Friday, July 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ተገንዝቤ የአቶ ማሞን ሹመት ሳየው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትክክለኛ ውሳኔ እንደሰጡ ነው የሚመሰማኝ›› አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) አዳዲስ ሹመቶችን ሰጥተዋል፡፡ አቶ ማሞ ምሕረቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ሆነው መሾማቸው ግን ከሌሎች በተለየ የተለያዩ አስተያየቶች ሲስተናገዱበት ነበር፡፡ በተለይ ‹‹ይህ የኃላፊነት ቦታ አይገባቸውም›› በሚል የተሰጡ አስተያየቶች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲዘዋወሩ ነበር፡፡ እንዲህ ያሉት አስተያየቶች የተሰነዘሩበት ምክንያት ተሿሚው በፋይናንስ የሥራ ዘርፍ ልምድ የላቸውም የትምህርት ዝግጅታቸውም ከፋይናንስ ሥራ ጋር የተገናኘ አይደለም ከሚል የመነጨ ነው። ታዋቂው የፋይናንስ ባለሙያው አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ ግን፣ የአቶ ማሞን ሹመት በመንቀፍ የተሰጡ አስተያየቶችን ተገቢነት የሌላቸው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ አዲሱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥን በቅርብ የሚያውቋቸው በመሆኑ፣ ብዙዎች ትችቶች የመረጃ እጥረት ያለባቸው ከመሆኑም በላይ፣ ነገሮችን ያለመገንዘብ ሁኔታዎችን እንደተመለከቱባቸው ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ሹመትና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ዳዊት ታዬ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉን አነጋግሯቿል፡፡  

ሪፖርተርጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) ከሰሞኑ አዳዲስ ሹመቶችን ሰጥተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል አቶ ማሞ ምሕረቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አድርገው መሰየማቸው ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህንን ሹመት እርስዎ እንዴት ያዩታል?

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- ይህ ጉዳይ ቀደም ብሎም ተወርቶ ነበር፡፡ ‹‹አቶ ማሞ ምሕረቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይሆናሉ፤›› የሚለውን ወሬ ከሰማሁበት ጊዜ ጀምሮ በሁለት ምክንያት ነገሮችን አወጣና አወርድ ነበር፡፡ አንደኛ አቶ ማሞን ለረዥም ጊዜ ስለማውቃቸው ነው፡፡ በተለያየ ጊዜ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሁኔታ፣ የአገራችንን የግል ዘርፍ በተመለከቱ ጉዳዮች በተነሱባቸው መድረኮች ላይ ተገናኝተናል፡፡ እንደምታውቀው የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤቶች ምክትል ፕሬዚዳንትነትና ፕሬዚዳንትነት በመሆን ለአሥር ዓመታት ባገለገልኩበት ወቅት እሳቸውን በደንብ እንዳውቃቸው አድርጎኛል፡፡ አቶ ማሞን በይበልጥ ያወቅኳቸውም የአይኤፍሲ (IFC) ኦፊሰር ሆነው ከግል ዘርፉ ጋር ሲሠሩ በነበረበት ወቅት ነው ማለት እችላለሁ፡፡ አቶ ማሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይሆናሉ የሚለውን ጭምጭምታ ብሰማም አልጠየኳቸውም፡፡ በግል ባውቃቸውም ስንገናኝ እንዲህ ሊሆኑ ነው ወይ? ብዬ አልጠየቅኋቸውም፡፡ ሁለተኛው ከየአቅጣጫው ሰዎች የሚሰጧቸውን አስተያየቶች በቅርብ እየተከታተልኩ ስለነበር ነገሩ ብዥታን ፈጥሮብኝ ነበር፡፡ በግል ግን ከመሾማች ከጥቂት ጊዜያት በፊት አግኝቻቸው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ቢሮዋቸውን አይቻለሁ፡፡ ስለዚህ በሹመታቸው ዙሪያ ባልጠይቃቸውም የእሳቸው መሾም ተገቢ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሌላው ሹመታቸውን ከመስማቴ በፊት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪዎች አንዱና ለረዥም ጊዜ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ የነበሩት አቶ ተክለወልድ አጥናፉ የሁለተኛውን አገር በቀል የልማት ዕቅድ በተመለከተ  የሰጡትን ማብራሪያ ከሪፖርተር ጋዜጣ ላይ አንብቤ ስለነበር፣ አቶ ማሞ ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መጡ የሚለውን እንደሰማሁ ወዲያው የታወሰኝ ይኼው አቶ ተክለወልድ ከዓለም ባንክ ጋር መደረግ ስላለበት ድርድር የሰጡትን ማብራሪያ ነው፡፡ ማብራሪያውንም ከአቶ ማሞ ሹመት ጋር ማያያዝ ሞክሬያለሁ፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮችንም በማሰብ ሹመታቸው አግባብ እንደሆነ እንዳምን አድርጎኛል፡፡ 

ሪፖርተርአንዳንድ ወገኖች ግን በእሳቸው ሹመት ዙሪያ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ተሰምተዋል፡፡ በተለይ የባንክ ሥራን በመምራትም ሆነ በንግድ ባንኮች ውስጥ አገልግለው የማያውቁ ከመሆናቸው አንፃር ሹመቱ አግባብ አይደለም ይላሉ፡፡ ሌሎች የተለያዩ ነቀፌታዊ አስተያየቶችም እየተደመጡ ከመሆኑ እንፃር የእርስዎ ምልከታ ምንድነው? 

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- ከሰሞኑ ስለእሳቸው የተሰጡ አስተያየቶችን በሚገባ ተከታትያቸዋለሁ። የተለያዩ ሰዎች ሐሳብ ሲሰጡ ወጣትነታቸውን፣ እንደ እንከን በማየት ለሹመቱ ብቁ እንዳልሆኑ አድርገው ሲገልጹም አይቻለሁ፡፡ የትምህርት ዝግጅታቸው ደግሞ፣ ‹‹ሕግ ነው ያጠኑት›› በማለት፣ ‹‹የብሔራዊ ባንክ ገዥ መሆን አይችሉም›› የሚል ሐሳብም ተመልክቻለሁ፡፡ ሌሎች እጅግ ያሳዘኑኝ ሐሳቦችም ነበሩ፡፡ አንዳንዶችም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ኃላፊነትና ሥልጣን ያላገናዘበ አስተያየቶች ሰንዝረው ተመልክቻለሁ። ‹‹አቶ ማሞን ከመሾም ፈንታ እከሌን ነበር መሾም የነበረባቸው፤›› በማለት ሐሳብ የሰጡ ሰዎችንም ምልክታ አንብቤያለሁ፡፡ በእውነቱ እንዲህ ያለው ምልከታ ያለ ማወቅ ይመስለኛል፡፡ በእኔ እምነት ኃላፊነቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ ‹‹እከሌን መሾም አለብህ፣ እከሌን መሾም የለብህም፤›› የሚል ሐሳብ መስጠት በራሱ ትክክል አይመስለኝም፡፡ በአጠቃላይ ሹመታቸውን ከሚተቹ ሰዎች አብዛኛዎቹ በእኔ በኩል እንደተረዳሁት ነገሮችን በደንብ አመዛዝነው ያዩ አይመስለኝም፣ ይህንን የምለው በምክንያት ነው፡፡ ቅድም እንደገለጽኩልህ አቶ ማሞን የማውቃቸው ቀደም ብዬ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የነበራቸውን የሥራ ኃላፊነት አውቃለሁ፡፡ አይኤፍሲ ሲሠሩ ሥራቸውም ስለነበር የኢትዮጵያን የግል ዘርፍ ከብዙዎች የበለጠ ያውቁ ነበር፡፡ በተለይም ‹‹ዱይንግ ቢዝነስ›› ላይ አቶ ማሞ በቅርብ ይሠሩ ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ ደግሞ በሕግ ተመርቀው ከመጡ በኋላም የዓለም ንግድ ድርጅት ተደራዳሪ ሆነው እንዲሠሩ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ በአገራችን ውስጥ በሎጂስቲክስ ጉዳይም ብዙ ሠርተዋል፡፡ በሌሎች የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ይሠሩ የነበረውን ነገር አውቃለሁ፡፡ በኢኮኖሚው ዙሪያ ከሌላ አጋራቸው ጋር በመሆን የጻፉት ዳጎስ ያለ ጽሑፋቸውንም አንብቤያለሁ፡፡ ስለዚህ እኔ እስከማውቃቸው ድረስ ሲናገሩም ሲጽፉም ሰከን ያሉ ሰው መሆናቸውን ነው፡፡ እውነት ነው የአቶ ማሞ ፊት ሲታይ ወጣት ይመስላል፡፡ ግን ወጣትነት ሲባል በጣምም እንደ ልጅ አድርጎ ማሰብ አይገባም፡፡ ፊትን በማየት ብቻ ዕድሜያቸውን መተንበይ የሚያስቸግር ይመስለኛል፡፡ 15 ዓመት ወደ ኋላ ተመልሼ ሳስብና አሁን ያሉበትን ገጽታቸውን ወይም ፎቷቸውን ስመለከት በእውነት ብዙ ልዩነት የለም፡፡ ስለዚህ ስለእሳቸው የተሰጠው አስተያየት ተገቢ አይደለም፡፡ ለቦታው ብቁ የሚያደርጋቸው ብዙ መሥፈርቶችን ያሟላሉ፡፡ እኚህን ሰውዬ በቂ የትምህርት ወይም የልምድ ዝግጅት ያላቸውም ብለው የሚተቹ ሰዎችን ታዝቢያለሁ፡፡ ምክንያቱም ወደኋላ ተመልሰን ከዚህ ቀደም ኢሕአዴግ እንደገባ መጀመርያ ላይ የብሔራዊ ባንክ ገዥ የነበሩት አቶ ሌይኩን ብርሃኑ፣ አቶ ዱባለ ጀሌ፣ አቶ ተክለወልድ አጥናፉና ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በእውነቱ በወረቀት ላይ ቁጭ አድርገን ‹‹እከሌ ይህንን ተምሯል››፣ ‹‹ልምድ አለውና ይህ ነው ለብሔራዊ ባንክ የሚበጅ›› ተብሎ በመሥፈርት ተመዝነው የተመረጡ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን በአጠቃላይ እነዚህ ሰዎች የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኃላፊነቱን ሊሸከሙ ይችላሉ ተብለው የተሾሙ ናቸው፡፡ ከሞላ ጎደልም ደግሞ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ዓይተናል፡፡ ነገር ግን ለብሔራዊ ባንክ ተብሎ ለዚያ ሥራ ብቻ የታጨና የተኮተኮተ ሰው ተሹሞ አያውቅም፣ ወደፊትም አይሆንም፡፡ ስለዚህ የትምህርትና የሥራ ልምድ ዝግጅቱን ስመለከት አቶ ማሞ ከዚህ ቀደም በዚህ ቦታ ላይ ከተሾሙ ሰዎች የሚያንሱ ሰው አይደሉም፡፡ ሁለተኛ እንዲህ ያለው ቦታ ላይ ሰው መሾም የጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑን ማወቅ ይገባል፡፡ ፈረንጆች እንደሚሉት ‹‹ቤነፊት ኦፍ ዘዳውት›› መስጠት ነው እንጂ ያለብን፣ እከሌን ከመሾም እከሌን መሾም ይሻል ነበር እስከማለት ድረስ መሄዳችን ለእኔ ትክክል መስሎ አልታየኝም፡፡ ለማንኛውም እኔ አቶ ማሞን እስከማወቃቸው ድረስ በተገቢው ቦታ ተሾመዋል፡፡ አቶ ተክለወልድ ስለሁለተኛ የአገር በቀል ልማት ዕቅድ የሰጡትን አንብቤ፣ ኢትዮጵያ ዛሬ ያለችበትን ሁኔታ ተገንዝቤ የአቶ ማሞን ሹመት ሳየው ጠቅላይ ሚኒስትሩም በእውነቱ ትክክለኛ ውሳኔ የሰጡ (Smart Move) ነው የሚመስኝ፡፡   

ሪፖርተርእንዴት? ቢያብራሩልኝ፡፡

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- ምክንያቱም የአቶ ተክለወልድ ማብራሪያን ስመለከት ብዙ እንድገነዘብ ያደረገኝ ነገር ስላለ ነው፡፡ ለምሳሌ የመጀመርያው አገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም አሥር ቢሊዮን ዶላር ከዓለም ባንክና ከአበዳሪ ተቋሞች ብድር ይገኛል ተብሎ ታሳቢ ተደርጎ ነበር ወደ ሥራ የተገባው፡፡ ነገር ግን የሰላም ዕጦቱ ይህንን ገንዘብ እንዳናገኝ አድርጎናል፡፡ የሁለተኛው አገር በቀል ኢኮኖሚ ዕቅድ ሲዘጋጅም አንዱና እንደ ትልቅ ታሳቢ ተደርጎ የተወሰደው ከእነዚህ ገንዘብ ከሚያበድሩ ተቋማት፣ በተለይም ከአይኤምኤፍ ዳጎስ ያለ የውጭ ምንዛሪ ብድርና ድጋፍ ይገኛል በሚል ነው፡፡ ይህ ከሌለ ይህ ዕቅድ ምንም ትርጉም እንደሌለው ነው፡፡ አቶ ተክለወልድ ግልጽ አድርገው ነው ያስቀመጡት፡፡ አዲስ ብድር መገኘቱ ብቻ ሳይሆን የተበደርነውን ገንዘብ ክፍያም ለመቀነስ ከእነዚህ ተቋማት ጋር መደራደር የሚያስፈልግ መሆኑን ነው፡፡ ከአይኤምኤፍ ከዓለም ባንክ ጋር የተጀመረው ድርድር በመልካም ሁኔታ ከተጠናቀቀ አዲስ ገንዘብ መምጣቱ ብቻ ሳይሆን፣ በየዓመቱ የምንከፍለው የውጭ ዕዳ ሽግሽግ ተደርጎ አሁን በዓመት የምንከፍለውን ሁለት ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ለማውረድ ያስችላል፡፡ ስለዚህ ይህንን ታሳቢ እያደረገ ሥራ ካልተሠራና የዕዳ ሽግሽግና የገንዘብ ድጋፍ ካልተገኘ ሁለተኛው አገር በቀል የልማት ዕቅዳችን ምንም ያህል ወደፊት እንደማይሄድ አድርገው ነው የጠቀሱት፡፡ ይህንን አንብቤ ስለነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ማሞን መሾማቸው የተጠና ውሳኔ ነው ያደረጉት ብዬ እንዳምን አድርጎኛል፡፡ ምክንያቱም ለዚህ ዕቅድ ማስፈጸሚያ የሚፈለገውን ፋይናንስ ለማግኘት ከአበዳሪ ድርጅቶች ጋር በጥሩ ሁኔታ የመደራደር ችሎታ ብቻ ሳይሆን የሚያስፈልገው፣ የእነሱን አመኔታ ያገኘ ሰው በእጃችን እያለ ሌላ ፍለጋ ምን አስኬደን በማለት የተወሰነም ይመስለኛል፡፡ አቶ ማሞ ደግሞ የዓለም ባንክና የዓለም ገንዘብ ድርጅት ሠራተኛ የነበሩ ሰው ስለሆኑ ተቋሞቹን የሚያውቁና የሚያምኑት ሰው አግኝተዋል ለማለት ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- አንዳንዶች አቶ ማሞ ከእነዚህ ተቋማት ጋር ባላቸው ግንኙነት፣ ኢትዮጵያን በሚጎዳ ተግባር ላይ ሊያውሉት ይችላሉ፡፡ ተቋማቱ አቶ ማሞን መጠቀሚያ ያደርጋሉ ማለታቸውንስ እንዴት ያዩታል?

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- አንዳንዶች ይህንን በመጥፎ የተረጎሙ አሉ፡፡ የዓለም ባንክንና የዓለም ገንዘብ ድርጅት ለማስፈጸም ይጠቅሙበታል ብለው ሐሳብ የሰጡ አሉ፡፡ በዚህ ሐሳብ በጣም ነው የማዝነው፡፡ ምክንያቱም አቶ ማሞ በምንም መንገድ እስካሁን እየሠራ በመጣበት መንገድ፣ ወደፊትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥና ከሌላም ሥራ ሊያገኝ የሚችለው ጥቅም ቀድሞ ሲያገኝ ከነበረውና ጥሎ ከመጣው ያነሰ እንጂ የበለጠ ሊሆን አይችልም፡፡ በፊት በጥሩ ደመወዝ፣ ኮንዲሽንና በትልቅ ሥራ ላይ የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ ወደ መንግሥት ሥራ ሲመጡ ያለ ምንም ጥያቄ የቀድሞ ጥቅሙን መስዋዕትነት አድርጎ ነው የመጣው፡፡ 

ሪፖርተርእርግጠኛ ነዎት?

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- አዎ፡፡ ይህንን አውቃለሁ፡፡ በግልጽ አውቃለሁ፡፡ እኚህ ሰውዬ እዚህ ከመጡ በኋላ የዓለም ባንክና የዓለም ገንዘብ ድርጅት ማስፈጸሚያ አድርገው ይጠቀሙበታል ብሎ መፍራት አይገባም፡፡ ምክንያቱም ይህ ማለት ብሔራዊ ባንክን ማንም ሌላ አካል ሳይኖር ይህ ሰውዬ ብቻ የሚያዝበት አድርጎ እንደማሰብ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አይሆንም፡፡ ብሔራዊ ባንክ ቦርድ አለው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በታች አቶ ማሞ አለቃ አላቸው፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ባንክን በፈለገው አቅጣጫና ሁኔታ ሊያዙበት አይችሉም፡፡ ስለዚህ የዓለም ባንክና የዓለም ገንዘብ ድርጅት መጠቀሚያ ይሆናል የሚለው አስተሳሰብ ለእኔ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ይልቁንስ አሁን ረቂቁ አልቆ በማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ እየታየ ነው የተባለው ሁለተኛው የአገር በቀል ኢኮኖሚ ዕቅዱ ፀድቆ የሚፈለገውን ገንዘብ ለማግኘት ከዓለም ባንክና ከአይኤም ጋር ድርድር የሚገባ ከሆነ፣ አሁን ላለንበት ሁኔታ ከአቶ ማሞ የተሻለ ተደራዳሪ ኢትዮጵያ ልታገኝ አትችልም ብዬ ነው የማስበው፡፡ ለዚህም ነው እኔ የዚህ በሹመት አሰጣጥ “ስማርት ሙቭ” ነው የምለው፡፡  

ሪፖርተርከሰሞኑ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሰፊ ሲዘዋወር እንደነበረው፣ አንዳንዶቹም በድፍረት እየገለጹ ካሉት አስተያየቶች መካከል አቶ ማሞ ለብሔራዊ ባንክ ገዥ ሆነው መሰየማቸው አግባብ አይደለም ብለው ከጠቀሱት ውስጥ በባንክ ሥራ ላይ መሪ ሆነው ያለማገልገላቸው ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ከፋይናንስ ተቋማት ጋር እንዴት ይሠራሉ? የሚልም ጥያቄ የሚያነሱ አሉ፡፡ የእርስዎ ምልከታ ምንድነው? 

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- በጣም ከምወዳቸውና ከማከብራቸው ወዳጆቼ አታጣላኝ፡፡ ምን መሰለህ እንደ እኔ የግል አስተሳሰብና እኔ በሚገባኝ ደረጃ የግል ዘርፉ የኢትዮጵያ የልማት አጋር ነው፡፡ መንግሥት ብቻውን የዚህችን አገር የልማት ችግር ይፈታል ብዬ አምኜ አላውቅም፣ አሁንም አላምንም፡፡ ይህንን በተመለከተ አቶ ማሞ የግል ዘርፉን እስካሁን ድረስ ከነበሩት ከማውቃቸው የብሔራዊ ባንክ ገዥዎች የተሻሉ የግል ዘርፉን ያውቁታል፡፡ የተሻለ ከባቢ ይፈጥሩለታል ብዬ ነው ተስፋ የማደርገው፡፡ ያለፉትም ገዥዎች እጅግ በጣም ወዳጆቼ ናቸው፡፡ ነገር ግን የግል ዘርፉን በተመለከተ ከሁሉም የተሻለ ያውቁታል፡፡ ዱይንግ ቢዝነስ ኢንቫይሮመንትን በተመለከተ፣ የኢትዮጵያን ሎጂስቲክስ ሁኔታና ከዓለም የንግድ ድርጅት ጋር ሲያደርጉ የነበረው ድርድር ብቻ ስለግል ዘርፉ ብዙ ማንበብና ግንዛቤ መውሰድ ግዴታ እንደነበር ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይህንን ስለማውቅ ነው፡፡ በተለይም እኔም በጣም በብስጭት መልክ ለሚዲያ ስናገር የነበርኩት ነገር ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያኖች ባንክና ኢንሹራንስ ማቋቋም ይችላሉ የሚሉት አዋጆች የወጡት እ.ኤ.አ. 1994 ነው፡፡ አሁን ከ50 በላይ ባንክና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች አሉ፡፡ ለእነዚህ ተቋሞች ግን የተማረ የሰው ኃይል የሚያቀርብ ተቋም የለም፡፡ ይህ እንዲቋቋም አቶ ማሞ አቋም ወስደው ይሠራሉ ብዬ እጠብቃለሁ፡፡ ይህ ተቋም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው አገሮች ጭምር እንደሚሆን ይህንን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በሌላ ሁኔታ ደግሞ ቀደም ሲል ንግድ ምክር ቤቶች ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ አቶ ግርማ ብሩ (አምባሳደር) የንግድ ሚኒስትር ስለነበሩ፣ በመንግሥት በኩል እኔ በንግዱ ኅብረተሰብ በኩል ሆነን የመንግሥትና የግሉ ክፍል ኢኮኖሚ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል፡፡ መንግሥትና የንግዱ ኅብረተሰብ ውይይት የሚያደርጉት የሚፈጠሩ ችግሮች ተወያይተው መፍትሔ እንዲያገኙ ተብሎ በሰነድ የተፈረመ ነው፡፡ ይህንን ለመተግበር ዕርዳታ አስፈልጎ ስለነበር ንግድ ምክር ቤቶችም ሆነ የውጭ አጥኚዎችና ወጣት ኢኮኖሚስቶች ያስፈልጉ ነበር፡፡ በወቅቱ ደግሞ አቶ ማሞ የአይኤፍሲ ኦፊሰር ነበሩና ለሁለት ዓመት የቆየና ለእያንዳንዱ ዓመት 900 ሺሕ ዶላር ለግል ዘርፉ የሰጡ ሰው ናቸው፡፡ በወቅቱ ስለጉዳዩ አጥንተው ምክረ ሐሳብ ካቀረቡ በኋላ ነው ያንን ገንዘብ ያስፈቀዱልን፡፡ ስለዚህ አቶ ማሞ ያለ ምንም ማጋነን የግል ዘርፉን የሚደግፉ ናቸው፡፡ እስካሁን ድረስ የነበሩ የባንክ ገዥዎቻችን እስከማውቀው ድረስ ጎበዞች ቢሆኑም፣ የግል ዘርፉን በተመለከተ ግን ከአቶ ማሞ የቀረበና የሚያውቅ የተሻለ የለም፡፡ እኔ በዚህ ግንባሬን እሰጣለሁ፡፡   

ሪፖርተርብሔራዊ ባንክ ከዚህ ቀደም ሊያደርግ የሚገባው ነገር ኖሮ ያላደግነው ነገር በአቶ ማሞ ሊመለሱ ይችላሉ ብለው ያምናሉ? ይህንን ለማድረግ ምን ያህል ይጓዛሉ ብለው ያስባሉ? 

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- እኔ ከሁሉም ጋር ቀረቤታና መግባባት ይኖራል አይኖርም? አላውቅም፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ ግን አቶ ማሞ የማሰብና ሐሳብ የማፍለቅ ችሎታ ብቻ ሳይሆን የማድመጥ ችሎታ አላቸው፡፡ ሁሉ ነገር እኔ አውቃለሁ፣ ሥልጣኑ የእኔ ነው ብለው በማስፈራራት መልክ የሚነሱ ሰው አይደሉም፡፡ ማንኛውንም ሰው ያደምጣሉ፡፡ ካደመጡ በኋላ ነው ሐሳቡንና ምክሩን የሚሰጡት፡፡ ይህ ራሱ በጎ መጀመርያ ነው፡፡ የውጭ ባንኮች ወደ አገራችን የሚገቡበት መንገድ ተብሎ ለውይይት የቀረበው ሰነድ ላይ የተቀመጠው መዋቅር ቅር የሚያስብሉ ጉዳዮች ቢኖሩኝም እንኳን ይለወጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ እንዲያውም እሳቸው ራሳቸው የባንክ ባለሙያዎችን ብቻ አዳምጠው ውሳኔ ይሰጣሉ ብዬ አላስብም፡፡ የባንክ ባለቤቶችን የሚወክሉ አካላትን ያነጋግራሉ ብዬ ነው የማስበው፡፡ እዚያ ቦርድ ላይ ቀደም ያለው የኢኮኖሚ ወይም የፋይናንስ ዘርፉ አስተሳሰብ ነው ያለው፡፡ ከቀድሞ አስተሳሰብ የተለየ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ የቱንም ያህል ከድሮ የተለወጠ እንደሆነ ለመናገር አልችልም፡፡ ስለዚህ ስለግል ዘርፉ ዝም ብሎ ከሚወራው በስተቀር በተጨባጭ የአቶ ማሞ አለቆች የሚሉትን አሜን አሜን ከማለት ፈንታ አቋም ወስደው የግል ዘርፉን ቦታ ይሰጣሉ ብዬ ነው የማስበው፡፡ በእሱ መልክ ካልሆነ በስተቀር ዝም ብሎ ነገሮችን በተለመደው ማስቀጠል ከሆነ፣ የፋይናንስ ዘርፉ ብዙ የምንመኘውን ፍሬ ላያመጣ ይችላል ብዬ እፈራለሁ፡፡ ይህ ሰው ከዓለም ባንክና ከዓለም ገንዘብ ድርጅት ጋር መደራደር ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎችንም በተለይ የግል ዘርፉን ተሳትፎ በተመለከተ አቋም ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ ልማት አጋዥ የሆነን የግል ዘርፍ ይህንን እንደሚያበረታታ ነው የማውቀው፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች እንዲመጡ ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ እኔ ለግል ዘርፉ በተለይ ለፋይናንስ ዘርፉ የተሻለ መጻኢ ዕድል ነው የማይለት፡፡

ሪፖርተርመንግሥት የባንክ ዘርፉን ለውጭ ባንኮች ክፍት አድርጓል፡፡ ይህ ውሳኔ ተስፋና ፈተናዎቹ ምንድን ናቸው ብለው ያምናሉ?

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ሐሳቤን በተደጋጋሚ አካፍያለሁ፡፡ የውጭ ባንኮች ኢትዮጵያ ሊገቡ የሚገባቸው ምናልባት ስምንትና አሥር ዓመት በፊት ነበር፡፡ ከመነሻው የውጭ ባንኮች መግባታቸው ስለማይቀር የአገር ውስጥ ባንኮች አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ አስፈላጊውን ዝግጅት ከአሁን ጀምረን ማድረግ አለብን የሚል መንፈስ መኖር ነበረበት፣ ግን ሳይሆን ቀረ፡፡ ነገር ግን ለምሳሌ አቃቂ ቃሊቲ ላይ ትልቅ የፋይናንስ ማሠልጠኛ ተቋም ይፈጠራል ተብሎ፣ በጣም ብዙ ገንዘብ ወጥቶ ፋሲሊቲው በሙሉ ተገንብቷል፡፡ ይህ የታሰበው የውጭ ባንኮች ስለሚገቡና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት ታስቦም ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የሠለጠነ ሰው ያፈራል የተባለው ተቋም ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተሰጠ የተባለ፡፡ ከዚያም በኪራይ ይሁን በስጦታ አላውቅም ለዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዝ አፍሪካ (Unisa) ተሰጠ፡፡ ብሔራዊ ባንክ ይህንን ተቋም ወደ ሥራ ለማስገባት አስፈላጊውን ዝግጅት አደርጋለሁ ብሎ ከዓለም ባንክ ከ13 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዕርዳታ ተቀብሎ ነበር፣ አስፈላጊውን ውጤት ግን አላገኘንም፡፡ ገንዘቡ ምን ላይ እንደዋለ አናውቅም፡፡ ለማንኛውም የውጭ ባንኮች እንዲገቡ የተፈለገው በፍላጎታቸውን ብቻ የወሰነው ነው ብዬ አላምንም፡፡ ለዚህ ውሳኔ የደረስንበት አንዱ ምክንያት የውጭ ምንዛሪ ችግራችን ነው፡፡ አገራችን ውስጥ ያሉ ባንኮች ከዚህ የበለጠ ደወል ሊደወልላቸው አይችልም፡፡ ቀደም ብሎ መታሰብ የነበረበት ብዙ ነገሮች ነበሩ፡፡ ዝም ብሎ በጎጥ በመሳሰሉ መቋቋምን ትቶ በአገልግሎት ልህቀት ብቻ ውድድርን ለማሸነፍ ታቅዶ ባንኮች መቋቋም ነበረባቸው፡፡ አብዛኞቹ ግን በዚህ መንገድ እየተቋቋሙ አይደሉም፡፡ አሁን ግን የውጭ ባንኮች ይገባሉ ሲባል አንዳንዶቹ ባንኮቻቸው የካፒታል አቅማቸውን በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ያሳስባል፡፡ በአገር ደረጃ ደግሞ የባንክ ኃላፊ ሆኖ መሥራት የሚችሉ ብዙ ሰዎች የሉንም፡፡ ማኩረፊያ እንኳን የለንም፡፡ አንዳንድ ጊዜ የባንክ ኃላፊ አድርገህ የምታስቀምጠው ሰው አማራጭህ እጅግ በጣም የተወሰነ ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህ በሰው ኃይልም አብዛኛዎቹ ባንኮቻችን ደካሞች ናቸው፡፡ ስለዚህ መጀመርያ ወደ ጎን ማየትና እያንዳንዳችን ከማን ጋር ብንጣመር የተሻለ ጠንካሮች መሆን እንችላለን ብሎ ቶሎ መወሰንና ወደ ሥራ መግባት አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህ ሌላ ከውጭ ባንኮች ጋር ተጣምሮ ለመሥራት ትናንት ከትናንት ወዲያ መሆን የነበረበት ቢሆንም፣ አሁን ሥራ መጀመር አለበት፡፡ ነገር ግን እስካሁን ሳይ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጣድፈው እየሠሩ ያሉ ባንኮች እያየሁ አይደለም፡፡ በጣም ዳተኞች ነንና ይህ መለወጥ አለበት፡፡ ባንኮች ተዋህደው መሥራት እንዳለባቸው እንደ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ያሉ ባለሙያዎች ሲያካፍሉ አያለሁ፡፡ ከዚህ ቀደም ግን እኔና አቶ ዘመዴነህ በተለያዩ ጉዳዮች የተለያየ ሐሳብ እንደምናንፀባርቅ ቢታወቅም፣ የውጭ ባንኮች ወደ አገር መግባትን በተመለከተ ግን ሐሳባችን አንድ ነው፡፡ የባንክ ቁጥር አሳንሶ ጉልበታቸውን ጠንካራ ማድረግ ላይ እኔና አቶ ዘመዴነህ በጣም እየተስማማን መጥተናል፡፡ ስለዚህ የውጭ ባንኮች ይግቡ ሲባል የአገር ውስጥ ባንኮች ጥሩ ተወዳዳሪ ለመሆን ይዋሀዱ የሚለውን ጉዳይ ላይ መወትወቴን እቀጥላለሁ፡፡ አቶ ዘመዴነህም እየወተወቱ ነው፡፡ 

ሪፖርተርየብር መግዛት አቅም ተዳክመዋል፡፡ ኢኮኖሚውም ላይ ጫና ፈጥሯል፡፡ በዚህ ዙሪያ ያለዎት ምልከታ ምንድነው?

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- የኢትዮጵያ የብር የመግዛት አቅም መውደቅ የዋጋ ንረት የአገራችን ትልቅ ችግር ሆኗል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አሳሳቢ የሚባል እንደሆነ ተነግሯል፡፡ የአቶ ማሞ መሾምም ለድርድሩ ትክክል ነው ብያለሁ፡፡ ነገር ግን ከዚህ ሁሉ የሚቀድመው ሰላም ነው፡፡ ሰላም ከሌለ የፈለግከውን ያህል ዶላር እዚህ ብታፈስ ለብልጣብልጦች መክበሪያ ካልሆነ በቀር ለኢትዮጵያ ልማት የሚጨምረው ነገር የለም፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ችግር ውስጥ የገባችው በሰላም ዕጦት ነው፡፡ ለሰላም ሁሉም በየራሱ የተለያየ መፍትሔ እያቀረበ ነው፡፡ እኔ ከሌሎች አውቃለሁ የምለው ነገር ባይኖርም፣ ሹመቱ የዓለም ባንክ ብድር ተወውና የፈለግከው ነገር ቢኖር ያለ ሰላም የሚሆን ነገር ስለሌለ ለሰላም ቅድሚያ መስጠት አለበት፡፡ ነገር ግን ለኢኮኖሚ መዳከምና ችግር ውስጥ መግባት ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ ሕገወጥ ተግባራት ዛሬም ይታያሉ፡፡ በ100 እና በ200 ዶላር ኤልሲ እየተከፈተ መኪና የሚገባበት አገር ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ስለዚህ ችግሩ ብዙ ስለሆነ ሕጋዊ አሠራርን ማስፈን ለብዙ ችግሮቻችን መፍትሔ ይሆናል፡፡ 

ሪፖርተርከሰሞኑ እንደሰማነው በአቶ ማሞ መሾም የዓለም የገንዘብ ተቋማት እጅ አለበት የሚሉም አሉ?

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- ከዓለም ባንክ ጋር ለሚደረገው ድርድር አማራጮቻችንን አስቀምጠን ካየን የማሞ መሾም ምናልባት ትንሽ አድቫንቴጅ ይኖረዋል፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች ጋር ሲሠሩ የነበሩና ስለሚውቁት የተሻለ ነው፡፡ አሁን እንደምንሰማውም የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የእሳቸው ሹመት በበጎ እያነሱ ነው፡፡ በጣም ይቅር በለኝና ምናልባትም እስከ እነዚህ ተቋሞች በተዘዋዋሪ እንደ አቶ ማሞ ያሉትን እንደዚህ ብታደርጉ ለድርድራችሁ ሊቀል ይችላል ብለውም ሊሆን ይችላል፡፡ የሚያውቁትን ሰው ለሹመት ሊጠቁሙ ይችላሉ፡፡ እንዲህ አይሆንም አይባልም፡፡ ይህም ይደረጋል ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ነገር ግን በእኔ እምነት ሹመቱ የተሰጠው በመንግሥት አመኔታ ነው፡፡

ሪፖርተርእንዲህ ከታሰበ ግን አንዳንዶች ሰሞኑን እንዳነሱት፣ ‹‹የማሞ መሾም የእነዚህን ተቋማት ፖሊሲ ለማስወሰን ይጠቀሙባቸዋል፤›› የሚል ሐሳብ ይነሳልና ይህ ሥጋት አይኖርም?

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- እኔ ሥጋት የለኝም፡፡ ነገርኩህ እኮ ማሞ ብሔራዊ ባንክን እንደ ግል ንብረታቸው የፈለጉትን ሊያደርጉ የሚችሉ አይደሉም፡፡ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ሊደርጋቸው የሚችለው ነገር አለ፡፡ ሥልጣኑ የተገደበ ነው፣ ቦርድ አለው፣ አማካሪዎች አሉት፡፡ አቶ ማሞም ደግሞ እኔ እስከማውቀው ድረስ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የአገሩን ኢንተረስት በምንም ነገር አስተላልፎ ይሰጣል ብዬ አላምንም፡፡ ከአቶ ሌይኩን ጀምሮ እስካሁን ያሉ ገዥዎችንም ሁሉንም ስለማውቅ ጥሩ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ አሁንም አቶ ማሞ የአገሩን ኢንተረስት ለውጭ ኢንተረስት ኮምፕሮማዝድ ያደርጋል ብዬ ጨርሶ ሊታሰብ አይችልም፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች