Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ በግል ባንኮች ያስቀመጠውን የውጭ ምንዛሪ በፈለገው ጊዜ ማግኘት እንዳልቻለ አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመርያዎቹ ስድስት ወራት ከሚሰጣቸው አገልግሎቶችና ከሌሎች የገቢ ምንጮች 19.4 ቢሊዮን ብር ገቢ እንዳገኘ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት፣ በአገር ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ የግል ባንኮች ውስጥ ያስቀመጠውን የውጭ ምንዛሪ በፈለገው ጊዜ ለማግኘት መቸገሩን አስታወቀ፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ፣ በአሁኑ ጊዜ ድርጅቱ 220 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ክምችት በአገር ውስጥ ባንኮች ቢኖሩትም፣ የውጭ ምንዛሪውን ከግል ባንኮች በፈለገው ጊዜ ማግኘት እንዳልቻለ ተናግረዋል፡፡

‹‹የግል ባንኮች የክፍያ ግዴታቸውን እየፈጸሙ አይደደለም፡፡ የራሳችንን ገንዘብ ማንቀሳቀስ አልቻልንም፣ ተቸግረናል፡፡ አንዳንዴ እስከ ሙግት ወይም ወደ ፍርድ ቤት ክስ ለመመሥረት የሄድንበት ሁኔታ አለ፤›› ሲሉ አቶ ሮባ አስረድዋል፡፡

የባንኮቹን ስም መጥቀስ ቢቻልም አስፈላጊ አለመሆኑን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ጉዳዩ ድርጅቱን በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳው ስለሆነ ወደፊት ማንነታቸውን ለመግለጽ እንደሚገደዱ አስታውቀዋል፡፡

‹‹እስካሁን ድረስ በእጅጉ እያገዘን ያለው ንግድ ባንክ ነው፡፡ የራሳችን የውጭ ምንዛሪ ቢሆንም፣ ካለበት ኃላፊነት አንፃር ቅድሚያ ሰጥቶ ለማስተናገድ እየሄደበት ያለው ርቀት ጥሩ ነው፤›› ሲሉ አቶ ሮባ ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ ከደንበኞቹ የሚሰበስበውን የውጭ ምንዛሪ በሁሉም የአገሪቱ ባንኮች በከፈተው አካውንት እንደሚያስቀምጥ፣ ለመርከብና ለድርጅቱ አገልግሎት ከሰጡ የውጭ አካላት ጋር ያለውን የክፍያ ግንኙነት የሚመራበት አካውንት በአውሮፓና በጂቡቲ እንዳለውና ከአገር ውስጥ ባንኮች ይህንን የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስተላልፍ ተገልጿል፡፡

ድርጅቱ በራሱ መርከቦች የውጭ አገልግሎት በመስጠት የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ስለጀመረ፣ በተወሰነ ደረጃ የተፈጠረበትን ተፅዕኖ መቋቋም መቻሉን አስታውቋል፡፡

በተያያዘም ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ከጂቡቲ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ የሚዘረጋው መንገድ እንደተጎዳ የተገለጸ ሲሆን፣ ችግሩ በሁለቱ አገሮች መንግሥታት ክትትል ቢደረግለትም በቂ ስላልሆነ በድጋሚ ጠንከር ያለ ውይይት ማድረግ ይገባል ተብሏል፡፡

ድርጅቱ በሌለ የውጭ ምንዛሪ የተሽከርካሪ ጎማዎችና የመለዋወጫ ዕቃዎች እየተጎዱበት እየሠራ እንደሚገኝ አስረድቶ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን ቢከታተለውም በጂቡቲ በኩል የመንገድ ፕሮጀክቱን በሚፈለገው ደረጃ ያለማስኬድ ችግር እንዳለ አስታውቋል፡፡

‹‹ጎማና የተሽከርካሪ ክፍል እየተጎዳ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የማጓጓዣ ዋጋ በጣም ጨምሯል፤›› ያሉት አቶ ሮባ፣ ከዚህ በተጨማሪ ጭነቶች እንደሚወድቁና አሽከርካሪዎችም እየተንገላቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዘርፉ ካስቀመጠቻቸው የቅልጥፍና መለኪያዎች አንዱ የተሽከርካሪ ምልልስ ቢሆንም፣ መንገዱ በጂቡቲ በኩል በመጎዳቱ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅትም በወር ሦስት ጊዜ አደርገዋለሁ ያለውን የተሽከርካሪ ምልልስ ወደ 2.3 ጊዜ እንዲሆን መገደቡ ተገልጿል፡፡ የዚህም ምክንያቱ ከመንገዱ ችግር የመነጨ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አክለዋል፡፡

አቶ ሮባ ጂቡቲ ሄደው የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊውን አግኝተው በጉዳዩ ላይ እንደተነጋገሩና በእነሱ (በጂቡቲ) በኩል በጣም የተጎዳውን 60 ኪሎ ሜትር መንገድ ሊጠገን በሚችልበት ሁኔታ ላይ አማራጭ እየታየ ወደ ተግባር ሊገባ እንደሚችል ማረጋገጫ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡

እስከዚያው ድረስ የደወሌ መስመር ጥሩ አማራጭ መሆኑ ተገልጾ፣ ነገር ግን ዋናው መንገድ የጋላፊ መስመር ከመሆኑ አንፃር የዚህ መስመር መሠራት ችግሩን እንደሚያቃልለው ተብራርቷል፡፡

ከዚያ ውጪ በአገር ውስጥ የሚገኙ መንገዶች በተለይም ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የሚወስደው የዓባይ መንገድና በወረታ በኩል ያለው የወልዲያ መንገድ  እንደተጎዱ፣ የወረታ ደረቅ ወደብ ንግድ ጥሩ ሆኖ በሚፈለገው ደረጃ ማሳደግ ያልተቻለው በጦርነቱና ከግንባታ ችግር በመነጨ የመንገድ ብልሽት መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡  

በግማሽ ዓመቱ ድርጅቱ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶችና ከሌሎች የገቢ ምንጮች 19.4 ቢሊዮን ብር ገቢ እንዳገኘ፣ ከታክስ በፊት ብር 2.19 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡

የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት በድርጅቱ መርከቦች ለጎረቤት አገሮች በምፅዋ፣ በሞምባሳና በበርበራ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህ በጀት ዓመት በተጨማሪ በሌሎች ወደቦች አገልግሎቱን ለማስፋት እየሠራ እንደሚገኝ አቶ ሮባ አስረድተዋል፡፡

  ድርጅቱ በግማሽ ዓመቱ 2.4 ሚሊዮን ቶን የኦፕሬሽን አገልግሎት መስጠቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ከዕቅድ አንፃር አፈጻጸሙ ከፍተኛ እንደሆነና ነገር ግን  የኮንቴይነር ጭነት ካለፉት ዓመታት ከተጓጓዘው መጠን ጋር ሲነፃፀር የ12.8 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን፣ በአንፃሩ ተሽከርካሪዎችን የማጓጓዝ መጠን መጨመሩን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች