Saturday, May 25, 2024

የድሬዳዋ ዕጣ ፈንታ ላይ የተሰነዘሩ ሐሳቦች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹የበረሃ ገነት›› እያሉ ተወላጆቿ ይጠሯታል፡፡ የፍቅር ከተማ የሚሏትም ብዙ ናቸው፡፡ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ የከተሜነት ሥልጣኔ ቀድሞ ከፈነጠቀባቸው አካባቢዎች አንዷ መሆኗ ይነገራል፡፡ ከአዲስ አበባ በመቀጠል የኢትዮጵያ ሁለተኛዋ ሥልጡንና ትልቅ ከተማ ስትባል ኖራለች፡፡ ድሬዳዋ ከተማ በብዙ መንገዶች ቀዳሚ ስትባል ብትኖርም፣ በየጊዜው በሚያገረሸው የይገባኛል ጥያቄና የፌዴራል ሥርዓቱ በፈጠረው ክፍተት የተነሳ ዕድገቷ ተጓቶ መቆየቱ ይነገራል፡፡

ጥር 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ተካሂዶ በነበረው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ላይ የድሬዳዋ ከተማ ተወካዮች አነሱት የተባለው ጥያቄ ደግሞ፣ የድሬዳዋ ጉዳይን ዳግም የውይይት ርዕስ እንዲሆን ያደረገ ነበር፡፡

በአቶ አብዱልጀዋድ መሐመድ መቅረቡ የተነገረው ድሬዳዋ ‹ወደ ኦሮሚያ አልያም ወደ ሶማሌ ክልል ትካለል› የሚለው ጥያቄ በርካታ ግብረ መልስ እያስተናገደ ይገኛል፡፡ ከተማዋ በቻርተር በፌዴራል መንግሥት ሥር መተዳደሯ ጎድቷታል ተብሎ የቀረበው ወደ አንዱ ክልል ትጠቃለል የሚለው ምክረ ሐሳብ፣ ከረዥም ጊዜ በፊት መልስ ያገኘ የሚመስለውን የድሬዳዋ ባለቤትነት ጥያቄ ዳግም እዲቀሰቀስ ያደረገ ሆኗል፡፡

ድሬዳዋ በኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን አንዳንዴ ካውንስል ሌላ ጊዜ ደግሞ የከተማ መስተዳድር፣ እንዲሁም ራሷን የቻለች ክልል ስትባል ለረዥም ጊዜ ዘልቃለች፡፡ ይህ ደግሞ ከተማዋን በተመለከተ የባለቤትነት ጥያቄ የሚያነሱ ኃይሎችን እንዳበራከተ ይነገራል፡፡

በለው ወርቁ እ.ኤ.አ. በ2017 ባቀረቡት የድሬዳዋ አስተዳደርን የተመለከተ ጥናት፣ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የከተማዋን ጥያቄ ሳይመልስ ዘሎታል ይላሉ፡፡ ብዝኃነት ያለው ማኅበረሰብ የሚኖርባት ከተማ ከ1983 እስከ 2000 ዓ.ም. ድረስ በማዕከላዊ መንግሥት በሚሾሙ ሰዎች ስትተዳደር መቆየቷን አጥኚው ያወሳሉ፡፡

ከተማዋ በ2000 ዓ.ም. ግን የራሷን ምክር ቤት አቋቋመች፡፡ ለረዥም ጊዜ ለዘለቀው የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች የድሬዳዋ ባለቤትነት ጥያቄም መፍትሔ ለመስጠት ያስችላል የተባለ የፖለቲካ ሥልጣን ድልድል አደረገች ይላሉ፡፡ ኦሮሚያ ክልል 40 በመቶ፣ ሶማሌ ክልል 40 በመቶ የድሬዳዋ ሥልጣንን እንዲቆጣጠሩ ተደረገ፡፡ ቀሪ 20 በመቶ ሥልጣን ደግሞ ለሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ተሰጠ ሲሉ ያብራራሉ፡፡

