Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ማደያዎች መንግሥት ከሚያወጣው ታሪፍ በላይ የሚሸጡት ክልሎች የቤት ሥራቸውን በሚገባ ስላልተወጡ ነው›› ወ/ሮ ሳህረላ አብዱላሂ፣ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር

የቆይታ አምድ እንግዳችን የኅብረተሰብ ጤና ሳይንስ ምሩቅ ናቸው፡፡ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ሆነው ለአራት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ አሁን ደግሞ እንደ አዲስ የተዋቀረውን የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣንን በዋና ዳይሬክተርነት እየመሩ ናቸው፡፡ ወ/ሮ ሳህረላ አብዱላሂ፡፡ ወ/ሮ ሳህረላ ወደ ነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ከመጡ በኋላ መንግሥት በነዳጅ ዘርፍ ላይ የታለመለት ድጎማ መጀመርን ጨምሮ በርካታ አዳዲስ ነገሮች ተከስተዋል፡፡ ባለሥልጣኑ እየሠራቸው ስላሉ ሥራዎች፣ በዘርፉ ላይ እያጋጠሙ ስለሚገኙ ሕገወጥ ተግባራት፣ ስለነዳጅ ንግድና ምርቱ በአገርና በኅብረተሰቡ ላይ ስላሳደረው ጫና አስመልክቶ ሳሙኤል ቦጋለ ከወ/ሮ ሳህረላ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር– በዚህ ወቅት ለም ላይ የነዳጅ ዘርፍ ብዙ ትኩረት የሚበዛበትና እረፍት ሊሰጥ የሚችል አልሆነም። እርሶ ይህንን ዘርፍ በኢትጵያ በበላይነት መምራትን እንዴት አገኙት? አስቸጋሪ አልሆነብዎትም?

ወ/ሮ ሳህረላ፡- የእኔ መሠረት በሌላ ዘርፍ ላይ ነበር፣ በዚያ ላይ የነዳጅ ዘርፍም እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው። ወደኋላ ተከማችተው የነበሩ ብዙ ክፍተቶችና ውጥንቅጦች የበዙበት ዘርፍ ነው። ስመጣ ፍርሃት አድሮብኝ ነበር፣ ነገር ግን በኋላ ትንሽ ሥራዎች ብሠራ ኅብረተሰቡ ሊጠቀም የሚችለውን በማሰብ አሁን ላይ ደስ ብሎኝ ነው የምሠራው። ወቅቱን በሚመለከት ፈተናው ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ። በፊት የጤና ሚኒስትር ደኤታ በነበርኩበት ጊዜም የኮቪድ ወረርሽኝ የነበረበትና ፈታኝ ወቅት ነበር። ወደዚህ ስመጣ ለአንድ ሳምንት ቁጭ ብዬ ማሰብ በማልችልበት ሁኔታ ነው ወደ ሥራው የገባሁት፣ ተረጋግቶ ሥራውን የማወቅና የመምራት ዕድሉን አላገኘሁም ነበር። አሁን በፈተና ውስጥ እየተማርኩ መጥቼ ዘርፉን አውቄዋለሁ ብዬ አስባለሁ።

ሪፖርተርነዳጅ በበርካታ አገሮች ላይ ያለው የፖለቲካናኢኮኖሚ ተፅዕኖ ትልቅ ነው፡፡ ሆኖም እርስዎ የዚህን ዘርፍ እንደመምራትዎ ኢትዮጵያ ላይ ያለውን ተፅዕኖ እንዴት ያዩታል?

ወ/ሮ ሳህረላ፡- ከረዥም ጊዜ ጀምሮ እኛ አገር ነዳጅ የሚቀርበው በመንግሥት ነው፡፡ እንደ ጎረቤታችን ኬንያ ያሉ አንዳንድ አገሮች አብዛኛውን የማስገባቱን ሥራ ወደ ግል ዘርፉ ይወስዱና መንግሥቶቻቸው የተወሰነውን ድርሻ ይወጣሉ፡፡ በኬንያ መንግሥት 30 በመቶውንና የግሉ ዘርፍ 70 በመቶውን ነዳጅ ወደ አገራቸው ያስገባሉ፡፡ የሚገዛበትን ዋጋና አጠቃላይ የዋጋ ወርሐዊ ክለሳቸውን በእርግጥ መንግሥቶቻቸው ይወስናሉ፡፡ እስካሁን በነበረው ታሪክ በኢትዮጵያ መንግሥት ነው ሙሉ ለሙሉ ወጪውን፣ የውጭ ምንዛሪውንና ከምንገዛበት አገሮች ጋር ድርድር አድርጎ በብድር እያመጣ ያለው።

በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታም ነዳጅ እጅግ ፖለቲካዊና ስትራቴጂያዊ ምርት ነው። ከቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ጀምሮ የድጎማ ሥርዓቶች ነበሩ ኅብረተሰቡ እንዳይጎዳ በሚል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የነዳጀ መሸጫ ዋጋ የዓለም ገበያን የተከተለ አልነበረም። በዚህም የመንግሥት የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ እየተከማቸ መጥቶ፣ በ2013 እና በ2014 ዓ.ም. መጀመርያ ላይ መንግሥት ላይ የመጣው የማረጋጊያ ፈንድ ጉድለት በጣም እየሰፋ መጣ። ዓለም ላይ የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ መምጣት በየወሩ የሚደርሰው ጉድለትና መንግሥት የሚሞላው ከአሥር እስከ 15 ቢሊዮን መሆን ቻለ፡፡ በአሁን ጊዜ የዚህ የማረጋጊያ ፈንድ ዕዳ 187 ቢሊዮን ደርሷል። ከ2014 ዓ.ም. ሐምሌ ወር ጀምሮ ድጎማው ባይጀመር ሊመጣ የሚችለው ጉድለት ትልቅ ነበር።

ሪፖርተር– የታለመለት ድጎማ ከመጀመሩ በፊት መንግሥት ላይ የነበረው ጫና አሁንለው ጋር ልዩነቱ ምን ያህል እየጠበበ መጣ?

ወ/ሮ ሳህረላ፡- የታለመለት ድጎማው የተጀመረ ጊዜ በዓለም ላይ የነበረው የነዳጅ ዋጋና በኢትዮጵያ ይሸጥ የነበረው ዋጋ ልዩነት በአንድ ሊትር ወደ 40 ብር ደርሶ ነበር፡፡ በውጭ ምንዛሪ የሚገባው የነዳጅ ዋጋ ልዩነት እየሰፋ በመምጣቱ ተመልሶ ወደ ጎረቤት አገሮች በሕገወጥ መንገድ ይወጣ ነበር፡፡ ወደ አገር ውስጥ ምርት የምናስገባበት ጂቡቲን ጨምሮ ጎረቤት አገሮች ወደብ እያላቸውም ከእኛ አገር ወደ እነሱ ይሄዳል፡፡ ድጎማውን የማንሳት ዓላማዎች ይህን ሕገወጥ ንግድ ማስቀረት አንደኛው ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ መንግሥት ላይ እየተከማቸ የሚመጣውን ዕዳ ቀስ በቀስ እየቀነሱ መምጣት ነው፡፡

በ2014 ዓ.ም. ሰኔ ወር ላይ የነበረው የ15 ቢሊዮን ብር የወር ድጎማ ዕዳ አሁን በወር ወደ ሦስት ቢሊዮን ዝቅ ብሏል፡፡ ይህ ድጎማው ከመጀመሩ አንድ ወር በፊት በማረጋጊያ ፈንዱ ላይ የነበረው የወር 15 ቢሊዮን ብር ዕዳ በተደረጉት የታለመለት ድጎማ ዋጋ ማሻሻያዎች አሁን በወር ወደ ሰባት፣ አምስትና ሦስት ቢሊዮን ብር ወርዷል፡፡ ከጎረቤት አገሮች ጋርም ያለው የዋጋ ልዩነት አሁን እየጠበበ መጥቶ ትንሽ ከኬንያ ጋር ያለው ልዩነት ነው ሕገወጥ ንግዱን ሊያባብስ የሚችለው፡፡ በአሁን ጊዜም ቢሆን ከኬንያ ጋር በአንድ ሊትር ሰፊ የብር ልዩነት ነው ያለን፡፡

ሪፖርተር፡– እንደ ኬንያ በኢትዮጵያ ለምን የግል ኩባንያዎች ነዳጅ እንዲያቀርቡ አይፈድም? አሠራሩን ለመቀየርስ ሐሳብ አለ?

ወ/ሮ ሳህረላ፡- አሁን እንደ አገር ሐሳብ የለም፡፡ እናድርግ ብንል ያው መንግሥት ለሚያስመጡት የውጭ ምንዛሪ መመደብ ሊኖርበት ነው ማለት ነው፡፡ እነ ኬንያ የውጭ ምንዛሪ ችግር ስለሌለባቸው ግለሰቦች ያስገቡታል፡፡ እንደዚያ በራሳቸው አምጥተው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሸጡ ቢደረግ ደግም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፣ ምክንያቱም በፍራንኮ ቫሉታ ላይ የታየው ነው የሚሆነው፡፡ ፍራንኮ ቫሉታ መፈቀዱ እንደሚታወቀው በተለያዩ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ልዩነቶች አምጥቷል፡፡ የአገር ኢኮኖሚ ቀውስ ስለሚፈጥር መቼ መሆን እንዳለበት በደንብ ተጠንቶ ነው የሚሆነው፡፡ ፍራንኮ ቫሉታ በዘይትና ስኳር ዓይነት ሸቀጦች ላይ ያመጣውን ጫጫታ እያወቅን እሱን ነዳጅ ላይ መድገም በጣም ይከብዳል፡፡ በሒደት ግን አገር እያደገች ስትሄድና ኢኮኖሚው ሲስተካከል ለግሎች ሊፈቅድ ይችላል።

ሪፖርተር የነዳጅ ሽያጭ ላይ የተጣለው የታክስ አሰባሰብ ሒደት እንዴት እየሄደ ነው?

ወ/ሮ ሳህረላ፡- እንደሚታወቀው እንደ ሌላው ምርት ነዳጅ ላይ ታክስም ቫትም አይጣልም ነበር፡፡ ዋጋ ግንባታው ላይ እንዲገባ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከተወሰነ ጀምሮ በየጊዜው በሚደረጉ አሰባሰቦች በ25 በመቶ አድገው አሁን ሦስተኛው የታለመለት ነዳጅ ድጎማ ዋጋ ማስተካከያ ሲደረግ 75 በመቶ ሆኗል፡፡ እስከ ኅዳር 30 ቀን ድረስ የነበረን የተሰበሰበ ታክስ ወደ አምስት ቢሊዮን ደርሷል፡፡ ከዚህ ቀደም ዋጋ ግንባታውም ላይ አይካተትም ነበር እስከ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ድረስ፡፡ የታለመለት ድጎማ አካሄድም ያንን ተከትሎ እንዲሄድና አሰባሰቡም በየዙሩ 25 በመቶ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ከእነዚህ ማሻሻያዎች ባሻገር ነዳጅ ስትራቴጂያዊና ፖለቲካዊ ምርት መሆኑን ኅብረተሰቡ አይረዳውም፡፡ በኅብረተሰቡ በኩል የቁጠባ ባህላችን እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ በጣም ብክነት ያለበት ምርት ነው፡፡ ማኅበረሰቡ የሚጠቀመው በትናንሽ ኮዳዎችና መሰል ዕቃዎች እየቀዳ ነው፡፡

ሪፖርተርእጥረት አይደለም እንዴት ይህን የሚያስከትለው? በማደያዎች ነዳጁን ካገኘ ኅብረተሰቡ ለምንስ በኮዳ ይቀዳል?

ወ/ሮ ሳህረላ እጥረት አይደለም፡፡ ያልተፈለገ ትርፍ ለማግኝት ሲባል የሚደረጉ ድርጊቶች እንጂ አጥሮ አይደለም። ለምሳሌ አንድ ሙሉ ቦቴ መኪና ለምሥራቅ አካባቢ ተቀድቶለት መንገድ ስቼ ነው ብሎ አርባ ምንጭ ይዘነዋል፡፡ ቢሳካለት በኮንሶ አድርጎ ኬንያ ለመሸጥ ነው ፍላጎቱ፡፡ ኮንሶ ላይ በአሁን ጊዜ ከፍተኛ የሆነ ሕገወጥ ግብይት አለ፡፡ እኛ ናፍጣ 67 ብር እንሸጣለን ኬንያ 86 ብር ደርሷል በሊትር፡፡ አሁንም የሚያጓጓና ለኮንትሮባንዱ ከፍተኛ ልዩነቶች አሉ።

ሪፖርተር– በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የነዳጅ አቅርቦትና ፍላጎት ይመጣጠናል?

ወ/ሮ ሳህረላ በየቀኑ በእያንዳንዱ አካባቢ የሚጫነው የቤንዚንና ናፍጣ መጠን ይታወቃል፡፡ ለክልሎችም መረጃ ይደርሳቸዋል፣ እዚህም መረጃ ይኖራል፡፡ የአቅርቦት እጥረት የለም፡፡ ችግሩ ያለችዋን ነዳጅ በአግባቡ ባለመሸጡ ነው፡፡ በአግባቡ ቢሸጥ ለሌላውም መዳረስ ይችላል፡፡ የሶማሌ ክልልና ከፊል ኦሮሚያ ኮታ የተጣለባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የኮንትሮባንድ ንግድ ስላለ አንዴ ከተጫነ እንደፈለጉ ማዘዝ አይችሉም፡፡ ሌሎቹ ጋር ግን ነፃ  ገበያ ስለሆነ በማንኛውም ጊዜ ማዘዝና የከፈሉበትን ነዳጅ ማግኘት ይችላሉ፡፡

ሪፖርተርአሁን ያለው የአቅርቦትና ፍላጎት መጠን ምን ያህል ነው?

ወ/ሮ ሳህረላ፡- በቀን ወደ 9.2 ወይም አሥር ሚሊዮን ሊትር ናፍጣ ይገባል ናፍጣ ላይ ፍላጎቱም ያን ያህል ስለሆነ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን ብዙም አይታይም፡፡ ቤንዚን ደግሞ 2.4 ሚሊዮን ሊትር በቀን እንዲገባ ይጠበቃል፣ ነገር ግን የሚቀርበው ላይ ልዩነቶች አሉ፡፡ እንደየቀኑ ልዩነት 2.2፣ ሁለት፣ አንዳንዴም 1.9 ሚሊዮን ሊትር በቀን ሊገባ ይችላል፡፡ እንደ አገር ተጠቃሚነታችን ናፍጣ ላይ ስለሆነ ካለን ፍላጎት አንፃር ብዙም ልዩነቶች አይታዩም፡፡

ሪፖርተርሙሉ የቤንዚን ፍላጎትን 2.4 ሚሊዮን (ሊትር) ለምን ማቅረብ አልተቻለም?

ወ/ሮ ሳህረላ፡- በአቅርቦቱ በኩል የተወሰኑ ከሎጂስቲክስ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች አሉ፡፡

ሪፖርተርበደቡብ አካባቢ በጣም እጥረት እንዳለ ነው የሚነገረውዋጋውም እጅግ ውድ ነው እዚያ አካባቢ ለምንድን ነው?

ወ/ሮ ሳህረላ፡- ሕገወጥ ግብይቱ ወደዚያ አካባቢ ሳቢ እየሆነ ነው የመጣው፡፡ በጣም የተቸገርነው ከሌላ አካባቢ እየመጡ የፀጥታ መዋቅሩን በተለይ በመደለል በበርሜልና በጀሪካን ይዘው ለማለፍ በሚሞክሩት ነው፡፡ ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋርም አብረን ስንሠራ እንደሚነግሩን ወደ ኮንሶና ዲላ መስመር ላይ ያለው ሁኔታ ባልተለመደ መልኩ እንደጨመረ አንስተዋል፡፡ ክልሎችም ቢሆኑ የሚገባውን ነዳጅ በሥርዓት እንዲሸጥ ተቆጣጥረው ተፅዕኖ ማሳደር ላይ ክፍተት አለባቸው። ማደያዎች መንግሥት ከሚያወጣው ታሪፍ በላይ ሲሸጡ ሲታይ ክልሎች በደንብ የቤት ሥራቸውን ስላልተወጡ ነው። እኛም በደንብ የተቸገርንበት ጉዳይ ነው፡፡ እኛ የማድረስ አቅማችን ውስን ነው፡፡ በየጊዜው የሚገኙትን ግኝቶች የክልል መንግሥታት ደግፈውት አብረው አግዘውን ሊሄዱ አልቻሉም፡፡ ሐዋሳ ከተማ ላይ ቤንዚን ከሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ጋር በሱቅ ውስጥ አብሮ ይሸጣል፡፡ ነገር ግን ቤንዚንን ከሸቀጦች ጋር በሱቅ ውስጥ መሸጥ ክልክል ነው፡፡ ተቀጣጣይ ስለሆነ አደገኛ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን ከላይ እስከ ታች ያለው መዋቅር ደግፎት ካልሄደ አሁንም ችግሩ በዘላቂነት ይቀረፋል የሚል እምነት የለኝም፡፡

ነዳጅ ከቦቴዎች ማደያዎች ላይ ሄደው ስለመራገፋቸው በማኑዋል ቢሆንም ይረጋገጣል፡፡ ጂቡቲም ላይ ቦቴዎች የተረካከቡበትን እንዲያሳዩ ይገደዳሉ፡፡ አሠራሩ የተወሰኑ መንገጫገጮች ገጥመውት ከክልል ክልል አፈጻጸሙ ጉራማይሌ ሆኗል፡፡ ማረጋገጫ ካልያዙ ነዳጅ ስለማይጫንላቸው ተመልሶ ነዳጅ መጫን ላይ ክፍተት ስለነበረበት አሠራሩን ለቀቅ አድርገዋል፡፡

ሪፖርተርበአዲስ አበባ በታኅሳስ ወር መጨረሻ ላይ ተፈጥሮ የነበረው የነዳጅ እጥረት ምክንያት ምን ነበር?

ወ/ሮ ሳህረላ አዲስ አበባ ላይ የነበሩ ሠልፎች ከዋጋ ጋር በተያያዘ እንዳይብሱ ከሱሉልታ ዴፖ ነበር ለማደያዎች ሲጫንላቸው የነበረው፡፡ ጂቡቲ እንኳን ርቀት እንዳይሄዱ ነበር የሆነው፡፡ ነገር ግን የእኛ ቡድን ባደረገው ማጣራት አንዳንድ ቦቴዎች ከሱሉልታ ጭነው ማደያዎች ላይ ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡ ቦቴዎቹ የት እንደገቡ አላውቅም ግን ማጣራት ያስፈልጋል፡፡ አንዳንዶቹ ክልክል የነበረው አሠራር ጥሰው ከኩባንያ ሌላ ኩባንያ የተራገፉ አሉ፡፡ እንደ ምሳሌ ብናነሳ ለኖክ የተጫነን ነዳጅ በቶታል ማደያ ማራገፍ ማለት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የተገኙት ኩባንያዎች ማብራሪያ እንዲሰጡበት ተጠይቀዋል፡፡ በዚህ ዓይነቶች ችግሮች ላይ ተገኝተው የነበሩት 14 የሚሆኑ ማደያዎችና ስድስት ኩባንያዎች ናቸው፡፡ አንደኛው ለሌላኛው ተገልብጦ መገኘትና የመጣውም ነዳጅ በማደያው ሳይገኝ ቢቀር ታይተው የነበሩት ችግሮች በተመሳሳይ ደግሞ ተረካክበናል የሚል ሰነድ መገኘቱ ነበር፡፡ ይህ የበለጠ ምርመራ የሚያስፈልገው ነው፡፡ አንድ ያገኘነው ኩባንያ ለምሳሌ ከሱሉልታ ሦስት ቦቴዎች ለአንደኛው ማደያ ተጭኖለት እኛ ጋር የመጫኛ ሪፖርት መጣ፡፡ በማደያው ላይ ግን ሦስቱም ቦቴዎች የሉም ነበር፡፡ አሁን ይህ ነዳጅ የት ገባ የሚለውን መነጋገር ያስፈልገናል፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ትክክለኛ ያልሆኑ የስምሪት ሰነዶች በቅጂ ተመሳስለው ተሠርተው ዓይተናል፡፡ እኛም በደንብ ማጣራት ይኖርብናል፡፡

ሪፖርተር፡– የእነዚህ ችግሮች በተደጋጋሚ መፈጠር ግን ባለሥልጣኑ ከንግድ ቢሮዎች ጋር በመሆን ሲዘረጋ የነበረውንና ሌሎች አዳዲስራሮች መዘርጋት አለመሳካት አያሳዩም?

ወ/ሮ ሳህረላ፡- ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት የክልሎች ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡ የፌደራል መንግሥቱ ውስን ቦታዎች ላይ ስላለ የክልሎች ተሳትፎ እጅግ ያስፈልጋል፡፡ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ድጎማው ሲጀመር የነበረው ሞቅታ ጥሩ ነበር። እስከ ጥቅምት መጨረሻ ጥሩ ሆኖ ከዚያ በኋላ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ የተወሰኑ መንገጫገጮች አሉበት፡፡ እኛ ታኅሳስ መጨረሻ ላይ አዲስ አበባ ውስጥ ያየናቸው ቦታዎች በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ መታየት ነበረባቸው ግን ይህ አልተደረገም፡፡ ከተሽከርካሪዎች ጋር በተያያዘ ካሉን 3,700 የነዳጅ አመላላሽ ቦቴዎች ውስጥ 1,500 የሚሆኑት ጂፒኤስ (GPS) ተገጥሞላቸው መከታተል ተጀምሯል፡፡ ሌሉቹንም የመግጠም ሥራን ሠርተው በቀጣይ ሳምንታት ይጠናቀቃሉ፡፡ የመጨረሻው ቀን እስከ ባለፈው ታኅሳስ 30 ቀን ነበር፣ ለኩባንያዎቹ ትዕዛዝ ስለተሰጠ በቅርቡ ሪፖርት የሚቀርብልን ይሆናል።

ሪፖርተር፡– ጂፒኤስ (GPS) ሳይገጥሙ ቢቀሩ ምን ይሆናሉ?

ወ/ሮ ሳህረላ ይኼንን አቅጣጫ ያስቀመጥነው ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመሆን ነው፡ አጭር የማስገጠሚያ ጊዜ ይሰጣቸውና የማያስገጥሙ ከሆነ ከሥራው እንዲወጡ ነው የሚደረጉት፡፡

ሪፖርተር፡– ይቅር ብለው ቢወጡስ? ያሉት ትንሽ አይደሉም?

ወ/ሮ ሳህረላ፡- ባለውም ቢሆን ኅብረተሰቡ ተጨናንቆ ማግኘት ነው ያለበት፡፡ አሁንም ቢሆን ኅብረተሰቡ ጋ በሚፈለገው መልኩ እያደረሰ ነው የሚለው ያጠያይቃል፡፡ ወደ ምሥራቅ ለመሄድ ነዳጅ ጭኖ አንድ ቦቴ አርባ ምንጭ የሚገኝ ከሆነና መንገድ ስቼ ነው የሚል ከሆነ፣ ሕዝቡን እየጠቀመ ሳይሆን እየጎዳው ነው የሚመጣው፡፡ ስለዚህ እንደ ባለሥልጣን ይኼን ጨከን ብሎ መቁረጥም ያስፈልጋል፡፡ ከኩባንያዎቹ ጋር ተግባብተን እስከ ኅዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ነበር ያልነው፣ ነገር ግን መሣሪያውን ለመግጠም የማያስኬዱ ብዙ ምክንያቶች ነበሩ፡፡ የታዘዙት ጥቅምት ላይ የነበረ ሲሆን፣ በየወሩ እየተገናኘን እየተገማገምን ነበር፡፡ የአውሮፕላን ነዳጅ በማቅረብ በኩል አሁን ላይ እንቸገራለን፣ ምክንያቱም የአውሮፕላን ነዳጅን ከጂቡቲ ዴፖ አምጥቶ እዚህ ዴፖ ነው የሚያራግፈው፡፡ የሌላው ነዳጅ ግን ከዴፖ አምጥቶ ማደያ ላይ ስለሚያራግፉ መሀል ላይ የሚቀሸብ አለው፡፡

ሪፖርተር፡በተደጋጋሚ በዘርፉ ላይ ከተሰማሩ ሰዎች እንደምንሰማው ከንግድ ቢሮዎች የተሰማሩ ባለሙያዎች በሕገ ወጥ ንግድ ላይ እጃቸው እንዳለበት ነው፡፡ በእርግጥ ባለሥልጣኑ አብሮ እንደመሥራቱ በተጨባጭ ያገኘው ነገር ነበር?

ወ/ሮ ሳህረላእኔ አሁን በቅርብ የምሠራው ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ነው፣ እናም መረጃዎችን በፎቶ አስደግፈው በስልክ ወዲያው ይልኩልናል፡፡ በዚህኛው በኩል ሲደርሱ ያዩትን እየላኩልንም ውጤታማ መሆን ችለናል፣ እንዲያውም በሕገወጥ መልኩ ሲጓጓዝ የነበረን በተደጋጋሚ ለማስመለስ ችለናል። መረጋገጥም ስለሚኖርበት የንግድ ቢሮዎች ባለሙያዎች ሕገወጥ ተሳትፎ ሊኖር ይችላል አይችልም የሚውን መላ ምት መስጠት አልቻለም፡፡ ከዚህ አዲስ አበባ በጀሪካንና በበርሜል ተጭነው የሚወጡትን ነዳጆች አስመልክቶና ሌሎችም ሕገ ወጥ ሥራዎችን ለመከላከል ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ነው በቅርበት እየሠራን ያለነው፡፡ ከአካባቢ አካባቢ ሊለያይ ቢችልም የፀጥታ ኃይሉ በጣም እያገዘን ነው የሚገኘው፡፡

ሪፖርተር፡የአዲስ አበባን እንደ ምሳሌ ብናነሳ፣ ቅድም የጠቀሷቸው 14 ቦቴዎችን በማደያዎች ተሰማርተው የነበሩት የንግድ ቢሮ ባለሙያዎች ለምን ከእናንተ ቀድመው ሪፖርት አላደረጉም? ለምን አመለጣቸው?

ወ/ሮ ሳህረላ፡- እኛ ንግድ ቢሮን ተጠያቂ ወደ ማድረግ አልሄድንም፡፡ በአዲስ አበባ መስተዳደር ሥር ያለና የራሱ አስተዳደር ሥርዓት ያለው ትይዩ ተቋም ነው፡፡ በደረስንባቸው ቦታዎች ግን ኩባንያዎቹ ማብራሪያ እንዲሰጡንና እሱን ተከትለውም አስፈላጊውን ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫ ሰጥተናል፡፡ ከኩባንያዎቹ ጋር እያደረግን ባለው ንግግር የሚያቀርቡት ማስተባበያ ‹‹ስህተት ስለሆነ ነው እንጂ በእኛ በኩል ችግር የለም›› የሚል ነው፡፡ እሱን የሚያረጋግጥና ዕርምጃ የሚወስዱ ሒደቶች ይቀጥላሉ፡፡

ሪፖርተር፡– በዚህ መልኩ ዘርፉን ከሕገ ወጥ ሥራዎች ለማጽዳት ምን ያህል ጊዜ ሊፈጅ ነው?

ወ/ሮ ሳህረላ፡- እንደ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን እንደ ቡድን ይህን ባለሥልጣን ለማሻሻልና አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ብዙ ሥራዎች እየሠራን ነው፡፡ በተለይ በቴክኖሎጂ አስደግፈን ይህንን ዘርፍ ለማሻሻል ትልቅ ሥራዎችን እየሠራን ነው፡፡ ማደያዎችን በቴክኖሎጂ አስደግፈን ለማሠራት (Automation) ላይ ወደ 70 በመቶ ኃይል ሄደናል፡፡ ይህንን ሥራ የሚሠራልን ድርጅት አግኝተን ጨርሰናል፡፡ ማደያዎች ነዳጅ ሲራገፉ ጀምሮ እኛ ጋር በቀጥታ ማየት የምንችልበት፣ ከዚያም ሲሸጡት ማየት የምንችልበትና የሚደረገውን የቅሸባ ሥራም ማየት በምንችልበት መልኩ ለማድረግ ብዙ ርቀቶችን ሄደናል፡፡ አዲስ አበባን እንደ ማስጀመርያ ብንወስድ ብለን አስበናል፣ ነገር ግን በአጠቃላይ 1,089 ማደያዎች ላይ ለመተግበር ነው ዕቅድ የያዝነው፡፡ ተሳክቶልን ይኼን ከጨረስን ጥሩ ግኝት ነው የሚሆነው፡፡

በዚህ ቴክኖሎጂ በአንደኛ ደረጃ እንደ አገር የምንጠቀመውን ነዳጅ ማወቅ እንችላለን፣ ሁለተኛ ደግሞ በየጊዜው የሚኖረውን ጫጫታ በሰውኛ ሳይሆን በቴክኖሎጂ እንቆጣጠረዋለን፡፡ በርካታ ሥራዎችን ስለሚያቃልልን ቴክኖሎጂውን በአጭር ጊዜ ውስጥ እናስጀምረዋለን።

ሪፖርተር፡– ከጂፒኤስ (GPS) ቴክኖሎጂው ጋር አብሮ ነው ቴክኖሎጂው ተግባራዊ የሚደረገው?

ወ/ሮ ሳህረላ፡- ጂፒኤሱ (GPS) ከተስተካከለ ነዳጅ ልክ ከጂቡቲ ሲጫን ጀምሮ መንገድ ላይ ያለውን ሒደት የሚቆጣጠሩ ባለሙያዎችን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳዳሪ (INSA) ያሠለጥንልናል። የዚህን ጂፒኤስ (GPS) ቴክኖሎጂ ጋር ነው ማደያዎችንና ዴፖዎችን ከምናይበት ሶፍትዌር ጋር አብረን የምናሠራው፡፡ ከጂቡቲ ጀምሮ መንገድ ላይ ያለውንና ሲራገፍ ጀምሮ ሪፖርት ይደረግልናል ቴክኖሎጂው። አሁን ቦቴው መጥቶ መራገፉን በሰውኛ ነው የምንከታተለው፣ ነገር ግን ቴክኖሎጂዎቹ ሲተገበሩና በጂፒኤስ (GPS) የተከታተልነው ሲራገፉ ወዲያውኑ እኛ እናውቃለን፡፡ የትኛው ማደያ ምን ያህል ተራገፈለት የሚለውን በደንብ እናውቃለን፡፡ በተጨማሪም አሁን ያለውን የሰውኛ ቁጥጥርና እየሄድን የምናይበትን እዚሁ ቁጭ ብለን የምናይበት አሠራር ይሆናል፡፡

