ባለፈው ሳምንት በአንደኛው ቀን ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት አካባቢ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ ከሚገኘው ሸገር ሕንፃ ውስጥ ወጥቼ ወደ አትላስ የሚያመራውን የእግረኛ መንገድ ይዤ ስራመድ፣ ከአንድ የመጠጥ ግሮሰሪ አጠገብ ተለጥፎ የተሠራ ታዛ ሥር አምስት ያህል ሰዎች ባለሦስት እግር ዱካ ላይ ተቀምጠው ሳንዱች መሳይ ምግብ ሲመገቡ ተመለከትኩ፡፡ እኔም አጣዳፊ ሥራ ላይ ቀኑን ሙሉ ተጥድጄ በመዋሌ ሰዎቹን ሳይ ረሃቤ ተቀሰቀሰ፡፡ ወደፊት መራመዴን ትቼ አንድ ዱካ በመሳብ ሰዎቹን ተቀላቀልኩ፡፡ ወዲያው ኮመዲኖ የሚመስል ነገር ላይ ምግቡን የምታሰናዳ ወጣት ልጅ ቀረብ ብላኝ ምን እንደፈለግኩ ጠየቀችኝ፡፡
እኔም በጣም ርቦኝ ስለነበረ ምን ምን ምግቦች እንዳሉ ስጠይቃት፣ ‹‹እኛ ዘንድ የተለመደው እርጥብ ነው…›› አለችኝ፡፡ እኔ ይህንን ‹እርጥብ› የሚባል ነገር ስለማላውቅና የዚያን ቀን ብቻ ስሙንም ስለሰማሁ፣ ‹‹እርጥብ ምንድነው…›› ከማለቴ እየሳቀች፣ ‹‹እርጥብ በጣም ተወዳጅ የዘመኑ ምግብ ነው…›› ስትለኝ እስቲ ልቅመሰው ብዬ እንድትሠራልኝ ነገርኳት፡፡ በዚህ መሀል አንድ የማውቀው ሰው ስሜን መተላለፊያ መንገዱ ላይ ሆኖ ሲጠራኝ ሰማሁት፡፡ ቀና ብዬ ሳየው እየሳቀ መጥቶ፣ ‹‹ለካ አንተም ይህንን እርጥብ ለምደህልኛል…›› ሲለኝ እኔ ብቻ ለምግቡ ባይተዋር መሆኔ ታወቀኝ፡፡ እሱም አንድ ዱካ ስቦ ተቀምጦ ለራሱ አንድ ‹እርጥብ› አዘዘ፡፡
ያዘዝነው ተሠርቶ እስኪቀርብልን ወሬ ጀመርን፡፡ እኔ ስለተባለው ምግብ ምንም ዕውቀት እንደሌለኝ፣ ይልቁንም ድንገት ሰዎች ሳንዱች መሳይ ነገር ሲበሉ ርቦኝ ስለነበር መንገዴን አቋርጬ እዚያ መገኘቴን ስነግረው፣ ‹‹አምሳሉ አንተ ለእርጥብ እንግዳ ብትሆንም፣ ሰፊው ሕዝብ ግን መደበኛ ቀለቡ ካደረገው ሰነባበተ፡፡ የኑሮ ውድነቱ ስላልተቻለ እንደ በፊቱ የባንክ ሠራተኛ በል የቴሌ፣ የአነስተኛ ንግድ ባለቤት በል የታክሲ ሾፌርና ወያላ ከሬስቶራንት ወርደው እርጥብ ነው የሚበሉት፡፡ የምግብ ሰዓት አለፍ ሲል ደግሞ የማይመጣ የሰው ዓይነት የለም፡፡ ኑሮ በመክፋቱ እርጥብ ተመራጭ ምግብ ሆኗል…›› አለኝ፡፡
እሱ ይህንን መረጃ እየነገረኝ ምግባችን ደርሶ ተሰጠን፡፡ በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ የምቀምሰው የመሰኝ ምግብ ለካስ ዳቦና ድንች ነው፡፡ ድሮ በምስር፣ በቀይ ሥር ወይም በድንች ተሠርቶ ይሸጥ የነበረ ‹ኢምፖቲቶ› የምንለውን ይመስላል፡፡ የቀረበልኝን በአንድ አነስተኛ ጉርሻ ሳጣጥም የማላውቀው ዓይነት የሚያቃጥልና የሚጥም ጣዕም አለው፡፡ ከወዳጄ ጋር ይህንን የክፉ ቀን ደራሽ ምግብ እየተመገብን እየተጫወትን ሳለ ብዛት ያላቸው ወጣት ወንዶችና ሴቶች፣ ጎልማሶችና አዛውንቶች ‹እርጥብ› እያዘዙ ሲመገቡ አየሁ፡፡ የኑሮ መክፋት አብዛኛውን ከተሜ የጎዳና ምግብ ተመጋቢ እንዳደረገውም በቀላሉ አስተዋልኩ፡፡
በአንድ ወቅት በኮንቴይነር የተሠሩ አነስተኛ ታዛዎች ውስጥና በራፎቻቸው ላይ ይመገቡ የነበሩ እንደ ምስኪን ይታዩ ነበር፡፡ አሁን ግን በየጎዳናው ጥግና አውላላ ሜዳ ሳይቀር እየተኮለኮሉ ‹እርጥብ› መመገብ የብዙዎች ዕጣ ፈንታ ሆኗል፡፡ አደባባይ ላይ መታየት የማይፈልጉ የቢሮ ሠራተኞች ሳይቀሩ በ‹ዴሊቨሪ› አማካይነት ደንበኛ መሆናቸው የሰነባበተ ጉዳይ ከሆነ መቆየቱን ተረዳሁ፡፡ ኑሮ ከአቅም በላይ ሲሆንና አማርጦ መብላት ሲያዳግት ያለው ምርጫ መሆኑንም ተገነዘብኩ፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን ውስጤን አንድ ነገር እየከነከነኝ ነበር፡፡
ኢትዮጵያን የመሰለች ክረምት ከበጋ አብቃይ መሆን የምትችል አገር በተፈጥሮ የተቸረችውን ፀጋ ተገፋ፣ ልጆቿ በምግብ ችግር ሲሳቀቁ ከማየት የበለጠ ምን ውርደት ይኖራል የሚለው ነበር ውስጤን ሰቅዞ የያዘው፡፡ በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምሥራቅም ሆነ በምዕራብ ምንም ያልጎደለባት አገር ምግብ ጭንቅ ሆኖባት የረባ ነገር በልቶ ማደር ሲያቅት ምን የሚሉት ኑሮ ነው ያሰኛል፡፡ ዳቦ፣ ሥጋ፣ ዶሮ፣ እንቁላል፣ ወተት፣ ቅቤ፣ ዓይብ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ በቫይታሚንና በማዕድናት የበለፀጉ ምግቦች ብርቅ ሆነውብን የምንኖረው ምን አጥፍተን ነው ስልም በንዴት ተንጨረጨርኩ፡፡
እስቲ አንድ አነስተኛ ምግብ ቤት በምሣ ወይም በእራት ሰዓት ሂዱ፡፡ የምግብ ሜኖው ላይ አራትና አምስት ጊዜያት የተሰረዘበት የዋጋ ሰንጠረዥ ታገኛላችሁ፡፡ እኔማ ተስፋ የቆረጥኩት አንድ ቀን ጠዋት የዛሬ ስድስት ወር 80 ብር ይሸጥ የነበረ የፆም በየዓይነቱ፣ ይዘቱ ለውጥ ሳይደረግበት መጠኑ ቀንሶ 170 ብር ተብሎ ሲሸጥ ነው፡፡ የምግብ ቤቱን ባለቤት፣ ‹‹ምነው ግፍም አይደል…›› ብለው፣ ‹‹የዘንድሮን ኑሮ አላውቀውም እንዳትለኝ ብቻ…›› ሲለኝ ከዝምታ በስተቀር የምናገረው አልነበረኝም፡፡
እኛማ የማናውቀው ውስጣዊ ችግር አለብን እንጂ ይህችን የመሰለች ለም አገር ይዘን ምግብ አጥተን አንራብም ነበር፡፡ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀይሰን ለመላው አፍሪካ ገበያ መትረፍ የሚገባን ልሂቃን፣ የአዕምሮ ችግር ባይኖርብን ኖሮ እየራበን አንዴ በብሔር ሌላ ጊዜ በሃይማኖት ነገር እየተፈላለግን የዋሁን ሕዝባችንን አናስፈጅም ነበር፡፡ ናይሮቢና ዳሬሰላም ጎዳና ላይ ማንም ሰው በአነስተኛ ዋጋ የሚያገኛቸው ዶሮ፣ ሥጋ፣ ዓሳና የመሳሰሉ ምግቦች እንደ ሰማይ አይርቁንም ነበር፡፡ ከመሪ እስከ ተመሪ ያሉብን ውስጣዊ ደዌዎቻችን በፍጥነት ካልታከሙ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምንታወቅበት የረሃብ ማጣቀሻነት ተባብሶ እንደሚቀጥል ይሰማኛል፡፡
በቀደም ዕለት በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር) የሚመሩት የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ባቀረበው ጥናት፣ በኢትዮጵያ ያለው የምግብ ዋጋ ንረት ፈጣን ዕርምጃ ካልተወሰደበት ለአገር ሥጋት መደቀኑን አስጠንቅቋል፡፡ የዛሬን አያድርገውና የበየነ (ፕሮፌሰር) የፓርቲ አጋር የነበሩት መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹የሚበላው ያጣ ሕዝብ መሪውን ይበላል›› ያሉት ነገር እንዳይደርስ፣ ከወዲሁ የመፍትሔ ያለህ ማለት ያለበት መንግሥት መሆኑን በትህትና ማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡ ‹‹ውኃ ሲወስድ እያሳሰቀ ነው›› እንደሚባለው፣ በዚህ ጉዳይ ላይ መዘናጋት የሚያስከፍለው ዋጋ ከባድ መሆኑንም በአክብሮት አሳስባለሁ፡፡
(አምሳሉ አስረስ፣ ከባልደራስ ኮንዶሚኒየም)