ይህ የሥልጣንና የአስተዳደር ውቅር ግን ለድሬዳዋ የይገባኛል ጥያቄ መፍትሔ ይዞ እንዳልመጣ በለው ወርቁ በጥናታቸው ያስረዳሉ፡፡ የሥልጣን ድልድሉ በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከተማዋ ሁለት ከንቲባ እንዲኖራት የሚያስገድድ እንደሆነ የጠቀሱት አጥኚው፣ ሁለት ዓመት ተኩል ሶማሌ፣ ቀጣዩን አጋማሽ ደግሞ ኦሮሚያ ክልል የከንቲባነት ሥልጣኑን እንዲይዙ የሚያስገድድና ያልተለመደ አሠራር እንደፈጠረ ይዘረዝራሉ፡፡

ድሬዳዋ ከምሥረታዋ ጀምሮ ሕጋዊ ሰውነት ያጣችና የፖለቲካ ውክልና የተነፈገች መስተዳድር ሆና እንደኖረች የሚናገሩ እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ የድሬዳዋ ተወላጅ የሆነው የሕግ ባለሙያና የሚዲያ ሰው ሞገስ ዘውዱ፣ በድሬዳዋ ላይ ሲፈጸም የቆየው መዋቅራዊ ጥቃት እንደሆነ ይናገራል፡፡ ‹‹ድሬዳዋ ወደ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ ኖሯት ቢያንስ አሥር የሕዝብ ተወካዮች በፓርላማ ሲገባት ያሏት ግን ሁለት ተወካዮች ብቻ ናቸው፡፡ በድሬዳዋ ወይ ከኦሮሚያ ወይ ከሶማሌ ክልል ያልተወከለ ወደ ሥልጣን አይመጣም፡፡ ብዙኃኑ የከተማ ነዋሪ የፖለቲካ ውክልና የለውም፡፡ አንድ ሰው አንድ ድምፅ አለው የሚለው የዴሞክራሲ ሕግ አይሠራም፡፡ ከተማዋ ፖለቲካዊም ሆነ ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና ተነፍጋ ነው የኖረችው፡፡ ብልፅግና ሲመጣ ሁሉም  ተመጣጣኝ ውክልና የሚያገኝበት የፖለቲካ ሥርዓትና ችግሯም ይፈታል የሚል ተስፋ ቢፈጠርም፣ አሁንም ቢሆን ድሬዳዋ መዋቅራዊ ጥቃት እየተፈጸመባት ይገኛል፤›› በማለት ከሰሞኑ ስለተነሳው ውዝግብ ተናግሯል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ከድር ጃዋር፣ ‹‹በሕወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን ድሬዳዋን ራሳቸው ጠፍጥፈው የፈጠሯት ሲፈልጉ የሚያፈነዷት፣ ሲሻቸው ደግሞ መስመር የሚያስይዟት ከተማ ነበረች፤›› በማለት ይናገራሉ፡፡ እንደ አንድ ድሬዳዋ ከተማ ተወልዶ እንዳደገ አመራር፣ ከተማዋ በብልሹ መዋቅራዊና አስተዳደራዊ ችግር ተተብትባ ቁልቁል ስታድግ መኖሯ እንደሚቆጫቸውም ከንቲባው ያስረዳሉ፡፡

‹‹በድሬዳዋ የሕዝቡን ስሜትና አኗኗር የተከተለ፣ የነዋሪውን ፍላጎት ያማከለ አስተዳደር ተፈጥሮ አያውቅም፤›› ሲሉ የሚናገሩት ከንቲባው፣ ዕጣ ፈንታዋም በሕወሓት ባለሥልጣናት ሲወሰን መቆየቱን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹40 ፥ 40 ፥ 20 የሚለውን የአስተዳደር መዋቅር እንደ ዓባይ ፀሐዬ ያሉ ባለሥልጣናት ናቸው የፈጠሩት፤›› የሚሉት አቶ ከድር፣ በዚህ አሠራር መሠረትም ሕወሓት በሚዘውረው መስተዳደር ድሬዳዋ ስትተዳደር መቆየቷን ይናገራሉ፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ከተቋቋመ ከ2000 ዓ.ም. በኋላ ከተማዋ በራሷ ተወላጆች መተዳደር እንደጀመረች ከንቲባው ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ ወደ ከተማ መስተዳደሩ የመጡ ሰዎች ሥልጣኑ ቢኖራቸውም፣ የመወሰን አቅም ግን ሳይኖራቸው ነው የቆዩት፤›› ይላሉ፡፡

ለውጡ ከመጣ ወዲህ ግን የከተማ መስተዳድሩም ሆነ ሕዝቡ በራሱ ዕጣ ፈንታ ላይ የመወሰን ነፃነት እንዳገኘ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ የዋህ ነው፣ የድሬዳዋ ሰውም ትዕግሥተኛ ነው፡፡ ሕዝቡ ሲበዛበት እንጂ አይናገርም፡፡ አለ የሚለውን ችግር የሚነግረን በግልጽና በቀጥታ ነው፡፡ አሁን ያለው አስተዳደር የሕዝቡን የቀደመ አብሮነትና ፍቅር ለመመለስ በሚያስችል መንገድ እየሠራ ነው፤›› በማለትም አቶ ከድር ገልጸዋል፡፡

ከንቲባው አክለውም በኢኮኖሚም ሆነ በአስተዳደር ረገድ ድሬዳዋን ሊጠቅሙ የሚችሉ የማሻሻያ ዕቅዶችን፣ ‹‹በቻርተር አዘጋጅተን እየጠየቅን ነው፤›› ሲሉ ለብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው ተናግረው ነበር፡፡

ከንቲባው ይህን ከተናገሩ በኋላ የድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር ቻርተር ማሻሻያ ቻርተር ለተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡ ተነግሯል፡፡ በዚህ ማሻሻያ ቻርተር ደግሞ የከተማውን የሥራ ቋንቋ ከማብዛት ጥያቄ በተጨማሪ፣ የገቢ አሰባሰብና የበጀት አጠቃቀም ጉዳዮችን የተመለከቱ ማሻሻያዎች ተካተው መቅረባቸው ነው የተሰማው፡፡

ይህ የቻርተር ማሻሻያ ከዛሬ ነገ ምላሽ ያገኛል ተብሎ በሚጠበቅበት በዚህ ወቅት ግን የድሬዳዋ ባለቤትነት ጥያቄ ዳግም መስተጋባት ጀመረ፡፡ በ2000 ዓ.ም. በወጣው የድሬዳዋ ቻርተር መልስ አግኝቶ ምዕራፉ ተዘጋ የተባለው ‹‹ድሬዳዋ የእኛ ናት›› የሚለው የፖለቲካ መጓተት ዳግም ሲቀሰቀስ ታየ፡፡ ከተማዋ ራሷን የቻለች በቻርተር የምትተዳደር ከተማ መሆኗ ከታወጀ ከ15 ዓመታት በኋላ፣ ወደ ኦሮሚያ ወይም ወደ ሶማሌ ክልል ብትጠቃለል ነው የሚሻላት የሚል የቆየ ሙግት እንደገና ተጀመረ፡፡

የድሬዳዋ ተወላጅ የሆኑትና ስለድሬዳዋ ጉዳይ በመሞገት የሚታወቁት ሰለሞን ረታ (ዶ/ር)፣ ወደ አንዱ ክልል ትግባ መባሉ ተገቢ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ትንንሽ ከተሞች ወደ ክልልነት እያደጉ ራሷን ችላ ክልል የሆነች ከተማን ወደ አንድ ክልል ትጠቃለል ማለት ጤናማ አቋም አይደለም፤›› ይላሉ፡፡

የድሬዳዋን ጉዳይ በዘፈቀደና ያለ ሕዝብ ይሁንታ መወሰን አደገኛ አካሄድ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ ‹‹የወልቃይትና የራያ ጉዳይ ሄዶ ሄዶ ምን ዓይነት ቀውስ እንደፈጠረ እያየን ነው፡፡ አሁን በድሬዳዋ የሰፈነውን አንፃራዊ ሰላም ለምን ለማደፍረስ ይሞከራል?›› በማለትም ለአንከር ዩቲዩብ ሚዲያ አስረድተዋል፡፡  

ሌላኛው የድሬዳዋ ተወላጅና ተሟጋች አቶ ሙልጌታ ብሩ በበኩላቸው፣ የድሬዳዋ አስተዳደርን አቅም ለማጠናከር የቻርተር ማሻሻያ ተረቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ሳለ፣ ይህን የሚያሰናክል ምክረ ሐሳብ ለምክር ቤቱ ማቅረብ የተሳሳተ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ የድሬዳዋ አስተዳደር በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና እንዳይኖረው ሲደረግ ቆይቷል፡፡ የድሬዳዋ ሕዝብም ራሱ በመረጠው ሳይሆን በፌዴራል በሚሾሙ ምስለኔዎች ሲተዳደር ቆይቷል፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡

ምክር ቤት ተዋቀረ ከተባለ ጊዜ ወዲህም ቢሆን፣ ‹‹ምክር ቤት እያላት የሥልጣን ወሰኑ እንዳይታወቅ በማድረግ ሚናውን አሳጡት፤›› ሲሉም አቶ ሙልጌታ ይገልጻሉ፡፡ 40 ፥ 40 ፥ 20 በሚባል የሥልጣን ቀመር የሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች በድሬዳዋ ከተማ ላይ ከፍተኛ ሥልጣን እንዲኖራቸው መደረጉን የሚያወሱት አቶ ሙልጌታ፣ ይህ ደግሞ የከተማዋን ማኅበረሰብ ውክልና አልባ አድርጎት መቆየቱን ነው የሚከራከሩት፡፡

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የቀረበው የድሬዳዋ ዕጣ ፈንታ የሚወስነው ምክረ ሐሳብ፣ ከተማዋ ለኦሮሚያ ወይም ለሶማሌ ክልል እንድትሰጥ መጠየቁ በርካታ ውዝግብ እያስነሳ ነው የሚገኘው፡፡ ድሬዳዋ በቻርተር የምትተዳደር ራሷን የቻለች ከተማ መስተዳድር ሆና ከመቀጠል ይልቅ ወደ አንዱ ክልል ተጠቃላ የክልል ከተማ ብትሆን የተሻለ ልማትና ዕድገት ታስመዘግባለች መባሉ፣ ከባድ ተቃውሞና የሐሳብ ፍጭት በማስነሳት ላይ ነው፡፡

ይህ ምክረ ሐሳብ ለድሬዳዋ አዋጭ እንደማይሆን ከሚሞግቱት አንዱ፣ የድሬዳዋ ተወላጅና በድሬዳዋ ዩቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህሩ አቶ  አማኑኤል ታደሰ ሐሳቡ የማይሠራበትን ምክንያት በሰፊው ያስረዳሉ፡፡

‹‹በፌዴራል ሥርዓቱ ሁሉም ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት አላቸው፡፡ በፌዴራል መንግሥቱ ላይም የራሳቸው ሚና አላቸው፡፡ ድሬዳዋ በከተማ አስተዳደር ሥር ሆና ብትዋቀርም ራሱን እንደቻለ እንደ ሌላው ክልል ሁሉ ተገቢውን ጥቅምና ውክልና ሳይኖራት ነው የቆየችው፤›› በማለት ይሞግታሉ፡፡

በሕገ መንግሥት ዕውቅና ሳይሰጣት መኖሯን መሠረታዊ ችግር የሚሉት የሕግ ምሁሩ፣ ከተማዋ ውጪ ከኦሕዴድ ወይም ከሶዴፓ በተወከሉ አመራሮች ስትተዳደር መቆየቷ የዚህ ችግር ተቀጥላ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹በቻርተሩ ትተዳደር ተብሎም ለፌዴራል መንግሥቱ ተጠሪ ትሆናለች በመባሉ በበጀት፣ በኢኮኖሚና በገቢ ረገድ ራሷን ሳትችል ቆይታለች፤›› ሲሉም ማሳያ ይጠቅሳሉ፡፡

‹‹አሁን እንደተባለው በሪፈረንደም (ሕዝበ ውሳኔ) ወደ ኦሮሚያ ወይም ወደ ሶማሌ ክልል ብትጠቃለል፣ ድሬዳዋን የምታህል ትልቅ ከተማ የአንድ ክልል ከተማ ብቻ ሆና ትቀራለች፤›› ሲሉ የምክረ ሐሳቡን አንደኛ ችግር ያስረዳሉ፡፡

‹‹በሪፈረንደም የድሬን ችግር ለመፍታት ተብሎ ለአንድ ክልል መስጠት ዘላቂ ሰላም አያስገኝም፡፡ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች የተራዘመ ውዝግብ መፍጠር ነው የሚሆነው፤›› በማለትም የምክረ ሐሳቡን ሁለተኛ ችግር ያክላሉ፡፡

‹‹የበጀትና የፋይናንስ ችግሮችን ለመፍታት ድሬዳዋን ወደ አንድ ክልል ማጠቃለል ከተማዋ የዞን ከተማ እንድትሆን ስለሚያደርግ፣ የኢኮኖሚ ጥያቄውን አይመልስም፤›› በማለት ሦስተኛውን የምክረ ሐሳቡን ጉድለት ይናገራሉ፡፡

የድሬዳዋ ውስብስብ ችግርን ለመፍታት ይረዳሉ የሚሏቸውን የመፍትሔ ሐሳቦችን የሚያነሱት አቶ አማኑኤል፣ ወደ አንድ ክልል ትጠቃለል ማለት የተለየ ዕድል ለድሬዳዋ እንደማያመጣ ሞግተዋል፡፡

‹‹በፌዴራል ሥርዓት ውስጥ አባል የሚሆኑ የግዛት መንግሥታት የእርስ በርስ ግንኙነታቸው፣ እንዲሁም  በፌዴራል ሥርዓቱ ያላቸውን ሚና ይወስናል፤›› ሲሉ የሚናገሩት የሕግ ባለሙያው ድሬዳዋ ግን ይህን እንዳጣች ያስረዳሉ፡፡

‹‹አንድ ክልል ከሌላው ክልል ጋር ግንኙነት መፍጠርና መተባበር በአገራችን ቢቻልም፣ ድሬዳዋ ግን ይህን ማድረግ አትችልም፤›› ይላሉ፡፡ ድሬዳዋ የማዕከላዊ መንግሥቱን ይሁንታ ማግኘት ትፈልጋለች ብለዋል፡፡

‹‹ድሬዳዋ ራሷን ችላ የክልልነት ደረጃ እንድታገኝ ማድረጉ ለችግሩ የመጀመርያው መፍትሔ ነው፡፡ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግና የድሬዳዋን በገደብ የታጠረውን ራስን በራስ የማስተዳደር ሥልጣኗን በተሻለ ሁኔታ ማጎናፀፍ ቀጣይ የመፍትሔ ዕርምጃ ነው፤›› በማለትም የግል ምልከታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

ዘጠኝ የከተማና 38 የገጠር ቀበሌዎችን ይዛ የተዋቀረችውን ድሬዳዋ ከተማ መስተዳድርን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚነት ለማሳደግ በከተማ መስተዳድሩ በኩል የቻርተር ማሻሻያ መቅረቡን በጎ ዕርምጃ ሲሉ አቶ አማኑኤል ያሞግሳሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ በአጨቃጫቂ አገራዊ ጉዳዮች ምክክር መጀመሩን በጎ ዕርምጃ ይሉታል፡፡ የድሬዳዋ ባለቤትነት (ይገባኛል) ጥያቄም በዚህ መድረክ ለውይይት ቀርቦ በዘላቂነት ዕልባት እንዲያገኝ ማድረግ የተሻለ መንገድ መሆኑንም አቶ አማኑኤል ያሰምሩበታል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ወደ ሶማሌ ወይም ኦሮሚያ ክልሎች ይጠቃለላል የሚል ምክረ ሐሳብ መቅረቡን ተከትሎ፣ በድሬዳዋ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ በርካታ ወገኖች ሥጋታቸውን እያነሱ ነው፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ድሬዳዋ የብሔር የሃይማኖት መልክ ያላቸው ግጭቶች ስታስተናግድ እንደነበር በማስታወስ፣ ምክረ ሐሳቡ አሁን የሰፈነውን አንፃራዊ ሰላም ሊያደፈርስ እንደሚችል ሥጋታቸውን የገለጹ ብዙዎች ናቸው፡፡

ይህን ሥጋት የሚጋራ መግለጫ ፈጥኖ ያወጣው የከተማ መስተዳድሩም ቢሆን፣ ምክረ ሐሳቡ በግለሰቦች ተነሳሽነት የቀረበ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ‹‹የከተማ መስተዳድሩ ሳያውቀው አመራሩም ሳይመክርበት በግለሰቦች ተነሳሽነት የተሰጠ አስተያየት ነው፤›› በማለትም ምክረ ሐሳቡን ውድቅ አድርጎታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -