣነት እንዲውል ከመፍቀድ ባለፈ የመሬት ንብረት ባለቤትነት መብቶችን ሊፈቅድ እንደሚችል ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አንድ የመንግሥት የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል።

የመረጃ ምንጫችን እንደሚሉት የገጠር መሬት ግብይት ሥርዓትን ለመፍጠር የተያዘው ዕቅድ ወደፊት በሚወጣ ሕግ ሲዘረዘር፣ የረዥም ጊዜ የመሬት ንብረት ባለቤትነትን እንደሚፈቅድና ይህም የገጠር መሬት ባለይዞታ መሬቱን የመሸጥ የመለወጥና የባለቤትነት መብቱን የማስተላለፍ ዕድል ይሰጠዋል። 

የገጠር መሬትን ለብድር ማስያዣ እንዲውል ማድረግ ተብሎ በረቂቅ ሰነዱ በጥቅል የተቀመጠው አገላለጽ በጊዜ ወሰን የተገደበ የመሬት ንብረት ባለቤትነትን ያካተተ እንደሆነ ገልጸዋል።

የገጠር መሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ የታሰበው ለውጥ የመሬት ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች በመሬቱ ላይ የረዥም ጊዜ የባለቤትነት መብት (የመጠቀም ሕጋዊ ዋስትናን) አግኝተው፣ መሬቱን በዋስትና በማስያዝ በሚያገኙት ብድር የግብርና ልማት እንዲያከናውኑና ምርታማነታቸውን ከፍ እንዲያደርጉ ማገዝ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ዓላማ እንደሆነ አስረድተዋል።

አንድ የገጠር መሬት ባለይዞታ መሬቱን አስይዞ ለመበደር የሚችለው የተረጋገጠ በመሬቱ ላይ የረዥም ጊዜ የባለቤትነት መብት ሲኖረው እንደሆነ የገለጹት እኘሁ ምንጫችን፣ የፋይናንስ ተቋማትም መሬት ይዘው ማበደር የሚችሉት ይህ መብት መኖሩን ሲያረጋግጡ እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚህ መንገድ መሬቱን በማስያዣነት አቅርቦ የሚበደር አርሶ አደር ብድሩን መክፈል ባይችል በመሬቱ ላይ የነበረው የባለቤትነት መብት ለአበዳሪው የፋይናንስ ተቋም እንደሚተላለፍ፣ ይህም የገጠር መሬት የግብይት ሥርዓትን እንደሚፈጥር አስረድተዋል። ይህ የባለቤትነት መብት በመሬቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በመሬቱ ላይ የሚገኝ ሀብትን እንደሚጨምርም ገልጸዋል።

አጠቃላይ ሁኔታው በሊዝ አዋጅ አማካኝነት በተከማ መሬት ላይ ከሚቋቋመው የረጅም ጊዜ የባለቤትነት ወይም የመጠቀም መብት ጋር ተቀራራቢ እንደሆነ የገለጹት ምንጫችን፣ በሊዝ አዋጅ አማክኝነት የከተማ መሬት ላይ የሚፈጠር መብትን መሸጥ፣ መለወጥ፣ ወይም ማስተላለፍ እንደሚቻለው ሁሉ በገጠር መሬት ላይም አርሶ አደሮች ተመሳሳይ መብት እንዲያገኙ በማድረግ ምርታማነትን ለመጨመር መታቀዱን አስረድተዋል።

በገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅን በማሻሻል የገጠር መሬት የግብይት ሥርዓትን ለመዘርጋት የተያዘው ውጥን በጥንቃቄ የሚፈጸም እንደሆነ የገለጹት ምንጫችን፣ ያልተገባ የመሬት መቀራመትና ግጭት እንዳይፈጠር የእያንዳንዱ አርሶ አደርን መሬት የወሰን ዳርቻና መጠን ለይቶ በመመዝገብ የይዞታ ማረጋገጫ እንዲረው የሚደረግ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም የጋራ መሬት ባለቤትነትን በሕግ በመወሰን ያልተገባ የመሬት መቀራመትን የመቆጣጠርና ከገጠር መሬት ግብይት ውጪ የሚሆኑና ለጋራ ጥቅም የሚያገለግሉ ይዞታዎች እንደሚለዩ አስረድተዋል።

በታቀደው የሕግ ማሻሻያ አርሶ አደሩ በገጠር መሬት ላይ የረዥም ጊዜ ባለቤትነት ወይም የመጠቀም መብት አግኝቶ መሬቱን በማስያዝ መበደር፣ እንዲሁም መሸጥ፣ መለወጥና ማስተላለፍ እንዲችል ማድረግ የተፈለገበት ዋና ምክንያት ምርታማነትን ማሳደግና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንዲሁም የመሬትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አሟጦ ለመጠቀም ብቻ እንደሆነ ምንጫችን ገልጸዋል።

በመሆኑም የታሰበው ማሻሻያ ‹‹መሬት የማን እንደሆነ›› ከሚወስነው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ጋር አንደማይቃረን ገልጸዋል።

ከጥቂት ወራት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ፣ የአገሪቱ የመሬት ስሪት ማስተካከያ ያስፈልገዋል ብለው በግል እንደሚያምኑና ቢያንስ በተከሞች መሬትን የግል ማድረግ ሊጠቅም እንደሚችል መግለጻቸው ይታወሳል። 

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር “The Evolving Question of Land in Ethiopia” በሚል ርዕስ በሚያዚያ 2014 ባሳተመው ጥናት አሁን ያለው የገጠር መሬት የባለቤትነት መብት ሥርዓት የገጠሩ ሕዝብ በመሬት ላይ የሚገኝ ንብረቱን እንዳያስተላልፍ፣ መሬት እንዳይከራይ፣ በመሬት ላይ ያለውን ንብረት ለዋስትና ወይም ብድር እንዳይጠቀምና በአጠቃላይ የመሬት ንብረቱን ለንግድ በሚመች መልኩ እንዳያስተላልፍ የሚገድብ በመሆኑ የግብርና ምርታነማነትን አዳዳከመ አመለክቷል።

በመፍትሔነትም የኢትዮጵያ መንግሥት አፋጣኝ የመሬት ንብረት መብት ፖሊሲዎችን በመቅረጽ፣ የረዥም ጊዜ የኢንቨስትመንት ዋስትና በመስጠት ምርትና ምርታማነትን ማጎልበት እንዳለበት ይመክራል። ይህ ካልሆነ ግን አሁን ባለው ዝቅተኛ ምርታማነት በፍጥነት በማደግ ላይ ያለውን ሕዝብ የምግብ ፍላጎት ማሟላት እንደማይቻል ያሳስባል።

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ፣ ሁለተኛው አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም ረቂቅ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በረቂቅ የኢኮኖሚ ፕሮግራም ሰነዱ ላይ ብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ እየተነጋገረበት መሆኑን ጠቅሰው በቅርቡም ለውይይት ይፋ ተደርጎ ከግሉ ዘርፍና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ግብዓት ከተሰበሰበ በኋላ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚያገኝ ጠቁመዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...