- በወላይታ ሶዶ የተገነባው ሆቴል በዓመቱ መጨረሻ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል ተብሏል
በድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ምክንያት በኦሮሚያ በተለያዩ አካባቢዎች ተቀስቅሶ በነበረው ሁከትና ረብሻ፣ 88 በመቶ ውድመት የደረሰበት በሻሸመኔ ከተማ የሚገኘውና ንብረትነቱ የሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ የሆነው ‹‹ኃይሌ ሆቴል›› ይዞታ ላይ፣ አዲስ ባለሦስት ኮከብ ሆቴል ሊገነባበት መሆኑን ኃይሌና ዓለም ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አስታወቀ፡፡
ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በድምፃዊ ሃጫሉ ላይ በተፈጸመው ግድያን ምክንያት በማድረግ በሻሸመኔ ከተማ ኃይሌ ሆቴልን ጨምሮ፣ የንግድ ተቋማትና ከ15 በላይ ትልልቅ ሆቴሎች ላይ ቃጠሎ መድረሱ ይታወሳል፡፡
የኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ግሩፕ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ መልካሙ መኮንን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከሁለት ዓመት በፊት በሻሸመኔ ከተማ በተፈጠረው ሁከት በኃይሌ ሆቴል ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ደርሷል፡፡
በአሁኑ ወቅት እንደ አዲስ ሊገነባ የታሰበው ባለሦስት ኮከብ ሆቴል በግማሽ ቢሊዮን ብር ለመገንባት የታሰበ መሆኑን፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረትና በግንባታ ግብዓቶች መወደድ ምክንያት በሚከሰቱ ችግሮች፣ በተለያዩ ቦታዎች ላይ እየተገነቡ በሚገኙ ሆቴሎች ላይ እንቅፋት እየገጠመው እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡
የሪዞርቱ ግንባታ ከዚህ ቀደም ከነበረው ሆቴል በተሻለ የሚከናወን መሆኑን፣ የስብሰባ አዳራሾችና የተወሰኑ ክፍሎች በተጨማሪ እንደሚገነቡ አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በሁከት ምክንያት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የወደመውን ሆቴል በማፅዳት ግንባታ መጀመሩን፣ እንደዚህ ቀደሙ ሁከትና ረብሻ እንዳይከሰት መንግሥትም በዚህ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ኢንቨስተሮች ድጋፍ በማድረግ፣ የፀጥታ ሁኔታዎችን ከክልሎች ጋር በመቀናጀት ሰላምን ማስፈን እንደሚኖርበት አቶ መልካሙ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በፊት በሁከት ምክንያት በሆቴሉ ላይ በደረሰው ቃጠሎ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ንብረቶች መውደማቸውን፣ በዚህም ምክንያት ከ300 በላይ ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው መፈናቀላቸውን አስታውሰዋል፡፡
በተመሳሳይ በነሐሴ ወር መጨረሻ በወላይታ ሶዶ የተገነባው ባለአራት ኮከብ ሆቴል ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆንና ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል፡፡
በሻሸመኔ ከተማ እንደ አዲስ እየተገነባ የሚገኘው ባለሦስት ኮከብ ሆቴል ምን ያህል ካሬ ሜትር ላይ አርፏል ለሚለው ጥያቄ አቶ መልካሙ መረጃ የለኝም ብለዋል፡፡
ኃይሌና ዓለም ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በወላይታ ሶዶ፣ በደብረ ብርሃን፣ በአዳማ፣ በጎንደር፣ በአርባ ምንጭና በሌሎች ቦታዎች ሆቴሎች እየገነባ መሆኑን፣ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ላምበረት አካባቢ የሚገኘውን ኃይሌ ግራንድ አዲስ ሆቴልን ባስመረቀበት ወቅት ተገልጿል፡፡
በድምፃዊ ሃጫሉ ግድያ ሳቢያ በሻሸመኔ ከተማም በደረሰው ጉዳት ከሆቴሎች መገኘት የነበረበት ከ37 ሚሊዮን ብር በላይ የገቢ ግብር መታጣቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