Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ካፒታላቸውን በሰባት እጥፍ እንዲያሳድጉ የሚያስገድድ መመርያ ወጣ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ካፒታላቸውን እንዲያሳድጉ እየወሰደ ያለውን ዕርምጃ በመቀጠል፣ አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማት (የማክሮ ፋይናንስ) ካፒታላቸውን በሰባት ዕጥፍ እንዲያሳድጉ የሚያስገድድ መመርያ አወጣ፡፡ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰሞኑን ባወጣው መመርያ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋምን ለመመሥረት ያስቀመጠውን ዝቅተኛ የመመሥረቻ ካፒታል ከ10 ሚሊዮን ብር ወደ 75 ሚሊዮን ብር ከፍ አድርጎታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት የተከፈለ ካፒታላቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸው በማስታወቅ፣ የባንኮች መቋቋሚያ የተከፈለ ካፒታልን ከአምስት መቶ ሚሊዮን ብር ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ማሳደጉ የሚታወቅ ሲሆን፣ በተመሳሳይም የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን የመመሥረቻ ካፒታል ከ75 ሚሊዮን ብር ወደ አምስት መቶ ሚሊዮን ብር በቅርቡ አሳድጓል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰሞኑን ባወጣው መመርያም አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማት መመሥረቻ ካፒታልን በማሳደግ 75 ሚሊዮን ብር እንዲሆን የወሰነ ሲሆን፣ በቀድሞው ዝቅተኛ የመመሥረቻ ካፒታል የተቋቋሙ አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማት አዲስ በወጣው መመርያ መሠረት ካፒታላቸውን በሰባት ዓመት ውስጥ ወደ 75 ሚሊዮን ብር እንዲያሳድጉ የጊዜ ገደብ አስቀምጧል።

መመርያው ከወጣ በኋላ በማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት ለመሰማራት የፈቃድ ጥያቄ የሚያቀርቡ ግን የግድ 75 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ሲያቀርቡ ብቻ እንደሚስተናገዱ መመርያው ያመለክታል፡፡ 

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተመዝግበው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት 45 የነበሩ ቢሆንም፣ ከእነዚህ ውስጥ አምስቱ ወደ ባንክነት ተሸጋግረዋል። በመሆኑም አዲሱ መመርያ ተፈጻሚ የሚሆነው በቀሪዎቹ ተቋማትና አዲስ በሚገቡት ላይ ይሆናል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱ አሁን ካሉት የብድርና ቁጠባ ተቋማት መካከል ከሁለት ሦስተኛ በላይ የሚሆኑት ተቋማት የተከፈለ ካፒታል ከ75 ሚሊዮን ብር በታች ነው። በመሆኑም በአዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት በቀጣዩቹ ሰባት ዓመታት ውስጥ ካፒታላቸውን ወደ 75 ሚሊዮን ብር ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል። 

በዚህ መመርያ ዙሪያ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ያካፈሉት የምሥራች ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተሾመ የሺ፣ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ካፒታላቸውን እንዲያሳድጉ ተደጋጋሚ ጥያቄ ይቀርብ የነበረ በመሆኑ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው አዲሱ መመርያ የሚጠበቅ እንደሆነ ገልጸዋል።

ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን ለማበረታታት ሲባል የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የማቋቋሚያ ካፒታል መጠን አነስተኛ ሆኖ ቆይቷል የሚሉት አቶ ተሾመ፣ ይህ የካፒታል መጠን ዝቅተኛ በመሆኑ አስፈላጊውን የማይክሮ ፋይናንስ ሥራዎች ለመሥራት አዳጋች አድርጎ ስለነበር የመመርያው መውጣት ጠቃሚ እንደሆነ ይገልጻሉ። እንደ አቶ ተሾመ ገለጻ፣ በተለይ የካፒታል መጠናቸው አነስተኛ የሆኑ የብድርና ቁጠባ ተቋማት ይሰጡ የነበረው የብድር መጠን ላይ ጫና ሲያሳድርና የቆየ በመሆኑ፣ አሁን በወጣው መመርያ መሠረት ካፒታላቸውን ሲያሳድጉ የተሻለ ብድር የማቅረብ ዕድል የሚፈጥርና ይህም ዋነኛ ጠቀሜታ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡  

የብድርና ቁጠባ ተቋማት ለተበዳሪዎቻቸው የሚሰጡት ብድር ካፒታላቸውን መሠረት ያደረገ በመሆኑና ከወቅታዊው የብር የመግዛት አቅም አንፃር በቂ የሚባል ብድር ለመስጠት ያስቸግራቸው ስለነበር፣ የካፒታል ዕድገቱ ለአንድ ተበዳሪ መስጠት የሚችሉትን የብድር መጠን ከፍ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

ተቋማቱ ለአንድ ተበዳሪ ማቅረብ የሚችሉት ከፍተኛው የብድር መጠን ከጠቅላላው ካፒታላቸው ከአንድ በመቶ መብለጥ እንደማይችል በሕግ የተደነገገ በመሆኑ፣ ተበዳሪው ለሚሠራው ሥራ የሚፈልገውን ያህል ብድር እንዳያገኝ ማድረጉን አቶ ተሾመ ገልጸዋል፡፡ 

ለምሳሌ 10 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያለው አንድ የብድርና ቁጠባ ተቋም ለአንድ ተበዳሪ ሊያበድር የሚችለው 100 ሺሕ ብር ብቻ ነበር፡፡ ካፒታሉ 20 ሚሊዮን ብር የሆነ ተቋም ደግሞ ለአንድ ተበዳሪ ማቅረብ የሚችለው ከፍተኛ የብድር መጠን 200 ሺሕ ብር ነው፡፡ ስለዚህ አሁን የወጣው መመርያ እንዲህ ያሉ ውስንነቶችን ለመቅረፍና አንድ ተበዳሪ ማግኘት የሚችለውን የብድር መጠን ከፍ ከማድረግ አኳያ ጠቃሜታ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡ 

እንደ አቶ ተሾመ ገለጻ፣ አሁን በወጣው መመርያ መሠረት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ዝቅተኛ ካፒታላቸው 75 ሚሊዮን ብር ስለሚሆን ለአንድ ተበዳሪ የሚያቀርቡት የብድር መጠን ወደ 750 ሺሕ ብር ያድጋል።

ስለዚህ ነባሮቹም ሆኑ አዳዲሶቹ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በዚህ መመርያ መሠረት ሊኖራቸው የሚችለው ዝቅተኛ የካፒታል መጠን 75 ሚሊዮን ብር መሆኑ፣ የብድርና ቁጠባ ተቋማት የሚሰጡትን የብድር መጠን ከፍ ከማድረጉም በላይ ተደራሽነታቸውን በማስፋት ረገድም የራሱ የሆነ በጎ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ገልጸዋል።

ከወቅታዊው የማይክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታው የብር የመግዛት አቅም ከመዳከሙ አንፃር ሲታይ ካፒታል ማሳደጉ ተገቢ ስለመሆኑም ተጠቁሟል፡፡ 

ከአቶ ተሾመም ሆነ ከሌሎች የብድርና ቁጠባ ተቋማት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከ15 የሚሆኑት ማይክሮ ፋይናንስ ተቋሞች አሁን ያላቸው ካፒታል ከ10 እና 20 ሚሊዮን ብር መካከል ነው፡፡ ስለዚህ አሁን የያዙት ካፒታል ብዙ የሚያስጉዛቸው ባለመሆኑ፣ የዚህ መመርያ መውጣት አቅማቸውን ያጠነክረዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡ በአንፃሩ ከ100 ሚሊዮን እስከ 500 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያላቸው ተቋማት ያሉ በመሆኑም በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቋማት የተራራቀ የካፒታል መጠን ልዩነትን በተወሰነ ደረጃ ለማጥበብ እንደሚረዳም ተጠቁሟል። 

እንደ ባለሙያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ውሳኔው ተገቢና መልካም ዕድል ተደርጎ ቢወሰድም፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ካፒታላቸውን 75 ሚሊዮን ብር ያላደረሱ አብዛኛው ተቋማት ይህንን የተጠየቀውን ካፒታል ለማሟላት ግን ሊፈትናቸው ይችላል የሚል ሥጋት ሰንዝረዋል፡፡ 

በዚህ ረገድ አቶ ተሾመም እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ሊኖር የሚችልና አንዳንዶቹ በዛብን ሊሉ እንደሚችሉ ያምናሉ፡፡ ከሙያ አንፃር ሲታይ ግን አግባብነት ያለው ውሳኔ በመሆኑ፣ እነዚህ ዝቅተኛ ካፒታል ይዘው በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ የብድርና ቁጠባ ተቋማት ይህንን ካፒታላቸውን ለማሟላት ማድረግ የሚጠበቅባቸውን ከወዲሁ እንዲያስቡበት መክረዋል። ምን ማድረግ ይችላሉ? ለሚለው ጥያቄ  አቶ ተሾመ በሰጡት አስተያየት፣ የተለያዩ አማራጮች ሊኖሩ እንደሚችሉና ከእነዚህ መካከል ዓመታዊ የትርፍ ክፍፍል ከማድረግ ተቆጥበው ትርፉን ለካፒታል ማሳደጊያ ማዋል እንደሚችሉ ገልጸዋል። ይህንን በማድረግ እስከተሰጠው የጊዜ ገደብ ድረስ ሊያሟሉ የሚችሉበት ዕድል እንዳለም አስረድተዋል፡፡ 

