ከዚህ ቀደም ሕገ መንግሥቱ ካስቀመጠው መርሕ በተቃራኒ ለረዥም ጊዜያት የፌደራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ተቋምን የሥራ ባህሪና ተቋማዊ ሁኔታ መሠረት በማድረግ፣ የአስተዳደር ሠራተኞቻቸውን በራሳቸው እንዳያስተዳድሩ አድርጎ የነበረውን አሠራር የሚቀይር የፌደራል ፍርድ ቤቶች የሠራተኞች ደንብ ለመጀመሪያ ጊዜ ተዘጋጅቶ ለፓርላማው ቀረበ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው ዘጠነኛ መደበኛ ስብሰባ የቀረበው ረቂቁ ደንብ፣ ከዚህ ቀደም የማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ አስተዳደር የሚከናወነው በፌደራሉ ሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት ነው በሚል መነሻ የፍርድ ቤት ሠራተኞችም የመንግሥት ሠራተኞች በመሆናቸው፣ ‹‹ከዚህ ሥርዓት ውጪ ሊሆኑ አይችሉም›› በሚል በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እንደሚተዳደሩ ተብራርቷል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ አሠራር ምናልባት በሌሎች መሰል አስፈጻሚ ተቋማት የሚሠራ ቢሆንም፣ የዳኝነት ተቋማት ካላቸው ሕገመንግሥታዊ ደረጃና ሊረጋገጥ ከሚገባው ተቋማዊ ነፃነት እንዲሁም ከተሰጣቸው ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮ አንፃር በተለየ አስተዳደር እንዲተዳደሩ የሚረዳ የሕግ ማዕቀፍ የመዘጋጀቱ አስፈላጊነት ተገልጿል፡፡
ቀደም ብሎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፀደቀው የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 39 እና የፌደራል የዳኝነት አዋጅ ቁጥር 1233/2013 አንቀጽ 42 መሠረት፣ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አካሉን ተቋማዊ ሁኔታና የፍርድ ቤት የሥራ ባህሪ መሠረት በማድረግ፣ የራሳቸው የሠራተኞች አስተዳደር አደረጃጀት እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች የሚመሩበትን ሥርዓት እንዲዘረጉ የሚፈቅድ ሥልጣን መሰጠቱን አስቀምጧል፡፡
በረቂቁ እንደተመለከተ ደንቡ ሦስት ዋና ዋና ምሰሶዎች ያሉት ሲሆን በዚህም የፌደራል ፍርድ ቤቶችን ተቋማዊ አቅም መንባት፣ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አካሉን ተቋማዊ ቁመናና የሥራ ባህሪን መሠረት ያደረገ የሰው ኃይልና አቅም አደረጃጀት መገንባትና የሠራተኛውን መብትና ግዴታ በአግባቡ እንዲረጋገጥ ማድረግ የሚሉት ናቸው፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተዘጋጀው ይህ ደንብ በ102 አንቀጽና በአሥራ ሦስት ክፍሎች የተዋቀረ ነው፡፡ በረቂቁ በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ መሠረት ደንብና ሥርዓትን በተከተለ ሁኔታ ብቃትና ሥነ ምግባር ያላቸውን ሠራተኞች ለመቅጠር ለማስተዳደርና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ለማሰናበት የሚያስችል የአስተዳደር ደንብ ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡
ረቂቅ ደንቡ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የሰው ሀብት ሥራ አመራር ቦርድ አደረጃጀትን የሚያቋቁም ሲሆን፣ ቦርዱ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰው ሀብት ሥራ አመራር ዋና ዳይሬክቶሬት ተጠንተውና ተዘጋጅተው የሚቀርቡለትን የሰው ሀብት ሥራ አመራር የሚመለከቱ ፖሊሲዎችና መመርያዎች፣ እንዲሁም የአመራር ሥርዓቶችን መርምሮ ማፅደቅና በአግባቡ ስለመፈጸማቸው የክትትልና የግምገማ ሥርዓት እንደሚዘረጋ ተቀምጧል፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የቦርዱ ሰብሳቢ፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ምክትል ሰብሳቢ እንዲሁም የፌደራል ከፍተኛና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶች የቦርድ አባላት እንዲሁም ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንና ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከሌሎች ከፍርድ ቤቶች የሚወከሉ የተለያዩ ሠራተኞች አባል እንደሚሆኑበት ተቀምጧል፡፡
ፓርላማው በረቂቅ ደንቡ ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር እይታ በዋናነት ለሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አንዲሁም በተባሪነት ለሰው ሀብት ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