Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ይርጋለም አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ197 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ማዕከል ሊገነባ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገሪቱ ከተገነቡ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የተነቃቃ እንቅስቃሴ እየተደረገበት ነው ለሚባለው ይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግብዓቶች ማሰባሰቢያ የሚሆን ማዕከል፣ ከ197 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ሊገነባ ነው።

የሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በአለታ ወንዶ ወረዳ ጎዋዳሞ ቀበሌ ልዩ ስሙ ጫዌቴ ለመገንባት የታሰበው የገጠር የሽግግር ማዕከል (Rural transformation Center – RTC)፣ የኮንስትራክሽን ውል በተጠናቀቀው ሳምንት አጋማሽ መፈራረሙ ታውቋል።

የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እንዳስታወቀው፣ የገጠር ለውጥ ማዕከሉ በሲዳማ ክልል ውስጥ በይርጋለም የተቀናጀ ግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥር ለመገንባት ጥናት ከተደረገባቸው ሦስት ማዕከላት ውስጥ አንዱ ነው፡፡

ጠቅላላ ስፋቱ 11 ሔክታር ከሆነው የማዕከሉ የመሬት ይዞታ የአጥር ከለላ ተሠርቶለት በተጠናቀቀው ስድስት ሔክታር መሬት ላይ፣ በመጀመሪያ ምዕራፍ በ3,500 እና በ1,500 ካሬ መሬት ላይ የሚያርፉ ሼዶችንና የዋና መግቢያ በር ለማሠራት ኮርፖሬሽኑ ውል ማሠሩ ተገልጿል።

የሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መምሩ ሞኬ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት ለተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ትልቁ ጉዳይ የአቅርቦት ሒደቱ ሲሆን፣ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር ትስስር ለመፍጠር የገጠር ሽግግር ማዕከላት ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው፣ በተለይም በአነስተኛና ጥቃቅን የተደራጁ ወጣቶችን በማሰባሰብ በተወሰነ ደረጃ የማቀነባበር ሥራዎችን ሠርተው ለዋናው ፓርክ ግብዓቶችን እንዲያቀርቡ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በይርጋለም የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዙሪያ የሚገነቡት የገጠር የሽግግር ማዕከላት ከዋናው ፓርክ ከ19 እስከ 80 ኪሎ ሜትር ዙሪያ ውስጥ የሚገነቡ በመሆናቸው፣ ከአርሶ አደሩ ለጥሬ ዕቃነት የሚያገለግሉ ግብዓቶች የሚሰባሰቡባቸው፣ የሚለዩባቸው በተወሰነ መልኩ የማቀናበር (ፕሮሰሲንግ) ሥራ የሚከናወንባቸው ማዕከላት እንደሆነ አቶ መምሩ አስታውቀዋል፡፡

በዘጠኝ ወራት ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው የጫዌቴ የገጠር የሽግግር ማዕከል ከ197.5 ሚሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ ወጪ ፈሰስ እንደሚደረግበት የታወቀ ሲሆን፣ ከዘላቂ ልማት ፕሮጀክት በተገኘ የገንዘብ ምንጭ የሚገነባም እንደሆነ ተጠቅሷል።

የሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እንዳስታወቀው፣ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ማዕከል ግንባታው የአገር ውስጥ ጨረታ ወጥቶ አሸናፊ በሆነው ተስፋዬ ፀጋዬ ጠቅላላ ሕንፃ ተቋራጭ በተባለ ድርጅት የሚከናወን ነው።

የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ከአርሶ አደሩ በመቀበል የአቮካዶ ዘይት፣ ወተት፣ ማርና ቡናን በማቀነባበር ለአገር ውስጥና ውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ፋብሪካዎችን ወደ ተግባር ማስገባቱን ያስታወቁት አቶ መምሩ፣ ለአብነትም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ፓርኩ ውስጥ የሚገኙት ፋብሪካዎች ወደ ውጭ ከላኩት ምርት 2.6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ከማስገኘታቸው ባሻገር፣ ከ140 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር መፈጸማቸውን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ከሚያጋጥሙ ማነቆዎች ውስጥ ትልቁ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት መሆኑን ከዚህ ቀደም መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ ፋብሪካዎች እየጨመሩ በሄዱ ቁጥር አሁን ባለው ልክ የሚቀርበው ምርት እንደማይበቃቸው ሲገለጽ ነበር።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች