ብዙ ጊዜያቸውን ከአርሶ አደሩ ማኅበረሰብ ጋር እንዳሳለፉ ይናገራሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት የአካባቢ ጥበቃ ሕግ መምህር የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር መለሰ ዳምጤ (ዶ/ር)፣ በላንድ ፎር ኢትዮጵያ ተቋምን ጨምሮ በተለያዩ መድረኮች የመሬት ሥሪትን የተመለከቱ በርካታ ጥናቶችን አቅርበዋል፡፡ የውጭ አገሮችን የመሬት ሥሪት ልምዶችም ያጠኑት ምሁሩ፣ ኢትዮጵያ ብትከተለው ይበጃል የሚሉትን ተሞክሮ በማካፈልም ይታወቃሉ፡፡ ከሰሞኑ መንግሥት የገጠር መሬት ባለቤትነትንና ግብይትን የተመለከተ ማሻሻያ በሁለተኛው አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አካቶ ማቅረቡ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ የታቀደው የገጠር መሬት አጠቃቀም ማሻሻያ በመሬት ሥሪቱና በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ስለሚኖረው ተፅዕኖና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ዮናስ አማረ ከመለስ (ዶ/ር) ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ሪፖርተር፡- የገጠር መሬትን መሸጥ መለወጥ እንዲሁም አስይዞ መበደር የሚፈቅድ አሠራር በሁለተኛው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅድ ውስጥ ተካቶ መቅረቡ ተሰምቷል፡፡ ይህ ታዲያ በመሬት ሥሪቱ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ ይመስልዎታል?
መለሰ (ዶ/ር)፡- እስካሁን ያለው የመሬት ሥሪት ለብዙ ነገሮች ማነቆ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ በግሌ ሶሻሊስታዊ የሆነውን መሬት በመንግሥት እጅ ሥር መቆየት አለበት የሚለውን አሠራርን አልደግፍም፡፡ ይህን የምለው ደግሞ መሬት በመንግሥት ባለቤትነት ብቻ መቆየቱ ከምርታማነት አኳያ ውጤታማ አይሆንም በሚል ነው፡፡ ሰው ለራሱ እስከሆነ በጣም በርትቶ ይሠራል፡፡ በሰው ንብረት (በሰው መሬት) ከሆነ ግን ብዙም አይተጋም፡፡ በኢትዮጵያ አርሶ አደሩ በእርግጥ ይለፋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ልፋቱ በዕውቀት፣ በካፒታልና በቴክኖሎጂ መታገዝ አለበት፡፡ አርሶ አደሩ ነባር አገር በቀል ዕውቀት የለውም እያልኩ አይደለም፡፡ ነገር ግን አሁን ካለው የዓለም ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አብሮ መሄድ አለበት፡፡ መሬት ላይ ኢንቨስት ባለመደረጉ የተነሳ፣ እንዲሁም መሬት ላይ ከደረሰው ጉዳት አንፃር በአገሪቱ ምርታማነትን በሚፈለገው ልክ መጨመር አልተቻለም፡፡
በቂ እርጥበትና ውኃ ባለበት አካባቢ ያሉና ትርፍ አምራች በሆኑ አካባቢዎች ገበሬው ደህና ሀብት ለማፍራት ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ባገኙት ትንሽ ሀብት ሎንቺና ይገዙበታል፣ ወፍጮ ቤትና ቡና ቤት ይከፍቱበታል፣ ወይም ከተማ መሬት ገዝተው ቤት ይሠሩበታል፡፡ ይህን ካፒታል መልሰው መሬታቸው ላይ ኢንቨስት ቢያደርጉት ኖሮ ግን መሬቱ የበለጠ ምርታማ ይሆናል፡፡ ግብርናውም ያድግ ነበር፡፡ ካፒታላቸውን ወደ መሬት ልማት እንዳይመልሱት ግን መሬቱን ነገ መጥቶ ማንም የሚወስደው ስለሆነ መተማመኛ የላቸውም፡፡ መንግሥት መሬቱን ከገበሬው ሲወስድ ደግሞ የሚከፍለው በጣም ትንሽ ነው፡፡ መንግሥት በትንሽ ክፍያ ከአርሶ አደሩ ወስዶ በከፍተኛ ብር በሊዝ እንደሚያከፋፍል ይታወቃል፡፡ በርካታ ገበሬዎች መሬታቸው ላይ ኢንቨስት ከማድረግ የሚቆጠቡት ነገ ይወሰድብኛል በሚል ሥጋት ነው፡፡ አንዳንድ አካባቢዎች መሬታቸውን በትንሽ ክፍያ ላለማጣት ሲሉ ባህር ዛፍ ይተክሉበታል፡፡ ባህር ዛፉ ተሸጦ ከሚያመጣው ትርፍ በተጨማሪ፣ መንግሥት ድንገት መሬቱን ልውሰድ ቢል ከባዶ የእርሻ መሬት ይልቅ የካሳ ክፍያ ግምቱ ከፍ ያለ ስለሚሆን ከዚያ ለመጠቀም በማሰብ ነው ዛፍ የሚተክሉበት፡፡
ገበሬዎች የራሳቸውን መሬት ለማስጠበቅ ወይም መፈናቀል ቢመጣ ጠቀም ያለ ካሳ ለማግኘት ሲሉ ብዙ ዓይነት ዘዴዎችን ሲጠቀሙ ይታያል፡፡ የሁሉም ክልሎች የመሬት ሕጎች በእርሻ መሬት ላይ ቤት መሥራትን አይፈቅዱም፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ ገበሬዎች ይህን ተላልፈው በእርሻ መሬታቸው ላይ ቤት ይሠራሉ፡፡ በተለይ ከተማ ገብ በሆኑ አካባቢዎች ያሉ አርሶ አደሮች በልጆቻቸው ስም ወይ በራሳቸው እርሻቸው ላይ ቤት ይሠራሉ፡፡ ባለፈው ጊዜ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስንሄድ ገጠር ውስጥ ጭምር እርሻቸው ላይ ቤት የሚሠሩ ገበሬዎች ገጥመውናል፡፡ ለምን እንደሆነ ስንጠይቅ ብዙዎቹ የነገሩን ደግሞ ነገ መንግሥት ቢወስድብን ለልጆቻችን ምን እናቆይላቸው በሚል ሥጋት እንደሆነ ነው፡፡ ይህ መሬትን የራስ አድርጎ የማቆየት ጥረት ደግሞ ገበሬውን ከግብርና ቢሮዎችና ከታች መዋቅር አመራሮች ጋር ሲያነታርከው ነው የታዘብነው፡፡
ገበሬው የሚያርሰው መሬት የራሱ እንደሆነ እርግጠኝነት እንዲሰማው ይፈልጋል፡፡ የራሱ መሆኑን ካረጋገጠ ደግሞ በጣም ትንሽ ይዞታ ብትኖረውን እሱ ላይ ያለውን በሙሉ ኢንቨስት በማድረግ እጅግ ከፍተኛ ምርት ማምረት ይችላል፡፡ በትንሽ መሬት ብዙ ማምረት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ኔዘርላንድስ በምትባል ትንሽ አገር እ.ኤ.አ. በ2021 ብቻ የግብርና ምርት የወጪ ንግዳቸው ገቢ 110 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ሪፖርት ሳገላብጥ አይቻለሁ፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ስትነፃፀር ኔዘርላንድስ የዝሆንና የቁንጫ ያህል የምታንስ ብትሆንም፣ ነገር ግን ባላት ትንሽ መሬት እኛ ቡናውን፣ ወርቁንና ስንቱን ነገር ልከን ከምናገኛት የሦስት ቢሊዮን ዶላር ኤክስፖርት ገቢ ብዙ እጥፍ የሚበልጥ ገንዘብ በግብርና ያገኛሉ፡፡ አገር ሀብታም የሚሆነው ትልቅ መሬት ስላለ አይደለም፡፡ አገር ሀብታም የሚሆነው በሥራ ነው፡፡ ሥራ ደግሞ በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ፣ በዕውቀት፣ ወዘተ ሲከወን ነው ውጤታማ የሚኮነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ግን የሁሉ መሠረት የሆነውን መሬትን አንቆ የያዘ አሠራር ነው በኢትዮጵያ ያለው፡፡ መሬት ጥቅም የለሽ ሀብት (Dead Capital) ነው በኢትዮጵያ፡፡
ሪፖርተር፡- አዲሱ የገጠር መሬት አጠቃቀም ትርጉም ያለው ማሻሻያ መሬትን ወደ ኢኮኖሚ መለወጥ ያስችላል፡፡ ምርታማነትንስ በምን መንገድ ያሳድጋል?
መለሰ (ዶ/ር)፡- ባለፈው ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው የከተማ መሬት ካድሬና ማንም የሚጫወትበት ሆኗል፣ ስለዚህ የከተማ መሬት በግል ይዞታ ሥር ቢሆን የተሻለ ነው ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ልክ እንደዚሁ የገጠር መሬትን በግል ይዞታ ሥር እንዲሆን ለማድረግ መታቀዱ የመሬትን ምርታማነት የሚለውጥ ነው እላለሁ፡፡ ለምሳሌ በገጠር ፋይናንስ አገልግሎት መሬት ልማትን ማገዝ የተባለው አዲሱ ሐሳብ በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ 80/85 በመቶው በገጠር የሚኖር ነው ይባላል፡፡ ከ120 ሚሊዮን ሕዝብ ወደ 90 ሚሊዮኑ የገጠር ነዋሪ ነው እንደ ማለት ነው፡፡ ይህን ሁሉ ሕዝብ አንድ ዓይነት ሥራ እንዲሠራ ለምን ይፈረድበታል? እርሻም ሆነ ከብት እርባታ ያው ሁለቱም ግብርና ነው፡፡ ግብርና መክሊቱ ያልሆነ እኮ ብዙ ሊኖር ይችላል፡፡ በሌሎች አገሮች መሬታቸውን ሸጠው ወይም አስይዘው ተበድረው በሚሳካላቸው ሥራ ላይ ተሰማርተው ውጤታማ የሆኑ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ በሌሎች አገሮች ከግብርና ወደ ሌላ ዘርፍ ቀይሮ ለመሥራት ብዙ አመቺ ዕድል አለ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ገበሬው ይህ ዕድል የለውም፡፡ ግብርና ጡረታ የለውም፡፡ ልጆች ወይ ዘመድ የሌለው ገበሬ በእርጅና ዘመኑ መሬቴን ሸጬ፣ ከተማ የሚከራይ ቤት ገዝቼ ራሴን ልጡር ብሎ ለማሰብ የኢትዮጵያ ገበሬ አይችልም፡፡ የመሬት ሥሪታችን አማራጭም ሆነ መፈናፈኛ የማይሰጥ ነው፡፡ ብዙ መሬትን መንግሥት በባለቤትነት መጠቅለሉ አዋጪ መንገድ አልሆነም፡፡ መሬት በመንግሥት እጅ አይሁን እያልኩ አይደለም፡፡ ነገር ግን አማራጭ የመሬት ሥሪቶች ሊኖሩ ይገባል፡፡ ከመንግሥት በተጨማሪ በግለሰብ ይዞታ ሥር መሬት እንዲሆን ይፈቀድ፡፡ የጋራ ወይም የወል መሬት ይኑር፡፡ መንግሥትና ማኅበረሰቡ በጋራ መሬት ሊኖራቸው ይችላል፡፡
ኮሎምቢያ በሚባል አገር ሄጄ እንደታዘብኩት ስምንት ዓይነት የመሬት ሥሪት አላቸው፡፡ እኛ ጋ ግን መሬትን በአንድ ይዞታ ሥር አስገብተነዋል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም ማስተዳደሩን እንኳ በቅጡ መንግሥት እየቻለበት አይደለም፡፡ መሬት ለጥቂቶች እጅግ በጣም በአጭር ጊዜ መክበሪያ ለአብዛኛው ግን ምንም የማይጠቅም ነው የሆነው፡፡ ግብርናን ለማሳደግ የማያግዝና የእርሻ ምርታማነትንም የማይጨምር አሠራር ነው የምንከተለው፡፡
ሪፖርተር፡- የተበጣጠሰ መሬት ያለው አርሶ አደር ይዞ መጠነኛ የመሬት ሥሪት ማሻሻያ በማድረግ ብቻ እንዴት ምርታማነትን ማሳደግ ይቻላል?
መለሰ (ዶ/ር)፡– ገጠር ውስጥ ሊሠራ የሚችለው ሥራ ማረስ ብቻ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ኮምፖስት ማምረትም ሌላ አዋጭ ሥራ ነው፡፡ በትንሽ ቦታ ምናልባትም ልክ እንደ ከተማ ይዞታ 500 ካሬ መሬት ያለው ሰው ሁሉ ለኮምፖስት የሚሆኑ ትሎች እያመረተ ሊሸጥ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በህንድ ትሎች (ቨርሚ ዎርምስ) እያመረቱ የሚተዳደሩ ሰዎች አሉ፡፡ ለማዳበሪያነት በኪሎ ነው የሚሸጡት፡፡ ባለቻቸው ትንሽ ቦታ ይህን እየሠሩ እንዲያውም ከሚያርሱ ሰዎች በላይ ሀብታም ሲሆኑ ይታያል፡፡ ገጠር ውስጥ ብዙ ዓይነት ሥራዎች መሠራት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህን ሥራዎች ለመሥራት ፋይናንስ፣ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሁሉ እንዲመጣ ደግሞ መሬቱን በተወሰነ ደረጃ ወደ ካፒታልነት መቀየር ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰፊ መሬት ብዙ ትሪሊዮን ዶላር ሊያወጣ ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ የካፒታል ምንጭ ዝም ብሎ ያለ ጥቅም ይኖራል፡፡
ማሻሻያ ተብሎ ከተቀመጠው ውስጥ በጋራ መሬትን መያዝና መጠቀም የሚል ነገር አለ፡፡ የጋራ መሬት ባለቤትነትን በሕግ ለመወሰን ስለመታቀዱ ተነግሯል፡፡ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ 456/2005 ላይ ለውጥ ለማድረግ ስለመታሰቡም ተነግሯል፡፡ ለውጥ ስለመደረጉ ቅሬታ የለኝም፡፡ እስካሁንም መቆየት የለበትም፡፡ እዚህ ላይ ግን በጋራ ሲባል ምን ለማለት ታስቦ ነው? እንደ ባልና ሚስት ያሉ ሰዎችን አንድ ላይ አሰባስቦ መሬታቸውን በጋራ ለማድረግ ነው፡፡ ብድር ሲፈልጉም በጋራ ብድር እንዲያገኙ ለማድረግ ነው የሚሉ ጥያቄዎች አልተብራሩም፡፡
በሕግ ዘንድ በጋራና በተናጠል (Joint and Several Liabilities) የሚባል ኃላፊነት አለ፡፡ በጋራ የሆኑ ሰዎች ከባንክ ቢበደሩና ኃላፊነታቸው ደግሞ በጋራና በተናጠል ነው ከተባለ፣ ባንኩ ሁሉንም ወይም የመረጠውን አንድ ሰው አሳዶ ሊያስከፍለው ይችላል ማለት ነው፡፡ ሰው መሬትን ወደ ካፒታል ለመቀየር በጋራ መሆን እንደ ግዴታ ከተቀመጠ ስንፍናን የሚያበረታታና ጉብዝናን የሚያዳክም ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ አሠራር ግልጽ አይደለም፡፡
በማሻሻያው የገጠር መሬትን ልክ እንደ ሊዝ መሬት መጠቀም የሚያስችል ነጥብ መካተቱ ግን እጅግ ጥሩ ጎን ነው ብዬ እወስደዋለሁ፡፡ ቢቻል መንግሥት የገጠር መሬት የአርሶ አደሮች ስለሆነ እኔ አያገባኝም ብሎ ከዚህ ነገር ውስጥ ቢወጣ ጥሩ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ገበሬው በመሬቱ መበደር ወይም መሸጥና መለወጥ ይችላል መባሉ ራሱ ትልቅ ዕርምጃ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ፡፡ ልክ እንደ ከተማ የሊዝ መሬት ለአርሶ አደሩ ባለቤትነትን መስጠት በጎ ነው፡፡ ሥራ መቀየር የሚፈልጉ ሰዎች አሉ፡፡ ሊታከሙ የሚፈልጉ ሰዎችም ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ ካላቸው መሬት ቆርሰው ሸጠው ወይም ተበድረው ታክሞ መዳንና ሌላ ሥራ መሥራት እየቻሉ ለምን ይከለከላሉ? ይህ ለውጥ የገጠር ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ የሚያደርግ ነው፡፡ ወደ 90 ሚሊዮን ሕዝቦች ይኖሩበታል የምንለው የገጠሩ ክፍል ሲነቃቃ ደግሞ አገሪቱን በእጅጉ ያነቃንቃል፡፡
ከተሞችም ቢሆን በዚህ ብዙ ይጠቀማሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ከተሞች የገጠሩን ነዋሪ መሬት የሚቀሙና የሚውጡ ይሆናሉ ሲባል እሰማለሁ፡፡ ይህ ግን ትክክለኛ አይደለም፡፡ በዘፈን ገጠሩ ናፈቀኝ፣ ገጠሩ ይሻላል ብሎ ማዜሙ ሊወደድ ይችላል፡፡ ነገር ግን ገጠሩ ይሻላል ብሎ ማንም ከተማ ከመኖር ሲመለስ አላየንም፡፡ በየቀኑ ወደ ከተማ የሚመጣው ብዙ ነው፡፡ ከተማ በትንሽ ቦታ ብዙ ሐሳብና ብዙ የሥራ ዕድል የሚገኝበት፣ መሠረተ ልማት፣ ትምህርት፣ ቴክኖሎጂ፣ ሥልጣኔና የብዙ ነገሮች ማዕከል የሚሆን ቦታ ነው፡፡ በአፍሪካ ደረጃ የከተማ ዕድገት ወደ 40 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ የእኛ ግን 20 በመቶ አካባቢ ነው፡፡ የእኛ የከተማ ዕድገቱአዝጋሚ ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ እኮ እስከ 60 በመቶ ደርሷል፡፡ ከተማ የት ይቋቋምኧ እንዲሁም በፕላን መመራት አለበት የሚለው ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ማደጉና መስፋፋቱ ሊጠላ አይገባም፡፡ የከተሞች ማደግ ለገጠሩ ሕይወት አደጋና ሥጋት ነው ብሎ መፈረጁ አግባብ አይደለም፡፡ ዓለም በሙሉ ወደ ከተሜነት እየሄደ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ከዚህ ለውጥ ውጪ ልትሆን አትችልም፡፡ ከተሞች ማደጋቸው የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ በዘፈቀደ ሳይሆን በዕቅድ ይደጉ ነው መባል ያለበት፡፡
ሪፖርተር፡- የግል መሬት ባለቤትነት ቢፈቀድ በጥቂቶች የመሬት ቅርምት ይፈጠራል የሚል ሥጋት አለ እኮ?
መለሰ (ዶ/ር)፡– መሬት በጥቂቶች እጅ እንዲገባ አልፈልግም፡፡ ጥቂቶች እንዲጠቀልሉትና እንዲቀራመቱት አልደግፍም፡፡ ለዚህ ደግሞ አንድ ሰው ምን ያህል መሬት መያዝ እንደሚችል ጣሪያ መቀመጥ አለበት፡፡ እንደ አካባቢው፣ እንደ ክልሉ ወይም እንደ ወረዳው ነባራዊ ሁኔታ አንድ ሰው መሬት ሲገዛ ከዚህ ሔክታር መሬት በላይ መግዛት አትችልም ተብሎ መጠን ሊቀመጥ ይገባል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ ምጣኔን ማስቀመጥ ተገቢ ነው ብዬ አላስብም፡፡ አሁን መንግሥት መሬት አያከፋፍልም፡፡ ነገር ግን ሰው ራሱ በውርስ ከልጅ ወደ ልጅ እያከፋፈለ የገበሬው ይዞታ በጣም የተበጣጠሰ ሆኗል፡፡ ሕጉ ከሚፈቅደው በታች መሬት ተበጣጥሷል፡፡ በመስኖ ሊለሙ በሚችሉ ቦታዎች መሬት በጣም ትንሽ እስኪሆን ሊከፋፈል ይችላል፡፡ ነገር ግን በመስኖ በማይለማ አካባቢ የመሬት መበጣጠስን ሕጉ ይገድበዋል፡፡ ሰው ግን ሕጉን አይጠብቅም፡፡ እንደሚታወቀው የመሬት ፍላጎቱ ከሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ ዕድገት ጋር አብሮ በጣም ጨምሯል፡፡ ሥራ አጥነት ደግሞ በአገሪቱ ችግር ነው፡፡ ተምሮ ሥራ ያጣና ወደ ግብርና የሚመለስ የገበሬ ልጅ ብዙ ነው፡፡ ስለዚህ የወላጆቹን መሬት የሚከፋፈለው ብዙ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ማሻሻያው ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ጋር አይጋጭም?
መለሰ (ዶ/ር)፡- ሪፖርተር ባለፈው ሳምንት በሠራው ዘገባ ላይም የተጠቀሱት ሰው፣ መሬት የማን እንደሆነ ከሚያስቀምጠው የሕገ መንግሥት ድንጋጌ ጋር እንደማይጋጭ መግለጻቸው ተጽፏል፡፡ መሬትን ለረዥም ጊዜ የራስ አድርጎ ለመጠቀም እስከተፈቀደ ድረስ ባለቤትነቱ የመንግሥት ነው የሚለው ድንጋጌ ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን የብሔር ብሔረሰቦች ይሆናል ተብሎ የሚቀጥል ከሆነ አዲሱ አሠራር ከነባሩ ችግር አይላቀቅም፡፡ በአንድ አካባቢ ያለ ባለመሬት መሬቱን የሚሸጠው የገዥውን ብሔር መሠረት አድርጎ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ሕገ መንግሥቱ መሬትን የንግሥት ነው ይልና የብሔር ብሔረሰቦች እንደሆነም ይደነግጋል፡፡ ይህ የመሬት ባለቤትነት ደግሞ እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ አንድ ሰው መሬት ገዝቼ ልሥራ ቢል የሚገዛው መሬት ባለቤት ብሔረሰብ አባል መሆን አለበት ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሌላ አገር ሄደው መሬት ገዝተው ሊያርሱ ይችላሉ፡፡ ቅድም በጠቀስናት ትንሽቱ ኔዘርላንድስን ጨምሮ በብዙ አገሮች መሬት ይዘው ግብርና ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ እዚህ አገራቸው ሲሆን ግን ይህን ዕድል መነፈጋቸው እጅግ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡
ምናልባትም ለአገሩ ሉዓላዊነት ሲዋደቅ አካል ጉዳተኛ የሆነ የመከላከያ አባል አንድ አካባቢ ትንሽ መሬት ይዞ መጦሪያ የሚሆን ሥራ ልሥራ በሚል ጊዜ፣ ብሔርህ አይፈቅድም ቢባል የሚደርስበት የሥነ ልቦና ውድቀት ቀላል አይሆንም፡፡ አዲሱ ማሻሻያም የዜጎችን የአገር ባለቤትነት ግምት ውስጥ ማስገባት አለበት፡፡ አሁን ባሉ የክልል ሕገ መንግሥታት ሁሉም ሰው የመሬት ባለቤት መሆን እንደሚችል የሚደነግጉ ሕጎች ብዙም የላቸውም፡፡ በአጠቃላይ ማሻሻያው መሬት የብሔር ብሔረሰቦች ነው ከሚለው ሕግ ጋር ታርቆ ለመሄድ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ይገጥመዋል ነው የምለው፡፡
ሪፖርተር፡- ማሻሻያው የመሬት ሥሪቱን ሙሉ ለሙሉ የማይቀይር አነስተኛ የለውጥ ዕርምጃ ነው ይባላል፡፡ ከዚህ በፊትም ሕገ መንግሥቱና መሠረታዊ ነገሮች ሳይነኩ መለስተኛ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡ የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት መስጠትን የመሳሰሉ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ሆኖም መሠረታዊ ችግሮችን የሚቀይሩ ባለመሆናቸው አልተሳኩም ይባላል፡፡ የአሁኑ ከእነዚያ በምን ይለያል?
መለሰ (ዶ/ር)፡- ሰርተፊኬትና ምዝገባው ከአሁኑ በጣም የተለየ ነው፡፡ ያኛው ምንም ዓይነት በሊዝ የመጠቀም መብትን የሚሰጥ አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ገበሬው መሬት በነፃ የማግኘት መብት እንዳለውና ከመሬቱ ያለ መነቀል መብት እንዳለው ያስቀምጣል፡፡ ነገር ግን መልሶ መንግሥት ለጋራ ወይም ለሕዝብ ጥቅም ሲባል መሬቱን መውሰድ እንደሚችል ይናገራል፡፡ ይህ የሚጋጭ ሕግ ደግሞ በገበሬው ላይ የመሬት ዋስትና ጥያቄ የሚያስነሳ ነበር፡፡
ሰርተፊኬት የመስጠቱ ሥራ የመጀመሪያው ምዕራፍ ተሠርቶ አሁን ሁለተኛው ምዕራፍ እየተካሄደ ነው፡፡ አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብም የተወሰነ ሰርተፊኬት ሰጥተዋል፡፡ ይህ ገበሬውን የመሬት ባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው ተብሎ የተሠራ ነው፡፡ ወደ ገጠር የፋይናንስ ተጠቃሚነት ለማስፋት አስተዋጽኦ አልነበረውም፡፡ ገበሬውን ከመሬቴ አልፈናቀልም የሚል ሥነ ልቦናዊ ዕርካታ ከመስጠት ባለፈ ከመሬቱ የተለየ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲያገኝ አያደርገውም፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የመሬት ምዝገባና ሰርተፊኬት ሥራ እየተካሄደ ያለው በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመሆኑ፣ የገበሬው ወሰን ከየት እስከ የት ድረስ እንደሆነ በደንብ እንዲታወቅ አድርጎታል፡፡ አሠራሩ ከሰጣቸው ትልቅ ጥቅሞች አንዱ ይህ ነው፡፡ ማንም እየተነሳ የማንንም መሬት እንዳይነጥቅ የሚያደርግ ነው፡፡ የተመዘገቡ መሬቶች ወሰን እያንዳንዱ ነጠብጣብ ስለሚታወቅ፣ ደካማ ነው ወይም ጠያቂ የለውም እየተባለ በአንዳንድ ጉልበተኞች አቅመ ደካማው መሬቱ እንዳይነጠቅ አድርጎታል፡፡ የወሰን ጭቅጭቅንም የሚፈታ አሠራር ነው፡፡ የገበሬው ጥያቄ ግን ወሰን ማስከበር ብቻ ሳይሆን፣ መሬቴ ላይ የፈለግኩትን ባለማ ማንም ድንገት ተነስቶ ልቀቅ እንዳይለኝ ይደረግ የሚል ነበር፡፡ የአሁኑ አሠራር ደግሞ ባለቤትነትን በተግባር የሚያረጋግጥ በመሆኑ፣ ገበሬው እርግጠኛ ሆኖ በመሬቱ ላይ የፈለገውን ዓይነት ልማት መሥራት እንዲችል ያበረታታዋል፡፡ ገበሬው የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማግኘቱ አሥር ብር እንኳ ከባንክ ለመበደር የሚያበቃ አልነበረም፡፡ አሁን ግን በመሬቱ መበደርና መሥራት ይችላል፡፡ አበዳሪውም ቢሆን ብድሩ ባይመለስለት እንኳ መሬቱን ወደ ገንዘብ መለወጥና ማስመለስ ይችላል፡፡ በአዲሱ አሠራር መሬቱ ለኢንቨስትመንት ቢሰጥ እንኳን ለመሟገትና ይገባኛል የሚለውን ካሳ ለመጠየቅ ያስችለዋል፡፡
በከተማ ውስጥ መሬትና መሬት ላይ ያለ ንብረትን መሸጥ መለወጥ በመቻሉ፣ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ መንግሥትም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጥቅም ያገኛል፡፡ የመሬት መገላበጥ ኢኮኖሚን የሚያነቃንቅ ነው፡፡ መንግሥት ከቤት ሽያጭ እስከ ስድስት በመቶ የአሹራ ገቢ ያገኛል፡፡ ከትልልቅ ቤቶች ሽያጭ የሚያገኘው ከዚህም ይበልጣል፡፡ ይህ አሠራር ደግሞ ገጠር ውስጥ ቢገባ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ለአገር ከፍተኛ ነው፡፡ እግዚአብሔር እውነት ባደረገልን እንጂ አዲሱ የገጠር መሬት ማሻሻያ ሙት ሆኖ የቆየውን የመሬት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በእጅጉ ያነሳዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱንም ቢሆን መለወጥ ላያስፈልግ ይችላል፡፡ ይህን በአዋጅ በቶሎ ወደ ሥራ ማስገባት ከተቻለ ለአገሪቱ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ያለፍንበት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ቆፈን ገና አልለቀቀንም፡፡ በአንዴ ሕገ መንግሥትን የመቀየር ዓይነት ትልቅ ለውጥም ለማምጣት ከባድ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ይህን አንፃራዊ ማሻሻያም ቢሆን በተግባር ከተረጎምነው ውጤቱ ትልቅ ነው፡፡ በግሌ ሕገ መንግሥቱ ላይ ያለው የመሬት ባለቤትነት እንዲቀየር ብፈልግም፡፡ ያ ዕውን እስኪሆን የገጠር መሬትን ወደ ኢኮኖሚ መቀየር ከተቻለ በራሱ ጥሩ ጅምር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲና ስትራቴጂ አለመኖሩ ከሕገ መንግሥቱ በተጓዳኝ ትልቅ እንቅፋት ነው ይባላል፡፡ በመሬት አጠቃቀም ላይ አንፃራዊ ማሻሻያ መደረጉ ይህን የፖሊሲና የስትራቴጂ ክፍተት ይተካል?
መለሰ (ዶ/ር)፡– በፍፁም አይተካውም፡፡ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ አለመኖር ትልቁ ጉድለታችንና ራስ ምታታችን ነው፡፡ ከተሞች በዕቅድና በፕላን መመራት አለባቸው ብለን አውስተናል፡፡ በዕቅድና ፕላን ሲባል ግን ለምሳሌ ለመስኖ የሰጠና ለእርሻ እጅግ የተመቸ ለም መሬትን የከተማ ቦታ ማድረግ ትክክል አይደለም፡፡ ውኃ ገብ ሆነው ለእርሻ የማይመቹ ቦታዎች አሉ፡፡ እነሱን ከተማ ማድረግ ይቻላል፡፡ ከአራት ዓመታት በፊት ለጋምቤላ ክልል የመሬት አጠቃቀም ዕቅድ ሠርተን ነበር፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሠራው በዚህ ዕቅድ ብዙ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ የሕግ ጉዳዩን በተመለከተ እኔ ነበርኩ፡፡ ጥናት ሲደረግ ከቀረቡ ምክረ ሐሳቦች አንዱ የክልሉ መዲና ጋምቤላ ከተማ አሁን ካለበት ቦታ ባይሰፋ የሚል ይገኝበታል፡፡ ከተማው አሁን ያለበት ቦታ ለእርሻ በእጅጉ የሚመች ለም መሬት ነው፡፡ ከከተማው በሀቦቦ አቅጣጫ ጥቂት ወጣ ብሎ ግን ለከተማ መስፋፋት እጅግ የተመቸ ቦታ እንዳለ ተረጋገጠ፡፡ ቦታው ለግብርናም ሆነ ለደን የማይመች ነው፡፡ በከርሰ ምድሩ ውስጥም የተለየ የማዕድን ክምችት የለውም፡፡ ከዚያ ይልቅ ይህን ቦታ ለጋምቤላ ከተማ መስፋፋት ማዋል እንደሚቻል ተረጋግጧል፡፡ ይህ እንግዲህ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ቢኖረንና በሁሉም የአገራችን ክፍል ቢተገበር ውጤታማ የመሬት አጠቃቀም ሊኖረን እንደሚችል የሚጠቁም ነው፡፡
የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲው ብቻም ሳይሆን ዘርፉን የሚመራ ተቋምም የለንም፡፡ ሁሉ ነገር የሚሠራው መሬት ላይ ነው፡፡ ትራንስፖርት፣ እርሻው፣ ኢንዱስትሪው፣ ግድቡ፣ ከተማው፣ ወዘተ የሚሠራው መሬት ላይ ነው፡፡ ሁሉም ዘርፎች ደግሞ የሚመራቸው ሚኒስቴር ተቋም አላቸው፡፡ መሬት ግን የለውም፡፡ የሁሉም መሠረትና የበላይ ሆኖ ከሁሉም ወደኋላ ቀረ፡፡ እንደ ኡጋንዳና ሩዋንዳ የመሳሰሉ የአፍሪካ አገሮች ከሁሉም ሚኒስቴሮች ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡ እኛ ጋ የውጭ ጉዳይ መከላከያ የመሳሰሉት ከሌላው ጎልተው ቢጠሩም፣ በሌላው አገር ግን የመሬት ሚኒስቴር ከእነዚህ ያልተናነሰ ግዝፈት ተሰጥቶት ይታያል፡፡ ዘርፉን የሚመራው ተቋም የትኛው መሬት ለየትኛው ዘርፍ መዋል እንዳለበት ይወስናል፡፡ ሌሎች ዘርፎች የሚያቀርቡትን የመሬት ፍላጎት ተከትሎ ምላሽ ይሰጣል፡፡ ማንም መሥሪያ ቤት ተነስቶ አንድ መሬትን ለዚህ ሥራ ላውል ነው ብሎ አይወስንም፡፡ የመሬት ሚኒስቴር የአገሪቱን መሬት እያጠና ለምን አገልግሎት እንደሚውል ዕቅድ ያወጣል፡፡ ሁሉንም ሚኒስቴር ተቋማት እያማከረ ለሚቀርብለት ጥያቄ መልስ ይሰጣል እንጂ፣ እያንዳንዱ ተቋም በተናጠል የሚወስንበት አሠራር የለም፡፡
በአንድ ወቅት በአንድ የጥናት መድረክ ላይ ሦስት መሥሪያ ቤቶች ብቻ፣ የኢትዮጵያን 166 በመቶ የሆነ የመሬት ፍላጎት ማቅረባቸውን የተመለከተ ጥናት ቀርቦ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ከኬንያና ከጂቡቲ ጋር ተደምራ ካልሆነ የጠየቁት የመሬት ፍላጎት የሚመለስ አልነበረም፡፡ የመሬት ጉዳይን በቀጥታ የሚመራ ተቋም ባለመኖሩ የተነሳ የሚቀርበው የመሬት ፍላጎት እጅግ የተለጠጠ ይሆናል፡፡ ሦስቱ መሥሪያ ቤቶች የፈለጉት መሬት ኢትዮጵያ አልነበራትም፡፡ በኢትዮጵያ በመሬት ፍላጎት የተነሳ ምናልባት በፌደራል ደረጃ ግጭት ባይኖር እንኳ ወደ ወረዳ ሲኬድ ግን ብዙ ውዝግብ ሲነሳ ይታያል፡፡ በወረዳዎች ደረጃ የተለያዩ መሬቶችን አጠቃቀም በተመለከተ አሠራር አላቸው፡፡ የሰመረ ዕቅድ ባይሆንም ለተለያዩ አገልግሎቶች መሬት የመመደብ ነገር አለ፡፡ ሆኖም ለአንድ ሥራ የተባለ መሬት ላይ ሌላ ነገር እየተሠራ ብዙ ጭቅጭቅ ሲፈጠር ይታያል፡፡ እስከ ክልል መስተዳድር የደረሰ ከፍተኛ ጭቅጭቅ ይፈጠራል፡፡
መንግሥት ይህን ችግር ያውቀዋል፡፡ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲና ተቋም ባለመኖሩ፣ ችግሩ እንደሚፈጠር መንግሥት በተደጋጋሚ በጥናትም ቀርቦለታል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ዘመን ዕቅዱ ይወጣል ብሎ ብዙ መነቃቃት መንግሥት አሳይቶ የነበረ ቢሆንም፣ ከለውጡ በኋላ ግን ከስሟል፡፡ ምናልባት ሌላ አንገብጋቢ ነገር ይሠራ በሚል ቅድሚያ እንዳይሰጠው የሚያደርግ ሐሳብ በማዘንበሉ ሊሆን ይችላል የቀረው፡፡ ሆኖም ጉዳዩ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ መንገዶች በየት በኩል ይሠሩ፣ እርሻው የት ጋ ይሠራ፣ ኢንዱስትሪው ወይም ግድቡ የት ቦታ ይተከል የሚሉ ጥያቄዎች ሁሉ የሚመለሱት ይህ ሲቀድም ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም ለእርሻ ተብሎ ብቻ አይቆምም፡፡ ወደ ታች ለጤፍ፣ ለገብስ፣ ስንዴ፣ ማሽላ፣ በቆሎ እየተባለ በየሰብሉ አመቺነት ዕቅዱ ሊወርድ ይችላል፡፡ ገበሬው በራሱ ነባር አገር በቀል ዕውቀት ተመሥርቶ አካባቢውን (አግሮ ኢኮሎጂውን) የተስማማ የእርሻ ሥራ ይሠራል፡፡ ጎጃምና አድዓ አካባቢ ጤፍ ነው የሚዘራው፡፡ አርሲና ባሌ ደግሞ ገብስ፡፡ ሌላ አካባቢም ተስማሚ ሰብል ይመረታል፡፡ ይህ ግን በአገር ደረጃ በፖሊሲና በዕቅድ የተደገፈ ወይም በተቋም የተመራ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- አዲሱ የገጠር መሬት አጠቃቀም ማሻሻያ ሐሳብ የምዕራባዊያንና የውጭ ፋይናንስ ምንጮችን ጫና የተከተለ ነው? የኢኮኖሚ ሪፎርሙም ቢሆን የውጭ ጫና አለበት ይባላል፡፡ በዚያ ውስጥ የተካተተው ዕቅድ የዚህ ግፊት ውጤት አያሰኘውም?
መለሰ (ዶ/ር)፡- ለዚህ ግምቴን እንጂ በተጨባጭ መረጃ የተደገፈ ነገር መናገር ይከብደኛል፡፡ ምዕራባዊያን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች ላይ የፖሊሲ ጫና ለማሳደር መሞከራቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ ጫና የሚያሳርፉት ደግሞ ለእኛ ብለው ሳይሆን ለራሳቸው ጥቅም መሆኑን እናውቃለን፡፡ እኔ በግሌ ሶሻሊስታዊ ሥርዓት ሳይሆን ካፒታሊስት የሆነው መንገድ ለአገር ይበጃል ብልም፣ በአንድ መንገድ ጭልጥ ብሎ መንጎድን ግን እያበረታታሁ አይደለም፡፡ ትልቁና ዋናው የኢኮኖሚ ችግራችን ምርትና ምራታማነት ነው፡፡ ፍላጎት ያድጋል፣ ምርት ግን እያደገ አይደለም፡፡ ዛሬ በዜና ኢትዮጵያ በምግብ ዋጋ ግሽበት ዚምባብዌን ተከትላ በአፍሪካ ሁለተኛ፣ በዓለም ደግሞ ስምንተኛ ሆነች የሚል መረጃ ሰምተናል፡፡
ምዕራባዊያን የእኛን እጅ የመጠምዘዝ ፍላጎታቸው የዓባይ ምንጭ በመሆናችን ወይም ሌላ ሴራ ሊኖረው ይችላል፡፡ ሴራውን ትተን ግን በግርድፉ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ የመሬት ፖሊሲያችሁን ካልቀየራችሁ ብድርም ሆነ ዕርዳታ አንሰጥም ሊሉ እንደሚችሉ ሚዛን በሚደፋ ሁኔታ መገመት እንችላለን፡፡ በሌላም አገር ይላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም እኛንም ሲሉን እናውቃለን፡፡ ይሁን እንጂ ለውጡ በማንም ጫና ቢመጣ እኛን ጠቅሞናል ወይስ ጎድቶናል በሚል ሚዛን መፈተሽ ነው ያለበት፡፡ በእነሱ ፖሊሲም ቢሆን የተጠቀመ አገር መኖሩን ማጤን አለብን፡፡ ደቡብ ኮሪያና ሰሜን ኮሪያን እናነፃፅር፡፡ ሰሜን ኮሪያ ግትር ብላ ቆማ ምዕራባዊያኑን ታግላለች፡፡ ከደርግ ጋርም በነበራት ጠንካራ ወዳጅነት እኛ ለእሷ አጋርነት ለማሳየት ስንል፣ እነ በላይነህ ዲንሳሞ ጠንካራ በነበሩ ጊዜ የሲኦል ኦሎምፒክን አንሳተፍም ብለን ቀርተናል፡፡ ነገር ግን ደቡብ ኮሪያዎቹ ምዕራባዊያኑን በመጠጋታቸው በጣም እንደተጠቀሙ ዓይተናል፡፡ ጃፓንም ብትሆን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከምዕራባዊያኑ ብዙ ተጠቅማለች፡፡ ቬትናም በእነሱ ምክር ነበር ቡናን የጀመረችው፡፡ ዛሬ ከእኛ በላይ ቡና ሻጭ ሆናለች፡፡ ምዕራባዊያኑ የሚሰጡትን ብድርና ዕርዳታ ተማምኖ ሁል ጊዜ መኖር ትክክለኛ አይደለም፡፡ እንዲያውም አደገኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ጠንክሮ በራስ እግር ለመቆም የእነሱን ድጋፍ እንደ መነሻ መጠቀሙ ምንም ኃጢያት የለውም፡፡ በእነሱ ተረጂ በመሆን አዙሪት ውስጥ መቀጠሉ ግን አደገኛ ነው፡፡ አሁን ተፅዕኖ አያደርጉብንም ብዬ ለእነሱ ባልከራከርም ይህን ያደረጉት እነሱ ናቸው ብዬ ለመደምደምም አልችልም፡፡
ሪፖርተር፡– ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ በመነሳት ለእኛ አዋጭ የመሬት ሥሪት ምን ዓይነት ቢሆን የተሻለ ነው ይላሉ?
መለሰ (ዶ/ር)፡– የተለያዩ አሠራሮችን የቀየጠ ድብልቅ ቢሆን ይሻላል፡፡ ወጥ መሆኑ ጥሩ አይደለም፡፡ በኮሎምቢያ አሉ ካልኳቸው ስምንት የመሬት ሥሪቶች መካከል የመንግሥት፣ የግልና የማኅበር አሉ፡፡ አራተኛው ደግሞ ‹ሬስ ጓርዶስ› ብለው የሚጠሩት አሠራር አላቸው፡፡ መሬቱና ደኑ ቀይ ህንዶች (ሬድ ኢንዲያንስ) እያሉ ይጠሯቸው የነበሩ ነባር (ኔቲቭ) ሕዝቦች ነው የሚል ድንጋጌን የተከተለ ነው፡፡ አንዳንዴ መሬቱና ደኑ የእነሱ ነው ይባልና ሁለት ወይም ሦስት ሜትር ወደ ታች ጠልቆ ካለው መሬት ውስጥ የሚገኘው ማዕድን ወይም ነዳጅ የመንግሥት ነው ሊባል ይችላል፡፡ ይህን የከርሰ ምድር ሀብት ደግሞ መጠቀም የሚቻለው እነሱን አስፈቅዶና ይሁንታቸውን አግኝቶ ነው ተብሎ ሊደነገግ ይችላል፡፡ በዚህ ሕግ ነባር ሕዝቦቹ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ስለሚኖራቸው ያለ ፈቃዳቸው መሬቱ የፈለገ ሀብት ቢኖረውም መንግሥትም ሆነ ማንም አይነካውም፡፡ በሌላው አገር ልክ እንዲህ ያሉ ውስብስብ የመሬት አሠራሮች ይታያሉ፡፡
ኢትዮጵያ እንዲህ ያሉ ውስብስብ ነገሮች ውስጥ እንድትገባ አልፈልግም፡፡ በግሌ በመንግሥት እጅ ብዙ መሬት ቢኖር ችግር የለብኝም፡፡ የተፈጥሮ ደኖች፣ ወንዞች፣ ሐይቆች፣ ወዘተ የማንም ሊሆኑ ስለማይችሉ የመንግሥት ነው መሆን ያለባቸው፡፡ ከዚያ ጎን ለጎን ግን የአንድ አካባቢ ማኅበረሰብ የጋራ መሬትም ሊኖር ይገባል፡፡ ሊሸጡት ሊለውጡት የማይችሉት ቢሆንም ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን የመጠቀም መብትን በማከራየት፣ በኮንትራትና በትብብር አሳልፈው በመስጠት የጋራ መሬቱን ሊጠቀሙበት የሚያስችል ለቀቅ ያለ አሠራር ያስፈልጋል፡፡ ሦስተኛው ደግሞ የግለሰብ መሬት ባለቤትነት መብት መሰጠት ነው፡፡ አርሶ አደርም ሆነ አርብቶ አደር ወይ ሌላ ዜጋ መሸጥ መለወጥ የሚችለው መሬት ሊፈቀድለት ይገባል፡፡ ከፊል አርብቶ አደር ተብሎ ወይም በሌላ መንገድ አርብቶ አደሩም የተከለለ መሬት ሊኖረው ይገባል፡፡ ምክንያቱም አርብቶ አደርነት ዘላቂ የሆነ የኑሮ መሠረት መሆኑ በተፈጥሮና በብዙ አስገዳጅ ምክንያቶች እየቀነሰ ሊሄድ ይችላል፡፡ መሬት በአገራችን ከዳር ዳር የመንግሥት ተብሎ በአንድ ወጥ አሠራር ይሁን ከማለት፣ እነዚህን ሦስት መንገዶች ቀይጦ መከተል የተሻለ ነው እላለሁ፡፡ የመንግሥትም፣ የጋራም፣ የግልም መሬት ይኑር፡፡ የሕዝብ ቁጥር እየጨመረና የመሬት ፍላጎቱ እያደገ ነው፡፡ የመሬታችን መጠን ደግሞ ተዓምር ካልተፈጠረ በስተቀር አገሪቱ አሁን ካላት ሊሰፋ የሚችል ባለመሆኑ አጠቃቀሙ ላይ ዘመናዊና አዋጭ መንገዶችን መከተል ፍትሐዊ የመሬት ባለቤትነት ያሰፍናል እላለሁ፡፡ ራሳችንን መመገብ የሚያስችልና ቁልቁል ሳይሆን ወደ ላይ ለማደግ የሚያግዝ የመሬት አጠቃቀም ሊኖረን ይገባል፡፡