Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ስድስት የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለመጀመሪያ ጊዜ ኤክስፖርት ማድረግ ተጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተያዘው ግማሽ በጀት ዓመት የቢራ ብቅልና ጠርሙስን ጨምሮ ስድስት የሚሆኑ አዳዲስ የኢንዱስትሪ ምርቶች ለመጀመርያ ጊዜ ኤክስፖርት ተደርገው፣ 194 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ በኤክስፖርት ዝርዝር ውስጥ ከገቡት አዳዲስ የኢንዱስትሪ ምርቶች ጀላቲን ቆዳ (የቆዳ ተረፈ ምርት)፣ የተቆላና የተፈተገ ሰሊጥ፣ የቢራ ብቅል፣ የተለያየ ይዘት ያላቸው ጠርሙሶች ተጠቃሽ መሆናቸው ታውቋል፡፡

አዳዲስ ናቸው ከተባሉት የኢንዱስትሪ ምርቶች በአጠቃላይ በግማሽ ዓመቱ 7.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ከገቢ ድርሻው ጀላቲን ቆዳ 871 ሺሕ ዶላር፣ የተቆላና የተፈተገ ሰሊጥ 39 ሺሕ ዶላር፣ የቢራ ብቅል 200 ሺሕ ዶላር፣ የተለያዩ የምርት ውጤቶች የሚቀርቡባቸው ጠርሙሶች ከአምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ይሸፍናሉ ተብሏል፡፡

ከአራትና ከአምስት ዓመታት አስቀድሞ ለቢራ ፋብሪካዎች ግብዓት የሚሆነውን ብቅል ከውጭ ይገባ እንደነበር፣ በአሁኑ ወቅት ምርቱ ከአገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ መቅረብ መጀመሩን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የ2015 የበጀት ዓመት የስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸሙን በጎንደር ከተማ በገመገመበት መድረክ ላይ ተገልጿል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ኢትዮጵያ የአጎዋ ዕገዳ ጫና በነበረበት ዓመት ከ194 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያስገኘ ምርት ኤክስፖርት ማድረጓን፣ በተጨማሪም ስድስት አዳዲስ ምርቶችን ወደ ኤክስፖርት በማስገባት የተገኙት ውጤቶች አበረታች ተደርገው የሚወሰዱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከክልልና ከከተማ አስተዳዳር ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊዎች፣ ከተጠሪ ተቋማት አመራሮች፣ ከዘርፍ ማኅበራትና ከባለድርሻ አካላት ጋር ባካሄደው መድረክ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት በተለይ በጦርነቱ ምክንያት ሥራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት በትኩረት እንደሚሠራ አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡

 በጦርነት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ ለመመለስ ጥናት መደረጉን፣ ይህም ኢንዱስትሪዎቹ ምን ዓይነት ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውና እንዴት ወደ ማምረት ሊገቡ እንደሚችሉ የሚለይ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ የመጀመሪያው በመቀሌና በዙሪያው በሚገኙ ፋብሪካዎች ላይ ጥናት መደረጉንና ሪፖርቱ በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

ይፋ የሚደረገውን የጥናት ሪፖርት መሠረት በማድረግ ደረጃ በደረጃ በክልሉ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ችግሮቻቸው እየተፈታ ወደ ማምረት የሚገቡበት ሁኔታ እንደሚፈጠር፣ የተደረገው የሰላም ስምምነት በጦርነቱ ምክንያት ላለፉት ዓመታት ምርት የማይመረትባቸውን አካባቢዎች ወደ ምርት የመመለስና በአካባቢዎቹ ሰለማዊ ሁኔታ እንዲኖር በማድረግ ረገድ ዘርፉ የድርሻውን የሚያበረክትበት ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከላከቻቸው ምርቶች የአምራች ኢንዱስትሪው የገበያ ድርሻ 39 በመቶ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህ አኃዝ ከዚህ የበለጠ እንዲሆን ዘርፉ ያለበትን የፋይናንስ፣ የግብዓትና የመሠረተ ልማት እንዲሁም ሌሎች ማነቆዎች መቅረፍ እንደሚገባ በመድረኩ ተነስቷል፡፡

የኢንዱስትሪ ዘርፍን መምራት ቀላል የሚባል ተልዕኮ አለመሆኑን ያስታወቁት ሚኒስትሩ፣ ባለሀብቶችን ወደ ዘርፉ ከማስገባት አንስቶ የመሬት አቅርቦትና የመሠረተ ልማት ማሟላት ቀላል ሥራ እንዳልሆነ፣ በዚህ ሒደት በዘርፉ በተለይም በክልሎች ያሉ የመዋቅር ችግሮች ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በቀጣይ የግማሽ ዓመት የኢንዱስትሪ ዩኒቨርሲቲ ትስስር ማጠናከር፣ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ማጠናከር፣ በአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መጠናቀቅ ያለባቸው ሥራዎችን እንዲጠናቀቁ ለተጠሪ ተቋማት ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ክልሎች የሚስተዋሉባቸውን የአሠራር ማነቆዎች ፈተው የአንድ መስኮት አገልግሎት እንዲጀምሩ፣ ወደ ሥራ ያልተመለሱ ኢንዱስትሪዎች ተለይተው ዕቅድ ተዘጋጅቶላቸው ወደ ሥራ እንዲመለሱ፣ እንዲሁም ኤክስፖርትና ተኪ ምርቶች ላይ ከመጀመሪያው የግማሽ ዓመት የተሻለ አፈጻጸም እንዲመዘገብ በሚኒስትሩ አማካይነት መመርያ ተሰጥቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች