Wednesday, March 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየትግራይ አትሌቲክስን ለማንቀሳቀስ የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ድጋፍ እንዲያደርግለት የክልሉ ፌዴሬሽን ጠየቀ

የትግራይ አትሌቲክስን ለማንቀሳቀስ የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ድጋፍ እንዲያደርግለት የክልሉ ፌዴሬሽን ጠየቀ

ቀን:

የትግራይ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በክልሉ የነበረውን የአትሌቲክስ እንቅስቃሴ እንደገና ለማስጀመር የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ድጋፍ እንዲያደርግለት ጠየቀ፡፡

በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው አትሌቲክሱ፣ ክልሉ ከፌዴራል መንግሥት ጋር የደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ፣ ፌዴሬሽኑ የመጀመርያ ዙር የዳሰሳ ጥናት እያደረገ እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

ፌዴሬሽኑ በክልሉ የሚገኙትን የስፖርት ማዘውተሪያና ማሠልጠኛ ማዕከላት፣ እንዲሁም የስታዲየሞች አሁናዊ ገጽታ ላይ የዳሰሳ ጥናት መጀመሩን የገለጸ ሲሆን፣ ለዚህም ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያሻው የትግራይ  አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኪዳነ ተክለ ሃይማኖት ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ ኪዳኔ ማብራሪያ ከሆነ፣ የመጀመርያው ምልከታ የተደረገው በመቐለ ስታዲየም ነው፡፡ ነገሮች ምቹ ሲሆኑ በክልሉ ከተሞች ላይ በማምራት ያሉበትን ደረጃ ለመዳሰስ መታቀዱንም አስረድተዋል፡፡

‹‹ወደ ክልሉ ከተሞች ሄደን የዳሰሳ ጥናት ለማድረግ ምቹ ሁኔታ አለ ማለት አይቻልም፡፡ በጦርነቱ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸው ማዘውተሪያዎችን ከመለየት ባሻገር፣ ማን አለ? ማን የለም? የሚለውን ጉዳይ አላወቅንም፤›› በማለት አቶ ኪዳኔ ይናገራሉ፡፡

ከቀናት በፊት የመቐለ ስታዲየም የቃኘው ቡድን የመሮጫ ትራኩ ከጥቅም ውጪ መሆኑን ማረጋገጡን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ መልሶ እንደነበረው ለማድረግ ማገዝ ያለባቸው መንግሥታዊም ሆኑ ሌሎች አካላት ያለበትን ሁኔታ ተረድተው ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በደቡብ ትግራይ የሚገኘው የማይጨው ማሠልጠኛ ማዕከል ላይ የደረሰው ውድመት በዝርዝር የቀረበ ሲሆን፣ ወደፊት የሌሎችንም ጨምሮ አጠቃላይ ሪፖርቱ ይፋ እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡

በቅርቡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ የተመራውና በዓለም ሻምፒዮናና ኦሊምፒክ ላይ የተሳተፉ አትሌቶችን የያዘው ልዑክ ወደ መቐለ ማምራቱ ይታወሳል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለክልሉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማቋቋሚያ ሁለት ሚሊዮን ብር ከመርዳቱም ባሻገር፣ የሙያና የሥነ ልቦና ሥልጠና ለማድረግ ዕቅድ መያዙ ተገልጿል፡፡

በዕቅዱም መሠረት የዳሰሳ ጥናቱ ተጠናቆ ሲቀርብ በፌዴሬሽኑ፣ እንዲሁም ከሌሎች የባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር አትሌቲክሱ እንደገና እንቅስቃሴ እንዲጀመር መታቀዱን ፕሬዚዳንቱ አቶ ኪዳነ ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ ስምንት የወረዳ ማሠልጠኛ ተቋማት የነበሩ ሲሆን፣ በነዚህ ተቋማት ላይ ተመሳሳይ የዳሰሳ ጥናት ለማድረግ ቢታቀድም፣ በአንፃሩ ወደ ወረዳዎቹ ሄዶ ዳሰሳ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ አለመኖሩና የትራንስፖርት አገልግሎት ማግኘት አዳጋች መሆኑንም አውስተዋል፡፡

በሌላ በኩል የትግራይ ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ተክላይ ፈቃዱ አስተያየት ከሆነ፣ ምንም እንኳን በክልሉና በፌዴራል መንግሥት መካከል የተደረገው የሰላም ስምምነት ትኩስ መሆኑና በርካታ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ተከትሎ፣ ነገሮች ፈር እየያዙ ሲመጡ፣ አሁን የተጀመረው የስፖርት እንቅስቃሴው በታቀደለት መንገድ ይከናወናል የሚል እምነት እንዳላቸው ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

‹‹ከሰላም ስምምነቱ ክንውን አንፃር በክልሉ የስፖርቱን እንቅስቃሴ በሚፈለገው መንገድ ለማስጀመር እየተንቀሳቀስን ነው ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም እንቅስቃሴው እንደገና ለማስጀመር ምንም ሀብት የለም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያን በኦሊምፒክና በተለያዩ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች መወዳደርና ባለድል አትሌቶችን ያፈራው የትግራይ ክልል፣ በርካታ ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት እንዲችል በጦርነቱ ወቅት የወደሙበትን የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ማደስ እንዲቻል የፌዴራል መንግሥትና ሌሎች አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ የክልሉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጥሪ አቅርቧል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም ብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ላደረገው ድጋፍና በቀጣይም ለመደገፍ ለያዘው ዕቅድም ፕሬዚዳንቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...