Thursday, February 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበታዳጊዎች ሻምፒዮና ከአንድ ሺሕ በላይ አትሌቶች ይካፈላሉ

በታዳጊዎች ሻምፒዮና ከአንድ ሺሕ በላይ አትሌቶች ይካፈላሉ

ቀን:

  • የአገር አቋራጭ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን ጀምሯል

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አማካይነት ከሚሰናዱ ዓመታዊ ውድድሮች አንዱ የሆነውና በርካታ ተተኪ ታዳጊ ወጣቶች የሚሳተፉበት ሻምፒዮና፣ ከጥር 23 እስከ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. በአሰላ ከተማ ይከናወናል፡፡

ለስድስት ቀናት በሚከናወነው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ሰባት ክልሎች፣ አንድ ከተማ አስተዳደር፣ ከ24 ክለቦችና ተቋማት የተወጣጡ 1,050 አትሌቶች እንደሚሳተፉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡ በሻምፒዮና  606 ወንዶችና 444 ሴቶች አትሌቶች በተለያዩ ርቀቶች ላይ እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡

በአሰላ አረንጓዴ ስታዲየም ለ11ኛ ጊዜ የሚካሄደው ሻምፒዮናው፣ በቀጣይ በተለያዩ የዓለም አትሌቲክስ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ አትሌቶችን ለማፍራት ግብ ያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡ ሻምፒዮናው ለተተኪ አትሌቶች ሰፊ የውድድር ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ ክለቦችና ተቋማትም የሥልጠናና የውድድር አቅማቸውንና አቋማቸውን ለመለካት እንደሚረዳቸውም ጠቅሰዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በተለይ የተለያዩ ማናጀሮችና ዕውቅ አሠልጣኞች የነገ ተስፈኞችን ለመመልመል ትልቅ ዕድል ይፈጥርላቸዋል ተብሎ ይታመናል፡፡

በዘንድሮው ሻምፒዮና ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በላይ የሆኑ አትሌቶችን ማሳተፍ እንደማይገባና ለድርድር የማይቀርብ ጉዳይ መሆኑን ፌዴሬሽኑ ተሳታፊ ክለቦችን አስጠንቅቋል፡፡

በዚህም ፌዴሬሽኑ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ላይ ባካሄደው 26ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔው ላይ በዕድሜ ማጭበርበር ጉዳይ ላይ ቁርጠኛ አቋም ይዞ አስፈላጊ ዕርምጃ እንደሚወስድ መግለጹ ይታወሳል፡፡

ከዚህ ቀደም በዓመታዊ የታዳጊ ወጣቶች ሻምፒዮና ላይ በተደጋጋሚ የዕድሜ ማጭበርበር መፈጸሙ፣ ፌዴሬሽኑም ጥብቅ ዕርምጃ አለመውሰድ ችግሩን እንደባባሰው  ሲነገር መቆየቱ ይታወሳል፡፡  

ኢትዮጵያ በዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ላይ ከስመ ጥር አገሮች ተርታ የምትሠለፍ ሲሆን፣ ዓምና በኮሎምቢያ ካሊ ላይ በተካሄደው ሻምፒዮናም በ19 አትሌቶች፣ በሁለቱም ፆታ፣ በአሥር የውድድር ተግባራት በመሳተፍ ስድስት ወርቅ፣ አምስት ብር፣ አንድ ነሐስ፣ በድምሩ 12 ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ፣ አሜሪካንንና ጃማይካን ተከትለን ሦስተኛ ደረጃ ይዛ ስታጠናቅቅ፣ ከአፍሪካ ቀዳሚ ደረጃ ላይ መቀመጧ ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል በአውስትራሊያ ባትረስት ከተማ ለሚካሄደው 44ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ለመሳተፍ የተመረጡት የብሔራዊ ቡድን አትሌቶች በጃንሜዳ ልምምድ ማድረግ ጀምረዋል፡፡

ፌዴሬሽኑ በዚህ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሉ 14 ወንድና 14 ሴቶች አትሌቶችን ከእነ ተጠባባቂዎች ታኅሣሥ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ሱሉልታ ከተማ ባካሄደው 40ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ሻምፒዮና መምረጡ ይታወሳል፡፡

በሻምፒዮናው በወጣትና በአዋቂ ምድብ ውጤታማ የሆኑ አትሌቶችን በመመልመል ከውድድሩ ማግሥት ጀምሮ በካምፕ ሆነው እንዲሠለጥኑ ማድረጉን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡

በዚህም መሠረት በወጣት ሴቶች 6 ኪሎ ሜትር 6 አትሌቶች፣ በአዋቂ ሴቶች 10 ኪሎ ሜትር 6 አትሌቶች፣ በወጣት ወንዶች 8 ኪሎ ሜትር 6 አትሌቶች፣ በአዋቂ ወንዶች 10 ኪሎ ሜትር 6 አትሌቶች፣ በድብልቅ ሪሌይ ሁለት ወንዶችና ሁለት ሴቶች አትሌቶች፣ በአጠቃላይ 28 አትሌቶች ዝግጅት እያደረጉ ይገኛል፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ ካምፕ ካስገባቸው ስምንት አሠልጣኞች ባሻገር፣ የፌዴሬሽኑ ሁለት ከፍተኛ የሕክምና ባለሙያዎች በካምፑ የጤና ክትትል እያደረጉ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ በ35 የዓለም አገር አቋራጭ ውድድሮች የተወዳደረች ሲሆን፣ በውጤቷም ከተለያዩ አገሮች ከቀዳሚዎች ተርታ ትጠቀሳለች፡፡ ባለፉት የሻምፒዮናው ተሳትፎዋ በ105 ወርቅ፣ በ108 ብርና በ62 ነሐስ በአጠቃላይ በ275 ሜዳልያዎች ከዓለም ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

ከዚህ ቀደም በ43ኛው የዴንማርክ አርሁስ በተካሄደው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በ5 ወርቅ፣ በ3 ብርና በ3 ነሐስ፣ በአጠቃላይ በ11 ሜዳልያዎች በቀዳሚነት ማጠናቀቅ መቻሏ ይታወሳል፡፡

በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና 3 እና ከ3 በላይ የወርቅ ሜዳልያ ካስመዘገቡ ስመ ጥር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል፣ ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት 3 ጊዜ፣ ጥሩነሽ ዲባባ 3 ጊዜ፣ ከሴቶች የሚጠቀሱ ሲሆን፣ ቀነኒሳ በቀለ ደግሞ 6 ጊዜ በማሸነፍ በወንዶቹ ቀዳሚና ፈር ቀዳጆች ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...