Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትክለቦች የፈቃድ አሰጣጥ መመርያውን ለምን ችላ አሉት?

ክለቦች የፈቃድ አሰጣጥ መመርያውን ለምን ችላ አሉት?

ቀን:

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር በተለይ የክለቦች የፈቃድ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ መሠረታዊ ችግር እንዳለና የእግር ኳሱ ዋነኛ ማነቆ ሆኖ መሰንበቱን ባስጠናው ጥናት ላይ ተገልጿል፡፡

ጥናቱን ለማሰናዳት ከ90 ባለድርሻ አካላት ጋር ቆይታ ማድረጋቸውን  የጥናቱ አቅራቢ የፌስ ኮርነር አማካሪ ጋሻው አብዛ (ዶ/ር) ገልጸው፣ በዚህም የባለድርሻ አካላቱ በተለይ ከክለብ ፈቃድ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ እንቅፋት ሲሆንባቸው የዘለቀውን ጉዳይና በመመርያ አሰጣጥ ዙሪያ ስላላቸው ዕይታ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

የክለብ ፈቃድ አሰጣጥ መመርያ በእግር ኳሱ የላቀ ዕድገት ካሳዩት የአውሮፓ ሊጎች ጀምሮ፣ በተለያዩ አኅጉሮች ተተግብሮ እንደሚገኘ ያስቀምጣል፡፡ ካፍም እንዲሁም ከፊፋ አንድ መመርያውን ተቀብሎ ከአኅጉሩ ጋር በሚጣጣም መልኩ አዘጋጅቶ ለአባል አገሮቹ አቅርቧል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለዚህ መመርያ ተገዥ መሆኑን በመተዳደሪያ ደንቡ የገለጸ ቢሆንም፣ በጥናቱ ከተሳተፉ የእግር ኳሱ ቀጥተኛ የባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገው ቃለ ምልልስ እንደተመለከተው ለረዥም ጊዜ ፌዴሬሽኑ የማስታመም ሥራ ላይ እንደቆየና መመርያውን ለማስፈጸም ‹‹ቁርጠኝነት›› የተሞላበት አመራር መጥፋቱ (በሁሉም ተሳታፊዎች በሚባል ደረጃ) ተነስቷል።

 በፊፋና በካፍ የተቀመጡትን መሥፈርቶች እንዲያሟሉ በመጠየቅ በኩል ብዙ መጓዝ እንደሚጠበቅም ተሳታፊዎች በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

በፈቃድ አሰጣጡ ትግበራ ላይ ጥብቅ ዕርምጃ ላለመወሰዱ ምክንያቶች እንደሆኑ በተወሰኑ ተሳታፊዎች ከተገለጹት መካከል አንዱ አገር ወክለው በካፍ የክለብ ውድድሮች ለመሳተፍ ያለፉ ክለቦችን ማገድ ብሔራዊ ጥቅምን ይጎዳል መባሉ ነው፡፡ ሌላው ክለቦች መሥፈርቶቹን አለማሟላታቸውን ሲነገራቸው ከየአካባቢው ከፍተኛ ባለሥልጣናት በግል ቀርበው በቀጣይ እንደሚያሟሉ ቃል መግባታቸውና መማፀናቸው ነው፡፡ የክለብ ላይሰንሲንግን በሚመለክት እስካሁን በተሰጡት የግንዛቤ ማስጨበጫ ዐውደ ጥናቶች የተካፈሉት ግለሰቦች የሚመለከታቸውና ውሳኔ ሰጪ አካላት አለመሆናቸውም ተጠቅሷል።

ሌላው የግንዛቤ እጥረት ሲሆን፣ ይህም በክለቦች አመራር እንዲሁም አስተዳደር ዘንድ መመርያውን በአግባቡ ያለመረዳት የግንዛቤ ችግር መኖሩን የጥናቱ ተሳታፊዎች በስፋት አውስተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ከፍተኛውን የመሥፈርት ደረጃ እንደ አስገዳጅ የማየት የተሳሳተ ዝንባሌ፣ የተዛነፈ የስታዲየም ደረጃና የስታዲየም የባለቤትነት ይዞታ አረዳድ፣ ስታዲየሞች መጠነኛና ለእግር ኳስ ተብለው መገንባት (ለምሳሌ 10 ሺሕ) እንደሚችሉ አለመረዳት፣ ስታዲየሞች በባለቤትነት ሳይሆን በኪራይ ወይም በሊዝ ሊያዙ እንደሚችሉ አለማየት፣ የሕክምና፣ ፊዚዮቴራፒ፣ የምግብ ባለሙያ፣ ወዘተ ያሉ ባለሙያዎችን በኮንትራት መቅጠር እንደሚቻል አለመገንዘብ የሚሉ ክፍተቶች እንዳሉ በተሳታፊዎች ተነስተዋል።

‹‹ፈቃድ የመስጠት ሥራው መጀመር ያለበት ከአስተሳሰብና ከግንዛቤ ለውጥ ጋር ነው። ክለቦች ውድድር ላይ ብቻ አተኩረው፣ ከዕይታቸው ወጥተው ወደ ልማት አስተሳሰብ ሊመለሱ ይገባል፤›› በማለት በጥናቱ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ባለድርሻ አካላት ይነገራሉ፡፡

የጥናቱ አስተያየት ሰጪ ሲቀጥል፣ ‹‹የኢትዮጵያን የስፖርት ሕግ በደንብ ላስተዋለው፣ የመንግሥት ሚና ላይሰንሲጉ ላይ የተቀመጡትን ነገሮች ማሟላት ነው እንጂ የተጫዋቾቹን ደመወዝ መክፈል አይደለም፤›› በማለት ሐሳቡን አጋርቷል፡፡

ሌላው ባለድርሻ አካል አስተያየቱን ሲያስቀምጥ፣ መመርያው ሦስት የተለያዩ ደረጃዎች እንዳሉትና የመጀመሪያውን ደረጃ ለማሟላት የሚያስችል ቁመና የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች እንዳላቸው ብዙዎች አለመረዳታቸውን ጠቅሶ፣ ይህንን ለየክለባቱ ውሳኔ ሰጪዎች የሚያስረዳና ቁርጠኛ አመራር መጥፋቱን ይገልጻል፡፡

ከቁርጠኝነት ዕጦት ጋር በተያያዘ አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን በፊፋ፣ በካፍና በብሔራዊ ደረጃ የተቀመጠ መመርያ ቢኖርም፣ ከዚያ ባሻገርም ፊፋ ሊያደርግ በሚችለው ድንገተኛ ፍተሻ፣ ክለቦች አሟልተው ሳይገኙ ቢቀር ሊከተል የሚችለውን ዕርምጃ እንዳለ ሆኖ፣ መመርያው የክለባቱ የዕድገት ቁልፍ መሆኑን ተረድቶ፣ ለተግባራዊነቱ ቁርጠኝነት መጥፋቱ በርካታ ተሳታፊዎች እንግዳና እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው ይነገራል፡፡

 የፊፋ የክለብ ፈቃድ መመርያ፣ አንቀጽ 11 ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች፣ ኮንፌዴሬሽኖች የሚያሳልፉትን የክለብ ፈቃድ አሰጣጥ መመርያን ወሰደው እንዲያስፈጽሙ የሚጠይቅ በአንቀጽ 12 ላይ እንደተቀመጠ ያትታል፡፡

 ፊፋም ሆነ ካፍ ድንገተኛ ምርመራ እንደሚያደርጉ፣ ድንገተኛ ምርመራ ተደርጎ ለፊፋ መቅረብ እንዳለበት፣ አንድ አባል ፌዴሬሽን ከቀረፀው የፈቃድ አሰጣጥ መመርያ ጋር በማይጣጣም ሁኔታ ፈቃድ ሰጥቶ ከተገኘ በፊፋ የዲሲፕሊን ኮሚቴ በኮንፌዴሬሽኑ ደንቡ መሠረት ቅጣት እንደሚጣልበት ይገልጻል።

የመመርያውን መሥፈርቶች በሟማላትም ሆነ በማስፈጸም ረገድ ያለው ተነሳሽነት አናሳ መሆንን በሚመለከት፣ ሰፊ አስተያየት በጥናቱ በተሳተፉ የባለድርሻ አካላት ተነስቷል፡፡

በጥናቱ አስገዳጅ መሥፈርቶቹ መቀመጥ እንደሚገባቸው የተነሳ ሲሆን፣ አስገዳጅ ከማድረግ ጎን ለጎን ፕሪሚየር ሊጉ ሊያጋጥመው የሚችላቸው የተለያዩ ፈተናዎች እንደሚኖሩ በተሳታፊዎች ጠቅሰው፣ የተወሰኑ መሥፈርቶችን በጊዜ ሒደት የሚያሟሉ ክለቦችን ይዞ መንቀሳቀሱ ተመራጭ እንደሆነ ተነስቷል፡፡

 በዚህም መሠረት ለውጥ እንዲመጣ ካስፈለገ የሊግ ኮሚቴው አመራር መሥፈርቶቹን የሚያሟሉትን ብቻ በማወዳደር፣ ሌሎቹ አሟልተው እስኪመጡ በመቀነስ፣ ከብዛት ጥራትን አስቀድሞ አስገዳጅ ደንቦች በማውጣት ለለውጥ መዘጋጀት የሚል ምክረ ሐሳብ ቀርቧል፡፡

በአጠቃላይ የተሰባሰቡት መረጃዎችና ማስረጃዎች፣ የገዥ ሕጋዊ ሰነዶች፣ የክለባቱ ነባራዊ ሁኔታና የባለድርሻ አካላት ዕይታ ያቀረቡት ጭብጦችና ግኝቶች የሚያመላክቱት ኃላፊነት የሚሰማው አካል አፋጣኝ ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበት የጥናቱ ባለድርሻ አካላት አንስተዋል፡፡ በተለይ ከዓለም አቀፍ እስከ አገር አቀፍ ያሉት ገዥ ሕግጋትን በተጠያቂነት ማስፈጸም እንደሚገባ ተነስቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...