Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊክልከላ ያልገደበው ሺሻ

ክልከላ ያልገደበው ሺሻ

ቀን:

ጫት፣ ሲጋራ፣ ሺሻና ሌሎች አደንዛዥ ዕፆችን መጠቀም ከጀመረ አምስት ዓመት አስቆጥሯል፡፡ በወጣትነት ዕድሜው ሱስ ውስጥ መዘፈቁን የሚናገረው ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ወጣት፣ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ እያለ የተጠመደበት ሱስ ትምህርቱን እንዲያቋርጥ አድርጎታል፡፡

ትምህርቱን አቋርጦ ብዙም ሳይቆይ የተቀጠረበት የታክሲ ረዳትነት ሥራ ይበልጡኑ በሱስ እንዲዘፈቅ እንዳደረገው ይናገራል፡፡ ‹‹የታክሲ ረዳትነት ሥራ ከሱስ በዘለለ ሌላ አልጠቀመኝም፤›› የሚለው ወጣት፣ ቀኑን ሙሉ የሠራበትን ገንዘብ በሺሻ፣ በሲጋራ፣ በጫትና በአልኮል እንደሚያጠፋው ይናገራል፡፡

የሺሻና የሲጋራ ሱስ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳሳደረበት፣ በምሳ ሰዓትና ከሥራ በኋላ አንድም ቀን እነዚህን ዕፆች ሳይጠቀም ወደ ቤቱ እንደማይገባ ያስረዳል፡፡ በእነዚህ ሱሶች የተነሳ ሳንባውን ታሞ ከሱስ አምጪዎች ታቅቦ እንደነበር፣ ሆኖም ሲያገግም መልሶ እንደገባበት ያክላል፡፡

- Advertisement -

በሱስ በመጠመዱ የተነሳ ከቤተሰቦቹ ጋር መጋጨቱን የሚያስረዳው ወጣቱ፣ በአሁኑ ወቅት አዳሩም ሆነ ውሎው ታክሲ ላይ መሆኑንና ለጫት፣ ለሲጋራና ለሺሻ የሚሆን ገንዘብ እንደማያጣ፣ ባይኖረው እንኳን ጓደኞቹ እንደሚጋብዙት ይናገራል፡፡

ወጣቱ ሱሱን አቁሞ የተሻለ ሕይወት መኖር እንደሚፈልግ፣ ነገር ግን ከሱስ መላቀቅ እንዳቃተውም ያስረዳል፡፡

መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት ጫት፣ ሺሻና ሌሎች አደንዛዥ ዕፆችን የሚያስጠቅሙ የመሸታ ቤቶችም ሆነ ሆቴሎች ላይ ዕርምጃ በመውሰድ ወጣቱን ከተለያዩ ሱሶች ለመታደግ ሲጥር ይስተዋላል፡፡

ነገር ግን ችግሩን መቅረፍ አልተቻለም፡፡ ሲጋራ ላይ የተወሰደው የማይጨስበትን ቦታ የመገደብ አሠራር ለውጥ እያመጣ መሆኑን መታዘብ ቢቻልም፣ ጫት በአደባባይ ማንም መግዛት በሚቻልባቸው አካባቢዎች ወጣቱን መታደግ አልተቻለም፡፡

ሺሻ ላይ ገደብ ከተጣለ በኋላ በአደባባይ ‹‹ሺሻ አለ›› የሚሉ ባይስተዋሉም፣ በድብቅ የሚያስጠቅሙና የሚሸጡ መኖራቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ለዚህም የፀጥታ አካላት በየጊዜው ‹‹ከዚህ ቦታ ይህንን ያህል የሺሻ ዕቃ ያዝን›› እያሉ ማስታወቃቸው አንዱ ማሳያ ነው፡፡

የማቲዎስ ወንዱ ካንሰር ሶሳይቲ ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ዘላለም መንግሥቱ  ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ የትምባሆ ቅጠልን በመጠቀም ለተለያዩ ሱሶች የሚያጋልጡ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ተቋማትና ግለሰቦች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡

ከትምባሆ ቅጠልና ከዚሁ ጋር ከተያያዙ ግብዓቶች የሚሠሩ አደንዛዥ ዕፆች መበርከታቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በአሁኑ ወቅት በተለይ በከፍተኛ ሁኔታ በማኅበረሰቡ ዘንድ ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙት በሺሻና በሲጋራ መልኩ የሚሠሩት ዓይነት መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ትምባሆ በውስጡ ሰባት ሺሕ ኬሚካሎች እንዳሉት፣ ከዚህ ውስጥም 69 የሚሆኑት ለተለያዩ የካንሰር በሽታዎች የሚያጋልጡ እንደሆነ የገለጹት አቶ ዘላለም፣ ኒኮቲን የሚባለው ንጥረ ነገር ሱስ አምጪ በመሆኑ፣ አብዛኛው ሰዎች ለችግሩ ተጋላጭ እንደሚሆኑ አክለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሺሻና ሲጋራን የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን፣ አንድ ሰው በአንድ ጊዜ የሚያጨሰው ሺሻ ከ100 ሲጋራዎች ጋር  እንደሚመጣጠን፣ በዚህ ሱስ ውስጥ የተዘፈቁ ሰዎች ይህንን እንደማያውቁ አብራርተዋል፡፡

ሺሻ ከሚያጨሱ ሰዎች አብዛኛዎቹ የሺሻው መዓዛ በውኃ እንፋሎት ውስጥ ስለሚያልፍ ምንም ዓይነት ጉዳት አያስከትልም ብለው እንደሚያስቡና በቂ ግንዛቤም እንደሌላቸው አክለዋል፡፡

ሲጋራና ሺሻ የሚያጨሱ ሰዎች ለካንሰር፣ ለመተንፈሻ አካላትና ለልብ በሽታ እንደሚጋለጡ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ እንደሚገቡም ተናግረዋል፡፡

በተለይም ሲጋራና ሺሻን ከአልኮል መጠጦች ጋር የሚጠቀሙ ሰዎች ለተለያዩ የከፉ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድላቸው እንደሚጨምር ተናግረዋል፡፡

በሱስ ውስጥ ላሉ ሰዎች ካሉበት ሱስ እንዲወጡ የሕክምና ባለሙያዎች በቂ ግንዛቤ መስጠት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

በቅርቡ በእንደዚህ ዓይነት ተግባር የተሰማሩ ሆቴሎችና መሸታ ቤቶች ላይ ፍተሻ በማድረግ የማሸግ ሥራ መሥራቱንና ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስታውሰዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣንም የወጣውን ደንብ በአግባቡ በማስፈጸም ተልዕኮውን መወጣት እንዳለበትና በሕገወጥ መንገድ የሚዘዋወሩ የሺሻ ዕቃዎችን ለመቆጣጠር ከፀጥታ አካላት ጋር በትብብር ሊሠራ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

በሺሻና በሲጋራ ሱስ የተያዙ ሰዎች የሥነ ልቦና ምክር አገልግሎት እንዲያገኙ ጤና ሚኒስቴር እየሠራ መሆኑንና ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

በሱስ ውስጥ የገቡ ሰዎች ከሱስ ለመውጣት ይቸገራሉ፡፡ በቤተሰብና በማኅበረሰብ ግፊት ወይም በሕመም ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ ከሱስ አምጪ ነገሮች ራሳቸውን ቢያገሉም ተመልሰው ሲገቡበት ይስተዋላሉ፡፡ ከሱስ ለመውጣት ፍላጎት ያላቸው በሕክምና ረድቶ ከሱስ ለማላቀቅ የሚያስችል በቂ የሕክምና ሥርዓት የለም፡፡

ከችግሩ ስፋት አንፃር የሚመጣጠን ሰፊና ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራም ሲተገበር እምብዛም አይስተዋልም፡፡ አቶ ዘለዓለም የሕክምና አገልግሎቱንም በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተፈጻሚ ለማድረግ መንግሥት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ይላሉ፡፡

 በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ የመሸታ ቤቶችና ሆቴሎች ላይ ሕገወጥ ተግባራት ሲፈጸም ማየት ከተለመደ ሰነባብቷል፡፡ በተለይም ታዳጊ ሕፃናትና ወጣቶች በየመሸታ ቤቱ ሲጋራ፣ ጫት፣ ሺሻና ሌሎች አደንዛዥ ዕፆችን በመጠቀም አሸሸ ገዳሜ ይላሉ፡፡

የመሸታ ቤቶችም ሆኑ በሆቴሎች ላይ ሺሻ ማስጨስ የሚከለክል ሕግ ቢኖርም፣ በሕገወጥ መንገድ የሚያስጨሱ አካላት ሥፍር ቁጥር እንደሌላቸው ይታመናል፡፡

ከሰሞኑን እንኳን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ከፀጥታ አካላት ጋር በሠራው ሚስጥራዊ ኦፕሬሽን በሦስት ክፍለ ከተሞች ውስጥ በሚገኙ ስምንት ትልልቅ ሆቴሎችና ላውንጆች ላይ በወሰደው ዕርምጃ 296 የሺሻ ዕቃዎችን የመውረስና ቤቶቹን የማሸግ ሥራ አከናውኗል፡፡

ኦፕሬሽኑም የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባ ፖሊስና የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በመሆን የተሠራ ሲሆን፣ በአጠቃላይም 218 ግብረ ኃይሎች ተሳትፎ አድርገው ውጤታማ ሥራ መሥራት መቻሉን መረጃው ያሳያል፡፡

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሚገኙ ሪቮ አዲስ ላውንጅ፣ አቤም ሆቴል፣ ናሽናል ሆቴል፣ ሞሲ ሆቴልና ፍሬንድስ ላውንጅ ሲሆን፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ደግሞ ቀነኒሳ ሆቴል ውስጥ በሚገኝ ዲስትሪክት ላውንጅና ዘባንክ ላውንጅ ላይ እንዲሁም በየካ ክፍለ ከተማ ቤል ቪው ሆቴል ላይ ዕርምጃ ተወስዶ ባለቤቶቹ በደንቡ መሠረት ተጠያቂ ለማድረግ ቤቶቹን የማሸግ ሥራ መሥራቱን ቢሮው አስታውቋል፡፡

በወቅቱም በዚህ ተግባር ላይ የተሳተፉ ሆቴሎችና የመሸታ ቤቶች ውስጥ ሕገወጥ ተግባር ሲፈጽሙ የተገኙ ከ440 በላይ በተለያዩ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ዜጎች በቁጥጥር ሥር በማዋል በምክር መለቀቃቸውን መረጃው ያመላክታል፡፡

የሰላም ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ እንደገለጹት፣ በከተማዋ የሰላምና የፀጥታ ዋና ሥጋትና የወንጀል መጠንሰሻ እንዲሁም የወጣቱ ትውልድ መምከኛ ቦታ በሆኑት የአዋኪ ተግባር ማስፈጸሚያ ቤቶች ላይ ቢሮው ከተጠሪ ተቋሙና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ቀጣይነት ያለው ኦፕሬሽን በማካሄድ የማጥራት ሥራ ይሠራል፡፡

የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ በበኩላቸው፣ ባለሥልጣኑ በአዋጅ የተሰጠውን ሥልጣን ተጠቅሞ የአዋኪ ተግባርን ለመከላከል አስቀድሞ የተለያዩ ግንዛቤዎችን እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፣ ደንብ ተላልፈው በሚገኙ አካላት ላይ የሚወሰደውን ዕርምጃ በማጠናከር ማኅበረሰቡ ከአሉታዊ ድርጊት እንዲታቀብ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን የጤና ነክ ተቋማት ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ኢሳይያስ ፈይሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አዲስ አበባን ከትምባሆ ጭስ ነፃ ለማውጣትና ሌሎች አደንዛዥ ዕፆችን ለማስቀረት ባለሥልጣኑ የሦስት ዓመት ዕቅድ ይዞ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

ባለሥልጣኑ በከተማዋ ላይ የሚፈጸሙ ሕገወጥ ተግባራትን ለማስቆም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን የገለጹት ቡድን መሪው፣ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ከዚህ ቀደም የትምባሆ ምርቶች፣ የሺሻ ቁሳቁሶችና ሌሎች አደንዛዥ ዕፆችን ማስወገድ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ሆቴሎች፣ ባርና ሬስቶራንቶችና ሌሎች ተቋማት ላይ ቁጥጥር ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፣ ማኅበረሰቡም ከዚህ አዋኪ ልምድ ለማላቀቅ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ የሚሠራ ይሆናል ብለዋል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ የደንብ ማስከበር ባለሥልጣንና የፀጥታ አካላት በዚህ ጉዳይና ፕሮግራሞችን በመቅረፅ ተሳትፎ እያደረጉ ነው ያሉት አቶ ኢሳይያስ፣ የተለያዩ ሕገወጥ ሥራዎችን በመከላከል ማኅበረሰቡ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...