ከኢትዮ ቴሌኮም ጋርም ማደያዎች ባሉበት አካባቢ ሁሉ ኔትወርክ ሊኖርበት በሚችለው ሁኔታ እየተነጋገርን ነው። አሽከርካሪዎችም መተግበሪያው በበይነ መረብ ላይ ተጭኖላቸው እሱን እያወረዱ መጠቀም ይችላሉ፡፡ በዋነኛነት ለአሽከርካሪዎች የሚሰጠው ጥቅም የትኛው ማደያ ላይ ነዳጅ አለ የትኛው ላይ የለም የሚለውን ለማየት ነው፡፡ ማደያዎቹ የሚሠሩበትን ሰዓትም ጭምር ነው የሚያዩት በመተግበሪያው፡፡

ሪፖርተር፡– መቼ ተግባራዊ ሊደረግ ነው ቴክኖሎጂው? ያለማውስ የምን ድርጅት ነው?

ወ/ሮ ሳህረላ፡- ቴክኖሎጂውን ያለማው የእንግሊዝ ድርጅት ነው የግዢ ኤጀንሲ ቢሮክራሲን አልፈን ግዥ እንድናደርግ ተፈቅዶልን ዋጋም ተስማምተን ጨርሰናል፡፡ አሁን የቀረን ከአከፋፈል ጋር ተያይዞ አንድ መንግሥት እንዲወስን የምንፈልገው ጉዳይ አለ። ቴክኖሎጂው ሙሉ ተለምቶ አልቆ አሁን በጊዜ ክፍያ ይሁን በአንድ ጊዜ የሚለውን እንዲወሰን ብቻ ነው የምንጠብቀው፡፡ በእርግጥ በአንድ ጊዜ ከመንግሥት ካዝና ገንዘቡን ማውጣት ስለሚያስቸግር የተለያዩ የክፍያ ሞዴሎችን ለማየት እየሞከርን ነው፡፡ የገንዘቡን መጠን መንግሥት አከፋፈሉን ወስኖ ይፋ ሲሆን የምንናገረው ይሆናል፡፡ የተወሰኑ የድርጅቱ አባላት እዚሁ አዲስ አበባ ላይ አሉ፡፡ እኛ አገር ያሉ የነዳጅ ማደያዎች መቅጃ መሣሪያ የተለያዩ ዓይነቶች ስለሆኑ እሱን በአንድ ሳምንት ቅኝት አድርገው ተግባራዊ ይሆናል፤ የክፍያው ሁኔታ እንደተሰወነ።

ሪፖርተር፡ በአገሪቱ ያለው የነዳጅ ማደያዎች ብዛት ከጎረት አገሮች አንር እጅግ በጣም ትንሽ ነው። በመላ አገሪቱ ማደያዎችን ለማሳደግ ምን ታስቧል? አዲስ አበባ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ የነዳጅ ማደያ የተገነባው መ ነው?

ወ/ሮ ሳህረላ፡- አዲስ አበባ ላይ ራሱን የቻለ ፈተና ያለና መፈታት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ቀደም ብሎ ከንግድ ቢሮ ጋር እየሠራነው በነበረው መሠረት አዲስ አበባ ላይ ለማደያ ተብለው የተለዩ ቦታዎች ነበሩ። አዲስ አበባ ከተማ ላይ እየተዋጡ ነው እንጂ 136 ማደያዎች አሉ፣ ይህም ለከተማው ብዙ ሊባል የሚችል ነው። ትልቁ ችግር ያለው ከመሀል ከተማ ወደ ጫፍ ሲወጣ ያለው ትንሽ የማደያ ቁጥር ነው። አዳዲስ የገቡ ቢኖሩም በአዲስ አበባ ያሉት ማደያዎች የድሮዎች ናቸው፣ ስለዚህ የመያዝ አቅማቸው ሲታይ በተለይ የድሮዎቹ ትንሽ ነው፡፡ ማደያ አንሷል አላነሰም ለማለት እስካሁን ስታንዳርድ የለንም ነበር፣ አሁን ግን ስታንዳርድ ኤጀንሲ እንዲያፀድቅልን እየሠራን ነው። መሥፈርት ዓይነት ነገር እንጂ እንደ ሌሎች አገሮች ማደያ በስንት ኪሎ ሜትር፣ ምን ያህል ስፋት ሊኖረው ይገባል፣ ኩባንያ ሲቋቋም ምን ያህል መሥፈርቶች ሊኖሩት ይገባል የሚለው አስገዳጅ የሆነ ስታንዳርድ አልነበረንም። የዲፖ፣ የማደያ፣  እንዲሁም የችርቻሮ (ማደያ ለሌለባቸው አካባቢዎች) ቦታዎች ላይ እንደ ምርቱ ዓይነት፣ የማደያው ስፋትና የደህንነት ጉዳዮችን ተመልክቶ ነው ስታንዳርዱ የሚወጣው። እኛ አገር ትልቁ ችግር ማደያ ሲሠራ የአካባቢ ጥናት (Giographical Survey) አይሠራም ነበር፣ ተቋማችን አንዱ እየሠራ ያለው የአካባቢ ጥናትና የማደያዎች አቀማመጥ ላይ ነው። ስለዚህ አንድ ባለሀብት ሲመጣ መጀመሪያ ገንብቶ መጥቶ ፍቃድ ስጡን ሳይሆን ማለት ያለበት የትኛው አካባቢ ላይ የቢዝነስ ሁኔታዎች አሉ፣ በርከት ብሎ የሚገኝባቸው አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው? የሚለውን ለመጠቆም ይረዳናል። ሌላው ስታንዳርዱ የሚመልሳቸው የተገነባው ማደያ በቂ ነው አይደለም? አንድ ማደያ ለምን ያህል ሕዝብ ያገለግላል፣ የታንከሩ የመያዝ ዓቅምና መሰል ጉዳዮችንም ነው። የታንከሮቹን የመያዝ ዓቅም ማሳደግ፣ እሱም ባደገ ቁጥር በአንድ ጊዜ በርካታ ተሽከርካሪዎች እንዲያስተናግዱ የመቅጃ ማሽኖቹ (Dispenser) እንዲጨምሩ የማስገደድ አንድ የጀመርነው የተሃድሶ ሥራ ነው። ስታንዳርዱ እንደፀደቀልን አስገዳጅ ይሆንና የእፎይታ ጊዜ ተቀምጦለት ማደያዎቹ በዚህ መልኩ እንዲሠሩ ይደረጋል። ዝም ብለው የቆሙ አሉ፣ እነሱን አድሶና አስፋፍቶ ወደ ሥራ ማስገባት ላይ ከከተማ መስተዳደሩ ጋር እየተነጋገርን ነው። አዳዲስ ግንባታም እየተጠየቅን ባለፈው ሦስትና አራት ወራት ከ50 እና 60 በላይ ማደያዎች በአገሪቱ ተገንብተዋል። ትላንትናም ፍቃድ የወሰዱ አሉ።

ሪፖርተር፡- የማደያ ሥራ እንደማያዋጣቸው ቅሬታ እየቀረበ እንዴት ሊሆን ይችላል?

ወ/ሮ ሰሃረላ፡- አንዳንዴ ያለው እውነታና መረጃ የሚቀርብበት መንገድ ይለያል። በጊዜው የብቃት ማረጋገጫ እኛ ጋር መጥተው ስለሚወስዱ ከ2014 ዓ.ም. ሐምሌ ወር ጀምሮ ያለውን ቁጥርና የት አካባቢ እንዳሉ ማቅረብ ይቻላል። አሁን እየተቸገርንበት ያለው አንዳንድ ክልሎች ላይ ማደያ በከፍተኛ ሁኔታ እየተገነባ ነበር እሱንም አግደናል። ለምሳሌ ሞያሌ ጠረፍ ከተማ ነች ግን በየጊዜው አዳዲስ ማደያ ይገነባል። ኮንትሮባንዱን ተከትሎ የሚመጣ ነው፡፡ ሱማሌ ክልል ሰፊ የሆነ ግንባታዎች ይከናወናሉ።

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ቅድም የነገሩን 50 እና 60ቹ አዳዲስ ማደያዎችጋዊ ራ ብቻ ላይሆን ይችላ የተገነቡት?

ወ/ሮ ሰሃረላ፡- እንደዚያ ብለን መውሰድ እንችላልለን፣ ምክንያቱም ሌሎች ሁኔታዎችን ታሳቢ ተደርገው የተገነቡ ሊሆኑ ነው የሚችሉት። ኢንዱስትሪው አትራፊ ነው አይደለም በሚለው ጉዳይ፣ በሕጋዊ መንገድ ለሚሠራው የትርፍ መጠኑ ጉዳይ ስሜት የሚሰጥ ነው፣ መስተካከልም ነበረበት፡፡ አሁን ላይ አንድ ደረጃ ከፍ ብሏል። የኩባንያዎችን አልከለስንም፤ የተለያዩ ጉዳዮች ስለነበሩበት ነው። አንገብጋቢ የነበረውም የማደያዎች ነበር፣ ምክንያቱን በሦስት ሚሊዮን ነዳጅ እየገዛ አሥር ሺሕ ብር እያተረፈ እንዲቀጥል ማድረግ ኢንዱስትሪውንም እያቀጨጨው ይሄዳል። ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እየከተታቸው ሄዶ ስለነበር ለመንግሥትም የቅድሚያ ቅድሚያ ተሰጥቶት ያቀረብነው የማደያዎቹን ጉዳይ ነበር።

ሪፖርተር፡- የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ከተጀመረ ዘጠኝ ወራት ሆኖታል፣ ብዙ የሚነሱ ቅሬታዎች አሉ። እርስዎ መረጋጋትን እንደፈጠረና ለመንግሥትም ጫና እያቀለለት እንደሆነ ተናግረዋል፣ በርካታ ታክሲዎች ግድጎማውን ተቀብለው እንደማይሠሩ ይነገራል ኅብረተሰቡስ ጋር እየደረሰ ያለውን ችግር ገምግማችሁታል?

ወ/ሮ ሰሃረላ፡የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ሐምሌ 2014 ዓ.ም. ተጀምሮ መስከረም 2015 ዓ.ም. ላይ ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ ከነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን፣ ከንገድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ከነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የተውጣጣ ቡድን ሦስት ክልሎችን ያሳተፈ ግምገማ ተሠርቷል፡፡ ከመስከረም 2 እስከ 11 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ግምገማው በሁሉም አቅጣጫዎች ለመሸፈን ሞክሮ የነበረ ሲሆን፣ ይዞት የመጣው ውጤት እንደ አጠቃላይ የኅብረተሰቡ ተጠቃሚነት ላይ ችግር አለበት። ባጃጅ ላይ ሰፊ ችግር ነበረበት። በርግጥ  አዲስ አበባ ላይ ታክሲም ስለሆነ አገልግሎት ሰጪው ትንሽ ለመቆጣጠር ተችሏል፣ ቢሆንም ከ11 ሰዓት በኋላ ታክሲዎች እንደፈለጉ ነው የሚያስከፍሉት እንዲሁም ደግሞ ቀን ሲሆን መንገድ አቆራርጠው ያስከፍላሉ። ለምሳሌ ከመገናኛ  ሜክሲኮ ከሆነ የሚሄደው ኡራኤል ጋር ያራግፉና የሆነ ታሪፍ ያስከፍላል። ከኡራኤል ደግሞ ወደ ሜክሲኮ ጭኖ ሌላ ክፍያ ያስከፍላል። ይህ በኪሎ ሜትር የተገደበውን የክፍያ ሥርዓት ሆን ተብሎ በአንድ ጉዞ የአምስትና ስድስት ብር ጭማሪ ልዩነት እንዲኖር ማድረጉን ዓይተናል። በወቅቱ ለማክሮ ኢኮኖሚው ስለሆነ ሪፖርት የምናቀርበው ያለውን ሁኔታና ሊያስከትል የሚችለውን ውጤትም አቅርበን ነበር።

ሪፖርተር፡- በድጎማው ግን ተሽከርካሪዎቹ በደንብ እየተጠቀሙ ነው?

ወ/ሮ ሰሃረላ፡- አዎ፡፡ ለምሳሌ ሐምሌ አንድ ሲጀምር ድጎማው በአንድ ሊትር በቤንዚን ስድስትና በናፍጣ ስምንት ብር ነበር ለተሽከርካሪ የሚመለሰው። የመጀመሪያው ድጎማ ገብዘቡ ትንሽ ስለነበር እስከ መስከረም የነበረው የተደጓሚ መኪና ቁጥር በራሱ ትንሽ ነበር። ይሄ መስከረም ላይ የዋጋ ማሻሻያ ሲደረግ በድጎማ ተመላሹ ወደ 15 እና 17 ብር ከፍ ሲል ወዲያውኑ በወር ውስጥ የተደጓሚዎች ቁጥር ወደ 50 ሺሕ ተሽከርካሪ አድጓል። ድጎማው ከመጀመሩ በኋላ እስከ መስከረም 30 ድረስ በአንድ ቀን ከአምስትና ስድስት ሚሊዮን ብር አይበልጥም ነበር፡፡ አጠቃላይ ከመንግሥት ካዝና በድጎማ የሚመለሰው። በኋላ ግን በሚያስፈራ መልኩ መጠኑ አድጎ በቀን እንደ ድጎማ ለተሽከርካሪዎች የሚመለሰው 30 ሚሊዮን ብር ደርሷል። ከድጎማው መጀመር ጀምሮ እስከ ጥር 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ በአጠቃላይ በድጎማው የዋለው የገንዘብ መጠን 16 ቢሊዮን ብር ደርሷል፣ ለተሽከርካሪዎች ተመላሽ የተደረገው ደግሞ አራት ቢሊዮን ብር ደርሷል። ከኅዳር 15 እስከ ታኅሳስ 15 የ230 ሚሊዮን ተመላሽ ገንዘብ ልዩነት ነው የመጣው። ይህ ዕድገት እጅግ አሳሳቢ እየሆነ ነው የመጣው። ተሽከርካሪን ስናይ ባንድ ጊዜ ከመቶ ሺሕ በላይ የተደጓሚ ተሽከርካሪ አድጓል። መስከረም መጨረሻ ላይ 65,000 የነበረው ተደጓሚ ተሽከርካሪ በዚህ ሳምንት ላይ 191,000 ደርሷል። የሚመለስላቸው ገንዘብ ትልቅ ስለሆነ ብዙዎቹ እየገቡ ነው። አንዳንድ የምክር ቤት አባላት ያዩትን ሲነግሩኝ፣ ተሽከርካሪው ተንቀሳቅሶ ከሚሠራ የትም ሳይሄድ የድጎማውን ጥቅም እንደሚወስድ ነው። በጥቆማም በተለያየ መልኩ ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እየደረሰ ዕርምጃ እየተወሰደ ነው።

ሪፖርተር፡- የድጎማውን ጥቅም ወስደው በአግባቡ እየሩ ይሁን አይሁን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በምን ያውቃ?

ወ/ሮ ሰሃረላ፡- በእርግጥ መረጃው ሙሉ ለሙሉ አይደለም። በሰውኛ የሚሠራ ስለሆነ የራሱ ችግር አለበት፣ ይህ ችግር ለማደያዎችና ለተደጓሚ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ከፍ ማለትም ምክንያት ይሆናል። በክልሎች ላይ ሚኒስቴሩ ባለው ቅርንጫፎች ነው ይህን ለማረጋገጥ የሚሞክረው። ከተደጓሚዎቹ ሚኒባሶች 40 በመቶውን ይሸፍናሉ፣ እንደ ታክሲ የሚሠሩት ደግሞ 12 በመቶ ነው የሚይዘው። ሙሉ ለሙሉ የድጎማ አተገባበሩን ስናየው፣ የፌደራል መንግሥቱ ቁጥጥር ስለሚያረግባቸው ሦስት ካታጎሪዎች ብቻ ናቸው በደንብ በታሪፋቸው እየሠሩ ያሉት፣ እነርሱም የፐብሊክ ባሶች፣ አገር አቋራጮችና የከተማ አውቶቡሶች ብቻ ናቸው። እነ ባጃጅ፣ ታክሲም፣ ሚኒባስና ሌሎችን ባየን ጊዜ ግን ሕገወጥ አተገባበሮች አሉ። ክፍለ አገሮች ላይ የፀጥታ መዋቅሩ ተሽከርካሪዎችን ድንገት አስቁሞ ለታሪፎቹ የተከፈለበትን ደረሰኝ ሲያይ የሚቆረጠው ገንዘብ 70 ብር ብሎ ተሳፋሪዎች ግን 200 ብር ሊከፍሉ ይችላሉ፣ ይሄ ድርጊት የእኛም የክትትል ባለሙያዎች የደረሱበት ነው። በእርግጥ ትራንስፖርት አጣለሁ በሚል ሊሆን ይችላል ተሳፋሪውም የሚከፍለው፣ የኅብረተሰቡም ትብብር እጅግ አስፈላጊ ነው በዚህ ላይ።

ሪፖርተር፡– የድጎማ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች ላይ (GPS) ማስገጠም መጀመሪያ ላይ ግዴታ ነበር፡፡ ለምን ተተወ አሁን? ተሽከርካሪዎቹ ነዳጁን ይጠቀሙበት አይጠቀሙበት ስለማይታወቅ አይደለም ተደጉመው የሚጠፉት?

ወ/ሮ ሳህረላ፡- እሱ የቤት ሥራ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ነበር የተሰጠው፡፡ ብዙ ርቀት ሄደው እንደነበር እናውቃለን በኮሚቴው ላይ ስንገናኝ ስለምንነጋገርም፡፡ አሁን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (INSA) አንድ መፍትሔ አለኝ እያለን ነው፣ በተለይ ሚኒባሶች ላይ ሊሠራ የሚችል፡፡ ሙሉ ዝርዝሩን ብዙም አልተነጋገርንበትም ግን እንደ ጂፒኤስ (GPS) ሆኖ ታሪፉን አብሮ የሚያይ። ሌሎች አገሮችን ስለሚጠቀሙበት ወደዚህ አገር ማስመጣት ነው ዓላማው፡፡ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ስለሚያስፈልግ እሱን ነው እኛም የምንፈልገው፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ እንዴት መተግበር ይቻላል በሚለው ላይ በደንብ እያዩበት እንዳሉ እናውቃለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረመድህን፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...