ከዚህም ሌላ ለውጭ ሰዎች አክሲዮናቸውን በመሸጥ በመመርያው ያተቀመጠውን ዝቅተኛ ካፒታል ማሟላት የሚችሉበት ዕድል እንዳለ ጠቁመዋል። የብድርና ቁጠባ ተቋማቱ የተጠየቀውን ካፒታል ለማሟላት ያላቸው ሌላ ዕድል ብለው አቶ ተሾመ የጠቆሙት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመርያ መሠረት ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት አክሲዮናቸውን ለትውልደ ኢትዮጵያውያን መሸጥ የሚችሉበት ዕድል ያለ በመሆኑ፣ በዚህ መመርያ መሠረት አክሲዮን ሸጠው ካፒታላቸውን ማሳደግ እንደሚችሉ ነው።

ነገር ግን ለተውልደ አትዮጵያውያን አክሲዮን ለመሸጥ የሚፈቅደውን መመርያ ለመተግበር አሁን ያለው ሁኔታ አመቺ ያለመሆኑና መመርያውን መልሶ ማስተካከል የሚጠይቅ እንደሆነም ከአቶ ተሾመ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይህም በመመርያው አክሲዮን የሚገዛው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ከተቋማቱ አክሲዮኖችን ለመግዛት የግድ ኢትዮጵያ መምጣት አለበት የሚል ድንጋጌ የያዘ በመሆኑ መመርያውን ለመተግበር አስቸግሯል፡፡ ይህ ደግሞ የተፈለገውን ያህል ትውልደ ኢትዮጵያውያን አክሲዮኖችን ለመግዛት እንዳላስቻለ ገልጸዋል፡፡ ብዙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እሳቸው ከሚመሩት የፋይናንስ ተቋምም ሆነ ከሌሎች ተቋማት አክሲዮን ለመግዛት ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ አክሲዮኑን ለመግዛት በአካል መገኘት አስገዳጅ መሥፈርት ሆኖ በሕጉ በመካተቱ ሰፊ ዕድሎች እንዳመለጣቸው ጠቁመዋል፡፡

የምሥራች ማይክሮ ፋይናንስን ጨምሮ አንዳንድ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ትውልደ ኢትዮጵያውያን አክሲዮን የገዙበትን በውጭ ምንዛሪ የሚያስቀምጡበት የዶላር አካውንት ተከፍቶ እንደነበርም፣ ይህንን ያደረጉት ከውጭ ብዙ ሰዎች አክሲዮኖችን ለመግዛት ጥያቄ በማቅረባቸው እንደሆነ አስታውሰዋል።  ይሁን እንጂ አክሲዮን ገዥው ትውልደ ኢትዮጵያዊ በአካል ቀርቦ መፈረም አለበት የሚለው ድንጋጌ አክሲዮን ለመሸጥ እንዳላስቻለ ገልጸዋል። ስለዚህ እንዲህ ያለው መመርያ የተወሰነ ማሻሻያ ቢደረግበት፣ ተቋማቱ በአዲሱ መመርያ መሠረት የሚጠበቅባቸውን ካፒታል ለማሳደግ የሚያስችላቸው መልካም ዕድል ሊያገኙ እንደሚችሉ ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡  

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዘርፉ ያሉ መመርያዎችን እያሻሻለ በመሆኑ አሁንም እንዲህ ያሉ መመርያዎችን ያሻሽላል ብለው እንደሚጠብቁም አመልክተዋል፡፡

የብድርና ቁጠባ ተቋማት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት አቶ ተሾመ፣ እየሰጡ ካሉት ዕድል አንፃር ካፒታላቸውን እንዲያሳድጉም ሆነ ግልጋሎታቸውን ለማስፋት ተጨማሪ ዕገዛዎች የሚያሻቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አብዛኛው የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት አነስተኛ ብድሮችን ከማቅረብ አኳያ ብዙዎችን እየደረሱ የሥራ ዕድል እየፈጠሩ መሆኑንም ተናግረዋል። የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ወደ አምስት ሚሊዮን የሚደርሱ ደንበኞችን ያፈሩና ብድር ያቀረቡ መሆናቸው ግንዛቤ ውስጥ ሊገባ እንደሚገባም ያመለክታሉ፡፡ ተቋማቱ ለዚህ ያህል የኅብረተሰብ ክፍል ብድር ማቅረብ የቻሉት ከባንኮች ይልቅ ከፍተኛ ተደራሽነት ያላቸው በመሆኑ ነው ብለዋል። በመሆኑም እነዚህ ተቋማት በኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸው ትልቅ ሚና ሊጤን እንደሚገባ ያሳስባሉ።

በተለይ አነስተኛና መካከለኛ ቢዝነሶች ብድር የሚያመቻቹት እነዚሁ የብድርና ቁጠባ ተቋማት በመሆናቸው ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው፡፡ አሁንም ማይክሮ ፋይናንሶች አቅም እያገኙ በመጡ ቁጥር ኢኮኖሚ ጠቀሜታቸው የበለጠ እንዲጎላ ያደርጋል ብለዋል። የእነዚህ ተቋማት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የበለጠ የሚያጎላው ደግሞ ከሚያቀርቡት ብድር አብዛኛው በገጠር አካባቢ ለሚገኙ ዜጎች የሚውል በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡  

የባንክ ተደራሽነትን በገጠር አካባቢ ለመመልከት ጥናት ማድረጋቸውን ያስታወሱት አቶ ተሾመ፣ በዚህ የዳሰሳ ጥናታቸው በገጠር አካባቢ ከባንክ ብድር አግኝቶ ተጠቃሚ መሆን የቻለ ሰው ማግኘት እንዳልቻሉ ይገልጻሉ። በመሆኑም እነዚህ ተቋማት ለገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል ብድርና ቁጠባን በማስተዋወቅና በማስለመድ ረገድ ያበረከቱት ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚሳየው፣ በ2013 በጀት ዓመት አጠቃላይ የባንኮች ተበዳሪዎች 250 ሺሕ ነበር ከአንድ ዓመት በኋላ 300 ሺሕ አካባቢ ደርሷል፡፡ ከማክሮ ፋይናንስ ተቋማት የተበደሩ ዜጎች ደግሞ አምስት ሚሊዮን መድረሱም የሚያሳየው ይህ ስለሆነ የብድርና ቁጠባ ተቋማት የፋይናንስ ተደራሽነትንና በተለይ በገጠር የቁጠባ ባህልን ከማሳደግ አኳያ ከፍተኛውን ድርሻ መያዛቸውን ተጠቅሷል፡፡  

ከድህነት ቅነሳ አኳያም ቢሆን ተቋማቱ ብድር የማግኘት ዕድል ላላገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ መሆናቸው ሌላው መለያቸው በመሆኑ ዘርፉ ትኩረት የሚሻ ነው ተብሏል፡፡ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 2013 የሒሳብ ዓመት ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት በ2013 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የካፒታል መጠናቸው 27.9 ቢሊዮን ብር ደርሶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ ካፒታል ውስጥ 84.8 በመቶ የሚሆነው በአራቱ ዋና ዋና የብድርና የቁጠባ ተቋማት ይዘው የቆዩት ነው፡፡ እነዚህ አራት ተቋማት አንድ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ከብሔዊ ባንክ ፈቃድ የተሰጠው የማክሮ ፋይናንስ ተቋም ወደ ከመሸጋገራቸው ጋር ተያይዞ 40ዎቹ ተቋማት በ2014 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ ካፒታላቸውን 15.4 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡ 

ብሔራዊ ባንክ ወደ ባንክ እንዲሸጋገሩ የተፈቀደላቸው አራቱ ተቋማት አማራ፣ ደደቢት፣ ኦሞ፣ አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋሞች ናቸው፡፡ እነዚህም ተቋሞች በ2013 ከጠቅላላ የብድርና ቁጠባ 88.8 በመቶን፣ እንዲሁም 82.7 በመቶ ብድር፣ 84.2 ሀብት በእነሱ እጅ ነበር፡፡ በ2014 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ግን ቀሪዎቹ 40 የብድርና ቁጠባ ተቋማት የቁጠባ መጠናቸው 28.3 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ የብድር ክምችታቸው ደግሞ 36 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ አጠቃላይ የሀብት መጠናቸው ደግሞ 58.8 ቢሊዮን ብር መድረሱን ይኼው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 2014 የአራተኛ ሩብ ዓመት ሪፖርት  ያመለክታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች