- ፓርላማ ‹‹እግረ መንገድ›› የሚመጣበት አይደለም
አቶ ክርስቲያን ታደለ
በመንግሥት መሥሪያቤቶች የኦዲት ሪፖርት ግምገማ ላይ የመንግሥት አካላት እንዲገኙ በፓርላማው ሲጠሩ ተቋማት ጉዳዩ የሚለከታቸውን ባላሙያዎች ብቻ እንዲልኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አሳሰቡ፡፡
ለተቋማቱ ማሳሰቢያው የተላለፈው ጥር 17 ቀን 2015 ዓ.ም. የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት ሥርዓት አፈጻጸምን በተመለከተ የ2013/2014 ዓ.ም. የክዋኔ ኦዲት ግኝት ሪፖርት ሲገመግም ከተገኙ አካላት መካካል ጉዳይ የማይመለከታቸው አካላት በመድረኩ በመሳተፋቸው ነው፡፡
ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከፋይናንስና ግዥ ክፍል ተወክለው የተገኙት ተሳታፊ እንዲናገሩ ዕድል ሲሰጣቸው ‹‹ብዙም የማነሳው ነገር ባይኖርም ሚኒስትሩን ወክዬ ስለተገኘሁ ሐሳብ መስጠት እፈልጋለሁ፤›› ማለታቸውን ተከትሎ የመንግሥት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ ጠንከር ያለ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡
‹‹የአሥር ዓመት ዕቅድ ብላችሁ እያስተባበላችሁ ያላችሁት እናንተ አይደላችሁ?›› በማለት ጠይቀው፣ ‹‹ቴክኒካል መሪነቱን የያዛችሁና የአገሪቱን አሥር ዓመት ዕቅድ የምታስተባብሩት እናንተ ናችሁ፤›› ብለዋል፡፡
አቶ ክርስቲያን አክለውም የቅመማ ቅመም ግብይት ለባለሥልጣኑ ከተሰጡ ኃላፊነቶች አንዱ መሆኑን በመግለጽ ፕላንና ልማት ሚንስቴር ይህን መቆጣጠር ካልቻለ ማን ሊቆጣጠር ነው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
‹‹በየጊዜው የእያንዳንዱን መሥሪያ ቤት ትገመግማላችሁ? በተለይም ዕቅድና አፈጻጸሙ ከተጣለበት አገራዊ ኃላፊነት አንፃርና ከአሥር ዓመታት መሪ የልማት ዕቅድ ጋር መሆኑን ታያላችሁ?›› በሚል ከፕላንና ልማት ሚንስቴር ለተላኩት ተወካይ ጥያቄ ሰንዝረዋል፡፡
ይህ ኃላፊነት ለፕላንና ልማት ሚኒስቴር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተጣለበት ኃላፊነት አንዱ እንደሆነ በመግለጽ ‹‹ታዲያ ይህን የማትሠሩ ከሆነ ምን ትሠራላቸሁ፡፡ እናንተን እዚህ ስንጠራችሁ አስተያየት እንድትሰጡ ብቻ ሳይሆን በእናንተ ደረጃ መወጣት ያለባችሁን ኃላፊነት ተወጥታችኋል ወይስ አልተወጣችሁም?›› የሚለውን ለመገምገም መሆኑን አቶ ክርስቲያን ተናግረዋል፡፡
‹‹የመጣችሁበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በሕግ ደረጃ የአገሪቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል ነው፡፡ በፌዴራል ደረጃ ከፍተኛ የሥልጣን አካል በሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጥታችሁ እያለ ‹‹ሻይ ቤት›› የመጣችሁ ይመስል ‹‹ከመጣሁ አይቀር›› ተብሎ አስተያየት አይሰጥም መታረም አለበት›› ሲሉ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
በመሆኑም ለወደፊቱ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች እንዲመጡ በተደጋጋሚ የጠየቁት አቶ ክርስቲያን ፓርላማ ‹‹እግረ መንገድ የሚመጣበት አይደለም›› በተቻለ መጠን የሚሰጡ አቅጣጫዎችን ተቀብለው ውሳኔ መስጠት የሚችሉ አመራሮች መገኘት አለባቸው ብለዋል፡፡
በተለያየ ምክንያት ችግር ሊኖር ስለሚችል የተለያየ ምክንያት በሚል ልንቻቻል እንችላለን፡፡ ነገር ግን ውሳኔ መስጠት የማትችሉ ከሆነና የሚሰጥን አስተያየት ወስዳችሁ በተጨባጭ ወደ ሥራ መተርጎም የማትችሉ ከሆነ ግን ፓርላማ መምጣት ተገቢነትም እንደሌለው ነግረዋቸዋል፡፡
‹‹ይህ ምክር ቤት ነው፡፡ ለምክር ቤቱ ክብር ሞገስ አጠቃላይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ክብር በሚመጥን አቀራረብ ነው መቅረብ የሚገባን፡፡ ወደዚህ ስንመጣ የኦዲት ሪፖርቱን አንብበን፣ ተዘጋጅተን እንደ የመሥሪያ ቤቱ ከተሰጠን ኃላፊነት አንፃር የእኛ ድርሻ ምንድነው? ብለን ለመውሰድ ተዘጋጅተን መምጣት አለብን፤›› ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ባለድርሻ አካላትን ወደ ኦዲት ሪፖርት ግመገማ ሲልኩ ለሥራው ትክክለኛ የሆኑ ሰዎችን መላክ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
ይህን የምንለው የሚሠራው ሥራ ላይ በትክክለኛ መረጃ መተላለፍ ስለሚገባውና በእያንዳንዱ ሥራ ዘርፉን የሚመሩ ባለሙያዎች በመላክ መረጃ በትክክለኛው መንገድ ቢተላለፍ ይሻላል በሚል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ከፕላንና ልማት ሚንስቴር የተላኩት ተሳታፊ ከፋይናንስና ግዥ ዘርፍ መሆናቸውን ተናግረው ንግግራቸው ላይ ‹‹ቋንቋውም ሁለተኛ ቋንቋ መሆኑን መረዳት አለባቸሁ›› በማለት ተናግረው ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ‹‹የመጣሁትም የኦዲት ሪፖርት ላይ ተሳታፊ በሚል እንጂ አሁን መድረኩ ላይ በሚነሳው ልክ ተዘጋጅቶ መምጣት እንዳለብኝ ግንዛቤውም አልነበረኝም፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም ‹‹ሁኔታውን ሳይ እኔ አልነበርኩም መሳተፍ የነበረብኝ የመድረኩን ክብደት ዓይቼ አልነበረም የመጣሁት ተሳተፍ ተብዬ መጣሁ እንጂ፤›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