Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

ቀን:

  • በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው ተብሏል

በተለያዩ የአገሪቱ ከፍሎች በሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት ወደ አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱን፣ የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰማኮ) ለተፈናቃዮች ሰብዓዊ መብትን መሠረት ያደረገ ዘላቂ መፍትሔ ስለሚሰጥበት ሁኔታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የዕርዳታ ድርጅቶች፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ተወካዮች፣ እንዲሁም ሌሎች ተሳታፊዎች በተገኙበት ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም. የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡

በውይይቱ በአማራ ክልል በጎርፍ፣ በአንበጣ መንጋ፣ በሦስት ዙሮች በተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትና ሌሎች ግጭቶች ሳቢያ የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 2.3 ሚሊዮን ያህል መድረሳቸውንና የተወሰኑት የሰላሙ ሁኔታ ሲስተካከል ወደ ቀዬአቸው መመለሳቸውን፣ የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ እታገኝ አደመ አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ብቻ ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብና ምሥራቅ ወለጋ 22 ሺሕ ያህል ዜጎች ተፈናቅለው አማራ ክልል መግባታቸውን የገለጹት ወ/ሮ እታገኝ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በሌሎች ተቋማት ዕርዳታ እየቀረበ መሆኑንና የሚቀርበው ግን በሁለትና በሦስት ወራት አንድ ጊዜ 15 ኪሎ ግራም እህል ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነቱ ምክንያት ከቤቱ ሳይወጣ ምንም ዓይነት ምርት አምርቶ ያልሰበሰበ ዕርዳታ ጠባቂ ሕዝብ ቁጥር 6.1 ሚሊዮን መድረሱን፣ በተጨማሪም ከተፈናቀሉት ውስጥ 80 ሺሕ ያህሉ በ37 መጠለያ ካምፖች እንዲሁም 650 ሺሕ የሚሆኑት ደግሞ በማኅበረሰቡ ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

በክልሉ በሚገኙ ሰባት ዞኖች በርካታ የመንግሥት ተቋማት ሙሉ በሙሉና በከፊል መውደማቸውን የገለጹት ወ/ሮ እታገኝ፣ ክልሉ ከነበረበት ወደኋላ በመመለሱ ሰፊና ተደራራቢ የሆነ ችግር ውስጥ መግባቱን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹እየጠየቅን ያለነው ሰው እንዳይሞትብን ሕይወቱን እንድንታደገው ነው፤›› ያሉት ምክትል ኮሚሽነሯ፣ ‹‹ይህንን ጊዜ የምናሳልፍበት ሰብዊ ዕርዳታ እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡ ችግሩ የተወሳሰበና የተደራረበ ቢሆንም ለአማራ ክልል የሚደረገው ትኩረት ዝቅተኛ በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕገዛ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአፋር ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽነር አቶ መሐመድ ሁሴን በክልሎች ተደጋጋሚ የሆነ ጦርነት፣ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ግጭትና የበረሃ አንበጣ መንጋ በክልሉ ያለውን የሰብዓዊ ዕርዳታ ጠባቂ ቁጥር እንዳባባሰው ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ በክልሉ ላለው የዕርዳታ ፍላጎት ከፌዴራል መንግሥትና ከዕርዳታ ድርጅቶች ጋር በተወሰነ ደረጃ እየተሠራ ቢሆንም፣ የአፋር ሕዝብ ግን በሚደረገው ሰብዓዊ ዕርዳታ ግልጽና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እየተላለፈ ነው በሚል ላይ ጥያቄ አለው ብለዋል፡፡ በክልሉ ያለው ችግር ግልጽና ሰፊ ሆኖ እያለ በዕርዳታ አቅራቢዎች የሚሰጠው ትኩረትና የሚደረገው ድጋፍ፣ በሌሎች አካባቢዎች በሚደረገው ልክ አለመሆኑ እየታየ ነው ብለዋል፡፡

‹‹የእኔ ጥያቄ የሚገባንን ሰብዓዊ ዕርዳታ ድርሻ እያገኘን አይደለም፡፡ አንዳንዴ ለሌሎች አካባቢዎች በተለየ ሁኔታ እንደሚደረገው ድጋፍ የእኛ ጥያቄ ጀኔቫ ወይም ሮም የሚሰማ አይመስለኝም፡፡ በመሆኑም አጀንዳችን ወደ ጠረጴዛ አምጡልን፣ ለአፋር ጉዳይ ትኩረት ስጡልን፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትናና ኮሚሽነር አቶ ታረቀኝ ታሲሳ በበኩላቸው፣ ክልሉ ካለው አጠቃላይ 1.5 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 450 ሺሕ ተፈናቃይ፣ 75 ሺሕ ከሱዳንና ከደቡብ ሱዳን የመጡ ስደተኞች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውንና 44 ሺሕ ቤቶች በእሳት መቃጠላቸውን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከጥቂት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካላት ውጪ በርካታ ድጋፍ አድራጊዎች ወደ ክልሉ ባለመሄዳቸው፣ በመንግሥት ድጋፍ ላይ ብቻ ጥገኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ችግሩ ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ አሁን አንፃራዊ ሰላም ቢኖርም በምዕራብ ኦሮሚያ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ወደ ክልሉ ዕርዳታ እየደረሰ ያለው በአማራ ክልል በኩል ነው ብለዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም ክልሉ የሚያስፈልገው ዕርዳታ ከፍተኛ በመሆኑ እንደሌላው አካባቢ አግዙን፤›› ብለዋል፡፡

ተመሳሳይ ችግሮችን በተለይ በጦርነትና በድርቅ ምክንያት እያስተናገዱ መሆኑን የገለጹት የኦሮሚያ ክልል አደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ምክትል ኮሚሽነር ማልቻ ሉጃ (ዶ/ር)፣ እስካሁን በአራቱ የወለጋ ዞኖች 1.3 ሚሊዮን ዜጎች ተፈናቅለውና ትምህርት ቤቶች ተዘግተው የግብርና ሥራ መቆሙንና ዜጎች ምንም ዓይነት ድጋፍ እያገኙ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እነዚህን ዜጎች ረስቷቸዋል ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ በደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ በባሌ ዞን 200 ሺሕ ተፈናቃዮች እንዳሉና በቦረና ዞን ከሚገኙት 100 ሺሕ ተፈናቃዮች ውስጥ የተወሰኑት ወደ ጎረቤት ኬንያ እየተሰደዱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡  

በውይይቱ የተገኙት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ልዩ አማካሪ ሮበርት ፓይፐር የተፈናቃዮችን ችግር ለመፍታት፣ በዋነኝነት የሰብዓዊ ዕርዳታ ከማቅረብ ባለፈ መንግሥት ከተመድ ጋር በመተባበር ቅደመ መከላከል ሥራዎች ላይ አተኩሮ እንዲሠራ ጠይቀዋል፡፡

የኢሰማኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የተፈናቃዮችን ቁጥር ትክክለኛ መረጃ ማግኘት አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡ ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች በጦርትና በድርቅ ከተፈናቀሉ ዜጎች ውስጥ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች እንዳሉ፣ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በፀጥታ ችግር የተፈናቀሉ ናቸው ብለዋል፡፡ ‹‹ለተፈናቃዮች የሚረዱ ተቋማዊ ሥራዎችና የሕግ ማዕቀፎች እንዲከናወኑ፣ ለተፈናቃዮች መሠረታዊ አቅርቦቶች እንዲሟሉና ወደ ቀደመ ሕይወታቸው እንደሚለሱ የሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅባቸውን እንዲሠሩ ሁለጊዜም እንመክራለን፣ እንዘክራለን፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...