Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአማራ ክልል የብረት ማዕድን ክምችት ይገኝባቸዋል በተባሉ አካባቢዎች ጥናት ማድረግ ተጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአማራ ክልል ብረትን ለማምረት አስፈላጊ የሆነ የማዕድን ክምችት ይገኝባቸዋል በተባሉት የተከዜ ተፋሰስና የዓባይ ሸለቆ አካባቢዎች ጥናት እየተደረገ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በክልሉ በተለይ ብረትን ለማምረት አስፈላጊ የሆኑ ማዕድናት ላይ ዝርዝር ጥናት እየተደረገ ነው፡፡

በተለይም የማዕድን ክምችት ይገኝባቸዋል የተባሉት የተከዜ ተፋሰስ አካባቢዎች በተለይ በዋግ ህምራና በዓባይ ሸለቆ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ባለሀብቶች እንዳሉ፣ በአሁኑ ወቅትም ጥናት ማስጀመራቸውን የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ሌሎች በክልሉ በሥራ ላይ በሚገኙ ትልልቅ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎች እንቅስቃሴ የግሉ ዘርፍ ንቅናቄ መልካም እንደሆነና የጥሬ ዕቃ ወይም ማዕድን ፍለጋውን ጥናቱን መሠረት አድርጎ ክልሉ እንደሚሠራበት ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይ በአማራ ክልል የዓባይ ተፋሰስ አካል በሆነው ወረኢሉ በተደረገ የነዳጅ ፍለጋ ጥናት ከሁለት ቢሊዮን በርሜል በላይ ድፍድፍ ነዳጅ በከርሰ ምድር ውስጥ እንደሚገኝ በጥናት መታወቁን፣ የቀድሞው የማዕድን ሚኒስትር ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ከሰሞኑ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ መግለጻቸው ይታወሳል።

    ወረኢሉ አካባቢ ከዚህ ቀደም አንድ ኩባንያ የፍለጋ ሥራ እያከናወነ የነበረ ቢሆንም፣ በአቅም እጥረት ምክንያት ሥራውን ለማቋረጥ እንደተገደደና አሁን መንግሥት የነዳጅ ሀብቱ በአፋጣኝ ጥቅም ላይ የሚውልበትን መንገድ በማመቻቸት ላይ እንደሚገኝ ታከለ (ኢንጂነር) አስታውቀው ነበር፡፡

በሌላ በኩል በተለያዩ ዙሮች በተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በአማራ ክልል የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ብቻ ሳይሆን፣ በባለሀብቱ ዘንድ የሥነ ልቦና ስብራት መፍጠሩ ተገልጾ ክልሉም ይህንን ለመፍታት ‹‹እንዴት?››፣ ‹‹ማን ምን መሥራት አለበት?›› በሚለው ላይ ውይይቶች ተደርገው፣ በተለይም ከመንግሥት የሚጠበቁትን የባንክና የመሠረተ ልማት ጉዳዮች በማስተካከል በተያዘው ዓመት የግማሽ ዓመት ከኢንቨስትመንት አኳያ በአማራ ክልል የተሻለ ነገር መመዝገቡን፣ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

በግማሽ ዓመቱ ከ2,575 በላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ክልሉ ተቀብሎ ማስተናገዱ ታውቋል፡፡ ፕሮጀክቶቹ 344.4 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ መሆናቸው የታወቀ ሲሆን፣ በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ከገቡ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው ተብሏል፡፡

ባለፈው ዓመት ክልሉ የተቀበላቸው አጠቃላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች 2,700 እንደነበሩ ተገልጾ፣ በተጠቀሰው ዓመት ስድስት ወራት ግን ክልሉ ያገኘውን ሰላም መሠረት አድርጎ የተገኘ ውጤት እንደሆነና በቀጣይም ከፍተኛ ውጤት ይገኝበታል ተብሎ እንደሚታሰብ አቶ እንድሪስ ገልጸዋል፡፡

ክልሉን ተመራጭ የኢንዱስትሪ መዳረሻ ለማድረግ የአሠራር ማዕቀፎች ማሻሻያ እያደረገ እንደሚገኝ፣ በተለይም ከአገልግሎት አሰጣጥ አንፃር የክልሉ መንግሥት ኃላፊነት ወስዶበት እየሠራበት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

አቶ እንድሪስ እንዳስረዱት፣ በክልሉ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ ዘርፉ ሊመራበት የሚችልበት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡ ሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የራሳቸው ሀብትና ጥቅም ያላቸው በመሆኑ፣ በፍኖተ ካርታው ላይ ክልሉ በስድስት የልማት ቀጣና እንደተለየ የተገለጸ ሲሆን፣ በቀጣናዎቹ ምን ዓይነት ፕሮጀክቶች ውጤታማ ይሆናሉ? ጥሬ ዕቃና መሠረተ ልማት በቀላሉ እንዴት ይገኛል? የሚሉትን ፍኖተ ካርታው እንደሚያሳይ ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ለኢንቨስትንመት የሚሆንን መሬት ለባለሀብቱ የሚያቀርበው የክልሉ መንግሥት እንደነበር የተናገሩት አቶ እንድሪስ፣ ዘርፉን መንግሥት መሬት እያቀረበለት ማስቀጠል ስለማይችል ጉዳዩ ለባለሀብቶች ተገልጾ ካሳ ከፍለው በክልሉ ኢንቨስት ለማድረግ የገቡት ባለሀብቶች ቁጥር መጨመሩን አስረድተዋል፡፡

በተያዘው ዓመት ስድስት ወራት ብቻ ከ565 ሔክታር መሬት በላይ ለአምራች ኢንዱስትሪው ካሳ ተከፍሎበት የተላለፈ መሆኑ ታውቋል፡፡ ‹‹ባለሀብቱ በዚህ መንገድ ኃላፊነቱን ከተወጣ፣ የክልሉም መንግሥት በፊናው ኃላፊነቱን ከተገበረ የክልሉ ኢንቨስትመንት በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ይቻላል፤›› ሲሉ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች